የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተ.መ.ድ) እ.ኤ.አ 1945 የሁለተኛ ዓለም ጦርነት ማብቃቱን ተከትሎ የተቋቋመ ተቋም ነው፡፡ የጸጥታው ምክር ቤትም እ.ኤ.አ በ1948 የተቋቋመና የዓለምን የሠላም፣ ፀጥታና የደኅንነት ጉዳዮች እንዲከታተል በሚል የተመሠረተ የድርጅቱ ዋነኛ የሥልጣን አካል ነው፡፡
ምክር ቤቱ 15 አባል አገራት አሉት፡፡ ከ15ቱ አባል አገራት አምስቱ ማለትም አሜሪካ፣ ሩሲያ፣ ቻይና፣ እንግሊዝና ፈረንሳይ ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት ያላቸው ቋሚ አባላት /United Nations Security Council veto power/ ያላቸው አገራት ናቸው፡፡
ምክር ቤቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሰላምና ከደህንነት ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ከፍተኛው የድርጅቱ ክንፍ በመሆኑ ማዕቀቦችን ይጥላል፣ የኃይል እርምጃዎችን ያፀድቃል ወይንም ይሽራል:: በምክር ቤቱ ውሳኔዎችን ለማስተላለፍና ተግባራዊ ለማድረግም የቋሚ አባላቱ ሙሉ የስምምነት ድምፅ የግድ ይላል፡፡
ምክር ቤቱ የዓለም ሕዝቦች ዕጣ ፈንታ በአምስት አገሮች ፍላጐት እንዲወሰን በመፈቀዱ ምክንያት ዓለማችን ይሆናሉ ተብለው የማይገመቱ እልቂቶችንና አሳዛኝ ክስተቶችን እንድታስተናግድ ምክንያት እየሆነ ይገኛል የሚል ትችትም ይሰነዘርበታል፡፡
አምስቱ አገራት በያዙት ድምፅን በድምፅ የመሻር መብት ውሳኔዎች እንዲያልፉ ወይም እንዲወድቁ ድምፅ የሚሰጡት ከዓለም አቀፍ ሕግ በመነሳት ሳይሆን፣ ከራሳቸው መንግሥት ጥቅምና ፍላጎት አንፃር መሆኑ ደግሞ ድርጅቱን ተዓማኒነትና ገለልተኝነት ጥያቄ ውስጥ ሲያስገባና ዓለም አቀፋዊ አይደለም የሚሉት እንዲበራከቱ ምክንያት ሆኗል፡፡
ይህን ዋቢ የሚያደርጉ የተለያዩ ምሁራንና አገራትም፣ የተባበሩት መንግሥታት ሲመሰረት የነበረው ነባራዊ ሁኔታ አሁን ካለው ጋር በፍጹም የማይገናኝና የተለየ መሆኑን በተደጋጋሚ ሲያስረዱና ድርጅቱ ለውጥ እንደሚያስፈልገው፣ ከሁሉም በላይ ድምጽን በድምጽ የመሻር መቀመጫ ያላቸው አገራት ቁጥር ከፍ እንዲል ሲሟገቱ ቆይተዋል፡፡
ጃፓን፤ ሕንድና የብሪክስ አገሮች (ብራዚል፣ ራሽያ፣ ሕንድ፣ ቻይናና ደቡብ አፍሪካ) የፀጥታው ምክር ቤት አሁን ባለው አሠራር የብዙኃንን ጥቅም ማስከበር እንደማይቻል በተለያዩ ማስረጃዎች አስደግፈው በማቅረብ፣ አሠራር ላይ የማሻሻያ ለውጥ እንዲደረግ ከሚጎተጉቱ አገሮችና አካባቢያዊ ድርጅቶች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡
አፍሪካውያንም ምክር ቤቱ ኢ-ፍትሃዊ ነው በሚል አህጉሪቱ በምክር ቤቱ ቋሚ መቀመጫ ሊኖራት ይገባል የሚል ተደጋጋሚ ሃሳብ ሲያቀርቡ፣ ሲጠይቁና ሲሟገቱ ቆይተዋል፡፡ አፍሪካ በጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ ማግኘት አለባት የሚለው ጥያቄና ትግል የረጅም ጊዜ ታሪካዊ መሠረት ያለውና በአፍሪካ የነፃነት አባቶች የተጀመረ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ደግሞ በተጠናከረ ሁኔታ ቀጥሏል፡፡
አፍሪካ ህብረትም በፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንዲሰጣት በተደጋጋሚ ጥያቄ አቅርቧል፡፡ ከአፍሪካ ውጪ ያሉ ተቋማት፣ አገራትና ምሁራንም አህጉሪቱ ቋሚ መቀመጫ ይገባታል የሚል ጥያቄን ደጋግመው ጠይቀዋል። ድምፅን በድምፅ የመሻር ስልጣን ለዓለም አቀፍ ፖለቲካ ዋነኛ መሣሪያ ሆኖ እንደሚያገለግል ዋቢ በማድረግ የአፍሪካ አገራትም ድምፅን በድምፅ የመሻር መብትን ጨምሮ ተመሳሳይ የሆነ ስልጣንና ጥቅም ሊሰጣቸው ይገባል ሲሉም ሞግተዋል፡፡ የተለያዩ የአፍሪካ አገራት መሪዎችም ይህን ጥያቄ በተለያየ ጊዜ አንስተዋል፡፡
የቀድሞው የዚምባብዌ ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ ከጠያቂዎቹ መካከል በቀዳሚበት ከሚጠቀሱት አንዱ ነበሩ፡፡ ፕሬዚዳንቱ እ.ኤ.አ በ 2016 አዲስ አበባ ላይ በተካሄደው በ26ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ የተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ማሻሻያ እንዲያደርግ መጠየቃቸው ይታወሳል፡፡
በወቅቱም ‹‹በየአመቱ መስከረም ወር ላይ የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ስብሰባ ሲደረግ እንሳተፋለን። ይሁንና በእነዚህ የድርጅቱ ስብሰባዎች ላይ ስንገኝ ያለን ተወካይነት ለይስሙላ ነው። ንግግር አድርጎ ከመመለስ የዘለለ አይደለም፡፡ ይህም ብቻ አይደለም በጠቅላላው ጉባኤ ለመገኘት በርካታ ወጪዎች እናወጣለን።
በዚህ ዓይነት መልኩ አመታት አልፈዋል፡፡ ሌሎች አመታትም መጥተዋል። ይህ አሠራር እንዲለወጥ እኛም ያለማቋረጥ ትናንትም፣ ዛሬም ሆነ ነገ እንጠይቃለን፣ የጸጥታ ምክር ቤት ማሻሻያ ይደረግበት፣ አዎን ይደረግበት፣ አፍሪካ ተወካይ ይኑራት›› ሲሉ ጥያቄአቸውን አቅርበው ነበር፡፡
እንደ ትናንቱ ሁሉ በአሁኑ ወቅትም የተባበሩት መንግሥታት አዲስ በሆነ መልኩ የወቅቱን የዓለም ቁመና ከግምት ባስገባና በሚመጥን አደረጃጀት በተለይም የአፍሪካን ጥቅሞች በሚያስጠብቅ መልኩ መዋቀር የሚኖርበት ትክክለኛው ጊዜም አሁን ነው የሚሉ ድምፆች ከየቅጣጫው እያስተጋቡ ናቸው፡፡፡ የተለያዩ ምሁራንና ጸሐፍትም፣‹‹አፍሪካ በዓለም አቀፍ አስተዳደራዊ ተቋማት ውስጥ የተሻለ ውክልና ማግኘት ይገባታል፣ በተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ውስጥ አንድ ወይም ሁለት ወንበር ሊኖራት ይገባል፡፡
ከቋሚ አባላቱ ውስጥ የአፍሪካን ውክልና አንዱ የማድረግ ጥያቄ እንዲያውም እንደዘገየ ነው፣ ኃያላኑ አገራትም ለዚህ ዕቅድ ሙሉና የማያወላዳ ድጋፍ ሊሰጥ ይገባል፤›› እያሉ ናቸው፡፡ ከቀናት በፊት የተካሄደውን የቱርክ-አፍሪካ 3ኛው ጉባኤ መጠናቀቁን ተከትሎ የቱርክ ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት ባወጣው መግለጫም አፍሪካ በሚገባት መልኩ ውክልና እንድታገኝ ሁላችንም በትብብር መስራት ይጠበቅብናል ብሏል፡፡
‹‹የቱርኩ ፕሬዚዳንት ረጂብ ጣይብ ኤርዶጋንም፣ 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ሕዝብ ያላት አፍሪካ በተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንዳይኖራት መደረጉ ከባድ ኢፍትሃዊነት ስለመሆኑ አፅእኖት ሰጥተውታል፡፡ United Nations Association of the National Capital Area (UNA-NCA) ከፍተኛ አማካሪና ባለሙያ የሆነው ማርኮስ ሼድዊት፣ ይህን እሳቤ ከሚደግፉት አንዱ ነው፡፡ ‹‹አፍሪካ ከትናንት እስከ ዛሬ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት የይስሙላ ተሳታፊና በማንኛውም አጀንዳ ላይ የምትሰጠው ድምጽ የዜሮ ድምር ስለመሆኑ ያብራራሉ፡፡ ምክር ቤቱ የአፍሪካን የፀጥታና ደህንነት፣ ፖለቲካና ኢኮኖሚ በተጠና መልክ በእጅ አዙር እንደሚዘውርና
ይህም ግልፅ ኒዮ ኮሎኒያሊዝም ስለመሆኑ የሚያሰምሩበት አማካሪ፣ ይህ ታሪክ የሚቀየርበትና አፍሪካ በምክር ቤቱ ቋሚ መቀመጫ ማግኘት ያለባት ትክክለኛው ጊዜ ነገ ሳይን ዛሬ ነው›› ይላሉ፡፡
የአፍሪካ ቋሚ መቀመጫ ማግኘትም፣ ለአህጉሪቱ ሁለንተናዊ እድገት በተለይም ሰላምና ደህንነት እጅግ ወሳኝ ከመሆኑ ባሻገር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በዓለም አቀፍ ደረጃ በበርካቶች ዘንድ የሚሰነዘርበትን የአድሎአዊነት ትችት እንዲቀንስ እንዲሁም የተቋቋመበትን አላማ እያሳካ ለመቀጠል ያግዘዋል ያሉት አማካሪው፣ ለዚህ ደግሞ የድርጅቱ ዘዋሪዎች በተለይም አሜሪካ ለአፍሪካ ተገቢውን ክብርና ይሁንታን መስጠት ግድ እንደሚላቸው ሳያስገነዝብ አያልፍም፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት አባል መሆን በርካታ ጠቀሜታዎች እንዳሉት ይነገራል። የተለያዩ ስመጥር የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ምሁራኑ እንደሚያስረዱት፣ የምክር ቤቱ አባል መሆን አፍሪካ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላት ስፍራና ከበሬታ ከፍ ያደርገዋል፡፡ ተደማጭነትና ተጽዕኖ ፈጣሪነትን ያገዝፈዋል፡፡ ጥቅሟን እንድታስጠብቅ፣ የተለያዩ የሰላም አማራጮችን እንድታቀርብ፣ ዘላቂና አስተማማኝ ሰላም እንድታሰፍን እድል ይሰጣታል፡፡
ለአህጉሪቱ በጎ የማይመኙ አገራትን ስውርና ገሃድ ሴራዎቻቸውን በቅርበት በመከታተል አሉታዊ ውሳኔዎች እንዳይፀድቁ ጥብቅና ለመቆም፣ በሴራ ጥልፍልፎሽ የሚያደርሱ ጉዳቶችን ለመቀነስና ከተቻለም ለማስቆም ፋይዳው የጎላ ነው፡፡ የወቅቱ የአፍሪካ መሪዎችና በርካታ ምሁራን ‹‹አፍሪካ በተመድ ጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ አለማግኘቷ አሳዛኝ ነው›› በሚል ሲያቀነቅኑ ቆይተዋል፡፡
የፀጥታ ምክር ቤት የዓለም ቁመና ከግምት ያስገባ መዋቅራዊ ለውጥ እንደሚያስፈልገውም ይስማሙበታል፡፡ በምክር ቤቱ ውስጥ ተጨማሪ ቋሚ መቀመጫ የሚኖራቸውን አገራት መቀበል የግድ ነውም ይላሉ፡፡
የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎዛና የሴኔጋሉ አቻቸው ማኪ ሳል አፍሪካ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ጥበቃ ምክር ቤት ቋሚ ውክልና አለማግኘቷ ፍትሐዊ እንዳልሆነ አስታውቀዋል፡፡ ራማፎዛ በዳካር በተካሄደው የአፍሪካ የሰላም እና ጸጥታ ጉባዔ ላይ አፍሪካ በጸጥታው ምክር ቤት በተገቢው መንገድ እንድትወከል መደረግ አለበት ብለዋል፡፡ ከቀናት በፊትም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የአፍሪካ አገራት በተመድ የፀጥታው ምክር ቤት የተሻለ ውክልና እንዲያገኙ የሚጠይቀውንና ሌሎች አፍሪካውያን መሪዎች እያደረጉት ያለውን ንቅናቄ መቀላቀላቸውንም ገልጸዋል። በዚህ ንቅናቄ አፍሪካን በተመለከተ የሚወሰኑ ውሳኔዎች ከአፍሪካ ውክልና ውጪ መወሰን እንደሌለባቸውም አስምረውበታል።
‹‹1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ሕዝብ ያላት አፍሪካ በተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እና ድምፅ ሊኖራት ይገባል ነው›› ያሉት፡፡ የታሪክ ድርሳናት እንደሚያመላክቱት፣ ኢትዮጵያ የቀድሞ ሊግ ኦፍ ኔሽንስ የአሁኑ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መስራች አባል ብትሆንም በፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል ሆና የሰራችው ሦስት ጊዜ ብቻ ነበር:: ይህም እ.ኤ.አ. ከ1967 እስከ 1968 ፣ ከ1989 እስከ 1990 እና ከ2008 እስከ 2009 ዓ.ም. ፡፡ ይህ ተሳትፎዋ በተለይ የአፍሪካ ነፃነት ምልክት ከመሆኗ ባሻገር ከ1950ዎቹ አንስቶ እየጎላ ለመጣው አካባቢያዊና ዓለምአቀፍ ሰላምና ፀጥታ የማረጋገጥ ሚናዋ አንፃር ተለዋጭ ብቻ ሳይሆን ቋሚ አባል መሆን የሚገባት አገር ስለመሆኗም አፅእኖት ይሰጡታል፡፡ አንዳንድ ምሁራንም፣ ተለዋጭ መቀመጫ የቋሚን ያህል ሚና የለውም ይላሉ፡፡
ኢትዮጵያ በተመድ የጸጥታው ምክር ቤት አፍሪካ ቋሚ መቀመጫ ማግኘት አለባት የሚለውን እንቅስቃሴ መቀላቀሏ በታሪክ በአፍሪካውያንና በጥቁር ሕዝቦች ዘንድ ካላት ተቀባይነት አንጻር ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው መሆኑንም ያሰምሩበታል፡፡ አፍሪካ ለምን በፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ ይኑራት? የሚለው ጥያቄ መልስ አዲስና ፍትሐዊ ዓለም መፍጠርን ስለሚያስችል ነው ይላሉ፡፡
አፍሪካ ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንዲኖረው የተጀመረው እንቅስቃሴ ይህን አላማ ያነገበ፣ የነፃነት፣ የእኩልነትና የፍትሐዊነት ትግል በመሆኑ አፍሪካውያን መቀላቀል እንዳለባቸው ምክረ ሃሳባቸውን ይሰጣሉ፡፡ ትግሉ አሁን እንደ አዲስ መቀስቀሱ በዓለም ላይ ካለው ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር ውጤታማ ሊያደርገው እንደሚችል ምሁራን ይገልጻሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ በተለይም ‹‹የዓለም አቀፉ የፖለቲካ አሰላለፍ መቀየር ጥያቄው ተቀባይነት የማግኘት ዕድሉ ከፍተኛ ያደርገዋልም›› ይላሉ፡፡
በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህር ሰለሞን ተፈራ፣ ምክር ቤት ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ስለ አፍሪካ ያስተላለፋቸው ውሳኔዎችና የተመካከረባቸው ጉዳዮች ሚዛናዊነትና ግልጽነት የጎደለውና የምዕራባውያን ፍላጎት ያማከለና አህጉሪቷን በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካና በማህበራዊ ጉዳዮች ጥገኛ ለማድረግ የታለሙ መሆናቸውን ያመላክታሉ፡፡ ምክር ቤቱ አፍሪካውያን በሌሉበት ስለአፍሪካውያን ውይይት ማድረግና መወሰን አፍሪካን ለመቀራመት ከተካሄደው የበርሊን ኮንፈረንስ ልዩነት የለውም የሚሉት መምህሩ፣ አፍሪካውያን በሁሉም ዘርፍ እርስ በርሳቸው በመተጋገዝ ከእነዚህ የምዕራባውያን ተፅእኖዎች መላቀቅ የግድ እንደሚላቸውና በተለይም በምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራቸው ለማድረግ የተጀመሩትን እንቅስቃሴዎች አጠናክረው መቀጠል እንደሚኖርባቸው አፅእኖት ይሰጡታል፡፡
የምዕራባውያንን ፍላጎት ለማሳካት በሚጠራው ማንኛውም ስብሰባ ራሳቸውን ማግለል፣ ድምጻቸውን በጋራ ማሰማት፣ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካና በማህበራዊ ጉዳዮቻቸው ዙሪያ ቀጠናዊ ትስስራቸውን አጠናክረው ወደሚፈልጉት ብልጽግና መድረስ ይችላሉ ነው ያሉት፡፡ ፖለቲከኛና የጂኦፖለቲክስ ተንታኝ አቶ ትዕግስቱ አወሉም፣‹‹አፍሪካ በምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ አለማግኘቷ የራሷን ጉዳይ እንዳታነሳ ያደረገና ኃያላን አገራት በቅኝ አገዛዝ ዘመን የነበራቸውን አስተሳሰብ አሁንም በእጅ አዙር እየተገበሩት እንደሆነ ማሳያ ነው›› ይላሉ፡፡ የአንድ ነጥብ ሦስት ቢሊዮን ሕዝብ መኖሪያ የሆነችው አፍሪካ በተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት አለመወከሏ በኃያላን አገራት ተፅዕኖ እንድትወድቅ አድርጓታል፣ የራሷን ጉዳይ እንዳታነሳና ኃያላን አገራት በቅኝ አገዛዝ ዘመን የነበራቸውን አስተሳሰብ አሁንም በእጅ አዙር እየተገበሩት እንደሆነ ማሳያ ነው›› ይላሉ፡፡
የአፍሪካ በፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ ማግኘት ለመደራደር፣ መብቷንና ጥቅሟን ለማስከበር ትልቅ ዕድል የሚሰጥ መሆኑን የሚያስገነዝቡት አቶ ትግስቱ፣ የቅኝ ግዛት አስተሳሰቦችን ለመታገል፣ አፍሪካ የራሷን ጉዳይ በራሷ ቆማ በመታገል ተደማጭነት እንዲኖራትና የአፍሪካ ሀሳብ በዓለም ላይ ገዥ ሀሳብ እየሆነ የሚመጣበት እድል እንደሚፈጥር ነው ያስረዱት፡፡
‹‹ተለዋጭ መቀመጫ የቋሚን ያህል ሚና የለውም›› የሚሉት አቶ ትዕግስቱ፤ አፍሪካ በሕዝብ ብዛቷና አሁን በምትገኝበት የማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች ደረጃ የቋሚ መቀመጫ ቦታ እድሉ ሊኖራት እንደሚገባም ያመላክታሉ፡፡ በሰላም፣ በፀጥታ፣ በሌሎች ዘርፎች የጸጥታው ምክር ቤት ትልቅ ውሳኔ ማስተላለፍ የሚችል በመሆኑ አፍሪካ በራሷን ጉዳይ ሌላ ወገን ሲወስንባት ዳር ቆማ መመልከት እንደሌለባት የሚያስምሩበት አቶ ትግስቱ፣ አፍሪካ ምክር ቤት ቋሚ መቀጫ እንዲኖራት የተጀመረው ትግል የመላ አፍሪካውያን ጥያቄ ሆኖ ውጤት ማስመዝገብ እንዳለበትም ሳያስገነዝቡ አላለፉም፡፡
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ደረጃ የጸጥታው ምክር ቤት ተደራዳሪ እንደነበረች ያስታወሱት አቶ ትዕግስቱ፤ አፍሪካ በተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ ቢኖራት አሁን በኢትዮጵያ ላይ እየተደረገ ያለው የዲፕሎማሲ ጫና ይህን ያህል አይበረታም ነበር ነው›› ያሉት፡፡
አስተያየት ሰጪዎችም፣ አፍሪካ በፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራት ማድረግ አዲስና ፍትሐዊ ዓለም መፍጠር በመሆኑ በተለይም ‹‹የአፍሪካን ጉዳይ በአፍሪካ የሚለው ቁልፍ የፍትህ ጥያቄን ለመመለስ፣ ሁሉም የአፍሪካ ኅብረት አባል አገራት ጉዳዩን አጀንዳ አድርገው እንቅስቃሴ ውጤት እንዲያመጣ በተቀናጀ መንገድ ሀሳቡን ሊደግፉት እንደሚገባ አስምረውበታል፡፡
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 12/2014