ኢትዮጵያውያን አገራቸው የገጠማትን ፈተና ተከትሎ ከየትኛውም ጊዜ በላይ በመተባበር ላይ ይገኛሉ። በተለይ ኢትዮጵያውያኑና ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ ለዓለም አቀፍ ማህበረሰቡ የተዳፈነውን እውነት ለመግለፅ ድምፃቸውን በማሰማት እንዲሁም ለተጎጂ ማህበረሰብ ጥሪታቸውን በማካፈል የእናት አገራቸውን ውለታ እየከፈሉ የገኛሉ።
ከሰሞኑ ደግሞ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ከወዲሁ ወደ አገራቸው ለመግባት ዝግጅታቸውን ማጠናቀቃቸውን በተለያየ መንገድ ማወቅ ተችሏል። መንግሥትም ከፍተኛ ዝግጅት በማድረግ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ዲያስፖራዎችንና ሌሎች ወዳጅ ግለሰቦችን እንደሚቀበል ይፋ አድርጓል። ይሄ ደግሞ የተዳከመውን ኢኮኖሚ ከማነቃቃቱም ባሻገር የቱሪዝም ዘርፉን ለመደገፍ አይነተኛ ሚና እንደሚኖረው ታምኖበታል። የሁለንተናዊ ትግሉ አንድ አካል የሆነው ይህ ኢትዮጵያውያንን በታኀሳስ 29 ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ የተደረገ ጥሪን አስመልክቶ የአዲስ አበባ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ መልዕክታቸውን እንደሚከተለው ያስቀመጡ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊ ሆነዋል።
የአዲስ አበባ ከንቲባዋ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ “አዲስ አበባ በፍቅርና በናፍቆት ትጠብቃችኋለች!” የሚል ጠንካራ ቤተሰባዊ መልዕክት በማስተላለፍ፤ በሩቅና በቅርብ ኃይሎች የተጋረጠብንን የህልውና አደጋ በአንድነት በመመከትና በማሸነፍ፤ በድል አድራጊነት፤ በኢትዮጵያ አደባባይ እንደምንቆም ተማምነው ከያሉበት ድምፃቸውን ከፍ አድርገው የኢትዮጵያን እውነት በመላው ዓለም እያሰሙ ያሉ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ደራሽ ልጆች ናችሁ››።
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ዶክተር ዐቢይ አሕመድ መጪው የገና በዓልን በአገራችሁ ኢትዮጵያ ከያላችሁበት ተሰባስባችሁ በአንድነት እንድታከብሩ ባቀረቡት ጥሪ መሰረት የሁሉም ዞሮ መግቢያ ከተማቸው “አዲስ አበባ” እንደ ስሟ አበባ መስላ፤ የሰላም አየር እየተነፈሰች፤ በደስታና በናፍቆት ልጆቼ እንኳን ደህና መጣችሁ ብላ እንደምትቀበላቸውና ቅድመ ዝግጅቶቿንም ያጠናቀቀች መሆኑዋን አሳውቀዋል።
በተመሳሳይ “ዳያስፖራው ወደ ሀገር ቤት›› በሚል ወደ ሀገሩ ለመትመም የሚያደርገውን ዝግጅት መንግሥት በተለያየ መልኩ እገዛ ያደርጋል ያሉት ደግሞ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ ናቸው። በዚህ መሰረት ዳያስፖራው ወደ ሀገሩ ለመትመም የሚያደርገውን ዝግጅት መንግሥትም በተለያየ መልኩ ለማገዝ ቅድመ ዝግጅቶችን እያደረገ መሆኑን አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያን እውነት ለዓለም ለማሰማት ትልቅ አስተዋጽኦ ሲያደርግ የቆየውና በተሳሳተ መረጃ ላይ ተመስርተው የውጭ አገራት ዜጎቻቸውን ከኢትዮጵያ ውጡ እያሉ በሚወተውቱበት በዚህ ጊዜ ዳያስፖራው በአካል አገሩ ላይ ለመክተም ቀጠሮ እንደያዘም ተናግረዋል። “ወደ አገር ቤት “ በሚል ዳያስፖራው ወደ አገሩ ለመትመም የሚያደርገውን ዝግጅት መንግሥትም በተለያየ መልኩ ለማገዝ ከወዲሁ ቅድመ ዝግጅቶችን እያደረገ ነው። አንዱ በጦርነቱ የተጎዱ ወገኖቹን ሊያግዝ የሚችልበትን መንገድ ማመቻቸት መሆኑን ነው ሚኒስትር ዴኤታዋ ያስታወቁት።
የዝግጅት ክፍላችንም በታኀሳስ ወር መጨረሻ ተወዳጁን የገና በዓል አስመልክቶ ቆይታቸውን በአገራቸው ለማድረግ የሚመጡ ዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን የቱሪዝም መዳረሻዎችን በቀላሉ መጎብኘት እንዲችሉ የሚከተሉትን ጥቆማዎች ለማቅረብ ወድዷል። በዛሬው እትማችን ላይ ወደ እናት አገራቸው የሚመጡት ኢትዮጵያውያን “በአዲስ አበባ ውስጥ የሚገኙ እምቅ የቱሪዝም መዳረሻዎች የትኞቹ ናቸው” የሚለውን እንጠቁማችኋለን። በቀጣይ ደግሞ አገራችሁን በሚገባ ለማወቅና ለመደገፍ ያመቻችሁ ዘንድ በአዲስ አበባ ዙሪያ በቅርብ እርቀት የሚገኙ የመስህብ ስፍራዎችን እናቀርባለን። መረጃውን የቱሪዝም መዳረሻ ልማትና ብቃት ማረጋገጥና የቱሪዝም ማርኬቲንግና ፕሮሞሽን ዳይሬክተር አቶ አምደማርያም ማሞ አድርሰውናል።
አዲስ አበባና የመስህብ ስፍራዎች
ኢትዮጵያ የአስደናቂ መስህብ ስፍራዎች ባለቤት ናት። እነዚህ በተመልካች ዓይን በቀላሉ የሚገቡ መስህቦች ውስጥ ደግሞ ጥቂት የማይባሉት በአዲስ አበባ ይገኛሉ። እነዚህ መስህቦች ታሪካዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ባህላዊ፣ ተፈጥሯዊና መሰል መዳረሻዎች ሲሆኑ ጎብኚዎች በቀላሉ ሊማረኩባቸው የሚችሉና ስለ እናት ኢትዮጵያ አገራቸው በተገቢው እንዲያውቁ የሚረዱ ናቸው። ከዚህ እንደሚከተለው ጥቂቱን እናንሳላችሁና ወደ አገራችሁ ስትገቡ እንድትመለከቷቸው ይሁን።
የዳግማዊ ሚኒሊክ ሌሎች የመታሰቢያ ሐውልቶች
ሐውልቱ የሚያመለክተው በ1889 ዓ.ም በተደረገው የኢትዮ-ጣሊያን ጦርነት አፄ ምኒልክን ያደረጉትን ፀረ-ኮሎኒያሊዝም ትግል እንዲሁም አፍሪካውያኖች በአውሮፓውያን ቅኝ ገዢዎች ላይ ለተቀዳጁት ድል ምስክር ነው። ይህ ሐውልት ለዳግማዊ አፄ ምኒልክ መታሰቢያ እንዲሆን ንግስት ዘውዲቱ አሰርተው በ1922 ያቆሙት ነው። ንድፍ ያዘጋጀው ጀርመናዊው አርክቴክት ሀርቴል ስፔንግለር ነው።
ሌላው በመሀል አዲስ አበባ የሚገኘው ሐውልት ድላችን ሐውልት ነው። የኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ከአምስት ዓመታት ተጋድሎ በኋላ የፋሺስት ጣሊያን ባንዲራ አውርዶ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ የተሰቀለው ሚያዝያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም ነበር። ሚያዝያ 27 ሁለት ተያያዥ ጉልህ ታሪካዊ ክስተቶች የተስተናገዱበት ዕለት ነው። 1ኛው የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር አዲስ አበባ የገባው ሚያዝያ 27 ቀን 1928 ዓ.ም ነው። 2ኛ ሚያዝያ 27 1933 ዓ.ም ደግሞ ከአምስት ዓመታት የአርበኞች ተጋድሎ በኋላ ኢትዮጵያ ፋሺስት ጣሊያንን ያሸነፈችበት የድል ቀን ነው። ይህን የድል ብስራት ለማስታወስ የድላችን ሐውልት በአራት ኪሎ እንዲቆም ተደርጓል።
ሶስተኛው ሐውልት የአቡነ ጴጥሮስ ሐውልት ነው። በ1928 ዓ.ም ሰማዕት ለሆኑት አቡነ ጴጥሮስ፣ ከድል በኋላ በአዲስ አበባ የቆመው የመጀመሪያው የመታሰቢያ ሐውልት ነበር። የአቡነ ጴጥሮስ አለባበስ ‹‹የአርመን ጳጳሳት አለባበስ ይመስላል›› በሚል ሐውልቱ እንዲነሳ ተደርጎ፣ በመናገሻ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ሙዚየም እንዲቀመጥ ሲደረግ፣ በምትኩ አሁን በአደባባዩ የሚታየው ሐውልት እንዲተከል ተደርጓል። ከላይ ያነሳናቸው እነዚህ ሐውልቶች የአዲስ አበባ ድምቀቶችና የታሪክ ማስታወሻዎች ሲሆኑ በሁሉም ኢትዮጵያውያን ሊጎበኙና ሊታወቁ የሚገባቸው ናቸው።
ቤተ-መንግሥቶች
በአዲስ አበባ ያሉት ቤተመንግሥቶች በበርካታ መስህቦች የተሞላና በቱሪስቶች ለመጎብኘት በቀዳሚነት ተመራጭ መዳረሻዎች ናቸው። በከተማችን አምስት ቤተመንግሥቶች ሲኖሩ እነሱም፡-
የእንጦጦ ቤተመንግሥት- ይህ ቤተመንግሥት በከተማችን አዲስ አበባ የመጀመሪያውና በቀዳማዊ አፄ ሚኒሊክ ሁለተኛ የተገነባ ሲሆን በቅርስነት የተመዘገበ በታሪካዊዋ ማርያም ቤተክርስቲያን ቅጥር ግቢ ውስጥ የሚገኝ ነው። ብሔራዊ ቤተ-መንግሥት በውጭ ጉዳይ፣ ፊንፊኔ ሆቴል እና በሸራተን አዲስ ሆቴል ዙሪያ የሚገኘው ይህ ቤተ- መንገሥት በዕድሜ ከቀሩት የሚያንስ ነገር ግን በርካታ ቅርሶችንና ታሪካዊ ክንዋኔዎችን አቅፎ የያዘ ነው። ግንባታው በ1940ዎቹ መጀመሪያ ላይ የተጠናቀቀ ሲሆን ንጉሱ ከስልጣን እስከወረዱበት ድረስ እንደ ቤተ-መንግሥት ሆኖ አገልግሏል።
ገነተ ልዑል ቤተ-መንግሥት ከጣሊያን ሁለተኛ ወረራ ሁለት ዓመት በፊት በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በ1926 ዓ.ም የተገነባ ሲሆን ንጉሱ ቤተ-መንግሥቱን ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሆኖ እንዲያገለግል የሰጡ ቢሆንም ከ1928-1933 ድረስ የጣሊያን ዋና ቢሮ ሆኖ እንዲያገለግል አድርገዋል። አሁን ኤትኖግራፊ ሙዝየም ሆኖ ያገለግላል።
ታላቁ ቤተመንግሥት ይህ ቤተመንግሥት የተገነባው በአፄ ምኒልክ ሲሆን እተጌ ጣይቱ ከእንጦጦ ወደ ታች በመውረድ በተደጋጋሚ ፍል ውሃ ይጠቀሙ ስለነበር በቋሚነት ቤተመንግሥት እንዲሰራ ተደርጓል። አሁን አንድነት ፓርክም ቤተ- መንግሥትም ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።
ሼህ ሆጀሌ ቤተ-መንግሥት በዳግማዊ አፄ ምኒልክ ዘመን ከታወቁ ታላላቅ ሰዎች አንዱ የሆኑት የቤኒሻንጉሉ ንጉስ ሸህ ሆጀሌ ሲሆኑ በጉለሌ ሸጎሌ ተብሎ በሚጠራው ቦታ ላይ ይገኛል። ለበርካታ ዓመታት ከ45 በላይ አባወራዎች ተከፋፍሎ በቀበሌ በመሰጠቱ በጣም የተጎዳ ቅርስ ነው።
በከተማችን የሚገኙ ሙዝየሞች
በከተማችን 18 ሙዝየሞች ይገኛሉ። የከተማችንና የአገራችን ህዝብ ታሪክ የሚዘክሩ ናቸው። ሙዝየሞቹም የሚተደደሩት በመንግሥት፣ በሃይማኖት ተቋማት እና በግለሰብ ነው። እነዚህም፡-
እንጦጦ ሙዝየም፡- በእንጦጦ ተራራ አናት በማርያም ቤተክርስቲያን ውስጥ የሚገኝ ሙዝየም ሲሆን በውስጡም የአደዋ ዘመቻ የተነገረበት ነጋሪት፣ የምኒልክ አልጋ፣ የንግስና ዘውድ እና የመሳሰሉትን ይዟል።
ኤትኖግራፊ ሙዝየም፡- የሚገኘው አሁን የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ኢንስቲትዩት የቀድሞ ገነተ ልዑል ቤተ-መንግሥት ሲሆን እንደሙዝይም የተቋቋመው 1955ዓ.ም ነው። በውስጡም የአገሪቷን ባህል፤ ኪነ-ጥበብ፣ ቋንቋ፣ ታሪክ ፣ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መኝታ እና የመሳሰሉትን ቅርሶች አከማችቶ አገልግሎት እየሰጠ የሚገኝ ተቋም ነው።
ብሔራዊ ሙዝየም
በ1936ዓ.ም በጥቂት አርኪዎሎጂ ግኝትና የብሔር ብሔረሰቦች አልባሳትና መገልገያ ቁሶች የተጀመረው የማስጎብኘት ተግባር በአሁኑ ወቅት በአራት ቋሚ ኤግዚቢሽን ክፍል ተደራጅቷል። እነሱም፡- ባለንቶሎጂ ቅድመ ታሪክ ክፍል፣ አርኪዎሎጂና የታሪክ ክፍል (1ሚሊኒየም -16ክ/ዘ)፣ ኤትኖርራፊ ክፍል እና ዘመናዊ አርት/ኪነ-ጥበብ ክፍል ተብሎ ተከፍሏል። ሌላው ለዛሬ የመረጥንላችሁ ዞሎጂካል የተፈጥሮ ሙዝየም ሲሆን የሚገኘው በአራት ኪሎ በተፈጥሮ ሳይንስ ዩኒቨርሲቲ ሙዝየም ውስጥ ነው። ከ1100 በላይ ዝርያ ከ200 በላይ በውሀ ውስጥ ሚኖሩ ፍጥረታት የሚገኙበት በአገራችን ብቸኛው ሙዝየም ነው። እነዚህንና ሌሎችም በርካታ በአዲስ አበባ ውስጥ የሚገኙ ሙዚየሞች የአገርን ጥሪ ተቀብላችሁ ወደ አዲስ አበባ ስትመጡ ብትመለከቷቸው። በብዙ ታተርፋላችሁ የሚል እምነት አለን።
በከተማችን የሚገኙ ፓርኮች
በአዲስ አበባ ውስጥ እጅግ በርካታ ታሪካዊ፣ ተፈጥሯዊ እንዲሁም የተለያዩ ቅርሶችና የመስህብ ስፍራዎች አሉ። ከነዚህ መካከል ደግሞ ፓርኮች ይገኙበታል። በከተማችን አዲስ አበባ ወደ 22 የሚጠጉ ፓርኮች የሚገኙ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ ዋና ዋናዎቹ አፍሪካ ፓርክ፡- ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እስከ ሒልተን ሆቴል ታች ድረሰ በአስፋልቶቹ መካከል የሚገኝ ሲሆን በአፍሪካ አንድነት መስራች አባቶች በሆኑት መሪዎች የተተከለ ዛፍ ያሸበረቀ ፓርክ ነው፤ ሌላው አንድነት ፓርክ ሲሆን በታላቁ ቤተመንግሥት በቅርብ ጊዜ የተከፈተ ለቱሪስቶች ሰላምና ደህንነት የሚሰማቸው ፓርክ ነው።
በውስጡ የምኒልክ የግብር አዳራሽ፣ የንግስና ክፍል፣ እንቁላል ቤት፣ የንጉሱና የንግስቲቱ መኖሪያ ቤት እና የአፄ ኃይለ ሥላሴ ቢሮና ፍርድ የሚሰጡበትን ታሪካዊ ቤቶች ይዞ ይገኛል። በተጨማሪም የተለያዩ እንስሳዎች፣ የመጀመሪያዋን መኪና እና የመሳሰሉት የሚገኝበት ፓርክ ነው። ለዛሬ በመጨረሻው እረድፍ ልንጠቁማችሁ የወደድነው የሸገር ፓርክ ሲሆን በቅርብ ጊዜ የተከፈተ ፓርክ ነው። በወንዞች ተፋሰስ ልማት መሰረት ያደረገና ጥሩ አንፊ ትያትርና የመሳሰሉትን ለማከናወኛ የሚያገለግል ፓርክ ነው።
የዝግጅት ክፍላችን ለዛሬ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው ለመምጣት ማቀዳቸውንና መንግሥትም በልዩ ሁኔታ አቀባበል ለማድረግ መዘጋጀቱን ተከትሎ በአዲስ አበባ ውስጥ በእንግዶቹ ቢጎበኙ ያልናቸው የመስህብ ስፍራዎች ጥቆማ አቅርበንላችኋል። አገራችን በተለያዩ ችግሮች ተተብትባ በምትገኝበት በዚህ አስቸጋሪ ወቅት እናንተ ልጆቿ ከጎኗ ለመሆን ወደ ትውልድ መንደራችሁ ስለምትመጡ በዝግጅት ክፍላችን ስም ለማመስገን እንወድዳለን።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 10/2014