በመጪው ምርጫ 2012 ዓ.ም ህዝቡ የተሻለ አማራጭ እንዲያገኝ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ውህደት ወይም ጥምረት ማድረግ እንደሚያስፈልጋቸው ምሁራን ይገልጻሉ። ተመሳሳይ ፍላጎትና ፕሮግራም ያላቸው ፓርቲዎች ቢሰባሰቡ የሚያስቡትን ግብ ከማሳካትና የፖለቲካ ስልጣን ከመቆጣጠር አንጻር አቅም እንደሚፈጥሩ፣ ጥምረታቸው ለአገርም ለህዝብም እንደሚጠቅም ያስረዳሉ።
በግጭት አፈታት ሁለተኛ ዲግሪያቸውንየሰሩት የመልታይ ዳይሜንሽናል ዴቨሎፕመንት ዳይሬክተር አቶ ከበደ ቀጄላ፤ ጥምረት የተበታተነን ኃይል ማሰባሰብ፣ የግብ እና የአመለካከት አንድነትን መፍጠር መሆኑን ይጠቅሱና፤ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥምረት መፍጠራቸው አመለካከታቸውን እና አማራጫቸውን ለህብረተሰቡ ለማስተዋወቅና ለማስገንዘብ ቀላል ይሆናል።
ጉልበት፣ ጊዜና ገንዘብ እንደሚቆጥብ ያመለክታሉ። ተፎካካሪ ፓርቲዎቹ ጥምረት በመፍጠራቸው ዕውቀታቸውን፣ ጊዜያቸውን፣ ገንዘባቸውንና አመለካከታቸውን አጣምረው የተሻለ ውጤት የሚያገኙበት እንደሚሆን ይጠቁሙና፤ በመጣመራቸው ጉድለቶቻቸውን እየተሞላሉ በአቅም፤ በገንዘብና በዕውቀት እየተደጋገፉ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሆነው ለመቀጠል ይችላሉ ሲሉም ያስረዳሉ።
በህግና በፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን እንዲሁም በልማት ጥናት /Development Studies/ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን የሰሩት አቶ ዘሪሁን ጋሻውም፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዓላማቸው በዋናነት የፖለቲካ ስልጣን በመያዝ በህብረተሰቡ ውስጥ ያሉ ጥቅሞችና ፍላጎቶች እንዲጠበቁ መስራት፣ የሚታዩ ችግሮች እንዲቀረፉ የፖሊሲ አማራጭ አቅርበው መታገል መሆኑን ይጠቅሳሉ። ፓርቲዎች ፍላጎታቸው ከተቀራረበ ተለያይተው የሚሰሩበት ምክንያት አለ ተብሎ አይታሰብም የሚሉት አቶ ዘሪሁን፤ ተመሳሳይ ፍላጎትና ፕሮግራም ያላቸው ተፎካካሪ ፓርቲዎች ተሰባስበው ቢንቀሳቀሱ የሚያስቡትን ግብ ከማሳካትና የፖለቲካ ስልጣን ከመቆጣጠር አንጻር አቅም ሊፈጥሩ ይችላሉ ባይ ናቸው። የፖለቲካ ፓርቲዎች በጥምረት መንቀሳቀሳቸው ለህዝቡም ጥቅም እንዳለው ይጠቁማሉ።
ብዛት ያላቸው ፓርቲዎች ከተንቀሳቀሱ ህዝቡም ለመለየት እንደሚቸገር ያመለክታሉ። መሰባሰባቸው ግን ፓርቲዎቹን በቀላሉ ለይቶ ለመምረጥ የሚቻልበት ዕድል እንደሚፈጥር ይመክራሉ። አገርንና ህዝብን የሚጠቅም አጀንዳ ካላቸው መሰባሰቡ እንደሚመረጥም ያመለክታሉ። ለውጡ በፈጠረው መልካም አጋጣሚ ከ100 በላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች በመንቀሳቀስ ላይ መሆናቸውን የሚጠቅሱት አቶ ከበደ፤ ተበታትኖ መቀጠሉ ጠንከር ላሉ ፓርቲዎች ዕድል በወርቅ ሳህን እንደማቅረብ ይሆናል ይላሉ።
እንደ ፓርቲ ተበታትኖ መቀጠሉ የሚጠቅማቸው ነገር እንደሌለም ያብራራሉ። ተበታትነው መቀጠላቸው አቅም ይበታተናል፣ ጊዜ ያቃጥላል፣ ለመራጩ ህዝብም ግርታ ይፈጥራል። ለአገርም ለመራጩ ህዝብም ከጠቀሜታው ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ እና ሌሎችም ሰዎች ፓርቲዎች ቢሰባሰቡና ቢጠናከሩ የተሻለ መሆኑን ሲገልጹ መቆየታቸውን በማስታወስ፤ ይህንን ምክር በመንተራስ ፓርቲዎች ለመሰባሰብ እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ጥሩ መሆኑን ይገልጻሉ።
ያልተሰባሰቡ ፓርቲዎችም በፕሮግራም እቀራርባለሁ ከሚሉት ጋር ቢሰባሰቡ፣ ቢዋሃዱና ጥምረት ቢፈጥሩ ከፍተኛ ጥቅም እንዳለው አቶ ዘሪሁን ይናገራሉ። ላለፉት 30 እና 40 ዓመታት በአገር ውስጥ የተሞከረው ብሄርን መሰረት ያደረገው የፖለቲካ ፓርቲዎች አካሄድ ብዙም ውጤት አላስገኘም። ጥምረቱ ወደ ርዕዮተ ዓለማዊ አደረጃጀት ቢሄድ ይመረጣል ሲሉ አቶ ከበደ ይጠቁማሉ። በብሄር የሚደራጁ ፖለቲካ ፓርቲዎች ማንነትን አጉልተው በማውጣት እንደሚደራጁ በመጥቀስም፤ ለማንነታቸው ምክንያታዊነትን ያቀርቡና ለብሄራቸው ማስገኘት የሚፈልጉት ላይ ያመዝናሉ እንጂ አጠቃላይ ህብረተሰብ ላይ አያተኩሩም ሲሉ ይወቅሳሉ። በርዕዮተ ዓለም መሰባሰቡ ግን አገራዊ አመለካከት እንዲኖር ያግዛል፣ ፓርቲዎቹ የሚያማልል ነገር እንዲኖራቸው ያደርጋል ይላሉ።
የሚያስገድድ ጉዳይ ከሌለ ስስ በሆኑ አጀንዳዎች ተመስርቶ መደራጀት አይመከርም፣ ለአገርም ጠቃሚ አይደለም፤ ያሉት አቶ ዘሪሁን፤ ብሄርን መሰረት አድርገው የሚደራጁ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚደራጁት የህብረተሰቡን ችግር ለመፍታት እስከሆነ ድረስ ችግሮቹን መነሻ አድርገው ቢደራጁ እንደሚመረጥ ይጠቁማሉ።
የፌዴራል ሥርዓቱ በተወሰነ መልኩ በብሄር ላይ የተመሰረተ መሆኑ አንዳንድ የፖለቲካ ኃይሎችም በእዛው ላይ ተመስርተው እንዲደራጁ ዕድል መስጠቱን ያስታውሳሉ። በቀጣይነት ሁኔታው እየቀነሰ መምጣት አለበት። አንድ በሚያደርጉ ጉዳዮች ላይ መሰባሰቡ እንደሚመረጥ ይገልጻሉ። በርዕዮተ ዓለም ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ ትግበራ በዓለም አቀፍ ተመራጭና የኢኮኖሚና የፖለቲካ ሁኔታን መነሻ የሚያደርጉ መሆናቸውን በመጠቆምም፤ ይህም የአገሪቱን ህዝብ የፖለቲካ ወይም ኢኮኖሚ ተጨባጭ፤ ወቅታዊ ችግሮች ላይ እንዲመሰረት ያደርጋል ሲሉ ነው አቶ ዘሪሁን የሚጠቅሱት።
በብሄር ላይ የሚመሰረተው ባብዛኛው ‹‹የእኔና የእነሱ›› በሚል አስተሳሰብ ላይ እንደሚያጠነጥንና የእኔ ተብሎ የሚመሰረተው ሌሎችን በሚያቀርብ አንድነት ላይ ሳይሆን በልዩነት ላይ ሆኖ በተወሰነ የህብረተሰብ ክፍል ላይ ያተኮረ ይሆናል ሲሉ ያስረዳሉ።
ሰሞኑን በጥምረትና ግንባር ፈጥረው ለመስራት የተስማሙት ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)፣ የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢህአፓ)፣ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ህብረት(ኢዴህ)፣ የኢትዮጵያ ብሄራዊ አንድነት (ኢብአ)፣ የአፋር ህዝቦች ፍትሀዊ (አህፍ)፣ የአፋር ህዝቦች ነፃነት ፓርቲ እና የኦሮሞ ህዝብ ፍትሃዊ ፓርቲ ናቸው። በአሁኑ ወቅት 24 አገራዊና 42 ክልላዊ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እውቅና ተሰጥቷቸው በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ። ለውጡን ተከትሎም በጥቅሉ 104 የሚደርሱ ተፎካካሪ ፓርቲዎች መኖራቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።
ፓርቲዎቹ ጥምረትና ግንባር ለመፍጠር እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙ በተለያዩ አጋጣሚዎች እየተገለጸ ይገኛል። ተፎካካሪ ፓርቲዎች ወደ ጥምረት ባይመጡ እና እንደተለመደው በተበታተነ አካሄድ ቢቀጥሉ በቀጣይ ዓመት በሚደረገው ምርጫ ህዝቡ የተሻለ አማራጭ ያጣል። ህዝቡ የተሻሉ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ለመለየት ይቸገራል። ያልፈለገውን እንዲመርጥም ይገደዳል። ህዝቡ በበቂ ሁኔታ አይወከልም፣ ባልፈለገው አካል እንዲተዳደርም ይገደዳል። ችግሮችም ይቀጥላሉ። ግራ የሚያጋባና ምስቅልቅል ሁኔታ ይፈጠራል። ብዙ የባከኑ የምርጫ ወረቀቶች ይፈጠራሉ። ጊዜ፣ ገንዘብና ጉልበት ያላግባብ ይባክናል።
አዲስ ዘመን የካቲት 27/2011
በዘላለም ግዛው