አዲስ አበባ፡- የዓድዋን ድል ለመዘከር ለሚገነባው የዓድዋ ፓን አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ ግንባታ የሚውል ገንዘብ ለማሰባሰብ የሚያስችል ዝግ የባንክ አካውንት እንዲከፈት ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ጥያቄ አቅርቦ ምላሽ በመጠበቅ ላይ መሆኑን የዓድዋ ፓን አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ የምስረታ አስተባባሪ ኮሚቴ አስታወቀ።
የኮሚቴው አስተባባሪ አቶ ቢተው በላይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፣ለዩኒቨርሲቲው ምስረታ በርካታ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ድጋፍ ለመስጠት ፍላጎት አሳይተዋል። ኮሚቴው ድጋፉን ለመቀበል የሚያስችል የገንዘብ ማስገቢያ የባንክ አካውንት እንዲከፈትለት ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ጥያቄ አቅርቦ ምላሽ በመጠበቅ ላይ ይገኛል፡፡
ከመጋቢት 2010 ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን ድረስ ለሦስት ጊዜያት ያህል ጥያቄውን ለጽሕፈት ቤቱ ቢያቀርብም እስካሁን ድረስ ምላሽ አላገኘም፡፡ ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች የሚገኘውን ድጋፍ ለመቀበል እንዲሁም ሕዝቡ ከድጋፉ ስለሚገኘው ገንዘብ ማወቅና ገንዘቡም ሕጋዊ አሰራርን ተከትሎ ኦዲት መደረግ ስላለበት በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚከፈት ዝግ የባንክ አካውንት እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል፡፡
‹‹ባለፈው ዓመት የፌዴራል መንግሥት ለዩኒቨርሲቲው ግንባታ የገባውን የ200 ሚሊዮን ብር ድጋፍ በቅርቡ ይሰጣል የሚል ተስፋ አለን›› ያሉት ሰብሳቢው፣ የትግራይ ክልል መንግሥት 250 ሚሊዮን ብር ለመስጠት ቃል መግባቱንና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 10 ሚሊዮን ብር መስጠቱን ተናግረዋል፡፡ ሌሎች ክልሎችም ድጋፍ እንደሚያደርጉ ቃል ስለመግባታቸው ጠቁመዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም፣ ‹‹በውጭ አገራት የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና የሌሎች አገራት ምሁራንን አነጋግረናል፤ የተለያዩ ኮርሶችን ለማስተማርና የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግም ዝግጁ እንደሆኑ ገልጸውልናል›› ብለዋል፡፡ በ2010 ዓ.ም በአዲስ አበባና በዓድዋ አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶች መካሄዳቸውን አስታውሰው፣ በወቅቱ ከበርካታ አካላት ጋር ግንኙነት መፈጠሩን አስረድተዋል፡፡ አስተባባሪ ኮሚቴው ካሉት ዐቢይ ኮሚቴዎች መካከል በአሁኑ ወቅት በንቃት እየተንቀሳቀሱ ያሉት የስርዓተ-ትምህርት ቀረፃና የሕዝብ ግንኙነት ኮሚቴዎች እንደሆኑም አቶ ቢተው ተናግረዋል፡፡
ለግንባታው 10 ቢሊዮን ብር ያስፈልገዋል የተባለው የዓድዋ ፓን አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ የመሰረት ድንጋይ በሚያዚያ ወር 2009 ዓ.ም በቀድሞው የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝና በኡጋንዳው ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ካጉታ ሙሴቬኒ አማካኝነት መቀመጡ ይታወሳል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 27/2011
በአንተነህ ቸሬ