ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ በዚምባብዌ ላይ ጥላው የነበረውን ማዕቀብ ለተጨማሪ አንድ ዓመት አራዝመውታል፡ ፡ የፕሬዚዳንት ኤመርሰን ምናንጋግዋ አዲሱ መንግሥት በአሜሪካ የውጭ ፖሊሲ ላይ አደጋየደቀኑ ርምጃዎችን እየወሰደ በመሆኑ ማዕቀቡ መራዘሙን ፕሬዚዳንት ትራምፕ ተናግረዋል፡፡
የደቡብ አፍሪካውን ፕሬዚዳንት ስሪል ራማፎሳን ጨምሮ የሌሎች የአፍሪካ አገራት መሪዎች ዜምባብዌ ከገባችበት የምጣኔ ሀብት ቀውስ እንድትወጣ የተጣለባት ማዕቀብ እንዲነሳላት ጥሪ አቅርበው የነበረ ቢሆንም፤ የአሜሪካ ምላሽ ግን ማዕቀቡን ማራዘም ሆኗል፡፡ ፕሬዚዳንት ትራምፕ የማዕቀቡን መራዘም አስመልክቶ በሰጡት አጭር መግለጫ፤ ‹‹የዚምባብዌ ፖለቲከኞች ስትራቴጂዎችና ድርጊቶች በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ላይ አደጋ መደቀናቸውን ቀጥለዋል፡፡
በመሆኑም የማዕቀቡ መራዘም አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል›› ብለዋል፡፡ አሜሪካ በዚምባብዌ ላይ ማዕቀብ የጣለችው የአገሪቱ መንግሥት የዜጎችን ሰብዓዊ መብቶች ይጥሳል በሚል መነሻ ነበር፡፡ የፕሬዚዳንት ኤመርሰን ምናንጋግዋ መንግሥት በመገናኛ ብዙኃን ነፃነት ላይ ገደብ የሚጥሉ ሕጎችን እስካላነሳና መንግሥትን መቃወምን እስካልፈቀደ ድረስ ማዕቀቡ እንደሚቀጥል የአሜሪካ ባለስልጣናት ገልፀዋል፡፡ እንደባለስልጣናቱ ገለፃ፣ በአሁኑ ወቅት ፕሬዚዳንት ኤመርሰን ምናንጋግዋንና የቀድሞውን ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤን ጨምሮ 141 ግለሰቦችና ድርጅቶች ማዕቀብ ተጥሎባቸዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ምናንጋግዋ የዜምባብዌ ገዢ ፓርቲ (ZANU-PF)ን ጨምሮ፤ በቀድሞው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ የአስተዳደር ዘመን አሜሪካ ማዕቀብ የጣለችባቸው ግለሰቦችና ድርጅቶች ማዕቀቡ እንዲነሳላቸው ጠይቀው እንደነበርይታወሳል፡፡ ዚምባብዌ በአሁኑ ወቅት ካለፉት አስር ዓመታት ወዲህ የከፋ ነው በተባለ የምጣኔ ሀብት ቀውስ ውስጥ ትገኛለች፡፡ አገሪቱ ያላት የመጠባበቂያ ገንዘብ በእጅጉ እንደተመናመነ ይነገራል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም፤ የነዳጅ እጥረት ደቡብ አፍሪካዊቷን አገር ከባድ ፈተና ውስጥ ዘፍቋታል፡፡ የአገሪቱ መንግሥት ባለፈው ጥር ወር ይፋ ያደረገው የ150 በመቶ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ዜጎችን ለአደባባይ ተቃውሞ ዳርጎ ከእስራትና ብጥብጥ ባለፈ የሕይወት ዋጋ አስከፍሏል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 27/2011
በአንተነህ ቸሬ