አዲስ አበባ ፦ የዓለም ባንክ በኢትዮጵያ ያለውን የቱሪዝም ዘርፍ ለማሳደግ፤ ጥናት ለማድረግና ለማገዝ ከቱሪዝም ኢትዮጵያ ጋር ስምምነት ተፈራረመ። ስምምነቱን ትናንት በባንኩ የኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ሲፈረም የቱሪዝም ኢትዮጵያ ዋና ስራ አስፈፃሚ ወይዘሪት ሊንሳ መኮንን እንደተናገሩት፤ ባንኩ የኢትዮጵያን ቱሪዝም ዘርፍ በጥናት በመለየት በቀጣይ መሰራት ያለባቸውን አካሄዶች ፍኖተ ካርታ ያስቀምጣል።
ይህም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለመሆን የሚያስችል ተቋማዊ መዋቅር ለመዘርጋት እገዛ ያደርጋል። በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ በዓመት ከ10 ሚሊዮን በላይ መንገደኞች ይስተናገዳሉ።
ከዚህ ውስጥ ቱሪስቶች 10 በመቶ ብቻ ናቸው። አዲስ አበባ የዓለም አቀፍ የስብሰባ ማዕከል ብትሆንም የስብሰባ ቱሪዝሙ ዝቅተኛ ነው። ስምምነቱ በቦሌ አየር ማረፊያ የሚመጡ ቱሪስቶችን ቁጥር ወደ 20 በመቶ ለማሳደግ፤ እንዲሁም የስብሰባ ቱሪዝምን ለማሳደግ የሚታዩ ክፍተቶችን ለመለየት እንደሚያግዝ ገልጸዋል።
ባንኩ በሚያደርገው ጥናት ለቱሪዝሙ ዘርፍ እንቅፋት የሆኑ የመሰረተ ልማት፣ የባለሙያዎች ጉድለት፣ የአልሚዎች መጓደል፣ የገበያ ሥርዓት፣ የተቋማት አደረጃጀትና የዓለም አቀፍ ገበያ ስነ ዘዴ መጓደልና ሌሎች ችግሮችን በማጥናት ለችግሩ መፍትሄ የሚሆኑ አሰራሮችና ሀሳቦች ለድርጅቱ ያቀርባል።
የባንኩ የኢትዮጵያ ቢሮና የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ዳይሬክተር ጁሞኪ ጃግነዶኩሙ፤ በባንኩና በድርጅቱ መካከል የተደረገው ስምምነት ሶስት ዓመት የሚቆይ ሲሆን፤ በጥናቱ ዓለም አቀፍ አማካሪዎችና ባለሙያዎች ድጋፍ ያደርጋሉ። ለድጋፉ ከአንድ ሚሊዮን ዶላር በላይ ድጋፍ እንደሚደረግም አመላክተዋል።
የሚደረገው ድጋፍ ኢትዮጵያ ሰፊ ዕድል እያላት በአግባቡ ያልተጠቀመችበትን ሀብቷን ወደ ጥቅም ለመቀየር መሰረት ይጥላል። መረጃዎችን የማደራጀት ስራም ይሰራል። ይህም በቀጣይ የግሉና የመንግሥት አካላት መስራት ስላለባቸው አቅጣጫ በማስያዝ የዘርፉ ዕድገት እንዲፋጠን ያደርጋልም ብለዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 27/2011
በአጎናፍር ገዛኽኝ