የፀሀይ አሳታሚዎች ኩባንያ መሥራችና ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ኤልያስ ወንድሙ በወርሃ መጋቢት 2013 ዓ.ም የመጀመሪያ ቀናት አካባቢ ለአንባቢያን ያቀረቡት አንድ በተለይም አሁን ላይ በአገሪቱ እየታየ ካለው ሁኔታ አኳያ ጠቃሚ የሆነ መጣጥፍ አቅርበው ነበር፡፡ ፀሀፊው የታሪክ ሀቲቶችን፣ ንባባችንና አረዳዳችን የበላይነት ይዞ ከሚገኘውና ምዕራብ-ተኮር ከሆነው የቅኝ ገዥዎች ትረካና ወጥመድ መላቀቅ፣ እንዲሁም የመልክዕ ምድራዊ ፖለቲካ ግንዛቤና የኢትዮጵያዊያን በዓለም ላይ ባለንቦታ ላይ በመመርኮዝ መቃኘትና መተካት እንዳለበት ይሞግታሉ፡፡
የዓለም ታሪክ ትርክት በወሳኝ መልኩ የተፈጠረውና የተቃኘው አውሮፓውያን ዓለምን በሚመለከቱበት ዕይታ ነው፡፡ ይህ አውሮፓ-ተኮር የሆነው የዓለም የክስተቶች ትርክት በባህሪው ቅኝ ገዥነት፣ በዓላማው የነጮች የበላይነት በሚከተላቸው ዘዴዎችም ተንኳሽነትና ወራሪነት የተጠናወተው ነው፡፡
የትርክቱ አቀራረፅም ተስፋፊነትን መሰረት ያደረገ ነው፡፡ ይሁነኝ ብሎ የያዘውም አጀንዳ በአብዛኛው የአፍሪካዊያን የበታችነት ስሜትን ለመፍጠርና ለማንበር ካለው ቅዥት ይመነጫል፡፡ ዓለም አቀፍ የትምህርት፣ የሃይማኖት እና የመገናኛ ብዙሃን ተቋማትም የተፈጠሩት ይኽን አውሮፓ – ተኮር ትርክት ለማስፋፋት እንዲያገለግሉ ተብሎ ነው፡፡ ቅኝ አገዛዝ እንደ ሥርዓት ካበቃለት ከ50 እና 60 ዓመታት በኋላም ቢሆን አብዛኛው ሰው (ወይም ብዙሃኑ) ታሪክን የሚመለከተው በዚህ እጅጉን ጠባብና አውሮፓ- ተኮር በሆነው መነፅር ነው፡፡
ምሁራንና የምርምር ስራዎቻቸው እነዚህን ያረጁና ፍፁም ዘረኛ የሆኑ አስተሳሰቦችን ፀሀፊዎች ትርክቶች እንደ መልካም ነገር በአክብሮት በመጠቀምና በመጥቀስ ጥቁሮችንና ነባር ህዝቦችን የማንቋሸሹ ሂደትና ተግባር እንዲቀጥል እያደረጉ ነው፡፡ ዘመነኛ የመገናኛ ብዙሃን (ማህበራዊ ሜዲያውን ጨምሮ)፣ ሲኒማዎች እንዲሁም አዳዲስ የሰው ሰራሽ የማሰብ ችሎታ ቴክኖሎጂዎች (ማለትም አርቲፊሺያል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂ የሚባሉት) እነዚህን የህትመት ውጤቶች መፍጠር ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ የተከማቹትን አድሎአዊና ዘረኛ የመረጃ ጥርቅሞች መሠረት አድርገው ይዞታቸውን (ወይም ኮንቴንታቸውን) በመስራቱ ቀጥለውበታል፡፡
እውን ግን አውሮፓ የዓለም ዋነኛና ወሳኝ ክስተቶች ማዕከል ነበረችን? ሁለቱ ታላላቅ የዓለም ጦርነቶች የምዕራቡ ዓለም ትርክት ሊያሳምነን እንደሚሞክረው በተቃራኒው ፈፅሞ በአውሮፓ እንዳልተጀመሩ ቢነገራችሁ ምላሻችሁ ምን ይሆን?
በእርግጥ ለ 500 ዓመታት ያህል ሲጠናከር የቆየን የአንድ ዘር በተቀረው ዓለም ላይ የበላይ እንደሆነ የሚሰበከውን ዘረኛ ትርክት በእንድ ጽሁፍ መለወጥ እንደማይቻል አውቃለሁ፡፡ ይልቁንም ከአንባቢዎችና አድማጮች የምጠብቀው በአንድ ጀምበር የአስተሳሰብ ቅኝታቸውን መቀየር ሳይሆን፣ ሁላችንም በጋራ ያገኘናቸውን አሊያም ለማወቅ የቻልናቸውን የታሪክ እውቀቶች ምንጮችን ምክንያታዊ በሆነ እሳቤ እንድትጠይቁና እንድትመረምሩ፣ ወቅታዊ ጉዳዮችን በጥንቃቄ እንድትመለከቱ እንዲሁም የመገናኛ ብዙሃኑን (ማህበራዊ ሜዲያውን ጨምሮ) በጣም ጥንቃቄ በተሞላበትና በተጠየቃዊ ስልት መጠቀማችሁን ነው፡፡
በአራት ዓመታት ውስጥ ማለትም እ.ኤ.አ ከ 1914-1918 ዓ.ም. የተካሄደውና የ 16 ሚሊዮን ሰዎችን ህይወት የቀጠፈው አንደኛው የዓለም ጦነት በሳራዬቮ (በወቅቱ የሰርቢያ አሁን ደግሞ የቦሲኒያ ሄርዞጎቪኒያ ዋና ከተማ) ውስጥ የኦስትሮ -ሀንጋሪው ልዑል ፍራንዝ ፈርዲናንድ እ.ኤ.አ ሰኔ 28 ቀን 1914 ዓ.ም ግድያ ከተፈፀመበት በኋካ ስለመሆኑ ከታች ከአንደኛ ደረኛ ት/ቤት አንስቶ ስንማር አለያም ሲተረክልን ኖረናል፡፡ ይኽ ጦርነት የተካሄደው በአንደኛው ወገን ማዕከላዊ ኃይሎች (ማለትም ጀርመንን፣ ኦስትሮ-ሀንጋሪያን፣ ኦቶማን ኢምፓየርን/ቱርክን እና ቡልጋሪያን) የሚያካትተው ስብስብ፣ በሌላኛው ወገን ደግሞ ፈረንሣይን፣ ታላቋ ብሪታንያን፣ የሩሲያ ኤምፓየርን እና ጃፓንን ጨምሮ ሌሎችንም በሚይዘው ቀደም ብሎም የሶስትዮሽ ጥምረት በመባል ይታወቅ በነበረው የአገራት ስብስብ መካከል ነበር፡፡
እዚህ ላይ ከሁሉ አስቀድሞ ሊጠየቅ የሚገባው አንድ መሠረታዊ ጥያቄ አለ፤ ይኸውም እነዚህ ፖለቲካዊ ጥምረቶች ወይም ህብረቶች በመጀመሪያ መቼ፣ የት እና ለምንስ ተፈጠሩ? የሚለው ነው፡፡
ለዚህ ጥያቄ መልሱን በአውሮፓ በጦርነቱ ከተሳተፉት 21 አገራት ውስጥ ከየትኛቸውም ወይም ደግሞ ልዑሉ ከተገደለበት ሥፍራ ማግኘት አይቻልም፡፡ ይልቁንስ ጅማሮውን ማግኘት የሚቻለው በሌላ አህጉር ውስጥ በጣም በርቀት ከምትገኝ አንዲት አገር ከአስር ዓመታት አስቀድሞ ከተከሰተ እውነታ ውስጥ ነው፡፡
አዎ፣ ሁሉም የሚጀምረው ከ 125 ዓመታት በፊት ንጉሰ ነገስት ዳግማዊ አፄ ምንሊክ አድዋ ላይ የቅኝ ግዛት ኃይል የነበረችውን ኢጣሊያን እ.ኤ.አ መጋቢት 1 ቀን 1996 ዓ.ም ድል ካደረጉበት በኋላ ታላቅ የባቡር መስመር ዝርጋት ፕሮጀክት ከተፀነሰበት ጊዜ አንስቶ ነው፡፡ ከአድዋ ጦርነት ሁለት ዓምታት አስቀድሞ ማለትም ኢ.ኤ.አ መጋቢት 9 ቀን 1994 ዓ.ም ለአማካሪያቸው እና ለስውሳዊ መሀንዲስና አማካሪያቸው አልፍሬድ ኢልግ እንዲሁም ለፈረንሳዊ መሀንዲስ ሌኦ ቼፍነ ከጅቡቲ እስከ ኢትዮጵያ መዲና አዲስ አበባ የሚዘረጋ የባቡር መስመር እንዲዘረጉ የሚያዘውን ድንጋጌ ንጉሰ ነገስቱ ዳግማዊ አጼ ምንሊክ አውጀው ነበር። የባቡር መስመሩ የታቀደው የባህር በር አልባ የነበረችውን ኢትዮጵያን ለግንኝነት ክፍት ለማድረግና በቀይ ባህር ላይ የሚኖራትን የንግድ እንቅስቃሴም ለማጎልበት ነበር፡፡
ይኽ ግን የጅቡቲን ወደብ በምትቆጣጠረው ፈረንሳይ እና አብዛኛውቹን የሰሜን ምስራቅ አፍሪካ አገራትን ማለትም ግብጽን፣ ሱዳንን፣ ኬንያን፣ ኡጋንዳን እና ሱማሊላንድን በቅኝ ግዛትነት በምትቆጣጠረው በብሪታኒያ መካከል አስቀድሞ በመካከላቸው ለ 10 ዓመታት ፀንቶ በቆየው ውል ምክንያት ግጭትም ፈጥሮ ነበር፡፡ ግጭቱን ደግሞ ከፍ ባለ ሁኔታ የአባባሰው እ.ኤ.አ አቆጣጠር 1902 ዓ.ም በተፈፀመው የቦነኽ – ቼፍነ ስምምነት አማካኝነት አልፍሬድ ኢልግ እና ቸፍነ የባቡር መስመር የመዘርጋቱን ሥራ ለፈረንሳይ መንግስት መስጠታቸው ነበር፡፡ የተካረረው ግጭት መፍትሔ ሊደረስበት የቻለውም በአንግሎ–ፈረንሳይ የወዳጅነት ስምምነት እ.ኤ.አ ሚያዚያ 8 ቀን 1904 ዓ.ም ነበር፡፡
በአፍሪካም ውስጥ ሆነ ከአፍሪካ ውጪ ባሉ ቀኝ ግዛቶቻቸው ላይ የነበረውን ውጥረት ጭምር ለመፍታት አገራቱ የተጠቀሙበት ይኽ የወዳጅነት ስምምነት የብርታኒያን መንግስት በባቡሩ መስመር ዝርጋታ ውል ላይ እንዲገባ ከማድረጉ ባሻገር ዳግማዊ አፄ ምንሊክ አስቀድመው ካሰቡት በላይ አገራቱ በወደፊቱ የባቡር መሥመሩ ዕጣ ፋንታ ላይ የሰፋ ተፅዕኖና ቁጥጥር ለማድረግ የሚያስችል ነበር፡፡
በሁለቱ አገራት መካከል የነበረው የወዳጅነት ስምምነት ምስራቅ አፍሪካ ላይ ያሏቸውን ፍላጎቶችና ጥቅሞች በተለይም የጀርመንን ተፅዕኖ ለመቋቋምና ለማሸነፍ እርስ በርስ ለመደጋገፍ የሚያስችላቸው ነበር። መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ ፈረንሣይ በግሏ የወዳጅነት ስምምነቱን በመጠቀም ኢትዮጵያን ገቢያዎች ለብቻዋ ለመቆጣጠር በምስጢር አቅዳ ነበር፡፡ ይኽንን የፈረንሣይ ምስጢራዊ እቅድ ብሪታኒያ በወቅቱ ለመቃወም የቻለችውም ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ካላት ድጋፍ ሳይሆን እሷ ራሷ ካልሆነች በስተቀር ማናቸውንም አይነት የአውሮፓ ሞኖፖሊ ወይም በብቸኝነት የመቆጣጠር ተግባር በፅኑ ተፃርራ የምትቆም በመሆኑ ነበር፡፡
በተመሳሳይ ወቅት፣ ከአውሮፓ ከአራት ሺህ ስምንት መቶ ኪሎ ሜትር በምትርቀው ኢትዮጵያ ውስጥ የተለኮሰው ጠብ እዛው አውሮፓ ተባብሶ በመቀጠል ላይ ነበር። ልዑሏ የተገደለባት ኦስትሮ–ሀንጋሪ በተገደለበት አገር ማለትም ሰርቢያ ላይ ጦርነት አወጀች፡፡ ሩሲያም አጋሯ ከሆነችው ከሰርቢያ ጋር እንደወገነች ስታስታወቅ ፣ ጀርመን በበኩሏ ከኦስትሮ–ሀንጋሪ ጎን በመቆም ሩስያ ላይ ጦርነት አወጀች፡፡
ቀደም ሲል እ.ኤ.አ መጋቢት 7 ቀን 1905 ዓ.ም ጀርመን አንድ የልዑካን ቡድን ወደ ኢትዮጵያ ልካ ነበር፡፡ የልዑካኑን ቡድኑም ከንጉሰ ነገስት ዳግማዊ አፄ ምንሊክ መንግስት ጋር በይፋ የንግድ ስምምነት ውል ተዋውሎ ነበር፡፡ ይኽ ስምምነት በወቅቱ በከፍተኛ ደረጃ እያደገ ከመጣው የጀርመን ወታደራዊ ጡንቻ፣ እንዲሁም ኢትዮጵያ ላይ እንደ አዲስ ከተፈጠረው የአውሮፓዊይኑ መቃቃርና ውጥረት ጋር ተዳምሮ ፈረንሣይና ብሪታንያ ኢትዮጵያ በላይ የነበራቸውን ፍላጎትና እቅድ አደጋ ላይ ጣለው፡፡ ይኽ ደግሞ በተራው የኢትዮጵያን ሉአላዊነት እና የባቡር መስመር ሥራ በተመለከተ ፈረንሣይ፣ ኢጣልያ እና ብሪታንያ የሶስትዮሽ ስምምነት የሚባለውን እ.ኤ.አ ታህሣሥ 13 ቀን 1906 ዓ.ም እንዲፈራረሙ አደረጋቸው፡፡
ይኼ የሶስትዮሽ ስምምነት ከላይ ሲታይ በሦስቱ አገራት መካከል የነበረውን የንግድ ነክ ጉዳዮች ልዩነቶች የፈታ ቢመስልም በመሠረቱ ከዳግማዊ አፄ ምንሊክ ሞት በኋላ በተለይ ኢትዮጵያ ላይ ሊከተሉት ያሰቡትን የመጠባበቂያ እቅድ የቀረፁበት ነበር፡፡ የንጉስ ነገስቱ ስምምነትና ፈቃድ ፈፅሞ በሌለበት ሁኔታ በኢትዮጵያ መንግስትና በአውሮፓውያን መካከል ከፍተኛ ግጭት ሊፈጥር በሚችል መልኩ በስምምነታችው ላይ ሦስቱ አገራት በኢትዮጵያ ግዛት ላይ የሚኖራቸውን የተፅዕኖ ክልል ለእያንዳንዳቸው ተከፋፍለው ነበር፡፡
እንግዲህ በዚህ የሦስትዮሽ ስምምነት ነበር አገራቱ ከአንደኛው ዓለም ጦርነት አስር ዓመታት አስቀድመው ከጀርመን በተፃራሪ ለመቆምና ለመተባበር የሚያስችላቸውን መንገድ የጠረጉት፡፡ ዳግማዊ አፄ ምንሊክ እ.ኤ.አ ግንቦት 18 ቀን 1901 ዓ.ም የልጅ ልጃቸው የሆኑትን ልጅ እያሱን የዙፋናቸው ወራሽ ስለመሆናቸው በይፋ አውጀው ነበር፡፡ ከዚህ ተከትለው በመጡት ዓመታትና ንጉሰ ነገስቱም በፅኑ ህመም አልጋ ላይ በዋሉባቸው ጊዜያት ልጅ እያሱ ከእቴጌ ጣይቱ ስር በመሆን በእንደራሴነት አገልግለዋል፡፡
በዚህ ጊዜ ጀርመኖች ለቤተ መንግስቱ የነበራቸውን ቅርበት ይበልጥ ከማሳደጋቸውም ባሻገር ለንጉስ ነገስቱ ተንከባካቢ ሀኪም፣ ለልጅ እያሱ አስተማሪ እና ለፍትህ ሚንስትሩም የቅርብ አማካሪ እስከመሆን ደርሰው ነበር፡፡ አንደኛው የዓለም ጦርነት በተጀመረበት እ.ኤ.አ 1914 ዓ.ም ሐምሌ ወር ደግማዊ አፄ ምንሊክ እና እቴጌ ጣይቱ ከጀርመን ጋር የጠበቀ ግንኙነት ማድረግ የሚያስችላቸውን የትብብር ስምምነት ውል ከጀርመን መንግስት ተወካይ ጋር በይፋ ለመፈራረም ችለው ነበር፡፡ አፄ ምንልክ ሲሞቱም ከጀርመን ጋር የነበረውን ጠንካራ ግንኙነት ወራሽ ወደሆኑት ልጅ እያሱም ሊተላለፍ ችሏል፡፡
ልጅ እያሱ ብዝሃ–ብሔር እና ብዝሃ–ሃይማኖት በእኩልነት የሚስተናገዱባት ዘመናዊ ኢትዮጵያን የመፍጠር፣ እንዲሁም ኤርትራንና ሱማሊያን ከኢጣሊያ፣ ሱማሌላንድን ከብሪታንያ፣ ጅቡቲን ከፈረንሣይ ቅኝ ግዛትነት ለማላቀቅ ከፍ ያለ ምኞት ነበራቸው፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ ግን ራሣቸውን ያገኙት በራሳቸው አጋሮች ማለትም ጀርመንና በኦቶማን ቱርክ በአንድ ወገን፣ በሌላኛው ደግሞ ኢትዮጵያ በሃይማኖቶች እና በዘር ግጭቶች የተከፋፈለችና እጅጉን የተዳከመች አገር እንድትሆንላቸው ይመኙና ይተጉ በነበሩት የብሪታነያና የፈረንሳይ የቅኝ ገዥ ኃይሎች መካከል ተወጥረው ነበር፡፡
የተጠቀሱት ሁሉም አገራት የልጅ እያሱን አጋርነት የፈለጉት በቀይ ባር ላይ የራሳቸውን ወታደራዊና ኢኮኖሚያዊ ፍላጎቶትና ጥቅሞች ለማስከበር ነበር፡፡ ጀርመንንና ኦቶማን ቱርክ የመሳሰሉት በወቅቱም ማዕከላዊ ኃይሎች ተብለው የሚጠሩት በምስራቅ አፍሪካ ላይ ጠንካራ ይዞታ እንዲኖራቸው የፈለጉት የስዊዝ ካናልን ለመቆጣጠር እና ብሪታኒያን ከቀሩት የአፍሪካ ቀኝ ግዛቶቿ ለመነጠል ያስችለናል ብለው ስላሰቡ ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪ፣ ራሷ ጀርመንም ብትሆን እንደ አንድ አውሮፓዊ ኃይል በቅኝ ገዢነት የአፍሪካን ሀብት የመቦጥቦጥ ጽኑ ፍላጎት ነበራት፡፡
ለዚህም ደግሞ እ.ኤ.አ ከ1904 ዓ.ም ጀምሮ በምርምርና እውቀትን ፍለጋ ስም ምሁራን ተብዬ አሳሾችንም አፍሪካ ውስጥ አሰማርታለች፡፡ እንደ እ.ኤ.አ አቆጣጠር በ1915 ዓ.ም ወደ አፍሪካ ቀንድ ያሰማራችው ቡድን ግን ልጅ ኢያሱን የማዕከላዊ ኃይሎች አጋር ለማድረግ የስለላ ተልኮ የተሰጠው ነበር፡፡ የኦቶማን ቱርክ አላማም ቢሆን በተመሳሳይ የልጅ ኢያሱን የምስራቅ አፍሪካ አገራትን አንድ የማድረግ እቅድ በመደገፍ ብሪታንያን እና ፈረንሳይን ከአካባቢው ለማባረር ያቀደ ነበር፡፡
ጀርመንና ኦቶማን ቱርክ በየራሳቸውም ሆነ በልጅ እያሱ አማካኝነት በአፍሪካ ቀንድ አገራት ውስጥ የሚገኙ ጎሳዎች በገዢዎቻቸው በብርታኒያ እና በፈረንሳይ ላይ አመጽ እንዲያካሂዱ የማነሳሳት ሙከራዎችን ሲያደርጉ ነበር፡፡ ልጅ እያሱ የጀርመኖችና የኦቶማን ቱርኮችን ድጋፍ ቢያገኙም ተቃዋሚ ሆነው የተሰለፉባቸው ታላቋ ብሪታኒያ፣ ፈረንሣይ እና ኢጣሊያ ውስጥ ውስጡን ከፍተኛ ሴራ ሲሸርቡባቸው ነበር፡፡ በተለይ ብሪታኒያና እና ፈረንሣይ የልጅ ኢያሱ አካሄድ በምስራቅ አፍሪካ ላይ ያላቸውን ይዞታ አደጋ ላይ እንደሚጥልባቸው በማመን ከፍተኛ ስጋት አድሮባቸው ነበር፡፡
ልጅ እያሱ ስልጣናቸው ከተቆናጣጡበት ጊዜ አንስቶ ከኢትዮጵያ ድንበር ጋር የሚያዋስኑ ልድ ልዩ ጎሳዎችን የሚያጠንክሩና የሚደግፉ ተከታታይ ዘመቻዎችን ያደርጉ ነበር፡፡ ለዚህ ለልጅ እያሱ ተግባር በቀል እንዲሆን በማሰብ ብርታኒያና ፈረንሳይ ኢትጵያን ከማናቸውም አውሮፓውያን አጋሮቿ ጋር የማቆራረጥ ሙከራዎችን ያደርጉ ነበር፡፡ እነዚህ ሁለቱ አጋሮች እ.ኤ.አ በ1915 ዓ.ም ጀርመን ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ለመገናኘት ያደረገችውን ሁለት ሙከራዎች አጨናግፈዋል፡፡ በአገር ውስጥም፣ የልጅ እያሱን ስምና ክብር ለማጠልሸትና ለማዋረድ የሚያደርጉትን መጠነ ሰፊ ዘመቻ፣ እንዲሁም የፈረንሣይ ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑትና የወደፊቱን የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት ተፈሪ መኮንንን ለመደገፍ የሚያደርጉትን ጥረት አጧጡፈው ቀጥለው ነበር፡፡
እ.ኤ.አ መስከረም 27 ቀን 1916 (ወይም እንደ እኛ አቆጠጠር መስከረም 17 ቀን 1909 ዓ.ም መሆኑ ነው) ልጅ እያሱ ከስልጣን ተወገዱ። ይህም ብሪታኒያ እና ፈረንሣይ ገና ተደላድሎ በሁለት እግሩ ለመቆም ያልቻለውን የአፍሪካ ቀንድ ቀኝ ገዢነት አጠናክረው ለመቀጠል ምቹ ሁኔታን ፈጠረላቸው፡፡
ምንም እንኳን በታሪክ መፅሐፍቶቻችን ተጽፈው ባናነባቸውም፣ ይህንን ጉዳይ መነሻ አድርገው በተሰሩ ሲኒማዎች፣ ባናያቸውም፣ ወሳኝ የሆኑት አንደኛው የዓለም ጦርነት አጋርነት ወይም ጥምረቶች የተጀመሩት አፍሪካ ውስጥ መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል፡፡ ሌላው አውሮፓውያኑ ሊነግሩን ወይም በታሪክ ጽሁፎቻቸው ሊያስነብቡን የማይፈልጉት ሃቅ ደግሞ በዚሁ የአንደኛው የዓለም ጦርነት ላይ በተዋጊነትና በጉልበት ሥራዎች ተሳትፈው ከነበሩት እና ከማዕከላዊ ኃይሉ ጋር ከተሰለፉ ከሁለት ሚሊዮን የሚበልጡ አፍሪካውያን ሁለት መቶ ሃምሳ ሺህ ያህሉ በየግንባሩ መስዋዕት መሆናቸውን ነው፡፡ ከህብረቱ ኃይሎች ማለትም ከብሪታንያ፣ ፈረንሣይ፣ እና ኢጣሊያ ጋር አብረው የተሰለፉ አፍሪካውያን ቁጥርም ወደ ግማሽ ሚሊዮን ይደርሳል፡፡
አሁን ባለንበት ዘመን፣ በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአፍሪካ ቀንድም ሆነ በአጠቃላይ በምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ላይ ዋነኛቹ ተዋናዮች እንደቀደመው ዘመን ፈረንሣይ፣ ኢጣሊያ፣ ብርታነኒያ እና ጀርመን ብቻ አይደሉም፡፡ ቻይና፣ የአውሮፖ ሕብረት፣ አሜሪካ፣ ታላቋ ብሪታኒያ፣ ሩሲያ፣ ህንድ፣ ቱርክ፣ ኢራን፣ የባህረ ሰላጤው አገራት እንዲሁም ሌሎች፣ በቀጠናው የተጽእኖ ክልላቸውንና መጠናቸውን ለማስፋፋት በጣሙን እየጣሩ ነው፡፡ በእርግጥም የወቅታዊ ጉዳዮችና የታሪክ ንባባችን እና አረዳዳችን ትክክል ከሆነ በአፍሪካ ቀንድ እየተጀመረ ያለው ነገር ሌላው አፍሪካን ቅርጫ የማድረግ የዓለም ጦርነት ነው፡፡
እ.ኤ.አ አቆጣጠር እስካለፈው 2020 መጨረሻ አካባቢ በዶናልድ ትራምፕ በቻይናው ዢ ዢን ፒንግ፣ በቭላድሚር ፑቲንና በቱርክ ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ኤርዶጋን መካከል የነበረው ጥላቻና ፍቅር (ወይም ወዳጅነት) ይፈራረቅበት የነበረው ግንኙነት የዓለም አቀፍ አጋርነቶችንና አሰላለፍን በእጅጉ ቀይሮታል፡፡ ይህ ደግሞ ልክ እ.ኤ.አ በ 20ኛው ክፍለ ዘመን የመጀመሪያዎቹ ሁለት አስርት ዓመታትና በ 1940ዎቹ እንደታየው ሁሉ የአፍሪካ ቀንድ አካባቢን ሆነ ዓለምን በጠቅላላው ወደ ሌላ ዙር እጅግ አስከፊ ወደሆኑ ግጭቶች የማድረስ አቅም አለው፡፡
በታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ በኢትዮጵያ፣ በግብፅና በሱዳን መካከል በነበረው የድርድር ሂደት ላይ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ያካሂዱት የነበረው ለከት የለሽና የማያቋርጥ ጣልቃ ገብነት ወደ አደገኛ ሀኔታ እያመራ ሳለ የሰውየው በምርጫ መሸነፍ ቢያንስ አራት የሰላም ዓመታትን ይዞልን ይመጣል የሚል እምነት በብዙዎቻችን ዘንድ አሳድሮ ነበር፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ ግን አዲሱ የጆ ባይደን አስተዳደርም ወደተመሳሳይ አሳዛኝ ሁኔታ እያመራን ነው፡፡ ነገሮችን በሚያባብስ መልኩ የጆ ባይደን አስተዳደር ከግብፅና ከሱዳን ጋር ወግኗል፡፡ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ በከፍተኛ ደረጃ ጎጂ ሊሆን የሚችል ጣልቃ ገብነትን በድብቅ ሳይሆን በግልፅ እያካሄደ ይገኛል፡፡ ሩሲያና ቱርክ በበኩላቸው ከኢትዮጵያ ጋር ወታደራዊ እና የደህንነት ስምምነቶችን ተፈራርመዋል፡፡ ቻይናም የአዲስ አበባ–ጅቡቲን የባቡር መስመር ጨምሮ የቤልት እና ሮድ ፕሮጀክቷን ደህንነት የሚያስጠብቅ ስምምነቶችን ከኢትዮጵያ ጋር ተፈራርማለች፡፡ የአፍሪካው ቀንድ ከአንድ ምዕተ አመት በኋላም አዳዲስ ተዋናዮችን ይዞ አንደኛው የዓለም ጦርነትን በሚያስታውስ መልኩ የግጭቶች መባባሻ እየሆነ ነው፡፡
በርካታ ተመራማሪዎች እንደሚሞግቱትም፣ ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በዓለም ላይ የጋራ ደህንነት እና ፀጥታን ለማስጠበቅ ተቋቁሞ የነበረው የመንግስታቱ ማህበር (League of Nations)፣ ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ዳግም ለመውረር ታካሂደው የነበረውን ዝግጅትና ወረራዎችንም ለማስቆም ያለመቻሉ አሳዛኝ የታሪክ ክስተት እንዲሁም ታላቋ ብሪታኒያና ፈረንሣይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ይህንን ወረራ መደገፋቸው ለሁለተኛ ዓለም ጦርነት መነሳት መንገዱን እንደጠረገ ልብ ሊባል ይገባዋል፡፡
“ኢትዮጵያ ለሦስተኛው ዓለም ጦርነት የሚቀሰቀስባት ሀገር ትሆን?” የሚለውን ጥያቄ መመለስ የሚችለው ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ቀድሞ በነበሩት ዘመናትም ሆነ አሁን ላይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካና የሚያስከትላቸውን ድራማዎች በተመለከተ የበላይነቱን የያዘው የቀኝ ገዢዎች ትርክት ዓይናችንን ጋርዶት ቆይቷል፡፡ ስለዓለምና በዓለም ውስጥም የእኛ የኢትዮጵያዊያን እና አገራችን ኢትዮጵያ ያላትን ሥፍራ በተመለከተ ያለንን ግንዛቤ እና አረዳድ ማስፋት ካልቻልን የራሳችን የጋራ ዝንጋኤ ተጠቂዎች ከመሆን አናመልጥም፡፡ አእምሮአችንን ነፃ ማውጣትና ታሪክን ከተለያየ አቅጣጫና ማዕዘን ማንበብና መረዳት ደግሞ የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን ግዴታችን ነው።
ፀሀፊ- ኤልያስ ወንድሙ
ትርጉም- አዶናይ ሠይፉ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 10 ቀን 2014 ዓ ም