ፋሽን የዘመን ማሳያ መልክ ነው፤ መስታወት። መልክ ደግሞ በጥበበኛ እጆች ይበጃል፤ በሰለጠነ መልክ ይኳሻል። ፋሽን ባህልና አመለካከትን ያንፀባርቃል። ፋሽን ቀለምና ቅርፅ መነሻው ውበትና ምርጫ መዝለቂያውና መዳረሻው ናቸው። ይህ ፋሽን የተሰኘው እሳቤ በተለያየ መልኩ ሰዎች የፈጠራ አቅማቸውና ልምዳቸውን ተጠቅመው ያሳድጉታል። ለሌላው በማውረስም ይቀባበሉታል።
በዚህም የዘመኑን ሰው አመለካከት ተንተርሶ የዚያ የተገኘበትና የተፈጠረበት ዘመን ይመስላል። የግል ወይም የጋራ እሳቤ ታክሎበት በወቅቱ ሰዎች ይፈጠራል። ወቅታዊነቱ ሰፍቶ ይለመዳል ብሎም ሰፍቶ በብዙዎች የሚዘወተር ይሆናል። ፋሽን በብዙ መልኩ ይገለጻል። በተለይ በተለያየ የአልባሳት አሰራር፣ አጠቃቀም ይገለጻል፤ የጸጉር አሰራሩ፣ ሌሎች ውበት ለመጨመር ሲባል የሚደረጉ ጌጣ ጌጦች አጠቃቀምና አሰራር ሁሉ በእዚህ ውስጥ ይካተታሉ።
ፋሽን የዘመን መለኪያና መግለጫ ተግባር ነው። ከአልባሳት እስከ መገልገያ ቁስ ከመዋቢያ እስከ ማጌጫ ይዘልቃል። ሜክአፕም የፋሽን አንዱ መገለጫ ነው። ውበትን ለመጨመር ሲባል ሜክአፕ መጠቀም ይዘወተራል፤ ሜክአፕ /አቻ ትርጉም ስላጣን እንዳለ ይዘነዋል/ አንድን ውበት ይበልጥ ማሳደግ ማስዋብ ማስጌጥ አልያም ደግሞ በፊት የነበረው ገፅታ የተሻለ እንዲሆን ማድረግ ሲሆን፣ ሌሎች ጠቀሜታዎችም አሉት።
ከዚያም ውስጥ የተፈጥሮን ውበት ለመጠበቅ፣ ለማሳመር (ለማስዋብ)፣ የሰዎችን ፊት በተለያየ መልኩ ለመለወጥ (ለፊልም ገፀ ባህሪያት) የመሳሰሉት ስራዎች መጠሪያ ስያሜ መሆኑን ባለሙያዎች ይገልፃሉ። ከእነዚህ ውስጥ ለዛሬ ፋሽን ገፃችን ማስዋብና የማስዋቢያ ዘዴዎችን በተለይ ሜክአፕን እንዳስሳለን። በተለምዶ ሜካአፕ የሚባለው የውበት መጠበቂያ ዘዴ የሰዎችን ፊት ማስዋብና ተጋላጭ የሆኑ የሰውነት ክፍሎቻችን በውበት መጠበቂያዎች ማስዋብ ወይም
መቀባት ነው። ውበትን የሚጨምሩ ነገሮችን በፊት ላይ መጠቀም ጥንት ጀምሮ ያለ ነው። በየወቅቱ አዳዲስ ይፈጠራል፤ የቀድሞው ይሻሻላል። ራስን በተለያየ መልክ ማስዋብ ባለና ተፈጥሮ በለገሰ በቀላሉ በአካባቢ በሚገኝ ዕፅዋት የእንስሳት ተዋፅዖና በተለያዩ ጥራጥሬና ፍራፍሬዎች በመጠቀም ፊትና ሌላ አካላትን ማስዋብና መንከባከብ የቆየ ልማድ ነው። በድሮ ዘመን ኢትዮጵያውያን በተለይ እናቶችና ወይዛዝርት የፊት ውበታቸውን ለመጠበቅና ለማስዋብ የተለያዩ ዘዴዎችን ይጠቀሙ ነበር። ጥንት ሙሽራ እንደ ዛሬው የውበት ሰዓሎን ውስጥ ገብታ በባለሙያ ተቆነጃጅታ ለሰዓታት ቆይታ መውጣት አልነበረባትም። ይልቁን በአገር ልማድ መዋቢያዎች እነ እንሶስላ፣ ወይባ ጥስ (በእርግጥ ይህ በማንኛውም ሰዓት ሴቶች ለመዋቢያነት ይጠቀሙታል)፣ ፊት ላይ የሚቀቡ ቀላልና የተለያዩ ፊት ማሳመሪያ በቤት ውስጥ የሚዘጋጁ መድሀኒቶች ይጠቀማሉ።
ወጣት ኮረዶች ራሳቸውን የሚጠበቁባቸውንና የሚንከባከቡባቸውን መዋቢያዎች ሁሌም ይዘው ይገኛሉ፤ ወጣትነት አምረው የሚታዩበት ውድ ጊዜ ነውና መዋብ ማስዋብን የራስ ፊትና ሰውነት መንከባከብን ከእናቶቻቸው ተምረው ይከውኑታል።
እናቶች ባሎቻቸውን በምንም መልክ ተውበው መጠበቅ እንዳለባቸው ይገነዘባሉና ገርጥተው አይታዩም፤ ባህልና ልማድ ያስተማራቸውን የውበት መጠበቂያዎች ተገልግለው ራሳቸውን ይጠብቃሉ።
በሄለን የውበት ሙያ ማሰልጠኛ ለ6 ወራት ስልጠና ወስዳለች ሜካፕ አርቲስት ሜላት አየለ። በተለያዩ ፊልሞች ላይ በሜክአፕ አርቲስትነት ተሳትፋለች። በመንገዴ ላይ፣ ሳላይሽ፣ ሄዋን ስታፈቅርና፣ ስጪኝ በተሰኙ ፊልሞች ላይ የሜካፕ (ማስዋብ) ስራን በብቃት ተወጥታለች። በግልዋም ሙሽሮችን ማስዋብና የተለያዩ የውበት ሳሎኖች ውስጥ ታገለግላለች። ዘርፉ በአገር ደረጃ እያደገ እየመጣ መሆኑን የምትናገረው ወጣት ሜካአፕ አርቲስት ሜላት፣ ሜካአፕ ተፈጥሯዊ ውበትን በተሻለ መልኩ ለመጠበቅና አዕምሮ ለመታየት ትልቅ ፋይዳ እንዳለውና በራስ መተማመንን እንደሚያሳድግ ትገልፃለች። ነገር ግን በስፋት የሚታየው የሜካፕ አጠቃቀም እውቀት ከሆነ ጉዳቱ እንደሚያመዝንና ታስረዳለች።
አሁን ላይ ወጣቶች ያለ እውቀት በድፍረት በራሳቸው የሚጠቀሙት ሜካአፕ በተለይ ፊት ላይ ሲሆን ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችልም ትጠቁማለች። መዋቢያዎች በስፋት ገበያ ላይ እንደሚገኙ ጠቅሳ፣ ወጣቶች ምንም አይነት የአጠቃቀም ግንዛቤ ሳይኖራቸው እየተጠቀሙ መሆናቸው በስፋት እንደሚስተዋል ትናገራለች። ይህ ደግሞ ከጥቅሙ ጉዳቱ እንደሚያመዝንና ተፈጥሯዊ ውበትን ለአደጋ እንደሚያጋልጥም ታስገነዝባለች። ይህ የወጣቶቹ ፍላጎት እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ ለዚሁ ተግባር በተለያየ ምርምርና ጥናት የተዘጋጁ መዋቢያዎችና ማቅለሚያዎች ተዘጋጅተው ገበያው ላይ ሞልተዋል። ሱቅ ሄዶ የሚፈልጉትን መግዛት እቤት ተመልሶ በአጭር ጊዜ በፈለጉት ቀለምና ቅርፅ እራስን መኳል ፊትን ማፅዳትና ማሰማመር ቀላል ሆኗል። አሁን አሁን ደግሞ እንዳንድ የስነ ውበት ባለሙያዎች የማማከር ስራ ውስጥ የገቡበት ሁኔታ ተፈጥሯል ስትል ሜካአፕ አርቲስት ሜላት ትገልጻለች። የስነ ውበት ባለሙያዎች (ሜካፕ አርቲስቶች) ማስዋብና መዋብ በራሱ ጥልቅ የሆነ እውቀት የሚጠይቅና በጥንቃቄ
ሊከወን የሚገባው መሆኑን ያስረዳሉ። መሰረት በላይ በሙያው ሰልጥና ለበርካታ ዓመታት የሰራችና በአሁን ሰዓትም የራስዋን “መሲ ቤተ ውበት” የተሰኘ የውበት ሳሎን ከፍታ በመስራት ላይ የምትገኝ ወጣት ናት።
በአሁኑ ሰዓት የተለያዩ መዋቢያዎች በተለያዩ ሱቆችና የኮስሞቲክስ መሸጫዎች ያለገደብ እንደሚሸጡና ተጠቃሚዎች ያለ ዕውቀት እየተጠቀሙ መሆናቸው መሰረትም ትጠቁማች። ይህ ደግሞ የተለያዩ የቆዳ መጎዳቶች እንደሚያደርስና በተደጋጋሚ ያላግባብ ከተጠቀሙ ቋሚ ለሆነ የቆዳ ችግር ያጋልጣል ታስገነዝባለች። አይንና እና መሰል የሆኑ የሰውነታችን ክፍሎች ላይም በምንጠቀማቸው መዋቢያ ምርቶች ምክንያት ከባድ የሆነ ጉዳት ሊያሰስከትል ይችላል ነው የምትለው። ማንኛውም ለስነ ውበት ማስዋቢያ ተብለው የሚቀርቡ ምርቶች ከመጠቀም በፊት የምርቱ አይነት ከተጠቃሚው/ዋ ቆዳ ጋር ተስማሚ መሆኑን ማረጋገጥ ይገባል።
ከሰዎች ዋንኛ አካላትና ተጋላጭ የሆነው ፊት በልዩ ጥንቃቄ ሊያዝ እንደሚገባ የሚገልፁት ባለሙያዎቹ፣ የፊት ቆዳ ምንነት ከተለየ በኋላ የትኛው ሜካፕ ለዚያ ቆዳ ይስማማዋል የሚለው መለየት ዋንኛ ተግባር ሊሆን እንደሚገባ ያስገነዝባሉ። እንደ ባለሙያ የፊት ቅርፅ፣ የቆዳ ቀለም፣ የቆዳ ወዛማነት ወይም ደረቅነት የሚጠቀሙት ማስዋቢያ እንደሚለያይም መሰረት ታብራራለች።
እንደ መልካችንን ሁሉ ቆዳችንም የተለያየ ባህሪ ያለው መሆኑን የምትገልፀው ሜላት፣ ማስዋቢያዎች ለቆዳችን ተስማሚ መሆን ያለመሆናቸው ቅድሚያ እውቀት ሊኖረን ይገባል ባይ ናት። ባለሙያዋ ሜላትም በተደጋጋሚ በስራዋ ውስጥ ቀድመው ያለ እውቀት ራሳቸውን ለማስዋብ የሞከሩና ቆዳቸው የተበላሸ ወጣቶች እንደሚያጋጥማትና ለዚህ ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበት ታስረዳለች።
ባለሙያዎቹ የውበት ማሳመሪያ የተለያዩ ግብዓቶች ወይም በተለምዶ ሜካአፕ እያልን የምንጠራቸው ምርቶች በተገቢው አካልና አግባብ በሆነ መልኩ ሊከወኑ እንደሚገባ አፅንዖት ሰጥተው ይገልፃሉ። ሲያጌጡ ይመላለጡ እንዳይሆን ተገቢው ዕውቀት ያላቸውን የዘርፉ ባለሙያዎች ምክር መቀበል ይጠቅማል። አበቃን፤ ቸር ይግጠመን።
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 11/2014