ብዙውን ጊዜ ብዙዎቻችን ኢትዮጵያዊነት ምንድን ነው የሚለውን ለመተንተን እንቸገራለን። በዚህም የተነሳ ብዙውን ጊዜ ኢትዮጵያዊነት ምንድን ነው? ተብለን ስንጠየቅ “ኢትዮጵያዊነት ከቃል በላይ ነው” ፤ “ኢትዮጵያዊነት ጥልቅ ነው” ፤ ኢትዮጵያዊነት እንዲህ ነው፤ እንዲያ ነው እያልን ለማብራራት እንሞክራለን።
አንዳንዶች ኢትዮጵያዊነት ኩራትና ትህትና ነው በሚል ትርጓሜ ይሰጣሉ። ሌሎች ደግሞ ኢትዮጵያዊነት ማለት ብዝሀ ብሄር እና ብዝሀ ሃይማኖት ነው በማለት ከግለሰባዊ ይልቅ ቡድናዊ ትርጓሜ ይሰጡታል።
አሁን ግን ኢትዮጵያዊነት ማለት ምን እንደሆነ በሸዋሮቢቱ ሰማእት አቶ እሸቴ በኩል አይተነዋል። እሸቴ ሞገስ ከልጁ ይታገስ እሸቴ ጋር በመሆን የከሀዲውን ትህነግ ወራሪ ቡድን ታጣቂዎች በመደምሰስ ለሀገራቸው ኢትዮጵያ የተወዳቁ ሰማእታት ናቸው።
ኢትዮጵያዊነትን በእሸቴ ሞገስ በኩል አይተናል። ኢትዮጵያዊነት በእዚህ ሰማእት በሚገባ ታይቷል። ኢትዮጵያ በብዙዎች መስዋእትነት እዚህ ደርሳለች፤ አሁን ደግሞ በእነ እሸቴ መስዋእትነት ቀጥላለች። ለእኔ በእዚህ ዘመን ራስን ሰውቶ ሌሎችን ማኖር፣ኢትዮጵያን ማቆየት እሸቴያዊነት ነው። ኢትዮጵያዊነትም እሸቴያዊነት ነው እላለሁ።
እሸቴያዊነት ምን ስለመሆኑ ሰማእቱ እሸቴ ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ሲል ከመሰዋቱ በፊት ባደረገው የመጨረሻ የስልክ ልውውጡ ውስጥ ሰምተነዋል። በዚያ የስልክ ልውውጥ ውስጥ ኢትዮጵያዊን ኢትዮጵያዊ የሚያሰኙ መገለጫዎች በሙሉ ተጠቅሰዋል። ብዙዎችም በማህበራዊ ሚዲያ ገጻቸው እነዚህን የኢትዮጵያዊነት መገለጫዎች እንዳዩ ጠቁመዋል። ከነዚህ መካከል አንዱ እዮብ ምህረተአብ ነው። እዮብ ‹‹ቼ በለው›› የሚል መጽሐፍ አለው። ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ወጎችንና ማህበራዊ ሂሶችን ይጽፋል። እዮብ ስለዚያ የመጨረሻ የስልክ ምልልስ ቀጥሎ የተመለከተውን ጽፏል፡-
‘’ቅዱስ ሚካኤል ምስክሬ ነው።’’
‘’ይታገስን ጥዬ?’’
‘’ዘጠኝ ጥለናል።’’
‘’አላፈገፍግም!’’
‘’አላለቅስም!’’
‘’እኛ እየሞትን ነው።’’
‘’እኔ እና እሱ ብቻ!’’
‘’ለመንግሥት አሳውቅ።’’
….
ደግመህ አንብበውማ፦ ይሄ እኮ ተራ ምልልስ አይደለም። ዝም ብሎ ዘራፍ ዘራፌዋ አይደለም። እንዴኤኤኤ!? ይሄማ ድክሞ እንጉርጉሮ፣ የማይረባ ብሶት አይደለም። ጌታዬ ይሄ – ‘ቻው ሰላም በልልኝ’ አይነት ስንብት አይደለም። አይደለም
….
(አይደለማ!)
…
የስልክ ምልልሱ ውስጥ ፍልስፍና አለ። ማንነት አለ። ምንነት አለ። #ታላቅነት አለ። #ትልቅነት አለ። #ኢትዮጵያዊነት አለ።
ዕምነት ማተብ አለ።
ታማኝነት አለ።
ደፋርነት አለ።
ወንድነት አለ።
…
( ተረዳው እሸቴን)
…
‘’ለመንግሥት አሳውቅ’’ ሲልህ የአስተዳደር ተዋርድን ማወቅ አለ። ስርዓትን፣ መንግሥትን ማክበር አለ። መዋቅርን መረዳት አለ። ጨዋነት አለ።
…
(አባባሉን ተርጉመው) …
‘አላፈገፍግም’ ሲልህ በውስጡ ብዙ ነገር አለ። ሠፊ ነገር አለ። ጥልቅ ነገር አለ። በሚገባ የተደራጀና የተገነባ ልገልጸው የማይቻለኝ እሴት አለ።
መስዋዕትነት አለ።
ሰማዕትነት አለ።
የአገር ፍቅር አለ።
‘#እኔ ሞቼ #አንተ ተከብረህ ኑር’ አለ።
…
(ንገረው ለልጅህ)
….
‘’ይታገስን ጥዬ?’’ ሲልህ ፍቅር አለ። ወኔ አለ። ሰብዓዊነት አለ። ክብር አለ። ግርማ ሞገስ አለ።
…
ይመጣል ዘመን።
ይመጣል ጊዜ።
ይደርሳል ወቅቱ –
ከየት ነህ ሲባል ፦ ‘’ከእሸቴ ሀገር’’ ብዬ በኩራት የምመልስበት ዘመን ይመጣል ከፊቴ። ይመጣል ጊዜ። ይደርሳል ወቅቱ።
…
እሸቴ ሞገስ። ይታገስ እሸቴ። እሸቴ ሞገስ። ይታገስ እሸቴ። እሸቴ ሞገስ። ይታገስ እሸቴ። እሸቴ ሞገስ። ይታገስ እሸቴ። እሸቴ ሞገስ። ይታገስ እሸቴ። እሸቴ ሞገስ። ይታገስ እሸቴ። እሸቴ ሞገስ። ይታገስ እሸቴ። እሸቴ ሞገስ። ይታገስ እሸቴ። እሸቴ ሞገስ። ይታገስ እሸቴ። እሸቴ ሞገስ። ይታገስ እሸቴ። እሸቴ ሞገስ። ይታገስ እሸቴ። እሸቴ ሞገስ። ይታገስ እሸቴ። እሸቴ ሞገስ። ይታገስ እሸቴ። ሲል እዮብ ሰማእቱን እሸቴን ገልጾታል። እሸቴ
የእዮብ ትንታኔ ለዚህ የጀግናው ታሪካዊ ንግግር የሚስማማ እና የሚመጥን ነው። በዚህም መሰረት ንግግሩን ስንደምረው የምናገኘው ድምር ኢትዮጵያዊነት ማለት ምን ማለት ነው ለሚለው ፍቱን ብያኔ ይሰጠናል። ኢትዮጵያዊነት ማለት ጀግንነት ፤ ፍቅር ፤ ሰብአዊነት ፤ ግርማ፤ ተዋረድን (hierarchy) ማክበር፤ መዋቅርን መረዳት፤ ለሀገር መስዋእት ለመሆን መዘጋጀት ፤ ዕምነት፤ ታማኝነት፤ ደፋርነት፤ ኩሩነት፤ ባርነትን መጠየፍ፤ ባንዳነትን መናቅ፤ ኃላፊነትን መወጣት፤ ቤተሰብን ማክበር፤ ለቀጣይ ትውልድ መጨነቅ ነው።
ይህ በእሸቴ ውስጥ ያየነው ስብእና ለብዙ ሺህ ዘመናት ሲዳብር የመጣ ነው። ይህ ስብእና ያላቸው የፈጠሩት ማንነት ነው ሀገሪቱን ብዙ መከራዎችን ተሻግራ ብዙ ዘመናትን አልፋ ዛሬም እንደ ሀገር እንድትቆም ያደረጋት።
በእሸቴ ውስጥ ያየነው ስብእና የአንድ ብሄር አይደለም ፤ የአንድ ሃይማኖት አይደለም ፤ የአንድ አካባቢ አይደለም ፤ የመላው ኢትዮጵያ ነው። እሸቴን የሚመስሉ ብዙ ሰዎች ከያንዳንዱ ብሄር ፤ ከያንዳንዱ ሃይማኖት ፤ ከእያንዳንዱ አካባቢ መጥቀስ እንችላለን። ይህን ስብእና ነው አሁን ማዳበር ያለብን።
ኢትዮጵያዊነት በፖለቲካው አይን ሲታይ ህብረ ብሄራዊ ፣ህብረ ሃይማኖታዊ ነው። ነገር ግን እነዚህ ህብሮች በሙሉ አንድ የሚያደርጋቸው ደግሞ እሸቴአዊ ስብእና ነው። ከብሄር በፊት ሰው ይቀድማላ። ያ ሰው ግን በእሸቴአዊ ጠንካራ ስብእና ካልተገነባ ፋይዳ አይኖረውም።
ሀገር የምትመሰረተው ከቤተሰብ ነው። ሁሉም ቤተሰብ የየራሱ እሸቴ ያስፈልገዋል። ያ እሸቴ ነው ማህበረሰብ የሚገነባው። ያ በርከት ያሉ እሸቴዎችን የያዘ ማህበረሰብ ነው ከተሞችን የሚመሰርተው፤ ሀገርን የሚያቆመው። ጠላት ሲመጣም ጎልቶ የሚወጣው ይህ ወፍራም ስብእና ነው።
ልብ አድርጉ፤ ከላይ የጠቀስናቸው እሸቴአዊ ባህሪዎች ግለሰባዊ ባህሪዎች ናቸው። ለቡድን አይሰሩም። እነዚህ ባህሪያት ከቡድን ወደ ግለሰብ አይወርዱም ፤ ይህን ባህሪ የያዙ ግለሰቦች ግን ጠንካራ ቡድን ይመሰርታሉ። ያ ቡድን ሰፍሮ ሀገር ይሆናል። ኢትዮጵያ እስከ ዛሬ ወራሪዎቿን እያሳፈረች የቆመችውም በእሸቴ መሰል ሰዎች ነው። ስለዚህም እሸቴአዊነትን እናስፋፋ።
አቤል ገ/ኪዳን
አዲስ ዘመን ታህሳስ 9/2014