እልፍ አእላፋን ያለ ልዩነት ትናንትም ዛሬም ሆነ ነገ ስለ እፉኝቱና አሸባሪው ሕወሓት ቢጽፉ፣ ቢገጥሙ፣ ቅኔ ቢዘርፉ፣ ሸራ ወጥረው ቢስሉ፣ ነሐስ አቅልጠው ሐውልት ቢቀርጹ፣ ፖለቲካዊ ዲስኩር ቢያደርጉ፤ ወዘተረፈ የሚያነሷቸው ርዕሰ ጉዳዮች ከጨካኝነቱ፣ ከአረመኔነቱ፣ ከዘራፊነቱ ፣ ከከሀዲነቱ፣ ከኢትዮጵያ ጠልነቱ፣ ከውሸቱና ከባንዳነቱ አይወጡም። ባለፉት ሦስት አመታት ስለ ከሀዲው ሕወሓት የጻፍኋቸው በርካታ መጣጥፎች ለዚህ እማኝ ናቸው። አንዳንድ ጊዜ እንደ ዘፈን ግጥም አዝማች የመጣጥፍም አዝማች አለው እንዴ ብዬ ራሴን እንድጠይቅ ያስገድዱኛል። ታዲያ እንደ አዝማች ገዥው መልዕት ትኩረት እንዲያገኝ፤ ዜማው እንዲሰምር የሚደጋገሙ መጣጥፎች ማጋጠማቸው ይቀራል።
ሰሞኑን ነጻ በወጡ የአማራና የአፋር አካባቢዎች ለማየት የሚዘገንኑ፤ ለመስማት የሚሰቀጥጡ ግፎችንና ሰቆቃቸውን እንዲሁም የተዘረፉና የወደሙ ተቋማትን ስመለከት፤ በዚህ ላይ ሰሞኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከላሊበላ እንደገለጹት፤ የትግሬ ወራሪ ኃይል ገበሬው እንደ ልጁ የሚያየውን የእርሻ በሬ አርዶ ሞፈርና ቀንበሩን ፈልጦ በማንደድ እየጠበሰ መብላቱን ሲናገሩ ሳዳምጥ፤ ይሄን ልምምድ ከየት ተማረው !? ከኢትዮጵያውያን የልቦና ውቅር ባፈነገጠ አግባብ፤ እንዴት ተፈጥሮ፣ አድጎ ግዘፍ ነስቶ፣ በስጋና በእኩይ ግብር እንዲህ ሊገለጥ ቻለ !?
በዓለማችን ከ100 ሚሊዮን በላይ ቅጅዎች የተሸጠለት እስከ ዛሬ ድረስ ተወዳዳሪ ያልተገኘለት የታዋቂው፣ የተወዳጁና የፓፕ ሙዚቃዊ ዘውግ /ዠነር/ ንጉስ ማይክል ጃክሰን «ትሪለር» የተሰኘ ሙዚቃው ማጀቢያ ተንቀሳቃሽ ምስል/ክሊፕ/፤ ከፍቅር ጓደኛው ጋር በተቃጠረበት ቦታ ዙምቢ ሆኖ በመከሰቱ ስትደናገጥና ስትፈራ ያሳያል፡፡ የሙታን አጽሞች መቃብር ፈንቅለው በመነሳት (ዙምቢዎች) የሙዚቃ ስልቱን ተከትለው እየደነሱ ሲያጅቡት፤ ይህ ሳያንስ የሚያስገመግም አስፈሪ ድምፅ ከሙዚቃው ኋላ ሲሰማ ልብን ያሸብራል፡፡ በቁም ያርዳል፡፡ ብርክ ያሲዛል፡፡
በዚህ አስፈሪ ድባብ ውስጥ ተሁኖም የሙዚቃው ምትና ዜማ ስሜትንና እዝነ ህሊናን ምርኮኛ ከማድረጉ በላይ የቅንብሩን ከፍታ ያሳያል፡፡ ከ11 አመት በፊት ብዙ በሚያበረክትበት እድሜ በ50 አመቱ በሞት የተለየው ማይክል ጃክሰን በተለይ ለሙዚቃ ኢንዱስትሪው ትልቅ ማጣትና ጉዳት ነው፡ ፡ ባለብዙ ተሰጥኦ የነበረው ማይክል ጃክሰን ከሙዚቃ አቀናባሪውና ከዳንስ ኮቹ አእምሮ በላይ እንደነበር ይነገርለታል፡፡ ለመሆኑ ዙምቢ ምን ማለት ነው!? ከስብሀታዊያን ቡድን ከትህነግ/ ሕወሓት ጋርስ ምን ያመሳስለዋል!?
ዙምቢ ሰውን ለማጥቃት በጥንቆላ ወይም በአስማት መቃብር ፈንቅሎ የሚነሳና ሕይወት የሚዘራ አስፈሪ አፅምና የሙት መንፈስ ነው፡፡ ደመ ነፍስ ነው። የትግሬ ወራሪ ኃይል ከአገርና ከኢትዮጵያውያን የዘረፈውን ሀብት፤ የቀበረውን የጦር መሣሪያ፤ ተበትኖ የነበረውን ተዋጊ ኃይል እንደገና አሰባስቦና አደራጅቶ፤ ለሰብዓዊነት ሲል መንግሥት ያወጀውን የተናጠል የተኩስ አቁም እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም የአማራና የአፋር አካባቢዎችን በመውረር በሰው ልጅ ታሪክ ተሰምቶና ታይቶ የማያውቅ ሰቆቃ ግፍ ዘረፋና ውድመት ፈጽሟል። በማይካድራ የፈጸመው ዘር ማጥፋት ሳያንሰው በጭና በአጋምሳ በአንጾኪያ ገምዛ በንፋስ መውጫ በውጫሌ በጋሊኮማ ወዘተረፈ የዘር ማጥፋት፣ የጦር ወንጀልና በሰብዓዊ ፍጡር ላይ ወንጀል ፈጽሟል።
ሕፃናትን፣ እናቶችን፣ መነኮሳትን በቡድን አስገድዶ ደፍሯል። ሚስትን በባልና በልጆቿ ፊት ደፍሯል። ወንድም እህቱን እንዲደፍር አድርጓል። ክህነት ምንኩስና እንዲፈርስ አድርጓል። አብያተ ክርስቲያናትን እና መስጅዶችን አርክሷል። መጽሐፍ ቅዱስንና ቅዱስ ቁራንን ጨምሮ ቅዱሳን መጽሐፍትን አቃጥሏል። አውድሟል። ቀዳዶ መጸዳጃ አድርጓል። ከ7000 በላይ የጤናና የትምህርት ተቋማትን ዘርፏል። አውድሟል። የወሎ የወልድያ የመቅደላ ዩኒቨርሲቲዎችን ወደ 50 የሚጠጉ ፋብሪካዎችን ዘርፏል አውድሟል። በየደረሰበት ሁሉ የግለሰብ ንብረት መርፌ ሳይቀር ዘርፏል። አውድሟል።
የገበሬ የደረሰ ሰብል አጭዶ ወስዷል። የቤት እንስሳትን ዘርፏል። የተረፉት በጥይት ደብድቧል። የገበሬውን በሬ አርዶ ሞፈርና ቀንበሩን ፈልጦ በማንደድ ጠብሶ በልቷል። ባለፉት አምስት ወራት የፈጸማቸውን ኅልቆ መሳፍርት የሌላቸውን ዘግናኝ ግፎች ለተመለከተ በፈጣሪ አምሳል በተፈጠረ ሰው የተፈጸሙ ናቸው ለዚያውም የኢትዮጵያዊ የስነ ልቦና ውቅር አካል ከሆነው የትግራዋይ አብራክ የተገኘ ነው ብሎ ከማመን ይልቅ ወፍ ዘራሽ ዙምቢ ነው ቢባል ይቀላል። ለዚያውም የቆሰለ ተዋጊውን የሚገድል፤ ከእነ ሕይወቱ ከሙታን ጋር የሚቀብር፤ የተገደሉ ከፍተኛ አዋጊዎቹ እንዳይለዩ አንገት የሚቆርጥ ዙምቢ ነው።
የኦክስፎርድ የእንግሊዝኛ መዝገበ ቃላት የዙምቢ ሌላ ትርጉም፤ በዙሪያው እየሆነ ያለውን ነገር ተረድቶና ተገንዝቦ ምላሽ መስጠት የተሳነው ፡፡ የትግሬ ወራሪ ኃይል እንደ ዙምቢ በዙሪያው በአገሪቱ ከፍ ሲልም በዓለማችን እየተከናወነ ላለ ነባራዊ ሁኔታ መልስ መስጠት የተሳነው ፍዝና ድንዝ ነው፡፡ ይህ ኃይል በዙምቢ ዓለም ይኖር ስለነበር ለሕዝብ ሮሮ፣ አቤቱታና ጥያቄ ጆሮ ነፍጎ ኖሯል፡፡ የማዕከላዊ መንግሥት ሥልጣኑ ከእጁ ሙሉ በሙሉ ሲወጣም ተጭኖት ከነበረው የማንአህሎኝነትና የጀብደኝነት ድንዛዜ ገና አልነቃም ነበር፡፡
የሚያሳዝነው የእነ ሌኒን፣ ስታሊንና ማኦ አገርና ሕዝብ የማንነት ፖለቲካን፣ አብዮታዊ ዴሞክራሲንና የራስን እድል በራስ መወሰንን ለአገራችንና ለሕዝባችን አይበጅም ብለው እርም ብለው አሽቀንጥረው መጣላቸውን እንኳ ልብ ማለት ስለተሳነው ዛሬ ድረስ ጥዶ ማላዘኑን፣ ማለቃቀሱን ገፍቶበታል፡፡ ዘመኑ 21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መሆኑንና ልዩነቶች በጠረጴዛ ዙሪያ በሚደረግ ውይይት እንጂ በግጭት ከፍ ሲልም በጦርነት እንደማይፈቱ የታወቀ ቢሆንም በራሱ የቅዠት ዓለም የሚዳክረው የትግሬ ወራሪ ኃይል የሰሜን ዕዝን ክዶ በማጥቃቱ የኢፌዴሪ መንግሥት ሦስት ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ተደምስሶ ቆላ ተምቤን ከመሸገና አብዛኛዎቹ የፖለቲካና የጦር መሪዎቹ ከተገደሉና ከተያዙ በኋላ መንግሥት ለሰብዓዊነት ሲል የተናጠል የተኩስ አቁም አድርጎ ከትግራይ ሲወጣ፤ እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም በሕዝባዊ ማዕበል ዳግም ወደ አገዛዝ ለመምጣት ማሰቡ ዙምቢነቱን ያረጋግጣል።
5ሚሊዮን ሕዝብ ይዞ 115ሚሊዮን ሕዝብን በሕዝባዊ ማዕበል ለማንበርከክ፤ አንቅሮ በተፋው ሕዝብ ላይ እንደገና ለመጫን መፈራገጡ እንደ ዙምቢ ማንነቱንም ሆነ ነባራዊ ሁኔታን አለመገንዘቡን ያረጋግጣል። በዚህ ቀይ ስህተቱ ወደ ግማሽ ሚሊዮን የሚጠጉ ተዋጊዎቹንና በርካታ አዋጊዎቹን ከማጣቱ ባሻገር ከፍተኛ ወታደራዊና ፖለቲካዊ ክስረት ገጥሞታል። ከ15 ቀናት በፊት ጦርነቱ አልቋል ከማን ጋር ነው የምንደራደረው እያለ በእብሪት እንዳልደነፋ፤ ዛሬ ከደብረ ሲና በሁለት ሳምንት ድባቅ ተመትቶ ሲጠራረግ፤ ሲዘባበትበት የነበረውን የተናጠል የተኩስ አቁም ረስቶ ድረሱልኝ እያለ እየየውን እያቀለጠው ይገኛል። ተቀጥቅጦ ወጥቶ ለሰላም እድል ለመስጠት ከአማራና ከአፋር ክልሎች ወጥቻለሁ እያለ ከፍጥርጥሩ አንስቶ የተካነበትን ማምታታት ተያይዞታል።
የዙምቢ ሌላው ባህሪ የሟች ተጓዥ / ወኪንግ ዴድ/ መሆኑ ነው፡፡ ስብሀታዊው ትህነግ እንደ ዙምቢ የሟች ተጓዥ ሆኖ አራት ኪሎው ቤተ መንግሥት ባናየውም፤ የዙምቢው ትህነግ ሱስሎቭ (አይዶሎግ ) የሆኑትን እነ ጌታቸው ረዳን፣ አቦይ ስብሀትን ፣ አባይ ጸሐይዬን እንደ ዙምቢ የሟች ተጓዥ ሆነው ሸራተን፣ 2000 ሀበሻ ፣ ዮድ አቢሲኒያ፣ ዝጉብኝ ውስኪ ቤት የልጅ ልጃቸው ከሚሆኑ የሸገር ብላቴናዎች ጋር ሲዳሩና ሲቀብጡ ባናያቸውም ዙምቢው ትህነግ ግን የሟች ተጓዥ ሆኖ ከእያንዳንዱ ሰቆቃ ግፍ ሽብር አስገድዶ መድፈር ዘረፋና ውድመት ጀርባም ሆነም ፊት እሱ አለ ።
እንደ መውጫ
ዙምቢ ጥቃት ለመሰንዘር ሲል ከሞት የሚነሳ ሰው ነው፡፡ የትግሬ ወራሪ ኃይል የዚህ ዓይነት ዙምቢ ነው፡፡ አንድም ብዙም ዙምቢ ነው፡፡ አውራና ተከታይ፣ ህልቁ መሳፍርት የሌለው ጭፍራ ዙምቢዎች አሉት፡፡ ምሁራዊ ዙምቢ፣ ኢኮኖሚያዊ ዙምቢ፣ ፖለቲካዊ ዙምቢ፣ ማህበራዊ ዙምቢ፣ ወታደራዊ ዙምቢ፣ ደህንነታዊ ዙምቢ፣ የታሪክ ዙምቢ፣ ወዘተረፈ አሉት፡፡ የኢኮኖሚክስ የኖቤል አሸናፊና ተሸላሚው ፓል ክሩግማን የ«ምሁራን ዙምቢዎች» የሚላቸው ዙምቢያውያን ዋና መለያ ተጠየቃዊነትን፣ አመክኖዊነትና እውነትን መካድ ነው፡፡ እነዚህ የትህነግ ምሁራን ዙምቢዎች የጥቅምት 24ቱን የትህነግ ክህደት ሽምጥጥ አድርገው ክደው ጦርነት ተከፈተብን በማለታቸው ስንገረም ዛሬም ከዚህ ዙምቢ ጎን ቆመው የትግራዋይን ግፍና ሰቆቃ እያበዙት ነው።
ጆን ሳይድስ የተባለ የ« ፕሮስፔክት» ድረ ገፅ ጦማሪ በበኩሉ የዙምቢ ፖለቲካ የቁሞ ቀሮች ፖለቲካ ነው ይላል፡፡ አንድ ጊዜ የጨበጡትን ፖለቲካዊ አይዶሎጂ በምንም ታምር ማስጣል አይቻልም፡፡ ለአዲስ ሀሳብና ለውይይት የልቦና ውቅራቸው እንደ መቃብር ዝግ
ነው፡፡ የትግሬ ወራሪ ኃይል ወለፈንዲ መስመር እንደከሸፈ ልቡ ቢያውቅም የማንነት ፖለቲካ መጨረሻው አገር ብተና ፍርሰት እንደሆነ ግጥም አድርጎ ቢያውቅም ከቁሞ ቀር አቋሙ ዝንፍ አይልም፡፡ የአይዶሎጉ ባለቤቶች የእነ ማኦ፣ ሌኒንና ስታሊን ተከታዮች ቢተውትም በመማጸኛ ከተማው የመሸገው የትህነግ ፖለቲካዊ ዙምቢ ግን የመሸበትን አይዶሎጂ ይዤው ወደ መቃብር እወርዳለሁ እንዳለው ይዞት እየወረደ ነው። ኢኮኖሚያዊ ዙምቢው በሌብነት የተካነ፣ አልጠግብ ባይ፣ ስስታም፣ ያየው ሁሉ የሚያምረው፣ አገርን በቁሟ ግጦ መለመሏን ያስቀረ፤ እንደ መዥገር በአገር ስስ ብልት ላይ ተጣብቆ ደም የሚመጥ፤ ወቸገል የቀን ጅቦች አለቃና አውራ ነው፡፡ በአፋርና በአማራ ክልሎች የፈጸመው ዘረፋና ውድመት ለዚህ ጥሩ አብነት ነው። #እምቢ #Nomore
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን) fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ታህሳስ 14/2014