ኢትዮጵያ የመንግስታቱ ማህበር / ሊግ ኦፍ ኔሽን / አባል የሆነችው መስከረም 17 ቀን 1916 ዓም ነው። ባለፈው መስቀል ፣ መስከረም 17 ቀን 2014 ዓም አንድ ክፍለ ዘመን ፣ 100 ዓመት ሊሞላት ሁለት ዓመት ብቻ ይቀራታል። አባል በሆነች 12ኛው ዓመት እኤአ በሰኔ 30 ፣ 1936 ዓም፤ ጥላ ከለላ ይሆነኛል ባለችው ሊግ ኦፍ ኔሽን በአደባባይ ክህደት ተፈፅሞባታል። ለፋሺስት ጣሊያን በሀጢያት ተሸካሚነት ተላልፋ ተሰጣለች።
ንጉሠ ነገሥታት ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ከዚህ ታሪካዊና አሳፋሪ ክህደት በፊት፤ ሊግ ኦፍ ኔሽን ለአባል ሀገር ኢትዮጵያ የሚገባውን ጥበቃ፣ ከለላና እገዛ እንዲያደርግ፤ በመንግሥታቱ ማህበር 16ኛው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ተገኝተው ያደረጉትን ታሪካዊና ትንቢታዊ ንግግር፤ ጋዜጠኛ ፣ አምባሳደርና ደራሲ ዘውዴ ረታ ፣” የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መንግሥት “ በሚለው ድንቅ መፅሐፋቸው እንዲህ ከትበው አቆይተውናል። “…የዓለምን ሰላምና የአገሮችን ነጻነት ለማስከበር ከፍተኛ የቃል ኪዳን አደራ የተጣለበት የመንግሥታት ማህበር፤ የአንድ አባል አገር መሪ የሆነ ንጉሠ ነገሥት ሌላው አባል መንግሥት በጦር ኃይል ተደራጅቶ በሕዝቡ ላይ ስለአደረሰበት አሰቃቂ የሆነ እልቂት፤ በሊግ ኦፍ ኔሽን ሸንጎ ላይ ተገኝቶ አቤቱታውን የሚያቀርበው ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑን የሚስተው ይኖራል ብዬ አላስብም።
ከብዙ ሺህ ዓመታት ጀምሮ ነጻነቱን ጠብቆ የኖረውን የአገሬን የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ በአሁኑ ሰዓት የጣሊያን መንግሥት ቅኝው አድርጎ ለመግዛት በጦር ኃይልና በመርዝ ጋዝ የሚፈጽምበትን ግፍና ጭካኔ፤ ከዚህ ቀደም በሰለጠነው ዓለም ውስጥ ደርሶ ያልታየና ተወዳዳሪ የማይገኝለት መሆኑን የምገልጽላችሁ እጅግ በመረረ የኀዘን ስሜት ነው። የጣሊያን መንግሥት ካለፈው አንድ ዓመት ተኩል ጀምሮ በአገሬ በኢትዮጵያና በሕዝቤ ላይ ሲወስድ የቆየው ሕገ ወጥ እርምጃ፤ ምን ያህል አሳሳቢና ምን ያህል አደገኛ እንደሆነ፤ በየጊዜው ለመንግሥታቱ ማህበር ያመለከትኩባቸው ሰነዶች፤ በጽህፈት ቤቱ ተመዝግበው የሚገኙ መሆናቸውን ማስታወስ እፈልጋለሁ።
ሆኖም በዛሬው እለት የ52 መንግሥታት እንደራሴዎች የኢትዮ ጵያን አቤቱታ ሰምታችሁ ፍርዳችሁን ለመስጠት ስለተሰባሰባችሁ፤ የወልወል ግጭት ከተፈጠረበት ጊዜ አንስቶ እስከዛሬ ድረስ፤ የጣሊያን መንግሥት በአገሬና በሕዝቤ ላይ የፈጸማቸውን ግፍና በደል ዋና ዋናዎቹን ልገልጽላችሁ ከፊታችሁ ቀርቤያለሁ። “ ግርማዊነታቸውን በዚህ ታሪካዊ ንግግራቸው የጣሊያን ፋሽስት በኢትዮጵያ ላይ የፈጸመውን ግፍና ወረራ ከወልወል ግጭት አንስቶ፤ የመንግሥታቱ ማህበር በወራሪው ላይ የጣለው የይምሰል ኢኮኖሚያዊ ማዕቀብ ነዳጅ ፣ ዘይት ፣ ከሰልና ብረታብረትን ያካተተ ስላልነበር ግቡን ሊመታ ባለመቻሉ የጣሊያን ወራሪ ግፍና ጭካኔ እየተባባሰ መምጣቱን በሶስት ዋና ዋና ነጥቦች አትተው ካቀረቡ በኋላ በንግግራቸው ማጠቃለያ ላይ ይህን ትንቢታዊ መልዕክት አስተላልፈዋል፤”… ዛሬ ባለንበት ሰዓት ከሁሉ ይበልጥ የዓለምን ሕዝብ እጅግ ሊያስጨንቀውና ሊያሳስበው የሚችለው፤ የዓለም መንግሥታት ተስማምተው ለሰላም የሚያወጧቸውን ሕጎች፤ በጉልበትና በማን አለብኝነት መንፈስ እየተነሱ የሚደመስሱ መሪዎች መፈጠራቸው ነው።
በዚህም አኳኋን የፋሽስት መንግሥት ዛሬ በኢትዮጵያ ላይ የሚፈጽመውን የግፍ ሥራ ነገ በሌሎች ሀገሮች ላይ ለማድረግ ምን ያግደዋል ? ተብሎ የሚቀርበው ጥያቄ ነው። ለዚህም አስጨናቂ ጥያቄ ዛሬ መልስ ካልተገኘለትና አጥቂዎችን ለመቋቋም ተገቢው እርምጃ ካልተወሰደ፤ አደጋው በድሀ አገሮች ላይ ተወስኖ የሚቀር ሳይሆን፤ ታላላቆቹ መንግሥታት እንደሚደርስባቸው ሊያስቡበት ይገባል። …” ( ይህ የግርማዊነታቸው ትንቢት ከዓመታት በኋላ ተፈፅሞ ከታሪክ ድርሳናት አንብበናል።
የናዚ ጀርመኑ አዶልፍ ሒትለር የአርያም ዘሮች ነን በሚልና አውሮፓን ብሎም ዓለምን ለመቆጣጠር በነበረው እብሪት ጎረቤቶችን በኋላም እነ ፈረንሳይን በመውረሩ የ2ኛው የዓለም ጦርነት ተቀስቅሶ ሚሊዮኖቹ ሞቱ። ቆሰሉ። ስድስት ሚሊዮን አይሁዶችም በግፍ ተጨፈጨፉ። የዓለም ኢኮኖሚም እምሽክ ድቅቅ አለ። የሰው ልጅ ስልጣኔ ወድሞ ለጥቂት ዓመታት ቢሆንም ዓለማችን በድንቁርና ፣ በወረርሽኝና በችጋር ተመታች። የንጉሠ ነገሥቱ ታሪካዊ ንግግር ዛሬ ድረስ በትንቢትነት የሚወሰደው ለዚህ ነው። )
የግርማዊነታቸው የሊግ ኦፍ ኔሽን ንግግር እንዲህ ካቆመበት ቀጥሏል። “…ከሥነ ፍጥረት ሕግና ከሰባዊ መንፈስ ውጭ፤ ያ ሁሉ አሰቃቂ ዕልቂት ቢደርስበትም፤ ሰላማዊና ሀይማኖተኛ የሆነው ያገሬ የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ ለነጻነት የሚያደርገው ተጋድሎ እስከ ዕለተ ሞቱ የጠነከረ ስለሆነ፤ በየጫካው በዱር በገደሉና በየበርሀው እየተዘዋወረ በመዋጋት፤ ጠላቱን ማስጨነቅ አላቋረጠም።
እኔም በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ ጠላት ለመያዝ ሞክሮ ባቃተው በአንድ ልዩ ቦታ፤ አዲስ አበባ ያለውን መንግሥቴን ካዛወርኩ በኋላ ወደ ዤኔቭ የመጣሁት፤ እውነትን ብቻ ተመርኩዤ አቤቱታዬን ለእናንተ ለማመልከትና የመንግሥታት ማህበርን እርዳታ አግኝቼ፤ የነጻነት ትግሌን ወደምቀጥልበት ቦታ ለመሄድ መሆኑን እንድታውቁልኝ እፈልጋለሁ። ስለዚህ በንግግሬ መደምደሚያ ላይ የምጠይቃችሁ፤ ለሕዝቤ ምን ይዤለት እንደምመለስ መልሳችሁን እንድትሰጡኝ ነው። “
ግርማዊነታቸው ከመንግሥታቱ ማህበር ለሕዝባቸው ይዘውት እንዲሄዱ የተወሰነላቸው እንደ አባል ሀገር የምስራች ሳይሆን ይህን ቅስም ሰባሪ መርዶ ይዘው መመለሳቸው በዚሁ መፅሐፍ እንዲህ ተመዝግቦ ይገኛል፤ “… የ16ኛው የመንግሥታቱ ማህበር ጉባኤ ሊቀ መንበር ቫን ዚላንድ በኢትዮጵያ ግዛት አሁን ያለው የፋሽስት ይዞታ በይፋ እንዲወገዝና ለወደፊትም ምንም አይነት እውቅና እንዳይሰጠው የሚጠይቀውን የሀገራችንን የመጀመሪያ ረቂቅ ውሳኔ ለጉባኤው አላቀርብም ብሎ ከለከለ። …” ይህ አልበቃ ብሎ ፣”… የፋሽስት መንግሥት በሊግ ኦፍ ኔሽን ተፈርዶበት የነበረው የኢኮኖሚ ጭቆና / ማዕቀብ እንዲነሳ ተወሰነለት። የጣሊያን ፋሽስት በወረራ የያዘው ይዞታ እውቅና እንዳያገኝ ኢትዮጵያ ያቀረበችው ጥያቄ በጉባኤው ውድቅ ተደረገ።
የመንግሥታቱ ማህበር ሕግ በሚፈቅደው መሰረት ሀገራችን የጠየቀችው ብድር ተከለከለ። …” ይህ ፍርደ ገምድልነት አሀዱ ብሎ የጀመረው በወጉ ለአንድ ሀገር መሪ የሚደረገውን የፕሮቶኮል አቀባበል ለንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለስላሴ በመንፈግ እና ለጉባኤው ንግግር ለማድረግ ከመቀመጫቸው ሲነሱ በስብሰባው አዳራሽ ፎቅ ግራና ቀኝ ባሉት ጋላሪዎች ተሰግስገው የሚጠባበቁት የፋሽስት ደጋፊዎች ከፍ ባለ የብልግና ስድብ ፣ ጩኸትና ፉጨት አዳራሹን በማደባለቅ እንደነበር ፤ ጸሐፊው ያትታሉ።
ታሪክ ራሱን ይደግማል አይደግምም የሚለው ጉንጭ አልፋ ሙግት መልስ ሳያገኝ ዛሬ ድረስ የቀጠለ ቢሆንም፤ ለካርል ማርክስ ግን ታሪክ ራሱን የመድገም ጉዳይ አጠያያቂ አይደለም። ለዚህ ይመስላል ፣ “ ታሪክ ራሱን ሲደግም መጀመሪያ በአሳዛኝ ሁኔታ በማስከተል በአስቂኝ ሁኔታ “ ያለው። ከ80 ዓመት በኋላ በከፊል ታሪክ ራሱን ሊደግም ወደ ኋላ ማጠንጠን የጀመረ ይመስላል። ታሪክ ራሱን የሚደግመው እኤአ 1936 ዓ.ም በአሳዛኝ ሁኔታ ወይም በአስቂኝ ሁኔታ ይሁን አይሁን ወደፊት የምናየው ሆኖ፤ የዛን ጊዜ ሀገራችን ወራሪውንና አረመኔውን የጣሊያን ፋሽስት ከሳ ሸንጎ ፊት “ አቁማው “ ነበር፤ ባለፉት ሁለትና ሶስት ዓመታት በግብጽና በትግራይ ወራሪና አሸባሪ ኃይል ደጋፊዎች በሀሰት ተወንጅላ ለ13 ጊዜ ያህል በመንግሥታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር የተከሳሽ ሳጥን ላይ ቆማለች።
እውነትንና ፍትሕን ይዛ በፍርደ ገምድሎች አደባባይ ቆማለች። ምስጋናና ክብር እህት ወንድም ለሆኑ የቻይና የሩሲያ የሕንድና የአፍሪካ ሕዝቦች ይሁንና የግብጽ የአሸባሪውና የወራሪው የትግራይ ኃይል አዛዮች ኢትዮጵያን የማፍረስና ብቻዋን የማቆም መሰሪ ደባ በተደጋጋሚ ፉርሽ ሆኗል። ይሁንና ዛሬም አልተኙላትም። ከስህተታቸው ከመማር ይልቅ እልህና አፍረት ውስጥ ገብተዋል። ምን አለፋችሁ የቆሰለ አውሬ ሆነዋል። በሰብዓዊ መብት ስም የሚሸቅጡ ዓለምአማቀፍ ተቋማትና ሚዲያዎቻቸው ለዚህ ጥሩ አብነት ናቸው።
የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት አመነስቲ ኢንተርናሽናል ሒውማን ራይትስ ዋች እና ሌሎች ሀገራችንንና መንግሥታችንን፤ ርሀብን እንደ ጦር መሳሪያ በመጠቀም በሰብዓዊ መብት ጥሰት በዘር ማጥፋት በጦር ወንጀል እንዲሁም በሰብዓዊነት ላይ በሚፈጠር ወንጀል ከሰዋል። በእነ CNN BBC ALJAZEERA FRANCE 24 REUTERS AP AFP NEWYORK TIMES WASHINGTON POST THE ECONOMIST እንደ ማርቲን ፕላውት ባሉ ተከፋይ ጸሐፊዎች እና ሎቢስቶች የተቀናጀና የተናበበ ርብርብ ስም ማጠልሸቱን አራግበውታል።
በሁለት ቀናት ብቻ ከ70 በላይ ሀሰተኛና ሆን ተብለው የተዛቡ ዜናዎችን ፈብርከዋል። አዲስ አበባ ተከባለች በሚል ሽብር መንግሥትን በሽብር ለመፍታት ተንቀሳቅሰዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ አመራሩ ሀገር ጥሎ እንዲሸሽ ጫና አድርገዋል። በአሸባሪው ሕወሓት የሚመራ የሽግግር መንግሥት በአሜሪካ እስከማቋቋም ጥረዋል። ከቀዝቃዛው ጦርነት ማለትም ከሶሻሊዝም መክሰም ከሶቪየት ሕብረት መበታተንና ከበርሊን ግንብ መፍረስ ወዲህ እንዲህ በአንድ ሀገር ላይ ተነስተው አያውቁም። በስትራቴጂካል ተገዳዳሪነትና ጠላትነት በምታያቸው ቻይና ሩሲያ ኢራንና ሰሜን ኮሪያ ላይ እንኳ በሶስት ዓመታት ውስጥ 13 ጊዜ ወደ ጸጥታው ምክር ቤት አልመጡም። በ48 ሰዓታት 72 ሀሰተኛ ዘገባ አልፈበረኩም። ኢትዮጵያ ላይ ግን አድርገውታል። ዛሬም አልተኙላትም።
ባለፈው ዓርብ ሀገራችን ለ14ኛ ጊዜ በባይደን አስተዳደር ወትዋችነት በአውሮፓ ሕብረት ከሳሽነትና አስተባባሪነት 52 ሀገራትን ፊርማ በማሰባሰብ ጀኔቭ በሚገኘው የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ ምክር ቤት የተከሳሽ ሳጥን ዳግም ቆማለች። አንድም የአፍሪካ ሀገር ባልደገፈው በዚህ የፈጠራ ክስ እንደ ቀደሙት ጊዜያት ሁሉ የመንግሥታቱ ድርጅት ኢትዮጵያን ለማጥቃት በመሳሪያነት እያገለገለ መሆኑን አረጋግጧል። ገለልተኛነት ላይ የተጠናከረና ተጨባጭ ጥያቄ አስነስቷል። የአሜሪካውያንና የምዕራባውያን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ማስፈጸሚያ ፖለቲካዊ ለበቅ መሆኑን አረጋግጧል።
ከየኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ጋር በመተ ባበር ባደረገው ጥናት በትግራይ የዘር ማጥፋት ወንጀል አለመፈጸሙንና ጦርነቱ የተጀመረው አሸባሪው ሕወሓት በሰሜን ዕዝ ላይ በፈጸመው ጥቃት የተነሳ መሆኑን አረጋግጦ በሁለቱም ወገኖች ግን ከበድ ያሉ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች መፈጸማቸውን አመልክቶ ያስቀመጣቸውን ቢሆኑ ያላቸውን ማሳሰቢያዎች (ሪኮመንዴሽን) መንግሥት ተቀብሎ የሚኒስትሮች ግብረ ኃይል አቋቁሞ ተግባራዊ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ባለበትና ኮሚሽኑ በቅርብ ከትግራይ ወራሪ ኃይል ነጻ በወጡ የአማራና የአፋር ክልሎች ከመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ጋር ምርመራ ለማድረግ እየተነጋገረ ባለበት ሰዓት ሆን ተብሎ ትኩረት ለማስቀየር ሲባል እውነትንና ፍትሕን ያነገበ ሀገርና ሕዝብ ለ14ኛ ጊዜ በፍርደ ገምድሎችና ሴረኞች አደባባይ ቆሟል።
ዓለምአቀፍ ሚዲያውና የሰብዓዊ መብቶች በመና በብና በመመጋገብ ለዚሁ ስብሰባ ግብዓት የሚሆን ዘገባ አውጥተዋል። አመነስቲ ኢንተርናሽናልና ሒውማን ራይትስ ዋች እነሱ ምዕራብ ትግራይ በሚሉት አካባቢ ጥሰት መፈጸሙን የሚገልጽ የፈጠራ ሪፖርት አውጥተዋል። ኒው ዮርክ ታይምስ የለመደውን ሀሰተኛ ዘገባ ሲያወጣ፤ አሌክስ ዲዋል ደግሞ በእስራኤል በሚታተም ጋዜጣ የለመደውን ቅጥፈት ጽፏል።
የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤትም በእለቱ ባሳለፈው ውሳኔ ከዚህ በፊት ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን(ኢሰመጉ)ጋር ያወጣውን ሪፖርት የሚቃረን ውሳኔ አስተላልፏል። ይህን አይን ያወጣ አድሏዊነትና ደባ የኢትዮጵያ መንግሥት፤ ኢሰመኩና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ(ኢሰመጉ)አበክረው እንደሚቃወሙትና እንደማይቀበሉት ለተመድ አስታውቀዋል። እናሸንፋለን ! አንጠራጠርም።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ታህሳስ 10/2014