በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን ግንባታቸው የተጠናቀቀ ፕሮጀክቶችን የክልሉ ምክትል ፕሬዘዳንት ወ/ሮ ጠይባ ሐሰን እና ሌሎች ከፍተኛ የስራ ሃለፊዎች በተገኙበት ትላንት የካቲት 25 ቀን 2011 ዓ.ም ተመርቀዋል።
በአርሲ ዞን ሌሙ ቡልብሎ ወረዳ ሌሙ ሰርባ ከተማ የሚገኘው የሌሙ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ከተመረቁት ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ ሲሆን የፕሮጀክቱ ግንባታ ጥቅምት 2008 ዓ.ም ተጀምሮ ትላንት የካቲት 25 ቀን 2011 ዓ.ም ለምረቃ እንደበቃ በስነስርዓቱ ላይ ተገልጿል።
ለፕሮጀክቱ ግንባታ እና ልዩ ልዩ ቁሳቁሶች ማሟያ 14ሚሊዬን ብር ወጪ የተደረገበት ሲሆን የአካባቢው ህብረተሰብም የወጪውን 30 በመቶውን እንደሸፈነ ታውቋል::
ከዚህ ቀደም ተማሪዎች የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ለመከታተል 11ኪሎ ሜትር ርቀው በመጓዝ ለመማር ይገደዱ እንደነበር በምረቃው ስነስርዓት ላይ የተጠቀሰ ሲሆን ፣ ይህ ትምህርት ቤት በከተማዋ መገንባቱ በህብረተሰቡ ላይ ይደርስ ከነበረው ወጪና እንግልት እንደሚወገድ በስነስርዓቱ ላይ ተገልጿል።
ት/ቤቱ በአንድ ፈረቃ ከ400 በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተናገድ የሚችል ሲሆን አሁን ላይ 360 ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተማር እንደጀመረም ታውቋል። ትምህርት ቤቱ ደረጃውን የጠበቀ ቤተመፀሐፍት እና ቤተ ሙከራም የተሟላለት ከመሆኑም ባሻገር ለማጠናከርያ ትምህርት ለመሰጠት የሚያስችል ተጨማሪ የመማርያ ክፍሎችም እንዳሉት ታውቋል።
ሶሎሞን በየነ
ፎቶ -በዳኜ አበራ