ኢትዮጵያ አሁን ላይ የገጠማት የህልውና አደጋ ከምን ጊዜውም በላይ የከፋ ነበር:: ሕወሓት መራሹ የሽብር ቡድን በአገሪቱ ላይ የጋረጠው አደጋ ብዙ የሰው ሕይወት አስከፍሏል፤ ከባድ የአገርና የሕዝብ ሀብት እንዲወደም ምክንያት ሆኗል:: ኢትዮጵያም ይህንን ችግር በራሴ አቅም ቀልብሼው የሉዓላዊነትና የግዛት አንድነቴን ላስከብር ባለች የደከመች እንጂ የጠነከረች ኢትዮጵያን ማየት የማይፈልጉ የውስጥና የውጭ ኃይሎች ያልተገባ ጫና በማድረግ የተቀናጀ ዘመቻ ከፍተውባታል:: በተለይ ጁንታው ቡድን እኔ ካልመራኋት መፍረስ አለባት ብሎ የያዘውን አቅድ ለማሳካት ያለ የሌለ ኃይሉን ከውሸት ፕሮፖጋንዳው ጋር በማዛመት በአገር በሕዝብ ላይ ከፍ ያለ ጫናን በመፍጠር ላይ ነው::
ከአንድ አመት በላይ ባስቆጠረው ጦርነት ብዙ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡ ሴቶች ተደፍረዋል፤ ሕፃናትና አረጋውያን ተንገላተዋል፡፡ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል፤ ወጣቶች በግፍ ተረሽነው በጅምላ መቃብር ተቀብረዋል፡፡ አለፍ ሲልም አስከሬናቸው ለአውሬ እራት እንዲሆንና በእሳት እንዲቃጠል ሆኗል::
ይህ ግፍና በደል ምናልባትም ኢትዮጵያዊ ከሆኑ አገርን ለ27 ዓመት ከአስተዳደሩ አካላት የማይጠበቅ ለሰሚው ግራ የሆነ ተግባር ቢሆንም ድርጊቱ ግን ተፈጽሟል:: ይህ አሸባሪ ቡድን ግፋ በርታ ከሚሉት ጥቅመኞቹ አሜሪካንና ግብጽ ጋር በመመሳጠር አገር የማውደም ሥራውን አጠናክሮ ቀጥሏል::
የምህረትና የይቅርታ እጅን የገፋው የኢትዮጵያውያን ሁሉ ጠላት የሆነው ሕወሓት፤ ዛሬ ላይ ኢትዮጵያውያን ሁሉም ነገር ከትዕግስታቸው በላይ ሲሆን ምን ሊፈጠር እንደሚችሉ ባልገመተው ሁኔታ አሳሩን እያበሉት ነው:: ያልጠበቀው ነገር የገጠመው፤ ሁሌም ተፈሪና አሸናፊ ሆኖ እንደሚኖሩ ሞኙ ልቡ የመከረው፤ ይህ ስግብግብ ቡድን ዛሬ ላይ ዕቃውን ቁስለኛውን መሰብሰብ እንኳን በማይችልበት ሁኔታ እየተቀጠቀጠ የእግሬ አውጪኝ ሽሽቱን እንደቀጠለም በየቀኑ የምናየውና የምንሰማው ነው::
ወትሮም ኢትዮጵያውያን ለፍቅር እንጂ ለጸብ የሚመች ልብ እንደሌላቸው ያልተረዳው ሕወሓት፤ ዛሬ ላይ ያድኑኛል ያላቸው ሁሉ እየሸሹትና ሥራህ ያውጣህ እያሉት ባሉበት ጊዜ የሚይዘው የሚጨብጠው ከማጣቱ የተነሳ በየደረሰበት ሁሉ የአይጥ ሥራ እየሠራ አገር እያወደመና እያጠፋ መኮብለሉን ተያይዞታል::
ሕወሓት ሲነሳ ጀምሮ በጥላቻ በመከፋፈል እንዲሁም በጥፋት መንፈስ የተነሳ ነው፡፡ ይህንን ሁኔታ ደግሞ እነ አሜሪካንና አጋሮቿ አብዝተው ይፈልጉታል:: ከዚህ የተነሳ አሜሪካንና አጋሮቿ በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉት ጫና የመንግሥትን እጅ ጠምዝዘው ከሃዲውና አሸባሪው ቡድን ጋር ድርድር ለማስገባት ብሎም ደካማና የእነሱ ጥገኛ የሆነች ኢትዮጵያን ለመፍጠር መሆኑን በግልጽ እየታየ ያለ ሀቅ ነው:: የተጠናከረ ጫና የሚያደርጉትም በደካማ አገር ውስጥ የራሳቸውን ፍላጎት ለማሳካት ነው:: ነገር ግን ኢትዮጵያውያን የውጭ ጣልቃ ገብነትን የማያስተናግዱ በመሆናቸው ምዕራባውያኑ እንደማይሳካላቸው ከማሳየታቸውም በላይ የአፍሪካ ብርሃን የነፃነት ተምሳሌት መሆናቸውን ይዘው መቀጠል ችለዋል::
ኢትዮጵያ ላይ የተዛቱት ዛቻዎች የተጣሉት ማዕቀቦች ሁሉ አገሪቱን ለጊዜው ያዳክሙ ይሆናል እንጂ ሕዝቦቿ በፍላጎታቸው የመረጡትን መንግሥት ግን የሚቀይር ሊሆን እንደማይችል ዜጎች ለመከላከያው ደጀን በመሆን የተፈናቀሉ ዜጎችን ለማቋቋም የሚደረገውን ጥረት በሙሉ ልብ በማገዝ እያስመዘገቡ ነው::
በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ወደ ግንባር መሄዳቸውን ተከትሎ ሕዝቡ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮችና አመራሮች ኢትዮጵያ ላይ የተቃጣውን ወረራ ለማክሰም ብሎም ጠላትን አይቀጡ ቅጣት ቀጥቶ ወደመጣበት ለመመለስ የተቀናጀ ሥራን በማከናወናቸው እነሆ ዛሬ ላይ በየቀኑ የድል ዜናዎች እዚህም እዚያም በመሰማት ላይ ናቸው::
በሌላ በኩል አሜሪካና ምዕራባውያኑ የግብር አምሳላቸው ጁንታው ቡድን አገር ሲከዳ ተባባሪ ሆነው ቢነሱም ሕዝቡ ዳር እስከዳር ባሳየው አንድነትና ህብረት ቅስማቸው ተሰብሮ እንኳን እርሱን ደግፈውና ተንከባክበው ዳግም አገር እንዲመራ ሊያደርጉ ቀርቶ እነሱም ሃሳባቸው ሳይሞላ እንዲያውም በራሳቸው ላይ ዘንዶ የመጠምጠም ያህል አፍሪካውያን ሁሉ እምቢኝ ለነፃነቴ ብለው እንዲነሱ በዚህ ትልቅ ፍርሀትና ሽብር ውስጥ እንዲወድቁ ሆኗል::
በሰብዓዊነትና በዴሞክራሲ ስም የምትምለው አሜሪካን በኃይል በገባችባቸው ሊቢያ፣ ሶሪያ፣ አፍጋኒስታንና ሌሎችም አገራት ፈራርሰው አሳዛኝ ሆኑ እንጂ ተገንብተው አሰፍነዋለሁ ያለችውን ዴሞክራሲ አስፍናላቸው የሰላም አየር አላገኙም:: ታዲያ ነፃነታችንን አስከብረን በኖርን ሕዝቦች ላይ አሁን የገጠመንን ወቅታዊ ችግር ተንተርሶ ለመጡብን ኃይላት ፍላጎት ማስፈጸሚያነት እንዳናገለግል እንደ ቀደመው ወግ ባህላችን በአንድነት መነሳትና መቆም ከሁላችንም የሚጠበቅ ነው::
እኛም ፖለቲከኛ አሁን ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮምሽነር ከሆኑት አቶ ግርማ ሰይፉ ጋር በተለይም ግንባር ድረስ ሄደው የተመለከቱትን የጁንታውን እኩይ ተግባር የሰራዊቱን ቁርጠኝነት የሕዝቡን ደጀንነት በተመለከተ ቃለ ምልልስ አድርገናል::
አዲስ ዘመን፦ ወቅታዊውን አገራዊ ሁኔታ እንዴት ይመለከቱታል?
አቶ ግርማ፦ ወቅታዊው የአገራችን ሁኔታ እንግዲህ ከባድ ነው፡፡ በተለይም ባለፉት አንድ አመት ከምናምን ያሳለፍነው ነገር ጥሩ አይደለም፡፡ ሕወሓት መራሹ ቡድን በአገር ላይ ከፍተኛ ችግር ደቅኖ ብዙ ነገራችን ወደዚያ እንዲዞር አስገድዶን ቆይቷል:: አሁን ደግሞ ከጥቂት ወራት በፊት መንግሥት በጀመረው የመልሶ ማጥቃት ሂደት በርካታ ስጋቶች ተጋርጠው እንዲያውም ችግሩ እየገዘፈ የሄደበት ሁኔታም ነበር:: አሁን ላይ በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ግንባር ድረስ ሄደው ራሳቸው በመሩት ጦርነት ብዙ ድሎች ከመመዝገባቸውም በላይ እንደ አገር ከገባንበት የስጋት ስሜት የተለቀቅንበት ሁኔታ ነው ያለው::
የስጋታችን ምንጭ የሆነውን ሕወሓትን ወደመጣበት ጎሬ ለመመለስ የተቃረብንበት ሁኔታ በመኖሩ በአሁኑ ወቅት በተስፋ ውስጥ ነን:: ይህም ቢሆን ግን ቡድኑ ቀላል የሚባል መረብ የዘረጋ ባለመሆኑ፤ እየፈጠረ ያለው ችግርም በቀላሉ ሊወሰድ የሚገባው አይደለም፡፡ የመጨረሻዋን የድል ጽዋ እስክንጎነጭ ብሎም አሸባሪው ቡድን ወደመጣበት እስኪመላስ ድረስ ምንም ዓይነት መዘናጋት ሊኖር አይገባም::
አዲስ ዘመን፦ እርስዎ በሕወሓት የአገዛዝ ዘመን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ላይ ብቸኛ ተቃዋሚም ሆነው በሚሠሩበት ጊዜ ይህንን ቡድን ያውቁታል፡፡ ያኔ እና አሁን ያለውን የቡድኑን አቋም ሲያዩት ምን ይሰማዎታል?
አቶ ግርማ፦ በወቅቱ እኔ ስቃወም የነበረው በጠቅላላው ሥርዓቱን ነበር፡፡ በወቅቱም የቡድኑን ወይም የሥርዓቱን አስከፊነት ከራሱ በላይ ማንንም የማይወድ መሆኑ በተለይም ደግሞ ለስልጣን ብሎ የማያደርገው ነገር እንደሌለ እረዳ ነበር:: ነገር ግን የመጥፎነታቸው ጥግ እዚህ ደርሶ እንደ እብድ ያደርጋቸዋል ብዬ አስቤ አላውቅም:: በመሠረቱ እነሱ ራሱ ይህንን ያህል አቅላቸውን የሚያስት ደረጃ ውስጥ እንደሚወድቁ የሚያውቁ አይመስለኝም:: የተጣባቸው በሽታ እየቆየ ሲሄድ እያገረሸባቸው በመሄዱ ምክንያት በዓለም አቀፍ ደረጃ መለኪያ ወይም ደረጃ ሊወጣለት የሚከብድ የብልግና ጥግ ላይ አድርሷቸዋል::
ሕወሓቶች ለዚህ ሁሉ እብደት፣ ውንብድና፣ አገር የመካድና የባንዳነት ደረጃ ላይ ያደረሳቸው ትልቁ ነገር ስግብግብነት፣ አልጠግብ ባይነት ነው፡፡ ስስት፣ ራስን አበልጦ መውደድ፣ ለዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ዳርጓቸዋል:: ተረቱ የሚለውም «አልጠግብ ባይ ሲተፋ ያድራል» አይደል? እነሱን ዓይነት ብዙ ግለሰቦች በተለያየ ሁኔታ ይኖራሉ፡፡ ነገር ግን የእነሱን ልዩ የሚያደርገው አልጠግብ ባይነታቸው በቡድን መሆኑ ነው::
ይህንን እብደታቸውን ስግብግብነታቸው ደግሞ ሀይ ከማለት ይልቅ ደጋፊና አፈቀላጤ ሆኖ አብሯቸው ሆ የሚል ቀላል ቁጥር ያልያዘ ሕዝብ መኖሩ ነገሩን አስገራሚም ውስብስብም ያደርገዋል:: በመሆኑም ይህ ሁኔታ በአንዳንድ «ቲዎሪዎች» ላይ እንዲያውም እንደዚህ ያለን ውንብድና ብዙ ሰው ስለደገፈው ትክክል ቢመስልም ትክከል ያልሆነ መሆኑን ነው::
በነገራችን ላይ እንደዚህ እንደሕወሓቶች ሁሉ ጀርመኖች በናዚ ጊዜ በተመሳሳይ አቅላቸውን ስተው እብደት ውስጥ ገብተው ነበር፤ ውጤቱም ታይቷል:: አሁን በ21ኛው ክፍለ ዘመን ላይ ግን እንደዚህ ያሉ ፍጥረቶች ተፈጥረው ለ30 ዓመት የመሩትን አገርና ሕዝብ በዚህን ያህል ደረጃ ይጎዱታል ብሎ ማሰብ ምናልባትም ልዩ ተሰጥኦን የሚጠይቅ ይመስለኛል::
እርግጠኛ ሆኜ የምነግርሽ ነገር እነሱ ራሳቸው ወደዚህ ችግር ውስጥ ሲገቡ ነገሩ ይህንን ያህል ይሆናል ብለው አልገመቱም ነበር:: ነገር ግን ውሎ ሲያድር አንዱ ነገር ሌላውን ሲወልድ እነሱም ከአንዱ ወደ አንዱ እብደት ሲሻገሩ ችግሩ ውስጥ እየሰጠሙ የማይወጡት አዘቅት ውስጥ እየገቡ መጡ እንጂ፤ በእርግጠኝነት ይህንን አልገመቱም እንዲያውም የሆነባቸው «ውሃ ሲወስድ እያሳሳቀ» እንደሚባለው ዓይነት ነው:: ችግሩ እዚህ እንደሚደርስ አላወቁትም ብዬ አፌን ሞልቼ የምናገረው ሊከተላቸው የሚችለውን ነገር ቢያውቁ ኖሮ ቆም ብለው ያስቡ ነበር፡፡ የማይጋፉትን ባላንጣ እንደገጠሙም ይረዱ ነበር፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ ቆምንለት የሚሉትን ሕዝብ በዚህን ያህል ደረጃ ለመጉዳት አደጋ ላይ ለመጣልና ይህንን ያህል ለመጨከን ባልተነሱ ነበር::
እንዲያውም የኢትዮጵያ ሕዝብ አገናዛቢ አርቆ አሳቢ ባይሆን ኖሮ እነሱ በሚሰነዝሩት ልክ ልመልስ ቢል አደጋው ከባድ ከመሆኑም በላይ እዚህች አገር ላይ ምን ዓይነት ነገር ሊፈጠር እንደሚችል ሲታሰብ ይዘገንናል:: እግዚአብሔር ይህችን አገር ይጠብቃታል የሚሉ ሰዎች እጅግ በጣም ትክክል መሆናቸውን እያረጋገጥን ነው ::
ለምሳሌ ሃይማኖታዊ ትምህርቱ የሚለው ግራህን ለመታህ ቀኝህን ስጠው ነው፡፡ ነገር ግን ስንቶቻችን ነን ይህንን ተግባራዊ የምናደርገው ቢባል እንጃ ምን ያህል እንደሚገኝ አላውቅም፡፡ አሁን ሕወሓቶች ከፈጸሙት አንጻር ኢትዮጵያውያን እያሳዩት ያለው ትዕግስት ይህንን ነገር በተግባር ያሳየ ነው፡፡ እነሱ ከሠሩት አንጻር ቢታይ አገራችን ላይ ምን ሊከሰት እንደሚችል መገመቱ በጣም ከባድ ነው:: በበኩሌ ይዘገንነኛል፤ በመሆኑም ቆሽሸው እንዳያቆሽሹን ኢትዮጵያዊነት ከፍታችንን ያሳየንበት ነው ብዬ አስባለሁ::
አዲስ ዘመን፦ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደግንባር መሄዳቸውን ተከትሎ ብዙ ኢትዮጵያውያን ፖለቲከኞች ታዋቂ ሰዎች ወደ ግንባር ተከትለው ሄደዋል፡፡ እርስዎም የዚህ አካል ነበሩ፡፡ በቦታው ከተመለከቱት ጭካኔ ጎን ለጎን ያለው ጀግንነት እንዴት ይገለጻል?
አቶ ግርማ፦ አዎ ወደግንባር ሄጄ ነበር፡፡ በዚህም በጣም ደስ የሚል የኢትዮጵያዊነት ስሜት ተሰምቶኛል::
እዚያ ስሄድ የተመከትኩት ነገር እጅግ በጣም የሚያሳዝን ከመሆኑም በላይ እቤታችን ቁጭ ብለን በቴሌቪዥን መስኮት የምናየው በጣም ትንሹ ነው እንዲያውም ቴሌቪዥን ምንም አያሳይም ማለት ይቻላል::
እንደ እኔ እንዲያውም ሁሉም ኢትዮጵያዊ በቦታው ተገኝቶ ሁኔታውን ማየት መረዳት ይኖርበታል እላለሁ:: የሚገርምሽ ነገር በጦርነቱ ምክንያት የወደሙትን ሀብቶች ስመለከት የፈጠረብኝ ስሜት ምን ዓይነት የአይጥ ባህርይ ያላቸው ናቸው የሚለው ነው:: ይህንን ስለሽ አይጥ የእኔ ማስታወሻ ደብተር ወይም ካልሲ አልያም ሌላ ነገር ምንም አያደርግላትም፤ ነገር ግን ትበላዋለች:: እነሱም እንደዚያው ናቸው:: የኮምፒዩተር የመብራት የቴሌኮም ገመድ መበጠስ፤ መድኃኒት የሚጠቅማቸው ከሆነ ይዞ መሄድ ያባት ነበር፡፡ ነገር ግን ከእቃው አውጥቶ ሜዳ ላይ መበተን ምን የሚሉት ጥፋት ነው:: የሚሠሩት ሥራ ሁሉ ከሰውኛ ባህርይ የወጣ ትርጉም የማይሰጥ በጣም የሚቀፍ የአእምሯቸውን ጤንነት የሚያጠራጥር ሆኖ ነው ያገኘሁት::
በነገራችን ላይ አንድ የባንክ ቤት የጥበቃ ሠራተኛ በተለይም በኤቲኤም ማሽኖች ላይ የደረሰውን ጉዳት እያሳየኝ ያለው ነገር እስከ አሁን በአእምሮዬ ይመላለሳል፤ «እነዚህ ሰዎች አለ ቢያሸንፉ ግን ሊያስተዳድሩን አይደለም አንዴ የሚፈልጉት ግን ይህንን ያህል ጥፋት ማድረስ ምንድን ነው» አለኝ:: በጣም ልክ ነው፤ አዎ አሸንፈው አገር ለማስተዳደር ከሆነ ሃሳባቸው ይህንን ሁሉ ውድመት ማድረስ ምን የሚሉት የክፋት ጥግ እንደሆነ ለመረዳት እንዲያው ትልቅ ተዓምራዊ ሰው መሆን ሁሉ ሳይጠይቅ አይቀርም::
በሌላ በኩል ግን ግንባር ላይ ካሉት ወታደሮች ጋር አብሮ 30 ደቂቃ መቆየት በራሱ የሚፈጥረውን የደስታ ስሜት ደግሞ ልገልጸው ይከብደኛል:: በጣም የሚገርመው ነገር እነሱ እዚያ ቦታ ላይ የተገኙት ሕይወታቸውን ሊሰጡ እሳት የሚተፋ መሣሪያ ተሸክመው ቆመው እኛ እዚያ ስለተገኘን የሚያሳዩት ፍቅርና ደስታ በጣም ያሳፍራል፡፡ እዚህ ሆነን ለመከላከያው ይህንን ያንን አደረግን የምንለው ነገር ሁሉ በጣም ያንስብሻል:: በጣም ብዙ ጀግኖች ለአገራቸው ምንም መሆን የሚችሉ ሰዎች እንዳሉንም ታይበታለሽ:: በሄድንባቸው ግንባሮች በሙሉ መኮንኖቹ ጀኔራሎቹ የሚያሳዩት ትህትና በጣም ይገርማል፤ በዚህም ኢትዮጵያዊነት በጣም ትልቅ እንደሆነም ለመረዳት መንገድ ይሆናል::
ሐኪሙና ለእርዳታ የተኛው ቁስለኛ ወታደር በቋንቋ እንኳን ሳይግባቡ እንዴት እንደሚረዳዱ ስታይ ይደንቃል፡፡ ከዚህ በላይ የእርስ በእርስ ፍቅርና አንድነት ከየት ይመጣል ትያለሽ:: ወጣቱ አሁን በቃ ሰው አለን እየተባለ እምቢ ለአገሬ ብሎ ሲቆጭ ማየት ኢትዮጵያዊነት በራሱ ኩራት በራስ መተማመን መሆኑን ትረጂበታለሽ:: ወታደሩ ዛሬ ሞቃታማው አካባቢ ውሎ ከነበር አዳሩ እጅግ በጣም ብርዳማ በሆነ ቦታ ላይ ሊሆን ይችላል፡፡ ያንን ግን እንደ ተራ ነገር ቆጥሮ ማደር መዋል በዚህ ሁሉ መሃል ድል አድራጊነት ሲታሰብ እውነት የአገር ፍቅር ያለው ወታደሩ ጋር ነው ያስብላል፡፡ ለዚህ ትልቅ ኃላፊነትና ሥራቸው ደግሞ ክብርም ሙገሳም ድጋፍም በእጅጉ የሚያንሳቸው ይሆንብኛል::
አዲስ ዘመን፦ አገር ከገባችበት ቀውስ እንድትወጣ ወታደሩ በዚህ መልክ ከሚያደርገው ተጋድሎና እያስመዘገበ ካለው ድል ባሻገር የሕወሓትን እኩይ ተግባር አክሽፈን የነገዋን ኢትዮጵያን እንዴት ነው ማየት የምንችለው?
አቶ ግርማ፦ አገራችን ከተደቀነባት ችግር እንዴት መውጣት ትችላለች የሚለውን ስናስብ አንዱና ትልቁ ነገር የአደጋውን ምንጮች መልሰው በማያንሰራሩበት ሁኔታ ማስወገድ ነው:: ይህንን ለማድረግም ሆነ የነገዋን የበለጸገች ኢትዮጵያ ለማየት ደግሞ መንገዱ ተባብረን በአንድነት መቆም ነው:: ከተባበርን የውስጥም የውጭም ጠላቶቻችንን ለመቋቋም ኃይል ይኖረናል::
በመሆኑም ኢትዮጵያውያን ልዩነቶቻችንን ሁሉ ወደጎን ጥለን ተባብረን ከቆምን ምናልባት የጊዜ ጉዳይ ይሆናል እንጂ የማናልፈው መከራ የማንሻገረው ቀን ይኖራል ብዬ አላምንም:: አንዳንዶች ኢትዮጵያ ችግር ላይ እንዳለች ይሰማቸዋል፡፡ ይህንንም በተለያዩ መንገዶች ሲገልጹ እሰማለሁ፡፡ ለእኔ ግን እንደዚያ አይደለም እንዲያውም ኢትዮጵያ እንደዚህ ጊዜ ትልቅ የታሪክ አጋጣሚና እድል ላይ ሆና አታውቅም ብዬ ነው የማስበው:: እኔ ከችግሩ ይልቅ የሚታየኝ እድሉ ነው:: ምናልባትም ኢትዮጵያ ችግር ውስጥ ትወድቅ የነበረው በዚያን በተከፋፈልንበት ጊዜና ሁኔታ እንደዚህ አድርገው አንሳፈው ቢተውን ነበር አደጋ ላይ የምንወድቀው:: የተከፋፈለን ማህበረሰብ አንድ የማድረግ ፕሮጀክታችንም በጣም ይከብድብን ነበር::
ሕወሓት ላለፉት 27 ዓመታት ሲከፋፍለን እንዳልነበር፤ አሁን ላይ በመጨረሻ የስንብት ጊዜው አንድ አድርጎን ሄዷልና ይህንን አንድነታችንን ዘላቂ ማድረግ ከመከፋፈል ትርፍ እንደሌለ በአንድነት ውስጥ ግን ትልቅ መሆን አሸናፊነት እንዳለና አገራችንም ለሁላችንም የሚበቃ ሀብት ያላት መሆኑንም ማሳያ ሆኗል::
አዲስ ዘመን ፦ ሕወሓት በከፈተብን ጦርነት ከሰው ሕይወት መጥፋት ባሻገር እንደ አገር በርካታ መሠረተ ልማቶች የሕዝብ መገልገያ ተቋማት ሆስፒታሎች የትምህርት ተቋማት ወድመዋል፡፡ እነዚህን ወደ ነበሩበት ለመመለስ ከማን ምን ይጠበቃል ይላሉ?
አቶ ግርማ፦ እንግዲህ ይህ የጥፋት መልዕክተኛ የሆነ አካል በከፈተው ጦርነት ምክንያት እንደ አገርና ሕዝብ ያጣነው ሕይወት በጣም ያሳዝናል፡፡ በሌላ በኩል ጥሪታችን የገነባናቸው ሆስፒታሎች፣ ትምህርት ቤቶችና አገልግሎት መስጫ ተቋማትም በዚህ መልኩ የጥቃቱ ሰለባ ሆነው እንዳልነበር ሲሆኑ የመመልከትን ያህል ልብ የሚያደማ ነገር አለ ብዬም አላስብም:: ይህ እኩይ ተግባር ምናልባትም እንደ አገር በጣም ወደኋላ የመለሰን ነው ብዬ አስባለሁ:: ነገር ግን የወደመ ነገር ተመልሶ አይመጣም የተቃጠለ ነገር አመዱ ይተርፍ ይሆናል እንጂ የሚፈይደው አንዳችም ነገር የለም፡፡ ይህንን ሁኔታ ለመቀየር አንደኛ ጠንክረን መስራት ሁለተኛ አንድነታችንን ከዚህ በበለጠ ሁኔታ ማጠናከርና የጠላትን ቅስም መስበር አለብን::
ከላይ እንደገለጽኩት ኢትዮጵያ አሁን ላይ ከገጠማት ፈተና ይልቅ የበራላት ብርሃንና አዲስ እድል በጣም የሚበልጥ በመሆኑ እሱም መጠቀም ያስፈልጋል:: አሁን ላይ አዲስ ግንባታ አዲስ ትብብር አዲስ መነሳሳት በጠቅላላው አዲስ መንፈስና አስተሳሰብ ያስፈልገናል::
ዛሬ በሕወሓቶች የፈረሰብን የጭቃ ቤት ከሆነ ነገ የድንጋይ አድርገን መስራት ይኖርብናል፡፡ የድንጋይ ቤት ከሆነም ያጣነው ነገ በእምነበረድ አስውበን መስራት አለበን፡፡ በመሆኑም የጠፋብንን መተካት ብቻ ሳይሆን የጠፋብንን ብር በወርቅ መተካት ይጠቅመናል፡፡ ለጠላቶቻችን ማሳየት የሚያስፈልገን ይህንን ነው:: በእርግጠኝነት ደግሞ ኢትዮጵያውያን ላይ ከተፈጠረው የአንድነትና የአብሮነት ስሜት አንጻር ይህንን ማድረግ እጅግ በጣም ቀላል ነው::
አዲስ ዘመን፦ አገር ባቀረበችው ጥሪ መሠረት በያዝነው ወር 1ሚሊዮን ያህል ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው ይመጣሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ይህስ ለእኛ ምን ማለት ነው? በጠላቶቻችን ዘንድስ የሚኖረው አሉታዊ ገጽታ ምን ይመስላል?
አቶ ግርማ፦ በመጀመሪያ እነዚህ አንድ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የአገራቸውን የመሪያቸውን ጥሪ ተቀብለው ወደአገር ቤት ለመምጣት መወሰናቸው በራሱ ትልቁን ሚናቸውን ተወጥተዋል የሚያስብል ነው:: እስከ አሁን ባለው መረጃ እየመጡ ያሉት ኢትዮጵያውያን በአገራቸው ላይ ተሟርቶ የነበረውን ትልቅ ሟርት አክሽፈዋል:: በተለይም እየመጡ ያሉት የሌላ አገር ዜግነት ያላቸው ትውልደ ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ ነገር ግን ይህችን አገር ለቃችሁ ጥፉ እየተባለ ባለበት ወቅት ትልቅ ውሳኔ ወስነው እኛማ አገራችን እንገባለን ብለው ወደ አገራቸው በመምጣት ሟርቱን ማክሸፋቸው ትልቅ ስኬት ነው::
በመቀጠል ወደዚህ ለመምጣት ትኬት ቆርጠዋል፤ ቪዛ ይከፍላሉ፡፡ እዚህ ሲመጡ ደግሞ ብዙ ነገሮችን ያወጣሉ፡፡ ይህ ደግሞ በተለይም በጦርነት ምክንያት የተዳከመውን ኢኮኖሚያችንን እንዲያንሰራራ በማድረግ በኩል ትልቅ ሚና ይኖረዋል:: በመሆኑም ኢትዮጵያውያን በዚህን መልኩ ለአገራቸው አፋጣኝ ምላሽ መስጠታቸው እርግጠኛ ነኝ የጠላትን ቅስም የሚሰብር ለአገራችን ደግሞ የትንሳኤዋ ጊዜ ሩቅ እንደማይሆን ያሳየ ነው ::
አዲስ ዘመን፦ እንደ ኢንቨስትመንት ቢሮ እነዚህ ዳያስፖራዎች ሀብታቸውን እዚሁ ኢንቨስት አድርገው እንዲሄዱ የተመቻቸ ነገር ይኖር ይሆን?
አቶ ግርማ፦ አዎ! እንደ ኢንቨስትመንት ቢሮ አንዳንድ ቅድመ ዝግጅቶች እየተደረጉ ነው:: በተለይም እነዚህ ዳያስፖራዎች አገራቸው ገብተው ከሚገዟቸው የፍጆታና አላቂ ዕቃዎች በተጨማሪ ኢንቨስት አድርገው እንዲሄዱ እናበረታታለን:: አብዛኞቹ ትውልደ ኢትዮጵያውያን በአንድም ይሁን በሌላ ምክንያት ወደ አገራቸው መግባት ሳይችሉ እንኳን ዛሬ ነገ እያሉ የኖሩ በመሆኑ አሁን ላይ አገራቸው መጥተው ሀብታቸውን አፍሰው ቢሄዱ በስድስት ወርም በአመትም የመምጣት ዕድሉ እንዲኖራቸው ለማድረግ ኢንቨስት እንዲያደርጉ እናበረታታቸዋለን:: ኢንቨስት ያደረገ ሰው ደግሞ ሀብቱን ጥሎ ሌላ አገር አይቀመጥም፡፡ ኢንቨስትመንቱን ለማስፋፋት ይሠራል፡፡ ይህ ከአገራቸው ጋር የበለጠ እንዲተሳሰሩ ከቤተሰቦቻቸው ጀምሮ ለሌሎች ዜጎች የሥራ እድል እንዲፈጥሩም ያደርጋቸዋል::
አዲስ ዘመን፦ ይህ እንዲሆን ግን ቢሮው ከማበረታታት ባሻገር የፈጠረው ምቹ ሁኔታ እንዴት ይገለጻል?
አቶ ግርማ፦ ኢትዮጵያ ምቹ የአየር ጸባይ ተስማሚ መልከዓ ምድር ያላት አገር ናት፡፡ ይህ ደግሞ የሰው እጅ ያልተጠበበበት የፈጣሪ ሥራ ነው፡፡ ይህንን ወደ ሀብት እንዲቀይሩ ለማድረግ በተቻለ ሁኔታ ሳቢና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ተዘጋጅተናል:: በነገራችን ላይ የእኛን ቢሮ አገልግሎት ለማግኘት ዳያስፖራ መሆን አያስፈልግም::
ነገር ግን እነዚህ አካላት በተቻለ መጠን ከቢሮክራሲ የጸዳ አገልግሎት እንዲያገኙ ጉዳዮቻቸው በፍጥነት ሕግና ደንብን በተከተለ ሁኔታ እንዲፈጸሙ ያላሰለሰ ጥረት እናደርጋለን::
አዲስ ዘመን፦ የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ባደረገው ልዩ ስብሰባ እየተካሄደ ካለው ጦርነት ጋር በተያያዘ የተፈጸሙ የመብት ጥሰቶችን የሚያጣራ ዓለም አቀፍ መርማሪ አካል ለማቋቋም የቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ እንዴት ተመለከቱት?
አቶ ግርማ፦ ማንም የፈለገውን ውሳኔ ማሳለፍ ይችላል፤ ዋናው ነገር እኛ ጋር ተቀባይነት ያገኛል ወይ? የሚለው ነው፡፡ ይህ የውሳኔ ሀሳብ በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ውድቅ ሆኗል:: በነገርሽ ላይ አፍሪካን በእጅ አዙር የቅኝ ግዛት ውስጥ ለማስገባት ለሚፈልጉ ኃይሎች እኛ ኢትዮጵያውያን እምቢተኞች መሆናችንን ማሳየት አለብን፤ በመሠረቱ እያሳየናቸውም ነው:: እኛ እንደ አንድ ብዝሀነት እንዳለው (ከለርድ ሕዝብ) እነሱን ነጠላ (ከለርለስ) ብለን መንገር ይኖርብናል:: የተሳሳተም ቢሆን የምንፈልገውን ነገር እኛ ብቻ ነን እንጂ የምናደርገው እነሱ የሚወስኑልን ወይም የሚያደርጉልን ነገር እንደሌለ በግልጽ ማሳወቅ ብሎም የእነሱን በማር የተለወሰ መርዝ የምንቀበል ጅሎች እንዳልሆንን መንገር ይገባናል::
እኔ በበኩሌ ይህ ውሰኔ የሚያሳስበኝም ትርጉም የምሰጠውም ነገር አይደለም:: መንግሥትም አቋሙን ግልጽ አድርጎ ነግሯቸዋል:: ይህንን ሁሉም ዜጋ አክብሮ “ በቃ” (NO MORE) ብሎ መቀጠል አለበት::
አዲስ ዘመን፦ ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ::
አቶ ግርማ፦ እኔም አመሰግናለሁ፡፡
ዕፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 14/2014