
ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ ታሪክ ሕያው የሆኑ ኮከብ አትሌቶች መፍለቂያ መሆኗን ዓለም ይመሰክራል። ይህንንም በየዘመኑ የፈለቁ ከዋክብት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በታላላቅ የውድድር መድረኮች አሳይተዋል፣ እያሳዩም ይገኛሉ። ለዚህ ደግሞ የአትሌቲክስ ክለቦች ሚና ትልቅ ነው።
መነሻውን በጦሩ ክለቦች ውስጥ ያደረገው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ታሪክ ረጅም ዓመታትን ባስቆጠረ ዕድሜው በውጤታማነት ይቀጥል እንጂ በሚገባው የእድገት ደረጃ ላይ አይገኝም።
ከኢትዮጵያ ዘመናዊ ስፖርት ጅማሬ ጋር እኩያ ሊባሉ ከሚችሉ ክለቦች መካከል መቻል ተጠቃሽ ሲሆን፤ በ1936 ዓ.ም መመስረቱን ታሪክ ያወሳል። ጀግናውን አትሌት ሻለቃ አበበ ቢቂላ ያፈራው ክለብ ከሜልቦርን ኦሊምፒክ አንስቶ እስካሁን በርካታ ውጤታማ አትሌቶችን በማፍራት ላይ ይገኛል። በሚሊተሪ ተቋማት ስር ያሉ ክለቦችን ጨምሮ እንደየጊዜው ቢለያይም በቁጥጥር ከፍተኛ የሆኑ ክለቦች ተመስርተዋል።
እነዚህ ክለቦች በቀደመው ወቅት ከየአካባቢው ታዳጊዎችን መልምለው በማሰልጠንና በመግራት ኢትዮጵያን እንዲወክሉ ሲያበቁ ቆይተዋል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህም ከፕሮጀክቶች፣ የማሰልጠኛ ተቋማትና አካዳሚዎች ብቃት ያላቸውን አትሌቶች ወደ ክለቦቻቸው በማካተት ለዓለም አቀፍ ውድድር ብቁ እያደረጓቸው ይገኛል።
ክለቦቹ ለአትሌቶች ማረፊያ፣ ምግብና ደመወዝ ከማዘጋጀት ባለፈ አሰልጥነውና ውድድር አፈላልገው በማሳተፍ ለዓለም አቀፍ ቻምፒዮናዎች ያስመርጧቸዋል። ስመጥር አትሌቶችን ማፍራት የቻሉ የምርጥ አሰልጣኞች ባለቤትም ናቸው። እነዚህ ክለቦች ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ የዋሉት ውለታ በቀላሉ የሚገለጽ አይደለም። ይሁንና ስፖርቱ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየተቀየረና የታዋቂ አትሌቶች ምርጫም ከክለቦች ይልቅ በማናጀሮች ስር መሥራት እየሆነ መምጣቱን ተከትሎ የክለቦች ሕልውና አደጋ ላይ መውደቁ ነው የተጠቆመው። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከቀናት በፊት ከአሰልጣኞችና ባለሙያዎች ጋር በአሰራር ስርዓቶች ላይ ያደረገውን ውይይት ተከትሎም ይኸው ሃሳብ በስፋት ተንጸባርቋል።
የውጤታማ አትሌቶች ምንጭ ከሆኑ አንጋፋ ክለቦች መካከል አንዱ የኢትዮ ኤሌክትሪክ የአትሌቲክስ ክለብ ነው። በዚህ ክለብ የረጅም ርቀት ዋና አሰልጣኝ የሆኑትና እንደ ሐጎስ ገብረሕይወት ያሉ ጠንካራ አትሌቶችን ያፈሩት ኮማንደር ቶሌራ ዲንቃ፤ አትሌቶች በማናጀር እየሰለጠኑ በመሆኑ ክለቦች የመፍረስ አደጋ እንደተጋረጠባቸው ይጠቁማሉ። በርካታ ጀግና አትሌቶችን ያፈሩ ክለቦች የተበተኑ ሲሆን በመንገዳገድ ላይ ያሉትም ቀላል አይደሉም።
“ፌዴሬሽኑ ጥርስ አልባ በመሆኑ ስፖርቱ ከክለቦች ወጥቶ በግለሰቦች እጅ ላይ ወድቋል” ያሉት አሰልጣኝ ቶሌራ፣ ውድድሮች በሚካሄዱበት ወቅትም የሚታየው የጥቂት ክለቦች ጥረት ብቻ መሆኑን ተናግረዋል። ሀገር አቀፍ ውድድሮች ሲከናወኑ ፌዴሬሽኑ ጥሪ የሚያደርገው ለክለቦች ቢሆንም አትሌቶቹ ለብሄራዊ ቡድን ሲመረጡ ግን በግል አሰልጣኞቻቸውን በኩል መምጣት እንደሚፈልጉ አመላክተዋል።
ክለቦች በሚሊየን የሚቆጠር ገንዘብ እያፈሰሱ ሌሎች አሰልጣኞች ደግሞ በግላቸው ጥቂት ውጤታማ አትሌቶችን በመያዝ ንግድ ይሰራሉ። ይህንንም ሲያብራሩ ‹‹ለአብነት ኢትዮ ኤሌክትሪክ በየዓመቱ 87 ሚልየን ብር፤ በየወሩ ደግሞ 16 ሚልየን ብር ለደመወዝ ብቻ ያወጣል። በሜዳ ተግባራት እንዲሁም በአጭርና ረጅም ርቀት አትሌቶችን በመያዝም ያሰለጥናል። ቅድሚያ የሚሰጠው ግን ለሌላው በመሆኑ በመሰል ሁኔታ ውስጥ እያለፉ ያሉ ውጤታማ አሰልጣኞች ክለቦችን እያፈረሱ ወደ ግል አሰልጣኝነት እያመሩ ይገኛሉ›› ብለዋል።
የክለቦች አስተዋጽኦና ሕልውና ሁሌም ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ መሆኑን አጽንኦት የሰጡት ደግሞ የሸገር ሲቲ አትሌቲክስ ክለብ አሰልጣኙ ሃብታሙ ግርማ ናቸው። ቀድሞ ያሰለጥኑበት የነበረውና በርካታ ተተኪ አትሌቶችን ያፈራው ክለብ አሁን ያለበትን ስጋት በማሳያነት አንስተዋል። በመሆኑም በስፖርቱ ካለው እንቅስቃሴ አንጻር በርካታ ክለቦች ሥራ እስከማቆም ሊደርሱ የሚችሉ በመሆኑ እውቅና ሊያገኙ ይገባል ባይ ናቸው። ቀደም ብሎ በነበረው አሰራር መሰረትም አትሌቶች ለብሄራዊ ቡድን ሲመረጡ ቅድሚያ ለክለቦች ካልተሰጠ ሕልውናቸው እየሳሳ ሊሄድ እንደሚችልም ነው ስጋታቸውን ያንጸባረቁት።
ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አትሌቶችን ባያፈራው የኦሮሚያ ክልል የነበሩ በርካታ ክለቦች አሁን ላይ መኖር አለመኖራቸውን መለየት በሚያዳግትበት ሁኔታ ላይ መሆናቸውም በአስተያየት ሰጪዎች ተነስቷል። አሁን ላይ ከተፎካካሪነት ወጥተው ጥቂት አትሌቶችን በተወሰኑ ርቀቶች ይዘው መቀጠል ስለሚከብዳቸውም ቀጣይነታቸው አደጋ ላይ በመውደቁ ሊታሰብበት የሚገባ መሆኑም ተመላክቷል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 9 ቀን 2017 ዓ.ም