ማልደን አራት ኪሎ የሚገኘው ቅድስት ስላሴ ካቴድራል የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተገኝተናል። ተማሪዎቹ ከ5 እስከ 14 ዕድሜ ያላቸው ሲሆን የክፍል ደረጃቸውም ከአንድ እስከ ስምንተኛ ክፍል ነው። ህፃናቱ ሰርክ ጠዋት በየክፍላቸው ገብተው ትምህርት ከመጀመራቸው በፊት የኢትዮጵያ ሕዝብ መዝሙርን መዘመራቸው የተለመደ ነው። የመዝሙሩን ሰዓት በታላቅ ፍቅርና ጉጉት የሚጠብቁት መሆኑን ከሁኔታቸው ማየት ይቻላል። ሲዘምሩ በፍፁም ተመስጦ ውስጥ ሆነው ነው። ስሜታቸው አንድ ነው። መዝሙሩን ከልባቸው መውደዳቸውን ፈገግታ ከተላበሰውና በደስታ ከተሞላው የፊታቸው ገጽታ ማየት ይቻላል። መዝሙሩን እንደጨረሱ ከዚሁ ስሜት ሳይወጡ ፈጥነው እጅ ለእጅ በመያያዝ ‹‹ባንዲራችን›› የሚለውን መዝሙር ቀጠሉ። ድምፃቸው ኃያል ከመሆኑ የተነሳ ከጊቢው አልፎ በአካባቢው አስተጋባ። ወደ ክፍል ግቡ ሲባልም ቀኑን ሙሉ ሲዘምሩት ቢውሉ ፍላጎታቸው እንደሆነ በሚያሳይ ቅር እያላቸው ነበርወደ ክፍላቸው የገቡት።
የትምህርት ቤቱ የመማር ማስተማር ምክትል ርዕሰ መምህር መሐሪ መስፍን እንደገለፁልን ስሜቱ አሁን ላይ በውስጣቸው መጎልበት ጀምሯል። በጦርነት ለተፈናቀሉ ወገኖቻቸውና ሀገራቸውን ለሚጠብቀው መከላከያ ሠራዊት ድጋፍ የማድረግ ሀሳብ ቀድሞ የመጣው ከእነሱ ነው። ትልልቆቹም ትንንሾቹም በአካባቢያቸው የሚደረገውን ድጋፍ ስለሚያዩና በዜና ማሰራጫ ስለሚሰሙ ቢሮ ድረስ እየመጡ ገንዘብ ማዋጣት እንደሚፈልጉ ይገልፁላቸው ነበር።
ትምህርት ቤቱ የመጀመሪያውን ድጋፍ ያደረገው በዚሁ መነሻና ከአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ በወረደ መመርያም እንደሆነ መምህር መሐሪ ተናግረዋል። ከተማሪዎቹ በተሰበሰበው ገንዘብ ከአለ በጅምላ 20 ጆንያ ማኮሮኒ እና 17 እሽግ ካርቶን ፓስታ (በውስጡ 25፤25 ነጠላ የሚይዝ) ገዝተው አስረክበዋል። እያንዳንዱ ተማሪ 50 ብር እንዲያዋጣ ነው የተወሰነው። ሆኖም ለኪስ የሚሰጣቸውን ጨምረውና ወላጆቻቸውን ጠይቀው ከ50 ብር በላይ ያዋጡም አሉ።
ልደት ሠለሞን ከተወሰነው በላይ ጨምረው ካዋጡት ተማሪዎች መካከል አንዷ ናት። ዘንድሮ የስምንተኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የምትወስድ ተማሪ ስትሆን 14 ዓመቷ ነው። ልደት እንደነገረችን ከ50 ብር በላይ ለኪስ የተሰጣትን ጨምራ ማዋጣት ትችል ዘንድ ወላጆቿን ስትጠይቅ ተፈቅዶላት 100 ብር አዋጥታለች። ልደት ጎበዝ የደረጃ ተማሪ ስለሆነች ወላጆቿ የጠየቀችውን ያደርጉላታል፤ ነገር ግን የሚያደርጉላት ጥያቄዋ ጠቃሚ መሆኑን አባቷም እናቷም ከተወያዩበት በኋላ እንደሆነም አጫውታናለች። ለተፈናቀሉ ወገኖችና ለሀገር ሉዓላዊነት እየተዋደቀ ላለው ለመከላከያ ሠራዊት ማዋጣቷ ተገቢ መሆኑን ስላመኑበትም እንደሆነ ነግራናለች።
በምትኖርበት ወረዳና ክፍለ ከተማ ለመከላከያ ሠራዊቱ ወላጆቿ የአልባሳትና የገንዘብ ድጋፍ ሲያደርጉ እሷም ብዙ ልብሶች ስላሏትና አዘውትራ የምትለብሰው የትምህርት ቤት ዩኒፎርም በመሆኑ ብዙዎቹን ልብሶቿንና ጫማዎቿን ሰጥታለች። ልብስና ጫማው በጦርነቱ ምክንያት ከትምህርት ገበታቸውና ከቀዬአቸው ለተፈናቀሉ የዕድሜ እኩዮቿ በማሰቧ እንደሆነም ነግራናለች።
‹እኛ እዚህ እየበላንና እየጠጣን ትምህርታችንን ብንማርም ጦርነቱ ባለበት አካባቢ ያሉ ተማሪዎች ትምህርታቸውን አቋርጠዋል። ከፍተኛ ችግር አለባቸው። የሚበሉትና የሚጠጡትም እንደሌለ በቴሌቪዥን ሰምቻለሁ› ትላለች። ተማሪ ልደት ተማሪዎቹ ቅርብ ቢሆኑ ወላጆቿ የሚቋጥሩላትን ምሳዋን አካፍላ ታበላቸው እንደነበረም ኀዘን በተቀላቀለ ሁኔታ ገልፃልናለች።
ሌላው ያናገርነው ተማሪ ናሆም ልደቱ ይባላል። ናሆም የዚሁ ትምህርት ቤት ውስጥ በጦርነቱ ለተፈናቀሉ ወገኖችና ለመከላከያ ሠራዊት የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል። “ጦርነት እጅግ አስከፊ ነው። በተለይ ህፃናትን ይጎዳል። ልጆች ተማሪዎች በጦርነቱ ጉዳት ባይደርስባቸው እንኳን ወላጆቻቸው በጦርነት ሊሞቱ ይችላሉ። በዚህ ጊዜ ደግሞ የሚያሳድጋቸው አይኖርም። ትምህርትም ሊማሩ አይችሉም። ጎዳና ሊወጡ ይችላሉ…” ሲልም ሃሳቡን አካፍሎናል።
ናሆም ያዋጣው ትምህርት ቤቱ እያንዳንዱ ተማሪ እንዲያዋጣ የወሰነውን 50 ብር ብቻ ነው። ወላጆቹን ተጨማሪ ስጡኝ ብሎ አልጠየቃቸውም። ለኪስ ብለው የሰጡትም የለውም። ናሆም እንደነገረን እንደ ልደት ሁሉ ጎበዝ የደረጃ ተማሪ ነው። ሁሌም አንደኛ ነው የሚወጣው። ጎበዝ የሆነው ፀጥታ በሰፈነበትና በሰላማዊ ቦታ ተረጋግቶ ማጥናት ስለቻለ ነው። ጦርነት ቢኖር ግን በዚህ ሁኔታ ማጥናት እንደማይችልም ተገንዝቧል።
በመጨረሻም የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር መኮንን ጓለ እንደገለፁልን በትምህርት ቤቱ 872 ተማሪዎች አሉ። ሁሉም ለተፈናቀሉ ወገኖችና ለመከላከያ ሠራዊት ድጋፍ ብር አዋጥተዋል። ሁለተኛ ዙር ለማዋጣትም እየጠየቁ ነው። ተነሳሽነታቸውም ያስደስታል ብለውናል። ተማሪዎቹ በፀሎት ክፍለ ጊዜያቸው ለራሳቸው፣ ለመከላከያ ሠራዊት እና ለሀገር ደህንነት ይጸልያሉ።
እኛም የቅድስት ስላሴ ታዳጊ ተማሪ ልጆች ለተፈናቃይ ወገኖችና ለመከላከያ ሰራዊት ላደረጉት ድጋፍ እናመሰግናለን። ድጋፉን ማድረግ ያስቻላቸው ሀገር ፍቅር ስሜት እንዲኖራቸው ተደርገው በመቀረፃቸው በመሆኑ ተሞክሮው በሌሎች ትምህርት ቤቶችና በወላጆች ይስፋ እንላለን።
ሠላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 10 ቀን 2014 ዓ.ም