᎐ «ኡቡንቱ» ለ100 ቤተሰቦቹ የመኖሪያ ቤት ይገነባል
አምቦ፦ አምቦ ዩኒቨርሲቲ ለ547 ችግረኛ ወገኖች የነጻ ህክምና አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን ገለጸ። «ኡቡንቱ» ቤተሰብ አቀፍ የልጆች ድጋፍ መስጫ ድርጅት ለ100 ቤተሰቦቹ የመኖሪያ ቤት ሊገነባ ነው። የካቲት 22 ቀን 2011 ዓ.ም 4ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን በዩኒቨርሲቲው መሰብሰቢያ አዳራሽ አክብሯል። የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ታደሰ ቀነአ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደተናገሩት፤ ዩኒቨርሲቲው ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት በርካታ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል።
በጤናው ዘርፍ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ ነው። መሰረቱን በአምቦ ዩኒቨርሲቲ ካደረገው «ኡቡንቱ» ቤተሰብ አቀፍ የልጆች ድጋፍ መስጫ የበጎ አድራጎት ድርጅት ጋር በመሆን በድህነት ለሚኖሩ 547 ወገኖች በአምቦ ዩኒቨርሲቲ ሪፈራል ሆስፒታል የነጻ ህከምና አገልግሎት ይሰጣል።
«ኡቡንቱ» ቤተሰብ አቀፍ የልጆች ድጋፍ መስጫ ድርጅት በዩኒቨርሲቲው በሚገኙ መምህራንና በሌሎች ባልደረቦች በሚንቀሳቀስ የበጎ አድራጎት ድርጅት በሚሰጣቸው ድጋፎች ላይ ዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ ተሳትፎ የሚያደርግ መሆኑንም ገልጸዋል። ድርጅቱ ባለፉት አራት ዓመታት ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉንም ተናግረዋል። ዩኒቨርሲቲው ከኡቡንቱ ጋር በአብሮነት የሚያደርገውን ትብብር የሚቀጥል መሆኑንና እርሳቸውም በግላቸው በአባልነት ተመዝግበው ከደሞዛቸው 100 ብር ተቆራጭ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።
በአምቦ ዩኒቨርሲቲ መምህርና የኡቡንቱ ቤተሰብ አቀፍ የልጆች ድጋፍ ሰጪ ድርጅት መስራችና ኃላፊ አቶ ሰለሞን አለሙ በበኩላቸው፤ «ኡቡንቱ» በድህነት ምክንያት ልጆቻቸውን ማስተማር ያልቻሉ ቤተሰቦችን የመደገፍን አላማ በመሰነቅ በ12 የዩኒቨርሲቲው መምህራን ከአራት ዓመት በፊት የተመሰረተና በአሁኑ ወቅት 360 አባላትን አቅፎ የሚንቀሳቀስ በሀገር አቀፍ ደረጃ በዩኒቨርሲቲ ውስጥ የተቋቋመ ቀዳሚው የበጎ አድራጎት ድርጅት መሆኑን ተናግረዋል።
እንደ አቶ ሰለሞን ማብራሪያ፤ ድርጅቱ በየአመቱድጋፍ የሚሹትን ወገኖችን በመቀበል ለአራት አመታት የተጓዘ ሲሆን፤ በመጀመሪያው ዙር 26 ቤተሰቦች ተቀብሏል፣ በሁለተኛው ዙር ደግሞ 27፣ በሶስተኛው 39 ቤተሰቦችን ሲቀበል በአራተኛው ዙር ደግሞ 43 ቤተሰቦችን ተቀብሏል።
አብዛኛዎቹ ቤተሰቦች በእናት ብቻ የሚተዳደሩ ናቸው። ለእነዚህ ቤተሰቦች አምስት ሺህ ብር ለመስሪያ የሚሆን መነሻ ገንዘብ በመስጠት ለማቋቋም ጥረት ይደረጋል። ከዚህ በተጨማሪ የሚያስፈልጉ አልባሳት እንደ ብርድ ልብስ፣ አንሶላ፣ የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ እየተደረገ ይገኛል ።
ኡቡንቱ ቤተሰቦችን ለመደጎም በቀጣይም ሰፊ እቅድ እንደያዘ የተናገሩት አቶ ሰለሞን ፤ የቤተሰቦቹን መሰረታዊ ችግር በመረዳት ለ100 ቤተሰቦቹ መኖሪያ ቤት ለመገንባት እቅድ ይዟል። በዚህም «ኡቡንቱ ቪሌጅ »በሚል በአነስተኛ ወጪ ለ100 ቤተሰቦች የሚሆን መኖሪያ ቤት ለመገንባት እንቅስቃሴ መጀመሩን ገልጸው፤ የከተማ አስተዳደሩ መሬት እንዲሰጠን እየተነጋገርን ነው።
የዩኒቨርሲቲውን ማህበረሰብ በማንቀሳቀስና ከአጋር ድርጅቶችም ጋር በመሆን ለቀጣዩ አመት ቤቱን ሰርቶ ለማስረከብ መታቀዱን ገልጸዋል። አክለውም የዚሁ አካል የሆነ 40 አረጋውያንና አዕምሮ ህሙማን የሚደገፉበት ተቋም እንደሚገነባም ተናግረዋል ። ኡቡንቱ በአሁኑ ወቅት 135 ቤተሰቦችን በማቀፍ ድጋፍ እየሰጠ የሚገኝ ሲሆን፤ በዚህ ቤተሰብ ውስጥ በአማካኝ 4 ነጥብ 5 ህጻናት ሲኖሩ፤ አጠቃላይ የተጠቃሚ ቤተሰብ ቁጥር 547 መሆኑን ከድርጅቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። “ኡቡንቱ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል፤ “አንዱ እያዘነ ሌላው እንዴት ደስተኛ ይሆናል” የሚል ትርጉም እንዳለው ለማወቅ ተችሏል።
አዲስ ዘመን የካቲት 27/2011 በዳንኤል ዘነበ