ባደጉበት አካባቢ በነበረው የውሃ አቅርቦት ችግር ከትምህርት ቤት በፊት ጠዋት ተነስተው ውሃ መቅዳት የዘወትር ተግባራቸው ነበር። የውሃ እጥረት ችግሩ ውስጣቸውን እንዲጠይቁ አደረገ። የልጅነት ገጠመኛቸው አሁን ለደረሱበት ምክንያት ሆኗቸዋል። በልጅነታቸው የመስኖ ልማት በውስጣቸው ተቀረፀ። ኢትዮጵያ ካፈራቻቸው የውሃ መሃንዲሶች አንዱ ሆነዋል። በአርባ ምንጭ ውሃ ቴክኖሎጂ ዲን በመሆን ሰርተዋል፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም በመምህርነት አገልግለዋል።
በኢትዮጵያ ውስጥ በወንዝ ፍሰት፣ በመስኖና በመጠጥ ውሃ ጥናቶች፣ በውኃ ኤሌክትሪክ ማመንጨት ጥናቶችና በተመሳሳይ ጉዳዮች በባለሙያነትና በቡድን መሪነት ተሳትፈዋል። በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) ለሰባት ዓመታት በሥራ አስፈፃሚ አባልነት ሰርተዋል። በ1972 ዓ.ም በሲቪል ምህድስና ከአዲስ አበባ የኒቨርሲቲ የባችለርስ ዲግሪ፣ በ1976 ዓ.ም ደግሞ ከአየርላንድ ብሄራዊ ዩኒቨርሲቲ በሃይድሮሎጂ የማስተርስ ዲግሪ አግኝተዋል።
በውሃ ምህንድስና ከሮያል የቴክኖሎጂ ተቋም (ስቶኮልም፤ ስዊድን) በ1981 ዓ.ም የዶክትሬት ዲግሪ ተቀብለዋል። ለአምስት ዓመታት በኢደአፓ-መድኅን በሊቀመንበርነት፣ በ1997 ዓ.ም በተደረገው ምርጫ ከዝግጅቱ እስከ ፍፃሜው ድረስ በቅንጅት ምክትል ሊቀመንበርነት በመሳተፍ በኢትዮጵያ ፖለቲካም አሻራቸውን አሳርፈዋል። በሰብአዊ መብት፣ የሕግ የበላይነት፣ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሂደትና ተዛማጅ ጉዳዮች ላይ መሠረት ያደረገ ‹‹የመግባባት ዴሞክራሲ›› በሚል ርዕስ የተዘጋጀ መጽሃፍ በ2010 ዓ.ም አሳትመው ለንባብ አብቅተዋል። ከፕሮፌሰር አድማሱ ገበየሁ ጋር በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ያደረግነውን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበናል።
አዲስ ዘመን:- የውጭ ሃይሎች በኢትዮጵያ ላይ ሉዐላዊነትን የሚጋፋ ነገር የሚያደርጉበት ምክንያቱ ምንድን ነው? ጣልቃ ገብነቱን ለመቋቋምስ ምን መደረግ አለበት?
ፕሮፌሰር አድማሱ:- በእኔ እይታ ችግሩ ያለው እኛ ጋር ነው። እኛ የሰው እጅ ጠባቂ እና ጥገኞች ሆነናል። ራሳችንን አልቻልንም። በእዚህ ምክንያት ደገፍኩ የሚለው ወገን እንደማንኛውም ጥገኛ ዝቅተኛ አድርገው ቢመለከቱን አይገርምም። የምናደርገው ሁሉ እነርሱ በሚስማሙበት መልኩ የተቃኘ እንዲሆን ይፈልጋሉ።
በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ወደእዚህ ጦርነት ያስገባን እኛ ደግሞ ‹‹ለጊዜው ተቸገርን፣ ለጊዜው ደገፋችሁን እንጂ ክብራችንን ልትነኩ አትችሉም፤ ልንዋረድ ፍቃደኛ አይደለንም›› የሚል ግብ ግብ ውስጥ ነን። ይህንን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ማስወገድ እንችላለን። በማንኛውም መልኩ አሁን ባለንበት የድህነት ሁኔታ ውስጥ እንድንሆን ተፈጥሯዊ ገደብ የለብንም። በማንኛውም ዘርፉ እምቅ ሃብት አለን። ከእዚህ ማጥ፣ በባእዳን ፊት ከሚያዋርደን ድህነታችን መውጣት እንችላለን።
ምንም አያግደንም። ሕዝባችን ታታሪና ጠንካራ ሕዝብ ነው። አገራችንም በውስጧ ከሕዝቧ ተርፎ ለሌሎችም የሚሆን ሃብትና ጸጋ ይዛለች። ግን ይህ ሀሳብ ዕውን ሳይሆን ቀርቷል። ለእዚህ ምክንያቱ ሃላፊነት ወስዶ አገር ይመራል፣ እኛን አስተባብሮ የተሻለ ደረጃ ያደርሰናል ተብሎ የተጠበቀው የወያኔ መንግስት ባግባቡ ሊሰራ፣ ሕዝብን ከድህነት ሊያድን፣ ከመጥፎ ነገር ሊታደግ አለመቻሉ ነው። በሥልጣን ዘመኑ የቻለውን ሁሉ ዘርፎና ቀምቶ ሀብት አደራጅቶ ሕዝብ በቃህ ሲለው ከያዘው ሥልጣን ተገፍትሮ ወርዷል።
ወያኔ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የሠራው ግፍ በግልጽ የሚታይ ቢሆንም አንዳንድ የውጭ ሃይሎች አይናቸውን ጨፍነው እየደገፉት ነው። እነዚህ ወያኔ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ከዘረፈው ሀብት ተካፋዮች ናቸው የሚል እምነት አለኝ። ለወያኔ ወግነው በእኛ ላይ የሚያደርሱብን በደል ሁሉ ተገቢው መረጃ ስለሌላቸው ነው ብዬ አላምንም። እነዚህ ወገኖች ለመንግስታቸው አዛኝ፣ ደጋፊና ተቆርቋሪ በመምሰል ተደማጭነታቸውን በመጠቀም ጥቅማቸው እንዳይጓደል በማሰብ፣ ለወያኔ በመወገን በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት መዝዘዋል።
የአገርን ስም ማጠልሸት፣ ሚዲያውንና ሌሎች መዋቅሮችን በመጠቀም አገራችን ላይ ዘምተዋል። በዘመቻቸው እያደረሱብን ያለውን ጉዳት መቀነስ ብሎም ማስወገድ የምንችለው በአንድነት በመቆም ነው። የውጭ ዜጎች ብቻቸውን አይደሉም። አገራችንን እየጎዱ ያሉት በጥቅም መጋራት ሰበብ እየፈለጉ አገርን ከሚጎዱ አካላት ጋር የሚሰለፉ በድብቅም ሆነ በግልጽ የሚሰሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን አሉ። አብዛኞቹ ይህንን የሚያደርጉት ስልጣን ፈልገው ነው። ይህንን ከሥልጣን ፍላጎት ጋር የተያያዘ ችግር በተቻለ መጠን የሥልጣን መጋራትን በማስፋት መቀነስ ይቻላል። ከእዛ ውጭ የሚወራጨውን በቀላሉ ማሸነፍ ይቻላል።
በመሰረቱ በአገር ጉዳይ፣ በስልጣን ተሳትፎ ድርሻ ይኑረን ለሚሉ ወገኖች ማሸነፊያው መንገድ በስልጣን ማጋራት፣ በህጋዊ መንገድ፣ በምክክር፣ በብሔራዊ መግባባት ውይይት ሂደት ተገቢ መፍትሄ ላይ መደረስ አለበት።
ብሔራዊ መግባባት ውይይት ብዙ ጊዜ የሚነሳው ሽግግር ላይ ነው። እንደዚህ አይነት ስልጣን በተረጋጋ ሁኔታ ተይዞ ባለበት ጊዜ ግን መደረግ የሚችለው ስልጣን ላይ ያለው ወገን ሙሉ በሙሉ በጎ ፍቃድ ኖሮት ለእራሱ ስልጣን ሳይሳሳ ለአገሪቱ በሚበጅ መልኩ በእኩል የባለቤትነት ስሜት ሲመክር፣ ሲዘክር ነው። ሕገ መንግስቱን ለማሻሻል በሚደረገው ሂደት ውስጥ ሙሉ ስልጣን ያላቸው ወገኖች አገሪቱን የተሻለ አቅጣጫ በማስያዝ ሂደት ውስጥ ትልቅ ሚና አላቸው። በእዛ ላይ ሙሉ ቅን ልቦና ከሌለ፣ የስልጣን ካባ የሚፈጥረውን ስሜት አውልቆ ሃሳብን በሃሳብነቱ መዝኖ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ አብረው ካልመከሩ ጠቃሚ ውጤት አይገኝም።
በብሔራዊ መግባባት ሂደት ውስጥ የሚሳተፉ ሁሉ የራሳቸውን ሳይሆን የኢትዮጵያን ሕዝብ ጥቅም ለማስቀደም መወሰን አለባቸው። ለዚህ ደግሞ ከፍተኛውን የአደራ ሸክም የሚሸከሙት ሕጋዊ ሥልጣንን በእጃቸው የያዙት ወገኖች ናቸው። ምክንያቱም በብሔራዊ መግባባት ውይይት ሂደቱ የሚሳተፉት ወገኖች ምክር ለመስጠት እንጂ ውሳኔ ለማሳለፍ ምንም ሕጋዊ አቅም የላቸውም። ያንን ውሳኔ የሚያሳልፈው ስልጣን ላይ ያለው ሃይል ነው። ስለዚህ ብሄራዊ መግባባት ጥሩ ውጤት ያመጣል። ግን ዋናው ታሪካዊ ሃላፊነት ያለበት ስልጣን ላይ ያለው ፓርቲ ነው።
አዲስ ዘመን:- አሸባሪዎቹ ሕወሓትና ሸኔ ሰሞናዊ አገር የማፍረስ ሴራቸውን እንዴት ይገልጹታል?
ፕሮፌሰር አድማሱ:- በመሰረቱ አሸባሪው ሕወሓት ያለፉት 27 ዓመታት ወታደራዊ ጉልበት፣ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ጉልበት የትኛውንም ሃይል በፈለገው መልኩ ጨብጦ ለመቆጣጠር የሚያስችለው ስልጣን ነበረው። ይህንን ስልጣን በሕዝብ ጫና እንዲለቅ ተደርጓል። ይህ ማለት ግን ባዶ ቀርቷል ማለት አይደለም። ብሩ በካዝና አለ። መሳሪያውንም በተለያየ መንገድ አከማችቷል። ዘርፎ የደበቀው አልተነካበትም። በውጭም በጥቅማ ጥቅም ግንኙነት የፈጠረው ግንኙነት አለ። በእዚህ ምክንያትም የእርሱ ጥቅም ሲነካ የሚጓደልባቸውም ዝም አይሉም። በአጠቃላይ ከስልጣን በወረደ ጊዜ እነዚህን አጥቷል ማለት አይደለም። ከአሸባሪ ቡድን እነዚህን እንዲያጣና አቅሙ እንዲዳከም ለማድረግ ብዙ ትግል ተደርጓል። በጥበብ የተሞላ አካሄድ እንደነበርም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ገልጸዋል።
በመጨረሻም አሸናፊ በመሆን ጉዳዩ እዚህ ደርሷል። አሸባሪው ሕወሓት ሸኔን ብቻ ሳይሆን በየአቅጣጫው ግጭት የሚፈጥሩ ቡድኖችን አሰማርቷል። እነዚህ ሁሉ ግጭቶች በአሸባሪው ሕወሓት ድጋፍ ሰጪነት የሚንቀሳቀሱ መሆናቸውን መረጃዎች ያሳያሉ። የእነዚህ የጥፋት ሃይሎች የገንዘብ ምንጭ ልጠረጥር የምችለው ወያኔን ነው። ምክንያቱም በማንኛውም ቦታ የሚገኝ የኢትዮጵያን ሃብትና ንብረት ዘርፏል።
አቅሙ ሙሉ በሙሉ ባለመሟጠጡ የገንዘብ ሃይል እንዳለው መገንዘብ ይቻላል። የገንዘብ ለውጡ ይህንን አቅሙን በጣም ንዶበት ሊሆን ይችላል። ግን አሁንም ቢሆን ከማንኛውም ለጥፋት ከተሰማራ ወገን የበለጠ የገንዘብ አቅም ይኖረዋል። እነ ሸኔ “ወረሩን፣ጥቅማችንን ነጠቁን፣ ወዘተ” በሚል ሰበብ በመነሳሳት የግድያ፣ የንብረት ውድመት፣ ማፈናቀልና ሌሎች አሰቃቂ ግፎች በተደጋጋሚ የፈጽሙት፤ እየፈጸሙም ያሉት በአብዛኛው 1977 እና 1978 ዓ.ም ከቀዬአቸው ተፈናቅለው ወደ ወለጋ፣ ጅማ፣ከፋ፣ ጋምቤላ፣ መተከልና የመሳሰሉት አካባቢዎች የሰፈሩ በብዛት ከወሎ አካባቢ ተፈናቅለው የሚኖሩ ሰዎች ላይ ነው። አሸባሪዎቹ ሕወሓትና ሸኔ ዞሮ ዞሮ የሚያካሂዱት ጎሳዊ ግጭት ነው። በባህሪ አንድ ስለሆኑም ለሰብአዊ ርህራሄ የሌላቸው ናቸው። አንድ ባህሪ ስላላቸው ተፈላልገው አልተጣጡም።
አዲስ ዘመን:- አሸባሪው ሕወሓት ነጥያቸዋለሁ ያላቸው ሕዝቦች ኢትዮጵያዊነትን ለማጽናት እያሳዩ ያሉትን አንድነትና ሕብረትን እንዴት ተመለከቱት?
ፕሮፌሰር አድማሱ:- አሸባሪው ሕወሓት ነጥያቸዋለሁ ያላቸው ሕዝቦች ኢትዮጵያዊነትን ለማጽናት የመከላከያ፣ የክልል ታጣቂዎችና ሚሊሻዎች አንድነትና ሕብረትን እንዲሁም በያሉበት ሆነው በሚችሉት ሁሉ ድጋፍ የሚሰጡ ኢትዮጵያዊያን አኩሪ ታሪክ እያስመዘገቡ ነው።
አሸባሪው ሕወሓት ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያለው ጥላቻ ስልጣን ላይ ከወጣ በኋላ የመጣ አይደለም። ለምሳሌ ከ1965 እስከ 1967 ዓ.ም በመምህርነት ትግራይ ክልል አክሱም ውስጥ ባሳለፍኩበት ወቅት የነበረውን ላጫውትህ። በ1967 ዓ.ም ጥምቀት በዓል አካባቢ ለህክምና ወደ አዲስ አበባ መጥቼ ተመርምሬ ስመለስ ብዙዎቹ አክሱም የነበሩ መምህራን ጓደኞቼ ወደ ራያና አዘቦ፣ እንደርታ፣ ተቀይረው ጠበቁኝ። ይህ የሆነው በሕወሓት ምክንያት ነበር። አሸባሪው ሕወሓት ‹‹አምሐራ አድጊ›› አማራ አህያ ነው የሚል መፈክር በመያዝ፣ በየአስፋልቱ፣ በመምህራን መኖሪያ አካባቢ መልዕክቱን በቾክና በከሰል በመጻፍ አስመርሯቸው፣ ስጋት ውስጥም ከትቷቸው ነበር።
የቀየሩት በእዚህ ምክንያት ነው። እኔ ስደርስ አንተስ ቅያሪ ትፈልጋለህ? ችግር ተፈጥሯል አሉኝ። አማራ ተብለው ስጋት ውስጥ በመግባታቸው የተቀየሩት መምህራን ከወሎ፣ ከኦሮሚያ ሰሜን ሸዋ፣ ከሐረር አሰበ ተፈሪ፣ ከአርሲ፣ ከጉራጌ፣ እና ከሌሎችም አካባቢዎች የመጡ ነበሩ። አማራ የተባሉት ትግርኛ ተናጋሪ ያልሆኑት ሁሉ ናቸው።
የእዚያን ጊዜ ከትግራይና ከኤርትራ ውጭ የሆነ ማንኛውም አማርኛ የሚናገር ኢትዮጵያዊ ማለት ነበር። ያኔ 1967 ዓ.ም በነበረው ሁኔታ ኦሮሞ፣ ጉራጌ፣ ወላይታ፣ ከንባታ ወይም ሲዳማ የሚባሉ ብሄረሰቦች መኖራቸውን የሚያውቁም አይመስለኝም።
ለነገሩ እኔም ብሆን የዚያን ጊዜ አማራ የሚባል ሕዝብ ስያሜ መኖሩን አላውቅም ነበር። ወያኔ ሥልጣን ላይ ከመውጣቱ በፊት “አማራ” የሚለውን ቃል የማውቀው ኦርቶዶክስ ክርስቲያን በሚለው ትርጉሙ ብቻ ነበር። የኢትዮጵያ ሕዝብ 27 ዓመታት በአሸባሪው ሕወሓት በገፍ ቢቀጠቀጥም፣ ማሕበረሰቦችን ከማህበረሰብ ለማለያየት ያላሰለሰ ከፍተኛ ጥረት ቢያደርግም ቢያጎሳቁለውም ኢትዮጵያዊነትን እንዳሰበው ሊያጠፋው አልቻለም። ኢትዮጵያዊነት ለማንም የማይበገር ጥልቅና ሃያል መንፈስ ነው። ኢትዮጵያዊነት በበርካታ ተከታታይ ትውልዶች የተፈጠረ ለማንም፣ ለምንም የማይበገር ሃይል ነው።
ለዚህ ነው ወያኔም ሆነ ሌሎች በየዘመኑ ኢትጵያዊነትን ለማጥፋት የሞከሩ ሁሉ ያልተሳካላቸው። ወያኔ የዘራቸው ሰይጣናዊ አመለካከቶች የሚታዩትና መሰል አጥፊ ነገሮች የሚፈበረኩት በእንደኔ አይነቱ ልሂቃን ነው። ይህ ደግሞ የስልጣን ፍላጎት ነው። ለስልጣን አቋራጩ ይህ ነው ብሎ ከማመን ይመነጫል። በተለያዩ ቦታዎችና ጊዜዎች ግጭቶች ተከስተው ነበር። በአንድ ቦታ፣ አንድ ወቅት የተከሰተ ጎሳዊ ግጭት ቀጣይነት የለውም።
በአጥፊዎች የተፈጠረውን ግጭት የአካባቢው ሕብረተሰብ ስለማይቀበለው በአጭሩ ሲቀጭ ይታያል። ምክንያቱም የእኛ ሕዝብ ለእንግዳ የሚሰጠው ክብርና ጥበቃ ከፍተኛ ነው። ቢጋጭ እንኳን እርስ በእራሱ ነው እንጂ በጎሳና በሃይማኖት ልዩነት ምክንያት ግጭት ሲፈጥር አላየሁም፣ አልሰማሁም። እንግዳ የትም አካባቢ ይከበራል። በኢትዮጵያ ውስጥ ለ15 ዓመታት ያህል ሁሉንም ክልሎች፣ አብዛኛዎቹን ወረዳዎች በመስክ ጥናት ሥራ ምክንያት ተዘዋውሬ አይቻለሁ።
እኛ ኢትዮጵያዊያን የተለያዩ ቋንቋዎች እንናገር እንጂ የምንጋራቸው በርካታ እሴቶች አሉን። በተዘዋወርኩባችው አካባቢዎች ሁሉ በእንግድነቴ ሁሉም ተንከባክበውኛል። ክፉ ነገር እንዳያጋጥመኝ ጠብቀውኛል። ሥራዬም እንዲሳካልኝ አግዘውኛል። አካባቢያችውንም እንዳውቅ አበረታተውኛል። በመሆኑም መስክ የመውጣት ሱስ ይዞኝ ነበር። መስክ ሳልወጣ አንድ ወር ከሞላኝ ናፍቆቴ የበረታ ነበር።
የወያኔ ሰይጣናዊ ጥፋት የተላተመው ይህንን አይነት ምቾት ከሚሰጥ ሕዝብ ጋር ነው። ወያኔ ኢትዮጵያዊነትን ለማጥፋት ከአርባ አመታት በላይ ባለ በሌለ ሃይሉ ቢታገልም ሊሳካለት ያልቻለው ለዚህ ነው። እንዲያውም አሁን ኢትዮጵያዊነት እንኳን ሊጠፋ፣ ሊያጠፋው የተመኘውን ወያኔን ሊያጠፋው ነው። ለዚህ ነው ኢትዮጵያውያን ከዳር እስከ ዳር የተንቀሳቀስነው።
አዲስ ዘመን:- የትግራይ ሕዝብን ከትህነግ የሃሰት ፕሮፖጋንዳ አንጻር እንዴት ተመለከቱት?
ፕሮፌሰር አድማሱ:- ከሌላው ማህበረሰብ ይልቅ የትግራይ ሕዝብ በአሸባሪ ቡድኑና በአጫፋሪዎቹ ፕሮፓጋንዳ በጣም ደንዝዟል። በመምህርነትም ሆነ ለአይሪሽ የእርዳታ ድርጅትም በእዛ አካባቢ ለሚገኙ ፕሮጀክቶች በአማካሪነት ተቀጥሬ ሰርቻለሁ። የትግራይ ሕዝብ መረጃ የሚያገኘው ከወያኔና ካጫፋሪዎቹ ብቻ ነበር።
የወያኔ ትልቁ ጉልበት የፕሮፓጋንዳ አጠቃቀሙ ነው። ሃሰተኛ መረጃን እያመረተ ራሱን በሚያጎላ ሌላውን በሚያኮስስ መልኩ የመጠቀም ችሎታው ከፍተኛ ነው። ሌላውን ሕብረተሰብ የሚስለው መጥፎ አድርጎ ነው።
የትግራይ ሕዝብ ወያኔ የሚያሳየውን ሁሉ ማየት፣ የሚለውን ሁሉ መስማት እንጂ ሌላ አማራጭ የለውም። ያለው እድል ሰጥ ለጥ ብሎ መገዛት ብቻ ነው፤ የህልውና ጉዳይ ነው። ከዚህ ውጭ ከተጠረጠሩ በ”ክህደት” ተወንጅለው ይሰወራሉ። ልጆቻቸው ተሰውረው በደረሰባቸው ሀዘን ምክንያት አይናቸው ሊጠፋ የተቃረቡ በተለያየምክንያትየተዋወኳቸውእናቶችአጋጥመውኛል። ለሚበሉትም፣ ለሚጠጡትም ሆነ በማንኛውም ነገር ያሉት በወያኔ እጅ ነው። የእርዳታ እህልም እኮ የሚታደለው በወያኔ ፈቃድ ነበር። ለፈለገው ሊሰጥ ላልፈለገው ሊከለክል ይችል እንደነበር አውቃለሁ።
እንኳን እንዳሁኑ በእርዳታ ሰጪ አገሮችና ድርጅቶች ፊት አግኝቶ ይቅርና በራሱም ጊዜ የእርዳታ እህል የአገዛዝ መሣሪያው ነበር። ሕዝቡን በአንድ ለአምስት አደረጃጀት ጠርንፎ ይዞት ነበር። ስለዚህ እኛን እንደ ወገን ባይቀርቡን፣ ባያውቁን አይገርመኝም።
የትግራይ ሕዝብ ከአርባ ዓመታት በላይ ስለእኛ ትክክለኛ መረጃ የለውም። የትግራይ ሕዝብ ተፈጥሯዊ ባህሪይ ከአርባ ዓመታት ያለማቋረጥ በተሰራ የሀሠት ፕሮፖጋንዳ ስራ ሌላ መረጃ እንዳይኖራቸው ታፍነው ተቀጥቅጠዋል። ሌላው ማህበረሰብ ጭራቅ ተደርጎ ተስሎላቸዋል። በእኔ እምነት ይህ የተቃወሰ ስብዕና በቀላሉ የሚጠፋ አይመስለኝም።
ጊዜ ይፈልጋል። አዲስ ዘመን:- የትህነግ የሃሰት ፕሮፖጋንዳ ለመመከት ምን መደረግ አለበት ይላሉ? ፕሮፌሰር አድማሱ:- በውሸት ቁልል የታጀበ ፕሮፓጋንዳ ሥርጭት ለጊዜው ከባድ ጉዳት ያደርሳል፤ እያደር እየቀለለና ፈጣሪውንም እያቀለለ መሄዱ አይቀርም። በአንጻሩ ደግሞ ሐቅ ሁል ጊዜ እየጠነከረና እንደወርቅ እየጠራ መሄዱ አይቀርም። ሐቅ እንደ ውሸት መልኳን ባትቀያይርም ከውሸት ቀድማ ቶሎ ወደ ሕዝብ ጆሮ ካልደረሰች ትልቅ አደጋ ይከሰታል። ትክክለኛን መረጃ ፈጥኖ ለሕዝብ ባለማድረስ የሚከሰት ጉዳት አለ። በመሆኑም ልንሰራ የሚገባንን በፍጥነት መስራት ይገባናል።
ቀድሞ በሰው ጆሮ የደረሰን ትክክለኛ መረጃ በሃሰት ፕሮፓጋንዳ ለመፋቅ ያስቸግራል። ሐሰትም ቢሆን ቀድሞ በመድረሱ ቦታ ይይዛል። ትክክለኛው መረጃ ዘግይቶ ከደረሰ በጥርጣሬ እንደሚታይ መገንዘብ ያስፈልጋል። ትክክለኛ፣ ተአማኒነት ያለውን መረጃ በፍጥነት ማስተላለፍ ይገባል። ለዛሬ አላገለገለንም ብለን በምንም መልኩ ከሐቅ መሸሽ የለብንም። ብርታትና ጥንካሬ የሚሰጠን ከዳር የሚያደርሰንም ሐቅ ነው። ለእዚህ ስራ ደግሞ ተገቢውን ሃብትና ተገቢውን ባለሙያ የሰው ሃይል ማሰማራት ይገባል።
አዲስ ዘመን:- ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም አሸባሪው ሕወሓት የአገር ደጀን የሆነው የመከላከያ ሰራዊትን ከኋላ የወጋበት አጋጣሚ ሲያስቡ ወደ አይምሮዎ የሚመጣልዎት ምንድን ነው?
ፕሮፌሰር አድማሱ:- ወያኔ ይህንን ማድረጉ አላስገረመኝም። ወያኔ ስልጣን ከመያዙ በፊት ከጎንደር እንዳየሱስ አደባባይ አንስቶ በሐዋሳ፣ በአምቦ፣ በአዲስ አበባ እና በሌሎች በተለያዩ አካባቢዎች በተለያየ አቅጣጫ ያለምንም ምክንያት ምንም መሣሪያ ያልያዙ በርካታ ሰላማዊ ዜጎችን በአደባባይ ረሽናለች።
ይሄኛውን የሚለየው አገርን ለመከላከል የተሰለፈን ወገን፣ አብሮ እየበላና እየጠጣ የኖረን፣ ክፉንም ደጉንም አብረው የተካፈሉን የበረሃ ጓዶች፣ አዘናግቶና አድፍጦ ከጀርባ መውጋቱ ነው። ይህ ደግሞ በምንም ሁኔታ ውጤቱ የጀግና ሊሆን አይችልም።
የከሃዲ፣ የወራዳና የፈሪ ድርጊት ነው። እጅግ በጣም አሳፋሪም ነው። በአእምሮዬ የሚመጣልኝን ነገር በበቂ ሁኔታ ለመግለጽ ቃላት ያንሰኛል፤ ችሎታም የለኝም። እኔ በተወለድኩበት አካባቢ እንኳን በወዳጅህ ላይ በጠላትህ ላይ ማድረግ የሌለብህን ተግባር አስመልክቶ ማህበረሰባዊ ሕጎች አሉ። ከነዚህም ውስጥ ደመኛህን ከኋላው፣ በተኛበት፣ ሱሪውን ሳይታጠቅ በዱላም ይሁን በጠመንጃ ወይም በሌላ መሣሪያ ማጥቃት ነውር ነው። ነውረኛ ሰው በማህበረሰቡ ውስጥ ተቀላቅሎ በሰላም ለመኖር ይቸገራል። በመሆኑም የተጠቀሱትን ማህበረሰቡ በነውርነት የፈረጃቸውን ተግባራት የፈጸመ ስለመኖሩ እስካሁን ምንም አልሰማሁም። የወያኔ ድርጊት በነውርነትም ቢመዘን አቻ የለውም።
አዲስ ዘመን:- መንግስት ኢትዮጵያ አሁን ከገጠማት ችግር ለማዳን ምን ማድረግ አለበት?
ፕሮፌሰር አድማሱ:- መንግስት አሁን እያደረገ ያለው ትክክለኛ ተግባር ነው። ይሄንን ማጠናከር አለበት። በፌዴራል መንግስት በኩል በአንድነት አቀናጅቶ መምራቱ መኖሩ አስፈላጊ ነው። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በጣም ወሳኝና በአስፈላጊ ጊዜ የተወሰነ፣ ትክክለኛ አካሄድ አድርጌ እወስደዋለሁ።
ፊት ለፊት በግንባር በመፋለም መስዋዕትነት የሚከፍሉትን ወገኖቻችንን ጥረት በተለያዩ መንገዶች መደገፍ ያስፈልጋል። ድጋፉ አካባቢን በመጠበቅ፣ በገንዘብና በቁሳቁስ በመርዳት፣ በስንቅ ማቅረብ፣ የሕክምናና የእንክብካቤ አገልግሎት በመስጠት፣ በማበረታታት፣ በመሳሰሉት መንገዶች መደገፍ ይቻላል። በተጨማሪም የዘማች ቤተሰቦችን የመንከባከብ ስራ በመስራት ጦርነቱ በድል እንዲጠናቀቅ ማንኛውም ዜጋ የሚችለውን እንዲያደርግ ያስችላል። አሸባሪውን ቡድን በግምባር ፊት ለፊት የሚፋለመው ብቻ ሳይሆን በደጀን ያለውም ሕዝብ የፍልሚያው አካል ለመሆን በሚቻለው ሁሉ መረባረብ ይጠበቅበታል።
በዚህ የህልውና ትግል ተሳታፊ በመሆን ሁሉም የድርሻው በማበርከት የአገራችንን ህልውና ለመፈታተን የተሰለፉትን ሁሉ የሚያሳፍር ድል ባለቤት እንደሚሆን አልጠራጠርም።
አዲስ ዘመን:- በዚህ የቀውስ ወቅት የሰብአዊ መብት አያያዝ ጉዳይን በተመለከተ ምን መሆን አለበት?
ፕሮፌሰር አድማሱ:- የሰብአዊ መብት መጣስና አለመጣስ ያለንበት ሁኔታ አይደለም የሚወስነው። ምንጊዜም ቢሆን ሰብአዊ መብት መጣስ የለበትም። ነገር ግን አንዳንድ ሥነ ሥርዓት ነክ ጉዳዮችን በሚመለከት፣ ለምሳሌ አንድን ተጠርጣሪ ወደ ፍርድ ቤት የማቅረብ ሁኔታ በመደበኛ ህግ ውስጥ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ለማከናወን ፈታኝ ሊሆን ይችላል። ተጠርጣሪን በቁጥጥር ሥር ለማዋልና ለመፈተሽ መከናወን ያለባቸው ሥርዓቶች ላይ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አስፈላጊ ናቸው የተባሉ ጊዜያዊ ህጋዊ ለውጦች አድርጓል።
ይህ መደረጉ ነገሮችን በፍጥነት ለማከናወን፣ የማጣራት አቅምና የተጠርጣሪዎች መብዛት ግምት ውስጥ በማስገባት ነው የሚል ግምት አለኝ። ነገር ግን አንድ ተጠርጣሪ በቁጥጥር ስር ሲውል በሕግ የተደነገገ ሊጠበቅለት የሚገባ የማይሸራረፍ መብት አለው። በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁና መደበኛ ሕጎችን ያለአድልዎ በትክክል ስራ ላይ ማዋል ያስፈልጋል። በቁጣ፣ በግልፍተኝነት ከህግ ውጭ በሆነ መንገድ ተጠርጣሪዎችን ማንገላታትና በተጠርጣሪዎች ላይ በደል መፈጸም ራሱ የሚያስጠይቅ ወንጀል መሆኑን የሚመለክተው ሁሉ ሊያውቀው ይገባል።
ስለሆነም ትልቅ ጥንቃቄ መደረግ አለበት። በህግ ጥበቃ ስር ያሉ ሰዎችን መብት በተመለከተ ምንም የተለወጠ ሕግ የለም። በመሆኑም መሰረታዊው የሰብአዊ መብት ጥበቃ በተሟላ መልኩ መደረግ አለበት። ይሄንን ሁሉም እንዲያውቀውና እንዲያከብረው ደጋግሞ መንገር ያስፈልጋል። ከህጋዊ ስርዓት ውጪ ከተሄደ ነገሩ ይበላሻል። ለምን ተጠረጠርኩ የሚል ቅሬታም ጥያቄም ሊፈጠር አይገባም።
ሁላችንም አዋጁን ማክበር አለብን። ከዚህ አዋጅ መንፈስ ውጭ የወጣ ድርጊት እንዳይፈጸም ሁላችንም ዘብ መቆም አለብን። ስሜታዊነት በሃላፊነት መንፈስ ከሚከናወኑ ጉዳዮች ጋር ይጋጫል። በደም ፍላት የሚታሰብ ክንውን ክፍትህ ጋር ይጋጫል።
በመንግስት የሚመራው ዘመቻ ዋና ዓላማ በወያኔና በጌቶቹ እየደረሰብን ያለውን ጥቃት ለመመከትና ጥፋተኞች ወደ ሕግ ለማቅረብ ነው። ይህም በህጋዊ ስርኣትና በህጋዊ መንገድ ሕገወጥ ድርጊትን የመቋቋም ተግባር ነው። ስለዚህ በሕጋዊ መንገድ በቁጥጥር ስር ያሉ ሰዎች አያያዝ በቂ ጥንቃቄ ሊደረግለት ይገባል። ኢትዮጵያ የሕግ አገር ናት። ‹‹በሕግ አምላክ›› በማለት የህግን ግንዛቤ አስርጻ የኖረች አገር ናት። በህግ የበላይነት የማመን ከፈረንጅ የወረስነው አይደለም። “እነርሱ ግፍ ሰርተውብናል” በሚል ንዴት ሚዛን ስተን አስነዋሪና ሕገወጥ ተግባር እንዳንፈጥር አደራ እላለሁ።
አዲስ ዘመን:- አሁን ያሉ አገራዊ ችግሮችን ለመሻገር ምን መሰራት ይኖርበታል?
ፕሮፌሰር አድማሱ:- ወያኔ የምትሰራውን ግፍ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስወገድ ሁሉም እንዲረባረብ ጥሪ ቀርቦለታል። ጥሪውን ተቀብሎም በመንቀሳቀስ ላይ ነው።
ይህ አይነት አሰራር ለጦርነትብቻ መሆን የለበትም። የጦርነት አይነት ውጤት ያላቸውን አስከፊ ችግሮቻችንን ለማሸነፍ በተመሳሳይ መንገድ መረባረብ ይኖርብናል። ድህነታችንን ማስወገድ አለመቻላችን በስልጣን አያያዝ ላይ የሚያቀራርበንና የሚያስማማን ስርዓት አለመፍጠራችን በአብነት ማንሳት ይቻላል።
እነዚህና ሌሎች ብሄራዊ ችግሮቻችን መፈታት ያለባቸው በዚሁ መልክ ነው። ሁሉም ዜጋ የሚያሳትፍ ሥርዓት መፍጠር መቻል አለብን። ግዙፍ ብሄራዊ ችግሮቻችን በጥቂቶች ጥረት ብቻ ማስወገድ አይቻልም። ሕዝብ የተወሰኑ ሰዎችን ስለመረጠ በአገሩ ጉዳይ ያለው ተሳትፎ መገደብ አለበት ማለት አይደለም። የሕዝብ በአገር ጉዳይ በተለያዩ ደረጃዎች ባሉ ጉዳዮች መሳተፍ የዕለት ተዕለት ስራ መሆን አለበት። ሁልጊዜ፣ የትም ቦታ ሕዝብ አሳታፊ እንቅስቃሴዎች መኖር አለባቸው።
ሕዝብ በአገር ጉዳይ ሲገለል ጣጣ ይበዛል። ስርዓቱ ሕዝብን ተሳታፊ ካደረገ ከትውልድ ትውልድ ሲሸጋገር የቀደመውን እያሻሻለ የመቀጠል ሂደት ይኖረዋል። አፍርሶ እንደገና የመገንባት አካሄድ አይኖርም። አንዱን ባይተዋር ሌላውን ባለቤት የማድረግ አካሄድን ያስቀራል።
ሂደቱም የሰለጠኑ አገራት የደረሱበት ደረጃ ለመድረስ ረጅም ጊዜ አይወስድም። አሜሪካም ሆነች ሌሎች ትልቅ የሚመስሉ አገራት ውስጣቸው የተከፋፈለ ማህበረሰብ ያለበት ነው። የእነርሱ ስርዓት የውስጥ ክፍፍላቸውን ሊያርመው አልቻለም። በወታደራዊ ወይም በኢኮኖሚው ከፍተኛ ደረጃ ስለደረሱ ጤነኛ ይመስላል።
ዴሞክራሲያዊ ስርዓታቸው አገር የሚገነባ አይደለም። ሁል ጊዜም መጣላትና መቆራቆስ ይታይባቸዋል። አንዱ ስልጣን ሲይዝ ሌላው እንዳይሳካለት እንቅፋት ይሆናሉ። የአሜሪካና የብሪታኒያ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለእኛ አይሆነንም። ለእኛ የሚያዋጣን የመግባባት ሞዴል ዴሞክራሲ ነው። የመግባባት ሞዴል ዴሞክራሲ መሰላልና ድልድይ ሆኖ ቶሎ አስፈንጥሮ ወደምንፈልገው ደረጃ ያደርሰናል። በመሆኑም ያንን የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ መምረጥ ይኖርብናል።
አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ።
ፕሮፌሰር አድማሱ:- እኔም አመሰግናለሁ።
ዘላለም ግዛው
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 11/2014