• ቢሮው ከእጁ የወጡትን የቱሪስት መዳረሻዎች ለማስመለስ ጥረት እያደረገ ይገኛል
አምቦ ፦ በአምቦ ከተማ የቱሪስት መዳረሻ ተብለው የተለዩ ስፍራዎች በባህልና ቱሪዝም እጅ እንደማይገኙ የባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ጉሬ ታሱ ገለጹ። የአምቦ ከተማ ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ኃላፊ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደተናገሩት፤ በከተማዋ የቱሪስት መዳረሻዎችን ለመለየት በተደረገው እንቅስቃሴ አምስት ስፍራዎች፤ ማለትም የአምቦ ውሃ፣ ፊንጫ ኦብሴ (ፏፏቴ )፣ የእግዜር ድልድይ፣ ፍልውሃ እና የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቤተ መንግስት የተለዩ ሲሆን፤ በሁሉም ላይ ጽህፈት ቤቱ አያዝባቸውም፤ ብለዋል።
አያያዘውም፤ የተለዩትን ቦታዎች አስከብረን ከተማዋን የቱሪስት መዳረሻ የማድረግና ወጣቶች ተደራጅተው እንዲሰሩ የማብቃት እቅድ ቢኖርም አምስቱም የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎች በአሁኑ ወቅት በከተማው የባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ስር አይገኙም ብለዋል።
ከተለዩት የቱሪስት ቦታዎች የአምቦ ውሃ፣ የፊንጫ ኦብሴ (ፏፏቴ )፣ ፍልውሃ በግለሰብ እጅ የሚገኙ መሆናቸውን ገልጸው፤ የከተማው ህዝብ ሀብት በምን መንገድ ለግለሰብ እንደተሸጠናስፍራዎቹ እንዴት በግለሰብ እጅ እንደወደቁ የማጣራት ስራ እየተሰራ ይገኛል። የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቤተ መንግስት ደግሞ የመከላከያ ካምፕ ሆኗል ሲሉ ተናግረዋል። የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቤተ መንግስት ትልቅ የገቢ ምንጭ መሆን እንደሚችል ጠቅሰው፤በአሁኑ ወቅት ቤተ መንግስቱ የመከላከያ ካምፕ ተደርጓል።
አግባብ ያለው አያያዝና ጥበቃ ስለማይደረግለትም በውስጡ ያለው ሀብትና ንብረት በሙሉ ጠፍቷል። ታሪካዊ ቅርሶች ወድመዋል ብለዋል። በወቅቱ በተደረገው እይታ ሁሉም ከጥቅም ውጪ መሆናቸውን ለመታዘብ ተችሏል። በአሁኑ ወቅትም የከተማዋ ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ራሱ የመግቢያ ደብዳቤ/ፈቃድ ካልያዘ ወደ ቤተመንግስቱ መግባት እንደማይችል አረጋግጠናል።
ኃላፊዋ እንደገለጹት፤ ቤተ መንግስቱን ማስተዳደር ለሚገባው አካል ስለሚመለስበት ሁኔታና በቤተ መንግስቱ የነበሩ የተሰባበሩና የጠፉ የባህል እቃዎችን በተመለከተ የማን ሀላፊነት ነው በሚሉት ጉዳዮች ዙሪያ ከቀድሞው የከተማዋ ከንቲባ ጋር የተነጋገሩ ቢሆንም፤ ጉዳዩ እልባት ሳያገኝ ከንቲባው ከስልጣናቸው ተነስተዋል ።
ወይዘሮ ጉሬ የከተማው ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሆነው ወደ ቢሮው ከመጡ ገና ሁለት ወር መሆኑን ጠቅሰው፤ ቢሮው ከእጁ የወጡትን የቱሪስት መዳረሻዎች ለማስመለስ ጥረት እያደረገ ይገኛል። የክልሉም ሆነ የፌደራል መንግስት ጉዳዩን በሚገባ አጢነው መፍትሄ ሊያበጁለት ይገባል ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 27/2011
በዳንኤል ዘነበ