ኮሎኔል ሮዳሞ ኪአ ይባላሉ። አሁንም ሀገር በችግር ውስጥ ስትሆን ሀብት ንብረታቸውን፣ ልጆቻቸውንና ቤተሰባቸውን ጭምር ትተው ከዘመቱትና ትግል ላይ ካሉት ጀግኖች መካከል አንዱ ናቸው። ምክንያቱም ቤተሰባቸውንም ሆነ ሌላውን ማህበረሰብ መታደግ የሚችሉት ጦርነቱን በግንባር በመገኘት መፋለም ሲችሉ እንደሆነ ያምናሉ። ስለዚህም ከሞቀ ቤታቸው ቁርና ሀሩሩን መርጠው ጉዟቸውን ወደ ጦር አውድማው አድርገዋል። እስከዛሬም የሀገራቸውን ክብር ለማስመለስ እየተዋደቁ ይገኛሉ። በእርግጥ ይህ ልምዳቸው ዛሬ የተፈጠረና የመጣ ሳይሆን ትናንትም የነበረ ነው።
በሕወሓት ጊዜ በኢትዮጵያዊነት አለመደራደር ምን አይነት ዋጋ እንደሚያስከፍል ቀምሰውት አይተውታልና እርሱን ዝም ብሎ መቀመጥ ሀገርን ማዋረድና፣ ነጻነትን አሳልፎ መስጠት ነው ብለው ያስባሉ። ስለዚህም ለመዝመታቸው መነሻው የሕወሓትን ማንነት በቅርብ በመረዳታቸውና ለሀገራቸው እንዲሁም ለራሳቸው ነጻነትን ለመስጠት እንደሆነ ያነሳሉ። እናም ሕወሓት ማነው፤ ዘመቻው ምን ይመስላል፤ የኢትዮጵያውያን ድል ዘላለማዊ እንዲሆን ምን ይደረግና መሰል ጉዳዮችን በማንሳት ከእርሳቸው ተሞክሮና የሕይወት ልምድ ጋር በማዋሃድ ለዛሬ ‹‹የሕይወት ገጽታ›› አምድ እንግዳ አድርገናቸዋል። ከአወጉን ሃሳብ ላይ እናንተም ትምህርትን ትቃርሙ ዘንድ ጋበዝናችሁ።
የቤተሰብ ምክር የሠራው ልጅ
ትውልዳቸው ዛሬ ተከራክረውላት ክልል እንድትሆን ባደረጓት ሲዳማ ውስጥ ሲሆን፤ ዳሌ ወረዳ ሰሜን ቀጌ ቀበሌ ልዩ ቦታዋ ቆጮኔ በምትባል ስፍራ ነው። ይህ ቦታና የአካባቢው ማህበረሰብ እርሳቸውን በሚገባ ስላሳደጋቸው በባህሪያቸው ዝምተኛ አይነት ልጅ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። በእርግጥ ዝምታቸው ምክንያታዊነትን የያዘ እንደነበር ያስታውሳሉ። እንደውም መተውን መሰረት ያደረገ ነው ይሉታል። ከሦስት ጊዜ በላይም እድል አይሰጥበትም። ምክንያቱም ፈሪ መባል የእርሳቸው መለያ እንዲሆን አይፈልጉም። ስለዚህም መናገር እስካለባቸው ድረስ ማንንም ሳይፈሩና ሳይሸማቀቁ ያደርጉታል። ከተናገሩ በኋላ ግን ቂም መያዝ አይፈልጉም። እርቅ ማውረድ ልምዳቸውም ባህሪያቸውም ነው።
የአድማጭነት ባህሪ ያላቸው ሲሆኑ፤ ሁሉንም ነገር በቁምነገር ማየት ምርጫቸው ነው። በተለይም የአባቶችና እናቶች ምክርን ለሕይወታቸው ማድረግ ላይ የተካኑ ናቸው። ይህ መሆኑ ደግሞ ሰዎችን ከስህተታቸው ለመመለስ እንዳገዛቸው ይናገራሉ። ከቤተሰብ ውስጥ ተለውጠው የወጡ ልጅ እርሳቸው የመሆናቸው ምስጢርም ይህ እንደነበር ያብራራሉ።
ኮሎኔል ሮዳሞ የልጅነት ሕልማቸው በህክምናው ዘርፍ መሰማራት ሲሆን፤ ብዙዎችን ከህመማቸው ማከምን ይፈልጋሉ። ነገር ግን የ12ኛ ክፍል ውጤታቸው ለዚያ አላበቃቸውም። በዚህም ሌላ መርጠው እንዲጓዙ ሆነዋል። የአርት አፍቃሪ የሆኑትም በዚህ ምክንያት እንደነበር ያነሳሉ። ውትድርና ጥበብ እንደሆነም ስለተረዱ ሙያውን ተቀላቅለውታልም።
መጀመሪያ ራስን ለመፈለግ ያሰቡትን መሆን ብቻ አይጠበቅም። ከዚያ ይልቅ የገቡበትን አድምቶ መሥራት የበለጠውን ያቀዳጃል የሚሉት እንግዳችን፤ የገቡበትን መውደድ እንደሚያስፈልግ ያምናሉና በገቡበት ጠንክረው ጉዟቸውን ወደፊት አድርገዋል። የሚፈልጉትን የሆኑትም ከዚህ አኳያ እንደሆነና ራስን በመፈለግ ጉዞ ውስጥ ስጦታን ማግኘት እንደሚቻልም በራሳቸው ማየታቸውን አጫውተውናል።
ውትድርናና ትምህርቱ
ትምህርት ለሰው ልጅ መሰረት እንደሆነ እነርሱ ባይማሩም ቤተሰቦቻቸው ጠንቅቀው ያውቃሉ። በዚህም ሳይሰስቱ ካላቸው እየሰጡ እንዲማሩ አግዘዋቸዋል። ይከታተሏቸውም ነበር። ይህ ደግሞ ጠንካራ ተማሪ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል። ከመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ጀምሮ እስከ 12ኛ ክፍል ሲማሩም የደረጃ ተማሪ የነበሩት ለዚህ ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ አንድ ነገር ያነሳሉ። የቤተሰብ ክትትልና ድጋፍ ካለበት በትምህርት ጎበዝ አለመሆን አይቻልም። ይህ ሲሆን ደግሞ ግድ የተማረ ቤተሰብ መሆን ብቻ አይጠበቅም። ያልተማረውም ብዙ የሚፈይደው ነገር አለ። ድጋፉ ብቻ ያበረታል ይላሉ።
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በቀጌ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተከታተሉት ባለታሪካችን፤ እስከ ስድስተኛ ክፍል በቦታው ተምረዋል። ከዚያ ትምህርታቸውን ለመከታተል ወደ ይርጋዓለም ከተማ ተጓዙ። በከተማዋ በሚገኘው የካቲት 25 መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትም ሰባትና ስምንተኛ ክፍልን ተከታተሉ። ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ አሁንም በይርጋዓለም ከተማ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሩ። ውጤታቸውን ይዘውም ውትድርና ስቧቸዋልና ከ12ኛ ክፍል በኋላ የተለያዩ ወታደራዊ ስልጠናዎችን በብላቴ ማሰልጠኛ በመውሰድ ነው ጅማሮዋቸውን ያደረጉት።
ከምረቃ በኋላ ደግሞ ትግል ሲያደርጉ የተወሰኑ ዓመታትን አሳለፉ። ይሁን እንጂ መማር ልምዳቸው ነውና ዝም ብለው አልተቀመጡም። በ1986 እና 1988 ዓ.ም ከፍተኛ የወታደራዊ አመራርነት ኮርስን ወስደዋል። ከዓመት ቆይታ በኋላ ማለትም በ1989 ዓ.ም ደግሞ እንዲሁ በሥራቸው የተደሰተው መንግሥት ዳግመኛ ከፍተኛ ወታደራዊ የአመራርነት ስልጠና ኮርስ እንዲወስዱ በመከላከያ ዩኒቨርሲቲ አስገብቷቸዋል። እስከ ካርታ ሥራ ድረስ ጥልቅ እውቀት ጨብጠውም ነው የተመረቁት።
ለትምህርት ያላቸው ጉጉት ሁልጊዜ የሚያይልባቸው ኮሎኔል ሮዳሞ፤ በማኔጅመንት ዲፕሎማቸውን ከአልፋ ርቀት ኮሌጅ ይዘዋል። አሁንም ዲግሪያቸውን በዚሁ መስክ ከዚሁ ኮሌጅ አግኝተዋል። በ2002 ዓ.ም ደግሞ በክፍለ ጦሩ ከአበረከቱት አንጻር ታይቶ ወደ መከላከያ ኮማንድ ኤንድ ስታፍ ኮሌጅ እንዲገቡ ተደርገው በወታደራዊ ሳይንስ ኤንድ ሊደርሽፕ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ይዘዋል። ሁለተኛ ዲግሪያቸውንም ቢሆን በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን ሊድ ስታር ኮሌጅ ሰርተዋል።
አንድ ሰው መለወጥ ከፈለገ ሁልጊዜ መማር አለበት የሚል አቋም ያላቸው እንግዳችን፤ ከዚህ በኋላም መማር ይፈልጉ ነበር። ሆኖም ጊዜውና ሕወሓት አልፈቀዱላቸውም። ስለዚህ በራሳቸው ትግል ውስጥ እንዲያሳልፉ ሆነዋል። በእርግጥ እርሳቸው አልተማርኩም አይሉም። ምክንያቱም ወታደር ቤት ሁልጊዜ መማር አለና። ክፍል ገብቶ በመምህራን ከሚሰጥ ትምህርት በላይ በየቀኑ የሚሰጡ ትምህርት ሁልጊዜ እውቀትን፣ መሪዎች ልምድን አስቀሳሚዎች ናቸው ይላሉ። አሁንም ቢሆን ሀገር ይረጋጋ እንጂ እንደሚማሩ ያምናሉ።
ሀገርና ወታደራዊ ሥራ
መጀመሪያ ከሥራ ጋር የተገናኙት በውትድርናው ዓለም ላይ ሲሆን፤ በአካባቢያቸው ተመድበው የፈጸሙት ነው። በአለታ ወንዶና ጩኮ ወረዳ በጸጥታ መዋቅር ማደራጀት ላይ ሠርተዋል። ከዚያ የሲዳማ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ውስጥ ሲያገለግሉ ቆይተዋል። ከሁለት ዓመት የሥራ ላይ ቆይታ በኋላ ደግሞ የወረዳ አስተባባሪ መሆናቸውን ትተው በዚያ ውስጥ ሲዳማ ሬጅመንት የሚባል ድርጅት በመንግሥት ደረጃ እንዲቋቋም ስለተፈለገ በአንድ ሻለቃ የሚመራ ስድስት መቶ አባላትን የያዘውን ሬጅመንት እንዲመሩ ሆኑ። ለዓመት ያህልም በዞኑ በንሳ ወረዳ አገለገሉ።
ቀጣዩ የሥራ ቦታቸው ነገሌ ቦረና ሲሆን፤ ሰራዊቱን በመያዝና በመምራት ሲሠሩ ቆይተዋል። የደቡብ ክልል ጀነራሎችና የእነርሱን ጨምሮ ሰባት የሚደርሱ ሬጅመንቶች በጋራ ሆነው ወደ ሀገር መከላከያ ሰራዊትነት ሲቀላቀሉ እርሳቸውም አንዱ ነበሩ። በተለይም እርሳቸው የሲዳማ ሬጅመንትን ይዘው ስለገቡ በወቅቱ የነበረውን የሲዳማ አመራርነት ኮታ እንዲይዙ እድል ሰጥቷቸዋል። ከፍተኛውን የብርጌድነት የአመራር ቦታም ነበር የያዙት።
በእግረኛ ኃይሉ በኩል ተመድበው በብርጌድ አመራርነት እንዲሠሩ የተደረጉት ኮሎኔል ሮዳሞ፤ በ1987ዓ.ም ወደ ምስራቅ ዕዝ ተመድበው የብርጌድ ምክትል አዛዥ ሆነው ሠርተዋልም። ከ1988 ዓ.ም ስልጠና በኋላ ደግሞ ከኦነግ ጋር ተያይዞ የነበሩ ኦፕሬሽኖች ብዙ ችግር ያለባቸው ስለነበሩ እነርሱን ለመፍታትም ከዘመቱና ከሠሩት መካከል ናቸው። በተለይም ከምዕራብ ሀረርጌ እስከ ባሌ ያለውን እንቅስቃሴ በተጠና ሁኔታ በመምራት ኃላፊነታቸውን ተወጥተዋል። ይህ ሁሉ የሆነው የሲዳማን ሕዝብ በመወከልና የአመራርነት ድርሻውን በመያዝ እንደነበርም ይናገራሉ።
በ1990 ዓ.ም ከሻቢያ ጋር የተደረገውን ጦርነትም በኃላፊነት የመሩ ናቸው። በተለይ በውጊያ ላይ የነበሩበት የቡሬ ግንባር በብዙ መንገድ ድል እንዲያደርግ የተቻላቸውን ሁሉ አበርክተዋል። በጾረና ግንባርም ቢሆን እንዲሁ ብዙ ድል አስገኝተዋል። ጦርነቱ ከአበቃ በኋላ ደግሞ ወደ አዲስ አበባ እንዲመለሱ ተደርገው መከላከያ ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች ላይ በከፍተኛ አመራርነት እንዲሠሩ ሆነዋል። ይህ የሆነውም ለስድስት ዓመታት ያህል እንደነበር ያስታውሳሉ።
አዲስ አበባና አካባቢው በሚል ማዕከላዊ ክፍለ ጦር ወይም 17ኛ ክፍለ ጦር ተብሎ ሲቋቋም እርሳቸው ከአደራጁት አመራሮች አንዱ ነበሩ። ከዚያም አልፈው የክፍለ ጦሩ አመራርም ሆነው ከጸጥታ እስከ አመራርነት ድረስ ያሉ ተግባራትን ሲከውኑ ቆይተዋል።
‹‹ኢህአዴግ ሲገባ ይዞት የመጣው አላማ ብሔራዊ ጭቆና ነው። ፊቱ ለምለም ውስጡ ግን ጭቃና ታጥቦ የማይጠራም ነበር። ምክንያቱም ሕገመንግሥት አቋቁሞ ጭምር አገር የመናድ አላማን አንግቧል። በዚህም አገሬ፣ ሥራ፣ እውቀት የሚልና ከእነርሱ ጋር ቅራኔ ውስጥ የሚገባ ሰው ከመወገድ ውጪ አማራጭ የለውም። ›› የሚሉት እንግዳችን፤ ራስን በማንኛውም ነገር ከፍ ማድረግ ያስመታ እንደነበር ራሳቸውን አብነት በማድረግ ያነሳሉ። እርሳቸው ምንም አይነት ሕመም ሳይኖርባቸው የተሰናበቱትም ለዚህ እንደነበር ይጠቁማሉ።
ይህንን ጉዳይ ሲያስታውሱም ምን ያህል እንደሚያም ከንግግራቸው ተነስተን መናገር እንችላለን። በወቅቱ እንዳሉን ‹‹ሕወሓት በእኔ ላይ ያደረገው ነገር መቼም የማይረሳና በማንም ወገን ላይ መድረስ የሌለበት ጉዳይ ነው። ምክንያቱም ወታደር ለሀገርህ መቆም የለብህም ሲባል ምን ያህል ቅስምን እንደሚሰብር የኖረበትና ያየው ይናገረው። ተግባሩን ሲፈጽሙ እስካሁን ያልገባኝና እንቆቅልሽ የሆነብኝ በ2005 ዓ.ም ግንቦት ላይ ያሰናበቱኝ ነው። በወቅቱ ሲኒዬር ኮለኔል ነኝ። ጥሩ ውጤት ያላቸውና ጀነራል ይሆናሉ ተብለው ከተለዩት ውስጥም አንዱ ነበርኩ። ነገር ግን ማዕረጉን ከመስጠት ይልቅ እኔን ማሰናበቱን ምርጫቸው አደረጉ። ለዚህም የተጠቀሙበት ዶክተሩ በትዕዛዝ የሚሰራ ስለነበር ሙሉ ጤነኛ ሆኜ ሳለ 25 በመቶ ስጠው ተብሎ ታዟልና ታማሚ ነው አለኝ። በቦርድም እንድሰናበት ተደረግሁ›› ይላሉ ሰቀቀን የሞላበትን መሰናበት ሲያነሱ።
ባለታሪካችን እንደሚያብራሩት፤ ሕወሓት ያለምክንያት አንድም ነገር አያደርግም። ብዙ መወንጀያና መሸፈኛ ውሸቶችን አስቀድሞ ያዘጋጃል። ራስን ጭምር እውነት ነው የሚያሰኝ ተግባራትን ይፈጽማል። ከእነዚህ መካከል ደግሞ የሆነባቸው አንዱ እንደነበር ያስታውሳሉ። ይህም ከምረቃ መጥተው ሳለ እረፍት ውጡ የተባሉት ሲሆን፤ ሲመለሱ ግን ሥራ ይሠጠኝ ብለው ቢጠይቁም የሚሰማቸው አላገኙም። እንደውም ‹‹አንተ በቦርድ ትዕዛዝ ወጪ ነህ›› ተባሉ። በወቅቱ የተባሉትን ማመን አቅቷቸው ነበር። ነገሩ አልገባቸውምና መላልሰው የሚመለከተውን አካል ጠየቁ። ማንም አሁንም መልስ አልሰጣቸውም።
ሹመቱ ቢመጣም ለእርሳቸው እድገቱን ላለመስጠት ከምደባ ውጪ አደረጓቸው። የዚህን ጊዜም ነው የነቁት። ስልጣን ክፍፍሉ ለራስ ብሔር ብቻ ስለነበር አልተመለከተኝም አስባላቸው።
በየጊዜው በሚያበረክቷቸውና በሚለወጡባቸው ተግባራት ይቀኑባቸው እንደነበርም ተረዱ። በዚህም ባይቀበሉትም በስንብቱ ምክንያት ወደ ትውልድ አካባቢያቸው ሄዱ። በዚያ ሲደርሱም ብዙ አልቆዩም። ምክንያቱም እርሳቸው ያለሥራ መቀመጥን አለመዱም። ስለዚህም በሕወሓት መንግሥት ከመከላከያ ቢሰናበቱም በወረዳ፣ ዞንና በክልል ደረጃ በተለያዩ ኃላፊነቶች ላይ እንዲሠሩ ሆነዋል።
በሐዋሳ ከተማ አስተዳደር የሰላምና ጸጥታ መምሪያ ኃላፊ ሆነው አገልግለዋል። ብዙ የሰሩባቸው ቦታዎችም ነበሩ። በመጨረሻ ያረፉበትን ስናነሳ የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ኤጀንሲ ሥራ አስኪያጅ በመሆን የመሩበት ሲሆን፤ ዳግም ሀገርን የማዳን ዘመቻውን እስከተቀላቀሉ ድረስ እየሠሩበት ነበር።
የሲዳማ የክልልነት ጥያቄ እንዲመለስ ካስቻሉ መካከልም አንዱ የሆኑት ኮሎኔል ሮዳሞ፤ የአንድ ብሔር የበላይነት በነገሰበት የአስተዳደር ቦታ ላይ ከበታች ሆኖ መናገር ፋይዳ የለውም። አለመናገርም በሀገርና በወከለ ሕዝብ ላይ መቀለድ ነው። ስለዚህም በዚያ ውስጥ ሆነን ስንመራ ይህንን ፈተና እየተጋፈጥን ነው ይላሉ። አመራር ቢሆኑም ከቃል ያለፈ ነጻነት እንዳልነበራቸው ያስረዳሉ። ወደ ትግል የገቡትም የሕዝቡ ጥያቄ እንዲመለስለት እንጂ ሕዝብ ላይ ለመሳለቅ እንዳልሆነም ይናገራሉ።
እነርሱን አስደሰታቸውም አስከፋቸውም ከመናገር ወደ ኋላ ብለው የማያውቁት እንግዳችን፤ በተለያየ ጊዜ ብዙ በደልና ግፍ አድርሶባቸዋል። ሥራቸውን ጭምር እንዲለቁና አማራሪ እንዲሆኑም ጥረው ነበር። ምክንያቱም ዋና አላማው እነርሱን እድሜያቸው ሳይደርስ፤ አቅማቸው ሳይደክም ከአገር ማራቅና ኢትዮጵያዊነትን ከውስጣቸው ማጥፋት ነው። መተካካት በሚል ሽፋን የፈለጋቸውን ይከውናሉ። በዚህ ሽፋን ደግሞ እርሳቸው ብቻ ሳይሆኑ ብዙ ሰዎች ከሥራ ውጪ መሆናቸውን ያስታውሳሉ። ግን እርሳቸው ይህንን አልፈቀዱም። ዳግም ሥራ ጀምረው ሀገራቸውን ሲያገለግሉ ነው የቆዩት። አዲስ አሰራር ሲዘረጋ ደግሞ ዳግም መከላከያውን ተቀላቅለው ለሀገራቸው እንዲዋደቁ ሆነዋል።
ሲጀምር የኢህአዴግ መሪዎች አንዲት ትግራይ እንጂ አንዲት ኢትዮጵያ የሚል መርህን የሚከተሉ አይደሉም። በጀርባቸው ያዘሉትን ተግባራቸውን ሲፈጽሙ ማንም ያልታገላቸውና ያላስቆማቸውም ለዚህ ነው። ዛሬም ያንኑ እየደገሙትና እየሰሩበት ይገኛሉ። ማን በምን መልኩ አጋራቸው እንደሚሆን ልምዱ ስላላቸውም በሴራና በውሸት ፕሮፓጋንዳ ማንም የማያስበውን ተግባራቸውን እየፈጸሙ ናቸው።
ለዚህ ደግሞ ያገዛቸው አርቴፊሻል ኢትዮጵያዊነታቸው ነው። እርሱን ይዘውም እቅዳቸውን እውን ያደርጋሉ። ዝርፊያ፣ ሀገርን ማውደም፣ ትግራይን ማግነን ህልማቸው ነው፤ በመጠኑም አሳክተውታል። ይህንን ሲያደርጉ ደግሞ ሽፋን እንጂ ውስጣዊ ስሜት የላቸውም። በዚህም ኢትዮጵያን በብዙ መንገድ አደህይተዋታል። እነርሱ እስካሉበት ድረስ ኢትዮጵያዊነት በተግባር ሳይሆን በውሸት እንዲኖርና እንዲቆይም ሆኗል። ይህንን ማክሸፍ ያለበት ደግሞ እያንዳንዱ የችግሩ ተጋሪ መሆን አለበትና ገብቼበታለሁም ነው ያሉን።
በሕወሓት ዘመን ቁልፍ ኢኮኖሚስት፣ ባለሀብት፣ ፖለቲከኛና መሰል ሰዎች ከትግራይ ውጪ ማንም ዘንድ ያልነበረውም በሴራቸው ምክንያት ነው። ሁሉ ነገር የሚከፈተውና የሚቆለፈውም በእነርሱ ብቻ እንደሆነ ስላሳመነ ነው። በዚህም ወሳኝ የማንም ብሔር ሳይሆን የትግራይ ልጅና አመራር ሆኖ ቆይቷል። ስለዚህም የሌላው ክልል አመራርና ሕዝብ ምንም ቦታ ካለመኖሩም በላይ ምንም መወሰን አይችልም። በራሱ ላይ ጭምር የሚወስንለት ሕወሓት ብቻ ነበር። በስም ተቀማጭ እንጂ ፈላጭ ቆራጭ አልነበረም። ይህ ደግሞ ሌላውን ብሔር በብዙ መልኩ ሲያቆስለው ዘመናትን እንዲያሳልፍ አድርጎታል።
ዛሬ ድረስ በዚያ ሕመም ውስጥ እንዲቀመጥም ሆኗል። አሁን ግን ያ አይሆንም። ማንም ሳይሆን ወሳኙ ኢትዮጵያዊያን ብቻ ናቸው። ሁሉም ያልተስማማባት ኢትዮጵያ መቼም ቀና እንደማትል በሚታዩ ድሎች እየተመሰከሩ ይገኛሉ። ወታደር ብቻ ሳይሆን ሕዝብ እንደሕዝብ የመታገሉ ምስጢርም ወሳኟ ኢትዮጵያ እንጂ ብሔር አለመሆኑ እየታየ እንደሆነም ይናገራሉ። እርሳቸውም ቢሆኑ በዚህ ስሜት ነው አሁን ላይ በግንባር የአንድ ኮር ምክትል አዛዥ ሆነው እያገለገሉ የሚገኙት።
ዳግመኛ መከላከያን መቀላቀል
መከላከያ ሕይወታቸውና ኑሯቸው እንዲሁም የደስታቸው ምንጭ እንደሆነ ማመናቸው የመጀመሪያው ዳግመኛ የመቀላቀላቸው መንስኤ ነው። ይህንንም ሲያስረዱ መከላከያ ሀገሬ የሚለው ነገር አለው። እናም ከሲዳማ ስለወጡ የሲዳማን ነጻነት ማስከበር የመጀመሪያው የኃይላቸውና የገፊያቸው ምንጭ ሆኖላቸዋል። ከዚያ ተለቅ ወደሚለው እይታቸው ሲገቡ ደግሞ ሀገር የሚለውን ያነሳሉ። ለሀገር አለኝታ የሚሆነውና ከችግሯ የሚያላቅቃት የጀርባ አጥንቷ መከላከያ እንደሆነ እሙን ነው። ስለዚህም ለሀገር ደጀን መሆን ውዴታ ሳይሆን ግዴታቸው እንደሆነ በማመናቸው መከላከያ መሆንን ዳግም ተመኙ፤ ገቡበትም።
ፍትህ በሀገራችን የሚሰፍነው ሰላም በሁሉም አካባቢ ሲኖር በመሆኑ ፍትህና ሰላምን ለማምጣት ደግሞ አንድም ወታደር አለያም ታጋይ ሕዝብ መሆን ያስፈልጋል። ስለዚህም እርሳቸው ወታደርነቱ የበለጠ ብርታት እንደሚሆናቸው ስላወቁ ተቀላቅለውታል። በተለይ እንደ ሲዳማ አመራርነት በርቀት መታገል ብዙ እንደሚያስከፍላቸው ይረዳሉና ቅርብ መሆኑን መርጠዋል። አመራርነት መሪነት፣ አርአያነት መሆኑን ስለሚያውቁ ከመከላከያው ጋር ተሰልፈው ዘመቻውን እየመሩ እንዲቀጥሉም ሆነዋል።
አሁን ሀገር ባለችበት ወቅታዊ ሁኔታ ላይ በአንደኛው ግንባር ላይ ሆነው ወታደራዊ አመራር ከሚሰጡት መካከል ናቸው። ለዚህ ደግሞ መሰረቱ ሕወሓት ከቆየ ሀገራችን መቼም የተሻለች እንደማትሆንና ብልጽግናዋን እንደማታይ ያምናሉ። ስለዚህም እርሱን ማስወገድ ላይ አሻራቸውን ማኖር ስላለባቸው ያደረጉት ነው። የእነርሱ አረመኔነት ሁላችንም የማናስበውና የሰው ልጅ ያደርገዋል ብለን በማንገምተው መልኩ የተደረገና እየሆነ ያለ ነው። ከሕግ በላይ ሆነው የቆዩትን አሁንም መድገም ስለሚፈልጉ ብዙ ነገራቸውን ይሰዋሉ። ተበታትነው ጭምር ሀገርን ለማውደም የሚሯሯጡበት ያለምክንያት እንዳይደለም ያነሳሉ። ስለዚህም እነርሱን መዋጋት አማራጭ ሳይሆን ግዴታ ነው ይላሉ።
እንደ ኮሎኔል ሮዳሞ ገለጻ፤ ሀገር ለሰጠቻቸው ክብርና እውቀት በየደረጃው ያለው የመከላከያ ሰራዊት ትልቁን ድርሻ ይይዛል። ሕወሓት ደግሞ እነርሱን የጭካኔ ምት መቷል። ስለዚህም የመከላከያ ደቀ መዝሙር ሆኖ አልዘምትም ማለት ከሕወሓት ጋር ከመተባበር የማይለይ ነው። በዚያ ላይ በሕይወት እያለሁ ሥራዬን ነጥቀው ላሳመሙኝና ለሀገሬ እንዳላበረክት ላደረጉኝ መክፈል ካልቻልኩ የሀገሬና የወገኔ ልጅ ነኝ ማለት አይቻልም ብለው እንደዘመቱ ይናገራሉ።
‹‹የእኔ የሚለውን ሰራዊት ሲወጉ የተሰማኝ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ሳይሆን እንደ ሰራዊትና አመራርም ጭምር ነው። ስለዚህም መላ ኢትዮጵያ ላይ ያወጁት ጦርነት ተጨምሮበት እነርሱን መታገል እንዳለብኝ አሳምኖኛል። ከውጭ ኃይሎች ጋር ማበር ብቻ ሳይሆን መሸጥ ድረስ የሚደርስ ሥራ እያከናወኑ መቀመጥ ኢትዮጵያዊነትን ከመነጠቅ አይተናነስምና ኢትዮጵያን አሸንፎ ለመግዛት በእኛ ደም ላይ መረማመድ እንዳልበትም በማሰብ ጦርነቱን ተቀላቅያለሁ። ›› ብለውናልም።
ቤተሰብን ለማን በትነው ነው ጉዞውን ወደ ዘመቻ ያደረጉት ላልናቸው ጥያቄም መልሰው ጥያቄ ነበር የሰነዘሩልን። ሀገር ከሌለ ቤተሰብ እንዴት ይኖራል? በማለት። ቀጥለውም እንዳሉት፤ ማንም ቤተሰቡን አይጠላም፤ ማንም ቤተሰቡን አይተውም። ለዚያውም ወታደር። ምክንያቱም ወታደር ለቤተሰብ ብቻ የሚኖር ሳይሆን ለሀገር ጭምር የሚሞት ነው። ለእርሱ ቤተሰቡ ሀገሩ ናት። በዚህም እነርሱን ለማኖር ሀገርን ማቆየት ግድ ነው። ለቤተሰብ ብቻ ሳይሆን ለራሴም ጭምር ካሰብኩ እንዲሁም ወታደራዊ ግዴታዬን ልወጣ ካልኩ ያለምንም ማቅማማት ቅድሚያ ለሀገሬ ማለት ይጠበቅብኛልና አድርጌዋለሁም ይላሉ።
‹‹ሕወሓት ሁሉ ነገር በእኔ ብቻ ይጀመራል ያልቃል ማለቱ የኢትዮጵያን ሕብረብሔራዊነት አጠናክሮታል። እርስ በርሱ እንዲጠባበቅም መንገድ ጠርጎለታል። በብሔር መጋጨቱን እንዲያቆምም አድርጎታል። ከምንም በላይ የእስከዛሬው ኑሮው ምንን ለማግኘት እንደሆነ እንዲረዳና እንዴት ከሌሎች ጋር አብሮ መሻገር እንዳለበት እንዲያውቅ አግዞታል። አሁን እኔን ጨምሮ ብዙዎች ሀገር ወደማዳኑ የዘመቱት በምክንያት የሆነውም ለዚህ ነው›› ብለውናል።
‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ መሪ እንጂ ቀስቃሽ አያስፈልገውም። ምክንያቱም በሀገሩ ጉዳይ ከማንም ጋር ተደራድሮ አያውቅም። በኢትዮጵያዊነት ስሜት ብቻውን በተፈጥሮ የተቀሰቀሰም ነው›› ያሉን ኮሎኔሉ፤ ይህንን ስሜት በሱዳን ዓለም አቀፍ ወታደራዊ ታዛቢነት በሚሰሩበት ጊዜ ጭምር እንዳዩት ያስረዳሉ። በሀገር መከላከያ ሠራዊት በተለያዩ የጦር ክፍሎች ተልዕኳቸውን በብቃት ሲፈጽሙም እንዲሁ።
ኢትዮጵያ በእውነት ላይ የቆመች ሀገር በመሆኗ ሁልጊዜ አሸናፊ ናት። አማኝና በአቋማቸው የጸኑ መሆናቸውንም በሚገባ እያሳዩ ይገኛሉ ያሉን ኮሎኔል ሮዳሞ፤ እነርሱ የደሙትን ያህል እየደማንም ቢሆን ሀገራችንን እናድናታለን ባይ ናቸው።
የሕይወት ፍልስፍና
ሕይወት የምትከብደው እንደፈተናው ቅለትና ክብደት ሳይሆን እንደተሸካሚው ማንነት ነው። ስለዚህም በየደረጃው የሚደርሰው ፈተና እንደሰውዬው አቅምና ብርታት ይወሰናል። ሊከብደውም ሊቀለውም ይችላል። ነገር ግን በፈተና ውስጥ ሁሉም ይማራል፤ በውጣ ውረድ ውስጥ ማለፍን ያያል፤ ለቀጣይ ሕይወት ይዘጋጃል፤ ይጠነክራል፤ የመፍትሄ ሰው ይሆናል የሚለው ዋነኛ እምነታቸው ነው።
ሌላው ፍልስፍናቸው ከትምህርት ጋር ያለው አቋማቸው ነው። መማርን ከገንዘብ ጋር ማያያዝ አይገባም። ከዚያ ይልቅ ለሕይወት ከሚሰጠው ጥቅምና በራስ ላይ ከሚያመጣው ለውጥ አንጻር መቃኘት አለበት። ዶክተርና ሌላ ለመባልም ሊሰራበት አይገባም። ጎንዮሹን አይቶ የተሻለውን ማግኘት ለራስም፣ ለሀገርም መሰረት መጣል ነው የሚል አስተሳሰብ አላቸው።
መልእክት
ልባችን ንፁህ እና ቅን ሲሆን ሀሳባችን መልካም እና ተንኮል የሌለበት ይሆናል። መርዳታችን ለምን እንደሆነ ደንታ አይሰጠንም። ምክንያቱም ስንረዳም የምናገኘው፣ የምንረዳው ነገር ምን ያደርግልን ይሆን ብለን አናስብም። ከዚያ ይልቅ ሁሌም እንዲደረግልን ሳይሆን ለማድረግ ዝግጁነታችንን እናስባለንና። ስለሆነም ይህንን እምነት አድርገን በተለይ ዛሬ ላይ ያለንበትን ሀገራዊ ፈተና ማለፍ አለብን የሚለው የመጀመሪያው መልዕክታቸው ነው።
ሌላው ያነሱት ነገር ለኢትዮጵያ ይህ ችግር አዲስ አለመሆኑን ነው። ኢትዮጵያ በፊትም በራሷ አቅም ችግሮቿን ፈትታ ኖራለች፤ ዛሬም ነገም ትፈታለች። ስለዚህም በውጭ ያሉ የሚጠሏትም ሆኑ በውስጥ ያሉት ታሪካቸውን ታሪክ እንደምታደርግባቸው ያምናሉ። ለዚህም ነው አልሞት ባይ ተጋዳይ የሚሆኑት። የተቻላቸውን ሁሉ እያደረጉ ያሉትም ልሞክር በሚል ነው እንጂ እንደማይሳካላቸው ያውቃሉ። ምክንያቱም እነርሱ እርሷ እንዳትነሳ አስበው የሚሰሩና የሚያሴሩ ናቸው። ነገር ግን ችግሮቹ ይቀያየሩና ፈተና ይሁኑባት እንጂ ተሸንፋላቸው እንደማታውቅ በብዙ መንገድ ተረድተውታል። አሁንም በዜጎቿ ብርታትና ብቃት የአሰበችው ላይ መድረሷ አይቀርም። ድሉም ቅርብ ነው ይላሉ።
በመጨረሻ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ጨለማን ሳይሆን ብርሃንን እያዬ ከመከላከያ ጎን ሊሰለፍ ይገባዋል። ልጆቹንም በማዝመት የሀገር አለኝታነቱን ማሳየት አለበት። ከዚህ ትይዩ በአለው ገንዘብና ጉልበት የቀደመውን ልዕልና መመለስ ላይም መረባረብ ያስፈልገዋል። በተለይ አሁን ያለው ድል ተስፋ የሚያስቆርጥ ሳይሆን ተስፋ አለምላሚ በመሆኑ ወደፊት በመራመድ የፈራረሰውን አካባቢ መጠገንና ኢኮኖሚው ላይ ጫና እንዳይፈጠር ለማድረግም ሁሉም የበኩሉን ማበርከት ይጠበቅበታል ብለዋል። //
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ታህሳስ 10/2014