• ከአጋር ፓርቲዎች ጋርም በቅርቡ ውህደት ይፈጽማል
አዲስ አበባ፦ ኢህአዴግ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ለመቀላቀል በሩ ከፍት መሆኑን እና ከአጋር ፓርቲዎችም ጋር ውህደቱ በቅርቡ እውን እንደሚሆን አስታውቋል። የኢህአዴግ ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ መለሰ አለሙ፤ ለአዲስ ዘመን በሰጡት ማብራሪያ ድርጅቱ ማሻሻያ እያደረገ ነው። ማሻሻያ ሲያደርግ ለተፎካካሪ ፓርቲዎች በሩን ዘግቶ አይደለም። አብሮ መሆን የሚወሰነው ግን በተፎካካሪ ፓርቲዎች ፍላጎት ነው።
በዓላማ የሚጣጣም ካለና ዓላማውን የሚደግፍ ፓርቲም ሆነ ግለሰብ አብሮ ለመስራት ከፈለገ የኢህአዴግ በር ክፍት መሆኑን ገልጸው፤ ግን አብረን እንሁን ብሎ ማንንም አያስገድድም ብለዋል። ኢህአዴግ የህዝብ ድርጅት ነው ያሉት አቶ መለሰ፤ በባህሪይው ተራማጅ በመሆኑ እንደየጊዜው ስልቶቹን በመንደፍ አገሪቱን ከኋላ ቀርነት በማውጣትና የዳበረ ዴሞክራሲ በመፍጠር የበለጸገች ኢትዮጵያ ለመገንባት ይሰራል።
ይህ ረጅም ጊዜ የሚወስድና በኢህአዴግ ብቻ የሚያልቅ ሳይሆን የሌሎች ፓርቲዎችንና ግለሰቦችን የትግል አስተዋፅኦ የሚጠይቅ ነው። እንደ አንድ ፓርቲ የትውልዶችን ትግል ለሚጠይቀው ጉዞ ተመሳሳይ ዓላማ ያላቸው ድርጅቶች ካሉ ኢህአዴግ የእኔ ብቻ የሚልበት ምክንያት የለም። ከአጋር ፓርቲዎች ጋር ለመዋሀድ የሚደረገው ሂደት ቀደም ብሎ ጥናቱ ተጠናቅቋል።
የጥናቱ ውጤት ለፓርቲዎቹ ቀርቦ ውይይት ከተደረገ በኋላ በቅርቡ የኢህአዴግና የአጋር ድርጅቶች ውህደት ይፈፃማል። ፓርቲዎች ሰብሰብ ብለን ለአገር የሚጠቅም ሥራ ማከናወን አለብን። መሰባሰቡ አገሪቱ የምትፈልገውን ውጤት ለማምጣት ምቹ ሁኔታ ይፈጠራል ብለዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 27/2011
በአጎናፍር ገዛኸኝ