በአሁኑ
ወቅት ከየአቅጣጫው ኢትዮጵያ
ላይ ተነጣጥረው የሚወረውሩት
ቀስቶች በእጅጉ ተበራክተዋል፡፡
በስውር የታዩ የነበሩት
የምዕራባዊያን የተንኮል እጆች
በግልጽ ፍንትው ብሎ
እየታዩም ይገኛሉ፡፡
ምዕራባዊያኑ ከመቶ ዓመታት
በላይ በቋጠሩት የቂም
ቋጠሮ ኢትዮጵያን ለማሸማቀቅና
ለማንበርከከ አበክረው ቋምጠዋል፡፡
አሁን ላይ ግን ምኞታቸው እንዲያሳካላቸው በመረጡት የአሸባሪ ቡድን ስብስብ በኩል ቅዥታቸውን ዳግም እውን ለማድረግ መፍጨርጨር ይዘዋል፡፡ከጥንስሱ ከአሸባሪ ሕወሓት ጋር የጠበቀ ግንኙነት ያላቸው በመሆኑ ድብቁን ዓላማቸው ለማሳካት ይረዳቸው ዘንድ እሱኑ እንደፈረስ እየጋለቡ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ቆርጠው ተነስተዋል፡፡
ተላላኪና ደካማ መንግሥት እንዲኖር ጽኑ ፍላጎት ያላቸው እነዚህ አካላት የማይታዘዝላቸው መንግሥትና አገር የማፈራራስ የተካኑበት ለመሆኑ እነ ሶሪያ፣ ሊቢያ ህያው ምስክሮች ናቸው፡ ፡በተለይ የአፍሪካ ሀገራት አድገው እራሳቸውን እንዲችሉ ሳይሆን ሁልጊዜ ተመጽዋች ሆነው እንዲኖሩ አበክረው የሚሰሩ መሆናቸውም ከአለም ያልተሰወረ ሃቅ ነው፡፡
ለዚህም ነው በሰብዓዊ እርዳታ ሽፋን የበግ ለምድ ለብሰው ስውር ዓላማቸውን የሚያካሂዱት፡፡ ሴራቸው ሲገለጥ ደግሞ የሚይዙት የሚጨብጡት ያጣሉ፡፡ በመንግሥት ላይ እያጉረመረሙ በውስጥ ጉዳዮቻችን ሳይቀር ጣልቃ ለመግባትና አዛዥ ለመሆን ይፈልጋሉ፤ የማዕቀብ መዓት ለማዝነብ ይዝታሉ፡፡
ግርም የሚለው ደግሞ ለራሳቸው የሚጠየፉት አሸባሪ በኢትዮጵያ ላይ እንዲሰለጠን ፈቃድ ለመስጠት ሲዳዳቸው እንመለከታለን፡፡ ተቆርቋሪነታቸውም በኢትዮጵያ ውስጥ ጉዳይ ሳይቀር ጣልቃ በመግባት የአገር ልዑላዊነት እስከመድፈር ያለ አቋም እንዳላቸው በተደጋጋሚ ሲገልጹ ይስተዋላል፡፡ እንዲሁ ማዕቀብ ለመጣል ዛቻና ማስፈራሪያዎችን በማዥጎድጎድ እጅ ለመጠምዘዝ የሚያደርጉት ሙከራ የለም፡፡
ይህ ሁሉ ደግሞ ታዛዥ እና ተላላኪ እንዲሁም ደካማ መንግሥት ለመመሥረት ያላቸው ፍላጎት በገሃድ የሚያሳይ ነው፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት እንኳን በዓመት ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ከኢትዮጵያ ጉዳይ ውጪ ሌላ አጀንዳ የሌለ እስኪመስል ድረስ ስለ ኢትዮጵያ ጉዳይ ለመምከር በሕጉ ያስቀመጠውን ደንብ በመጣስ ከአሥራ አንድ ጊዜ በላይ ተሰብስቧል፡፡ ታዲያ አንድን አገር አጀንዳ አድርጎ በየጊዜው መሰብሰብ የጤና ነው ማለት ይቻላል፡፡
ዛቻ ማስፈራሪያ በተጨማሪ ማዕቀብ ለመጣል ቀዳሚ የሆነችው አሜሪካ የኢትዮጵያ ሰላም ጉዳይ አስጨንቋት ይሆን ወይ በየጊዜው መግለጫ የምትሰጠው፡፡ ውስጡ መመርመር አለበት፡፡ እውን በኢትዮጵያ ያለው የሰብዓዊ መብት የሚጎዱ ዜጎች ጉዳይ የሚያስጨንቃት ስለሆነ ነው በአጎዋ ንግድ ላይ ማዕቀብ በመጣል ሌላ ተጎጂዎች የምትፈጥር፡፡ በዚህ ምክንያት የሚጎዱ ዜጎች ጉዳይ ለምን አላሳሰባትም ብለን ልንጠይቅ ይገባል፡፡
ሌላው በኢትዮጵያ ላይ የሚዲያ ዘመቻ በመክፈት የሐሰት ፕሮፖጋንዳ በመንዛት የስነልቦና ጦርነት እያካሄድ መሆኑ ይታወቃል፡፡ እንደ ሲኤንኤን፣ ቢቢሲ ፣ አልጀዚራ እና ሮይተርስ ባሉ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን አውታሮቻቸው አማካይኝነት የተዛቡና የተሳሳቱ መረጃዎች ሆን ብለው እያሰራጩ ይገኛሉ፡፡ ይህም የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ስለኢትዮጵያ ያለው አመለካከት የተዛባ እንዲሆን የተሸረበ ሴራ መሆኑ በቀላሉ መረዳት የማያስቸግር ነው፡፡
በአሁኑ ወቅትም ምዕራባዊያኑ ቀዳሚ አጀንዳቸው ኢትዮጵያ ትሁን እንጂ፤በመላው አፍሪካ ላይ የመጣ መሆኑን ብዙዎቹ እየተረዱት ነው፡፡ አፍሪካዊያኑ ይህ የኢትዮጵያ ጉዳይ ብቻ ነው፤ጣልቃ ገብነታችሁን አቁሙ፤ የአፍሪካ ጉዳይ ለእኛ ለአፍሪካዊያን ተውልን እያሉ ጽምጻቸውን እያሰሙ ይገኛሉ፡፡
ከምዕራባዊያን ሚዲያዎች በኢትዮጵያ ላይ እያደረጉ ያለውን የተዛባና የተሳሳተ አመለካከት በግልጽ እየተቃወሙት ናቸው፡፡ በርካታ አፍሪካዊያን ከኢትዮጵያ እና ከህዝቦቿ ጎን በመቆም አይዟችሁ የአድዋ ኩራቶቻችን ዛሬ ድሉ የእናንተ ነው በማለት ስሜታቸውን እየገለጹ ይገኛሉ፡፡
የኢትዮጵያ ህመም ከተሰማቸው ውስጥ ጥቂቶችን ለማንሳት ያህል፤በአፍሪካ ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራው ፊውቸሪካል የተባለ የዩጋንዳ ዘጋቢ ጋዜጠኛ አንዱ
ነው፡፡ ጋዜጠኛው በትዊተር ገጹ ባስተላለፈው መልዕክቱ ‹‹የአፍሪካ መግቢያ በር በኢትዮጵያ በኩል መሆኑን አሜሪካኖች ጠንቅቀው ያውቃሉ። ኢትዮጵያን ማንበርከክ ከቻልን፣ ቀሪዎቹ ከዋሽንግተን በተላከ አንድ የቃል ትዕዛዝ ይንበረከካሉ ብለው ነው የሚያምኑት፤ ስለዚህም ነው ኢትዮጵያን እየተዋጉ ያሉት›› ብሏል ፡፡‹‹ምናልባት ይህን ጉዳይ አሁን ላናደንቀው እንችላለን፤ ነገር ግን ኢትዮጵያውያን የአፍሪካን ጦርነት እየተዋጉ ነው›› ሲልም አስፍራል፡፡
ሌላ ኬንያዊው ጋዜጠኛ ጆምቦ ኦንያንጎ በበኩሉ ‹‹ከታሪክ የምንረዳው ኢትዮጵያውያን ብዙ ፈተናዎችን ተጋፍጠው በአሸናፊነት ማለፍ እንደሚችሉ ነው›› ሲል ለኢትዮጵያ ያለውን ክብርና የአልሸነፍ ባይነት ተጋድሎ በአድናቆት ገልፆታል፡፡
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒዮ ብሊንከን ጋር በመሆን መግለጫ የሰጡት የኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሬይቸል ኦማሞ በበኩላቸው፣ኢትዮጵያ የራሷን ችግር በራሷ የመፍታት አቅም አላት ሲሉ መናገራቸውን አድምጠናል፡፡ በኢትዮጵያ ህዝብ ጥንካሬ እና ጥበብ ማመን አለብን፤ እንደጎረቤት አገር አሁን ለተጋረጡባት ችግሮች በሙሉ መፍትሔ እንደምታገኝ እናምናለንም ማለታቸውን አንዘነጋውም፡፡
ታዲያ አፍሪካውያን እንዲህ ያንገበገባቸው የጉዳዩ ባለቤት የሆንን እኛ ኢትዮጵያውን እንዴት ነው የማንገበገበው? አሸባሪ ሕወሓት በአማራ ክልልና በአፋር ክልል ባደረገው ወረራ የውጭ አገር ዜጎች (ነጮች) ሳይቀር መሳተፋቸው መንግሥት መግለጹ የሚታወስ ነው ፡፡
እናም አሁን ከፊታችን ተጋፍጦ እየተዋጋ ያለው አሸባሪ ሕወሓት ብቻ ሳይሆን በቴክኖሎጂ ከኛ ከሚበልጡ የውጭ ኃይሎች ጋር መሆኑን ገብቶናል፡፡ ስለዚህ አገራችን የገጠማትን ዘርፈ ብዙ ፈተናዎችን ለመጋፈጥ በአገር ውስጥና በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን በሙሉ በነቂስ ተሰልፈዋል፡፡ የአሁኑ ጦርነት ዳግማዊ አድዋ ጦርነት የሆነበት አንዱ ምክንያት ይሄው ነው፡፡
የፈረሰና የተበተነ የመሰለው የኢትዮጵያውያን አንድነት እንደ ብረት ጠንክሮ ጠላት ድባቅ እየተመታ ይገኛል፡፡ የውጭ ኃይሎች ለሚሹት ዘመናዊ ባርነት በፍጹም የማይገዙት ኢትዮጵያውያኑ ጠላት የሰበቀውን ቀስት እየሰባበሩ ዶግ አመድ እያደረጉት ነው፡፡ ኢትዮጵያ በታሪክ ተሸንፋ አታውቅምና ጀግኖች አባቶቻችን ጣሊያንን አሳፍረው በአድዋ ላይ የተጎናጸፉትን ድል በእኛ ኢትዮጵያውያን ሊደገም ጊዜው አሁን ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ እንዳሉት ‹‹ኢትዮጵያ አትፈርስም፣ አትበተንም ጠላቶቿን አሸንፋ የአፍሪካ ፈርጥና ምሳሌ ትሆናለች›› በአድዋ የደመቀው የነጻነት ቀን ዛሬም ለዘመናዊ ባርነት ሳይንበረከክ ጠላትን ድል ነስቶ ዳግም አድዋ እውን ይሆናል፡፡ ምዕራባዊያኑ ዛሬ የሐሰት ፕሮፖጋንዳ በተናገሩበት አንደበታቸው ሳይዋጥላቸውም ቢሆን የዳግም አድዋ ድል የሚያበስሩበት ቀን ሩቅ አይደለም፡፡
ኢትዮጵያ ታሸንፋለች ቸር እንሰንብት ፡፡
ትንሳኤ አበራ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 14 ቀን 2014 ዓ.ም