ኢትዮጵያ የተቃጣባትን ወረራ በቁርጥ ቀን ጀግኖች ልጆቿ ድባቅ መምታት በቻለችበት በዚህ ወቅት ሁለተኛ የጦርነት ግንባር የሆነውን ኢኮኖሚያዊ ጦርነት አሁንም እየተጋፈጠች ትገኛለች። ከተፈጸመባት ወረራ ባሻገር በኢኮኖሚ የጦርነት አውድ የምርትና የሸቀጦች ዋጋ መናር እንዲሁም አጠቃላይ የኑሮ ውድነት አገሪቷን በእጅጉ እየተፈታተናት ይገኛል። በተለይም በከተሞች አካባቢ በግብርና እና በሸቀጦች ምርት ላይ የሚስተዋለው ያልተገባ የዋጋ ንረት በዜጎች ላይ ከፍተኛ ጫና እያደረሰ በመሆኑ መንግሥት የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት የተለያዩ እርምጃዎችን ሊወስድ ተገዷል።
በመሆኑም በሸቀጣ ሸቀጥና በግብርና ምርት አቅርቦት ዙሪያ ያለውን ችግር ለመፍታት የኅብረት ሥራ ማኅበራት በሰንበት ገበያ ለኅብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ ምርቶችን እንዲያቀርቡ እየተደረገ ነው። የኅብረት ሥራ ማኅበራት ካላቸው ጉልህ ሚና አንጻር የገበያ ተደራሽነታቸውን ለማስፋት በርካታ ሥራዎችን በማከናወን የድርሻቸውን እየተወጡ ነው።
በምርት አቅርቦትና ግብይት ላይ ከፍተኛ ድርሻ ካላቸው አምራቾችና ሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት፣ መንግሥታዊ ድርጅቶች፣ ኢንዱስትሪዎች፣ አስመጪዎች፣ አቀናባሪዎችና ታላላቅ ግዢ ከሚፈጽሙ ተቋማት ጋር ቀጥተኛ የግብይት ትሥሥር መድረኮች በማመቻቸትና ግብይት እንዲፈጸም የውል ስምምነቶችን በመፈፀም የግብርና እና የሸቀጦች ምርት አቅርቦት ችግር እንዲፈታ ጥረት እየተደረገ ነው። እስካሁን በተደረገው የግብይት ትስስር ጥምረት ዘርፉ በአገሪቱ በተለይም በከተሞች አካባቢ የሚስተዋል የዋጋ ንረትና የምርት አቅርቦት እጥረትን በማቃለል አገራዊ የገበያ ማረጋጋት እንዲፈጠር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል። በተለይም በቅርቡ የተጀመረው የእሁድ ገበያ ለዚህ አንዱ ማሳያ ነው።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተለየ መልኩ የኅብረት ሥራ ማኅበራትን በፋይናንስ በመደገፍ የእሁድ ገበያ ማዕከላትን በአምስቱም የከተማዋ ማዕዘናት ከፍቶ የጀመረው የሸቀጥና የግብርና ምርት አቅርቦት ዋጋን በማረጋጋት የላቀ ሚናውን እየተወጣ ነው። ነዋሪዎችም የሳምንት አስቤዛቸውን በተመጣጣኝ ዋጋ መሸመት እንዳስቻለቸውና በተወሰነ መጠን የኑሮ ውድነቱን ማረጋጋት እንደቻለ በተለያየ ጊዜ ሲገልጹ ተደምጧል።
በአዲስ አበባ ከተማ የተጀመረውና ተስፋ ሰጪ ነው የተባለለት የእሁድ ገበያ በሁሉም የክልል ከተሞች በማስፋትና በማጠናከር የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ ተጨማሪ የገበያ ቦታዎችን በማዘጋጀት ዘላቂና አስተማማኝ የግብይት ትስስር በመፈጸም በአገሪቱ እየታየ ያለውን የኑሮ ውድነት በዘላቂነት ለመፍታት እየተሠራ መሆኑን የገለጹት በኢትዮጵያ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን የኅብረት ሥራ ግብይት ዳይሬክተር ወይዘሮ ይርጋለም እንየው ናቸው። ዳይሬክተሯ እንደገለጹት፤ በአዲስ አበባ ከተማ የተጀመረው የእሁድ ገበያ በአሁኑ ወቅት በ11 የተለያዩ አካባቢዎች ተግባራዊ ሲሆን በቀጣይም ተጨማሪ ዘጠኝ የገበያ ቦታዎችን በማዘጋጀት ገበያውን የማስፋትና የማጠናከር ሥራ ተጀምሯል። ይሁንና የሚታዩ የአሠራር፣ የአፈጻጸምና የአቅርቦት ተግዳሮት በመኖራቸው ችግሮቹን በመፍታት የሸማቹን ማኅበረሰብ ፍላጎት ለማሟላት ይሠራል ብለዋል።
ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ የእሁድ ገበያው ለሰባት ተከታታይ ሳምንታት የተከናወነ መሆኑን ያነሱት ዳይሬክተሯ፤ በአንድ የእሁድ ገበያ ብቻ እስከ 13 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ የምርት ግብይት እየተከናወነ መሆኑን ነው የተናገሩት። በዚህም 505 የሚደርሱ ምርት አቅራቢ ድርጅቶች ተሳትፈዋል።
በቀጣይም የእሁድ ገበያውን በማስፋት እንዲሁም የሚታዩ የአፈጻጸም ችግሮችን በመፍታት ውጤታማ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን ይናገራሉ። በዚህ ሂደትም 132 የሚደርሱ ሸማች የኅብረት ሥራ ማኅበራት፣ 60 የሚደርሱ አምራች የኅብረት ሥራ ማኅበራትና 20 የሚደርሱ የኢንዱስትሪ ባለቤቶችና ሌሎች በምርት አቅርቦት ተቋማት ይሳተፋሉ። ይህም ሳምንታዊ የሽያጭ መጠን ከ13 ሚሊዮን ወደ 20 ሚሊዮን ያድጋል የሚል ግምት አላቸው።
ከዚህ በተጨማሪ የአምራች ሸማች የግብይት ትስስርን በማጠናከር የምርት አቅርቦት ችግርን ለመፍታት ሥራዎች እየተሰሩ ነው። የእሁድ ገበያውን ለማስፋትና ለማጠናከር የተጀመረው ሥራም በአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ በሚመራው ብቻ 20 የሚደርሱ የገበያ ቦታዎች ይኖራሉ።
በእነዚህ 20 የገበያ ቦታዎች ደግሞ የሚሳተፉ የኅብረት ሥራ ማህበራት፣ የኢንዱስትሪ ባለቤቶችና ሌሎች የንግድ ተዋናዮች ቁጥርም እየጨመረ ይመጣል ማለት ነው። ከዚህ በተጨማሪም በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደርና በአምስት ክልሎች ማለትም አማራ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብ፣ ሲዳማና ቤኒሻንጉል ዋና ከተሞች ላይ የአዲስ አበባ ከተማን ተሞክሮ በመውሰድ በተመሳሳይ የእሁድ ገበያን በመጀመር አምራቹ የምርቱ ፍትሐዊ ተጠቃሚ እንዲሆንና ሸማቹም ምርቶቹን በተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘት እንዲችል የሚደረግ መሆኑን ያስረዳሉ።
ለዚህም ክልሎች ካላቸው ነባራዊ ሁኔታ በመነሳት የራሳቸውን ዕቅድ አቅደው በተያዘው በጀት ዓመት በአንድም ይሁን በሁለት ቦታዎች ላይ የእሁድ ገበያን መጀመር ያለባቸው መሆኑን የጠቆሙት ዳይሬክተሯ፤ ለተግባራዊነቱም አቋም ይዘው እየሠሩ መሆኑን ነው የተናገሩት። ከአዲስ አበባ ከተማ ጋር በተመሳሳይ ከፍተኛ የዋጋ ንረት የሚታይባቸው ድሬዳዋ ከተማን ጨምሮ እንደ አዳማ፣ ሀዋሳ፣ ባህርዳርና አሶሳ ዓይነት ትላልቅ ከተሞች ላይ የሚታዩ የዋጋ ንረቶች አሉ።
በመሆኑም አምራችና ሸማቹ በቀጥታ የሚገናኝበትን የእሁድ ገበያ በማስፋት ሸማቹ ማኅበረሰብ በተመጣጣኝ ዋጋ መሸመት እንዲችልና አርሶ አደሩም ተጠቃሚ በመሆን የዋጋ ንረቱን ለማረጋጋት የእሁድ ገበያው ዓይነተኛ ሚና ይጫወታል ተብሎ ይጠበቃል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ኃላፊ አቶ አደም ኑሪ በበኩላቸው፤ በከተማችን በተጀመረው የእሁድ ገበያ ላይ ያሉትን ደካማ ጎኖች ለማረም እንዲሁም በጎ ነገሮችን ደግሞ ለማስቀጠል እየተሠራ መሆኑን ነው የገለጹት።
በተለይም የምርት አቅርቦቱ ዘላቂና አስተማማኝ እንዲሆን ጥረት እየተደረገ ነው። አምራቾች አቅራቢ ከሆኑ ሸማች የኅብረት ሥራ ማህበራት፣ ጅምላ ነጋዴዎች፣ የፋብሪካ ባለቤቶችና ሌሎችም የዘርፉ ተዋናዮችን በማገናኘት ዘላቂ የምርት አቅርቦት ለመፍጠር እየተሠራ መሆኑን ይገልጻሉ። የእሁድ ገበያ ሲጀመር ዋና ዓላማ አድርጎ የተነሳው ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ነው።
ይህም ማለት አምራቹ ለለፋበትና ላፈሰሰው ጉልበት ዋጋ የሚያገኝበት እንዲሁም ደግሞ ሸማቹ ማኅበረሰብ በተመጣጣኝ ዋጋ የተለያዩ ምርቶችን መሸመት የሚቻልበት ገበያ ነው። ይህ ገበያ ሌሎች ከዚህ በፊት የነበሩ ገበያዎችን የሚተካ ወይም የሚያጣጥል ሳይሆን ነባር ገበያዎችን የሚያግዝ ነው። ከዚህ ዓላማ በመነሳትም እስካሁን ባለው ሂደት ውስጥ የእሁድ ገበያው ጥሩ ተሞክሮ የተገኘበት ስለመሆኑ ነው አቶ አደም ያብራሩት። የእሁድ ገበያው ሲጀመር በቀን እስከ አምስት ሚሊዮን ብር መገበያየት የተቻለ ሲሆን በአሁኑ ወቅትም ሰባተኛ ዙር የደረሰው ይህ ገበያ በአንድ ቀን 13 ሚሊዮን ብር መገበያየት መቻሉ አበረታች እንደሆነ አቶ አደም አስረድተዋል። ሌላው የእሁድ ገበያ ዓላማ አድርጎ የተነሳውከአምራቹ እስከ መጨረሻ ደረጃ ያሉ ሸማቾች እንዲሁም ሕጋዊ ከሆኑ ነጋዴዎች ውጪ መሀል ላይ ያሉ ደላሎችን መቁረጥ ሲሆን ለዚህም የእሁድ ገበያ አንዱ ማሳያ ነው።
መደበኛ የሆነውን የንግድ ሰንሰለት እንዲሁም ውጣ ውረዶችን አልፎ ከሚቀርበው ምርት ጋር የእሁድ ገበያው ሲነጻጸር ከ25 እስከ 40 በመቶ ቅናሽ ያለው ግብይት የተፈጸመ ስለመሆኑ መረጃዎች ያሳያሉ። ስለዚህ የእሁድ ገበያ እስካሁን ባለው ሂደት የታለመለትን ዓላማ አሳክቷል ማለት የሚቻል እንደሆነ አቶ አደም አንስተዋል። በጅምር ላይ ያለው የእሁድ ገበያ ያለምንም ውጣ ውረድ እየተከናወነ አለመሆኑን የጠቀሱት አቶ አደም፤ በተቻለ መጠን የሚመለከታቸውን አካላት አቀናጅተው እየሠሩ ያሉ ቢሆንም አሁንም ድረስ ምርቱ በተፈለገው መጠን ወደ እሁድ ገበያ የማይደርስበት አጋጣሚዎች አሉ።
ለዚህም ዋናው ምክንያት ከዚህ ቀደም እንደሚታወቀው በንግድ ሥርዓት ውስጥ ያሉ ረጃጅም ሰንሰለቶች ለዋጋ ንረትና ለኑሮ ውድነት ዓይነተኛ ሚና አላቸው። በመሆኑም አሁንም ድረስ የገበያ ሰንሰለቱ እንዲረዝምና አላስፈላጊ እጆች እንዲገቡበት የሚሠሩ ሕገወጥ ደላሎች የእሁድ ገበያውን እየተፈታተኑት ይገኛሉ። በተጨማሪም ከመሠረተ ልማት አለመሟላት ጋር ተያይዞ የገበያ ቦታዎች በበቂ ሁኔታ አይገኝም።
አልፎ አልፎም አምራቾች ማለትም አምራች የኅብረት ሥራ ማህበራት ምርት ሲያድርባቸው ማሳደሪያ ቦታ የሚቸገሩበት ሁኔታ መኖሩን የጠቆሙት አቶ አደም፤ ከእነዚህ ውጪ ያሉ ተዋናዮች የኢንዱስትሪ ባለቤቶች፣ በከተማዋ ውስጥና በዙሪያ ያሉ አርሶአደሮች፣ የሸማች ኅብረት ሥራ ማኅበራትና ትላልቅና ታማኝ የሆኑ ነጋዴዎች የግብይት ሰንሰለቱን ባሳጠረ መልኩ ቢያንስ በአንድ ደረጃ መቅረብ እንዲችል የጅምላ ነጋዴዎች ጭምር በእሁድ ገበያው ተጋብዘዋል። የእሁድ ገበያ አሠራር ተቀርጾለት የተጀመረ ባለመሆኑ የተለያዩ ችግሮች አጋጥመዋል። ይሁን እንጂ ያጋጠሙ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል የአሠራር ማንዋል እስካሁን ያለውን ተሞክሮ መነሻ በማድረግ ተዘጋጅቷል።
በመሆኑም በቀጣይ በእሁድ ገበያው ላይ የታዩት ተግዳሮቶች የሚፈቱ ይሆናል ብለዋል አቶ አደም። በአዲስ አበባ ከተማ በቀዳሚነት በአምስት ቦታዎች የተጀመረው የእሁድ ገበያ አሁን ከ11 አልፈው 13 የደረሱ መሆናቸውን የጠቆሙት አቶ አደም፤ በተያዘው በጀት ዓመት የገበያ ቦታውን 20 ለማድረስ ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን ነው የገለጹት። በእነዚህ 20 የገበያ ቦታዎችም ሁሉንም ተዋንያኖች ተጠቃሚ በማድረግ ለአብዛኛው የማኅበረሰብ ክፍል ተመጣጣኝ በሆነ ዋጋ ምርት እንዲደርስ ይደረጋል።
ለዚህም እስካሁን ባለው ሂደት በቂ ልምድ ማግኘት የተቻለ ሲሆን በቀጣይ በጀት ዓመት ደግሞ ተሞክሮን በማስፋት የበለጠ ተጠናክሮ የሚቀጥል ሆኗል። ‹‹የኑሮ ውድነት እጅግ ሰፊ ሀሳብ ነው›› ያሉት አቶ አደም፤ ነገር ግን ሰፊ ከሆነው ሀሳብና ተግባር ከሚጠይቀው ጉዳይ መካከል አንዱ የእሁድ ገበያ ነው። ይሄ ገበያ በኑሮ ውድነቱ ላይ እያበረከተ ያለው አዎንታዊ ተጽዕኖ በመኖሩ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አንስተዋል። ስለዚህ በገበያው ተሳታፊ የሆኑ በተለይም በአዲስ አበባ ከተማና በዙሪያዋ ያሉ አምራቾች እንዲሁም ሩቅ ያሉት አምራች የኅብረት ሥራዎች ያመረቱትን ምርት በቀጥታ ወደ ገበያው ይዘው መግባት እንዳለባቸውና ይህም የኑሮ ውድነቱን ለመከላከል ከሚኖረው ሚና በተጨማሪ አምራቹንና ሸማቹን ተጠቃሚ ያደርጋል ብለዋል።
በአምራቹና በሸማቹ መካከል ሆኖ ምንም እሴት ሳይጨምር ተጠቃሚ ይሆን የነበረውን ሕገወጥ ደላላን ከመሀል ቆርጦ ማውጣት እንዲቻልና ወደ ደላሎቹ ይሄድ የነበረውን ልዩነት ወደ አምራቹ ሄዶ አምራቹና ሸማቹ ተጠቃሚ እንዲሆን ለማድረግ ሁሉም አካል የድርሻውን መወጣት ይኖርበታል። በተለይም ዝቅተኛ ገቢና የኑሮ ደረጃ ያላቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች ወደ እሁድ ገበያ በመሄድ የሳምንት ፍጆታቸውን በተመጣጣኝ ዋጋ እየሸመቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 13/2014