ታሪክን የኋሊት፤
“…በምድር ላይ ኃይለኛ የሆነው መንግሥት ምንም በደል የሌለበትን የሌላውን መንግሥት ሕዝብ ለማጥፋት የሚገባው መስሎት በተነሣበት ጊዜ፤ ተጠቂው ወገን ለመንግሥታት ማኅበር የተበደለውን የሚያቀርብበት ሰዓት ነው። እግዚአብሔርና ታሪክ ለምትሰጡት ፍርድ ምስክር ሆነው ይመለከታሉ። ሕዝቤ ዘሩ ሊጠፋ በደረሰበት የመንግሥታት ማኅበርም እርዳታ ከጥፋት ለማዳን በሚችልበት ጊዜ ማናቸውንም ሳላስቀርና ሳላቆይ በተዛዋሪ ቃል ሳይሆን እውነቱን አውጥቼ እንድናገር ሊፈቀድልኝ የተገባ ነው። ” (ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ – ሰኔ 19 ቀን 1928 ዓ.ም፤ ጄኔቭ)
“ታሪክ የኋላ ማርሽ እንጂ ወደፊት የሚያስፈነጥር የሞተር አቅም የለውም” እያሉ የሚከራከሩ “የዘርፉ ጠበብት” ቆም ብለው አቋማቸውን እንዲፈትሹ የ2014 ዓ.ም የሀገራችንን አሳዛኝ ክስተት ከ1928 ዓ.ም መሪር የ85 ዓመታት ትውስታ ጋር እያነጻጸርን ለማሳየት ምስስሉ ግድ ይለናል። ለመሆኑ በተመሳሳይ ክስተት ታሪክ ራሱን ሊደግም እንደምን በቃ? እንዴትስ የግፉ ጽዋ እስከዛሬ እንደተሾመ ሊቆይ ቻለ? መልስ የሌለው ጥያቄ፤ ፍቺ የሌለው ዕንቆቅልሽ ይመስላል።
ፋሽስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን የወረረችው (ከ1928-1933 ዓ.ም) ወይ በጉርብትና አለያም በጋራ ጥቅም ክፍፍል ላይ የሚያጋጭ በቂ ምክንያት ኖሯት አልነበረም። “ግፍ የተሠራብን በእኛ፤ ካሱ ይሉናል በዳኝ” እንዲል ብሂላችን ኢጣሊያ የአድዋ ሽንፈቷን ተከናንባና አሜን ብላ ለመኖር የልቧ ትዕቢት አልፈቀደላትም። ይልቁንስ ለዓርባ ዓመታት ያህል አርግዛ የኖረችውን ቂምና ቁርሾ ለመወጣት በወረረችን ወቅት ኢትዮጵያ ራሷ መስራች የሆነችበት የወቅቱ የዓለም መንግሥታት ማኅበር (ሊግ ኦፍ ኔሽን) በደሏን አይቶ ሊታደጋት ፈቃደኛ አልነበረም። ንጉሡ ለማሳየት የሞከሩት ይህንንው ግፍ ነበር።
“እንኳን የ52 መንግሥታት ቃል ኪዳንና የሁለት ሰዎችም ቃል ኪዳን ቢሆን ተከብሮ መኖሩ ግድ ለሚልበት” ማኅበራዊ እሴት ተገዢ መሆን የተሳነው የመንግሥታቱ ሸንጎ ኢትዮጵያን ለኢጣሊያ አሳልፎ ለመስጠት መወሰኑ የታሪካችን አንዱ መሪር ትውስታ ነው። ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ “እግዚአብሔርና ታሪክ ለምትሰጡት ፍርድ ምስክር ሆነው ይመለከታሉ” ያሉትና እንደ ገደል ማሚቶ ከአጥናፍ አጥናፍ በዓለም የታሪክ ልሳን አማካይነት እያስተጋባ የሚኖረውን ይህንን አይረሴ መልዕክት በሸንጎው ፊት ቆመው የተናገሩት ምን ያህል የፍትሕ መዛባት እንደነበር ለማስታስ ነበር።
የተረባረበብን የዛሬው የመንግሥታቱ ሸንጎስ?
ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማግሥት እ.ኤ.አ በ1945 ዓ.ም ከሊግ ኦፍ ኔሽን ወደ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትነት ግብሩን ሳይሆን ስሙን ለውጦ በ50 ያህል መንግሥታት ሸንጎው እንደገና ሲቋቋምም ፊርማዋን ቀድማ በማኖር ለቻርተሩ ተግባራዊነት ቃል ከገቡት ሀገራት መካከል የእኛዋ ኢትዮጵያ አንዷ ነበረች።
በአሁኑ ወቅት 193 ያህል መንግሥታትን በአባልነት ያቀፈው ይህ ግዙፍ ተቋም ዋነኛ ተልዕኮው ዓለም አቀፍ ሰላምንና ጸጥታን ማስከበር፣ አባል ሀገራት የወዳጅነትና የወንድማማችነት እሴት ግድ ብሏቸው እርስ በእርስ በመተባበር እንዲደጋገፉና የበጎነት መንፈስ በመካከላቸው እንዲሰርጽ ለማገዝ መቆሙን “በቻርተሩ የቃል ኪዳን መሃላ” ደመቅ ተደርጎ ተጽፏል።
የተቋቋምኩት በዚህን መሰሉ የማይናወጥ “ፍልስፍና” ላይ ተመስርቼ ነው የሚለው ይህ ታላቅ ድርጅት ዛሬ ዛሬ ከመሠረታዊ መርሁ እያፈነገጠ መሆኑን በተለያዩ መድረኮች ላይ በሚንጸበረቁ አስተያየቶችና ጥናቶች እየተገለጸ ይገኛል። በራሱ የታሪክ ገጽ ላይ የሰፈረውን አንድ እውነታ ብቻ መዘን እንመልከት፤ “…Some commentators believe that the organization to be an important force for peace and human development, while others have called it ineffective, biased, or corrupt.”
ይኼው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በዓለም ላይ ከሚያከናውናቸው ግዙፍ የልማትና የሰብዓዊ ፕሮግራሞች መካከል የኢትዮጵያው አንዱ እንደሆነ እንደሚከተለው ተጠቅሷል፤ “Ethiopia is one of the largest in the world and covers both development and humanitarian assistance. The UN Country Team (UNCT) in Ethiopia is composed of representatives of 28 UN funds and programmers and specialized agencies. Some of the UN agencies in the UNCT have regional mandate or act as liaison offices to the UN Economic Commission in Africa and the African Union.”
በጽሑፍ ያሸበረቀው ይህ ገለጻ ተዓማኒነቱ እስከምን ደረጃ እንደሆነ እንድንጠራጠር የሚገፋፉንን በርካታ ክስተቶች እያስተዋልን ነው። በተለይም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በተባበሩት መንግሥታት በኩል በኢትዮጵያ ላይ እየተወሰዱ ያሉት አቋሞች በእጅጉ የሚያስገርሙና የመርሆውን ተዓማኒነት የሚያጠይቁ ናቸው። “እንደ በኸር ልጅ አቅፈው እሹሩሩ” በማለት ደረታቸው ላይ የለጠፉት አሸባሪው ሕወሓት “ለምን ይነካብናል” በማለት በአደባባይ ሲከራከሩ ማስተዋልም ከማስገረምም አልፎ በእጅጉ ትዝብት ላይ የሚጥል ድርጊት ስለመሆኑ ተደጋግሞ ተውስቷል። ጉዳዩን በዝርዝር እንዳስሰው።
በልዩ አደረጃጀታቸው ከሚታወቁት ከ15ቱ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተቋማት መካከል (Specialized agencies) በተለይም የምግብና የእርሻ ድርጅቱ (FAO)፣ በተለየ ሁኔታ ለእርሻ ልማት ቆሜያለሁ የሚለው (IFAD)፣ የሠራተኞች መብት ዋና ተቆርቋሪ ነኝ ባዩ (ILO)፣ የገንዘብ ጉዳዩን የሚዘውረው (IMF)፣ ዓለም አቀፉ የቴሌኮሚዩኒኬሽን ኅብረት (ITU)፣ የመንግሥታቱ የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ጠበቃ ነኝ የሚለው (UNESCO)፣ የኢንዱስትሪ ልማት ተጠሪው (UNIDO)፣ የቱሪዝም መልከኛው (UNWTO)፣ የዓለም ባንኮቹ ስብስብ (WBC)፣ የጤና ድርጅቱ (WHO) እና የተቀሩትም ተቋማት አሸባሪው ሕወሓት በሀገሪቱ ላይ የሰብዓዊና ቁሳዊ ከፍተኛ ወንጀሎችን ሲፈጽም እንደምን አስችሏቸው ዝምታን ሊመርጡ ቻሉ!?
የድሃ ገበሬ እርሻ በማሳ ላይ ሲጋይ፣ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ዜጎች ከመደበኛ ሥራቸውና ኑሯቸው ተፈናቅለው ለመከራ ሲዳረጉ፣ ቴሌኮሚዩኒኬሽንን የመሳሰሉ በርካታ መሠረተ ልማቶች ሲወድሙ፣ ባንኮችና ኢንሹራንሶች ተዘርፈውና ወደ ትቢያነት ሲለወጡ፣ በሺህዎች የሚቆጠሩ የጤና፣ የትምህርትና የባህል መገለጫ ተቋማት የዶግ አመድ ሆነው በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ምስኪን ልጆቻችን ከትምህርት ገበታ ተፈናቅለው ሲቆዝሙና ዘመናቸውን ሲረግሙ እነዚህ ተቋማት እንዴት ርህራሄ ሊያጡ ቻሉ። ሰብዓዊ ፍጡር ሊተገብረው ቀርቶ ሊታሰብ እንኳን የማይቻል የንጹሐን ዜጎች ጭፍጨፋ በሕወሓት አረመኔ ጀሌዎች በአደባባይ ሲፈጸም እነዚህ “ለዓለም ዜጎች ክብር ቆመናል” የሚሉ ግዙፍ ተደማጭ ድርጅቶች ምን ብለው ድምጻቸውን አሰሙ? እንዴትስ ለመታደግ አሰቡ? እንጃ።
በዋነኛነትም ድርቅና ርሃብ ሲከሰት ፈጥነው ምላሽ እንዲሰጡ የፕሮግራሞችን ማስተባበር ኃላፊነት የወሰዱት የዓለም ምግብ ድርጅት (WFP) እና በጦርነትና በተለያዩ ችግሮች ለሚፈናቀሉና ለስደት ለሚዳረጉት ምንዱባን ዜጎች አለኝታ እንዲሆን ታላቅ ተልዕኮ ያነገበውን (UNHCR) የመሳሰሉ “ምግባረ ሠናይ ነን” ባይ ድርጅቶች በርግጡ ለኢትዮጵያ ወቅታዊ ችግሮች የሚጠበቅባቸውን ያህል ምላሽ እየሰጡ ነው? ደግሜ እላለሁ እንጃ።
“አባት የያዘውን ልጅ ይወርሳል” እንዲሉ ለተግባር ስምሪት ቆመናል የሚሉት ፕሮግራም ፈጻሚዎችም ሆኑ ከላይ ከተዘረዘሩት ልዩ አደረጃጀቶች መካከል ጥቂት የማይባሉት ልክ እንደ ዋናው አባታቸው እንደ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሁሉ በኢትዮጵያ ሀገሬ ላይ ከፍተኛ አድልዎና አጠልሺ መረጃዎች በዓለም ላይ በማሰራጨት ተጨማሪ ፈተና መሆናቸው በእጅጉ የሚያሳፍር ነው።
የመንግሥታቱ የፀጥታው ምክር ቤት በማይመለከተውና በታሪኩ ውስጥ ከአሁን ቀደም ተመዝግቦ በማይታወቅ ሁኔታ ሲያሻው በህዳሴ ግድባችን ዙሪያ፣ በል ሲለው ደግሞ ለአሸባሪው ቡድን ቀጥተኛ ሽፋን በመስጠት “በተደራደሩ ስም” ሸንጎውን ሲያሟሙቅ፣ ይህም አልሆን ሲለው ሀገሪቱን በእምቢተኝነት ፈርጆ “በሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ፍረጃ” የማዕቀብ ጥሪ እንዲተላለፍ መወትወት ምን የሚሉት ሴራ እንደሆነ ለመገመት ያዳግታል። ይህ ድርጊት ከ85 ዓመታት በኋላ ያገረሸ የተቋሙ እኩይ ድርጊት ነው ቢባል ያንስ ካልሆነ በስተቀር ተጋነነ የሚባል አይደለም።
የእነዚህ ድርጅቶች ተቀጣሪ የሆኑ አንዳንድ ግለሰቦች በስንዴ መሃል ጥይት ወሽቀው፣ ከዱቄት ጋር የተራቀቁ የኮሚዩኒኬሽን መሳሪያዎችን ሸሽገው ለአሸባሪው ቡድን በራሳቸው መኪናዎች እያጓጓዙ ማቀበላቸው ተደጋግሞ የተገለጠ የሴራቸው አንዱ አካል ነው። የተጓጓዙባቸው መኪኖችም እዚያው ለጀሌዎቹ በገጸ በረከትነት ተመርቆላቸው ለጥፋት ተልዕኳቸው ማስፈጸሚያ እንዲሆኑ መደረጋቸው ለ“ማን አለብን ድፍረታቸው” ጥሩ ማሳያ ይሆናል።
በቅርቡም ከተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ምክር ቤት አባል ሀገራት መካከል 52 ያህሉ (17ቱ ቋሚ አባላት 35ቱ ደግሞ ታዛቢዎች መሆናቸውን ልብ ይሏል) ኢትዮጵያ ላይ ሌላ የተጎነጎነ ሴራ አውጠንጥነው ማዕቀብ እንዲጣልባት ለማድረግ ትናንት ታኀሣሥ 8 ቀን 2014 ዓ.ም ቀጠሮ ይዘው አዳራሻቸውን እያጸዳዱ እንዳሉ ተደምጧል። የስብሰባቸው ውጤት ምን አጀንዳ እንደተስተናገደበት በሚቀጥለው ጽሑፌ ለመዳሰስ እሞክራለሁ።
ለዕውቀትና ለጸሎት እንዲረዳ አንዳንድ እውነታዎችን እንጠቃቀስ። የመንግሥታቱ የሰብዓዊ ምክር ቤት ጠቅላላ አባላት ቁጥር 47 ሲሆን ስብጥራቸውን በተመለከተም 13 መቀመጫዎች ለአፍሪካ፣ 13 ለኤዢያ ፓስፊክ ሀገራት፣ 8 ለላቲንና ካሬቢያን ሀገራት፣ 7 ለምዕራብ አውሮፓ ሀገራት፣ 8 መቀመጫዎች ደግሞ ለምሥራቅ አውሮፓ ሀገራት የተደለደሉ ናቸው።
ለመሆኑ ከ47ቱ ቋሚ አባላት መካከል በ17ቱ ውስጥ የሚገኙት ሀገራት የትኞቹ ናቸው? ለምንስ በማያገባቸው ሉዓላዊ ጉዳያችን ላይ እንደዚህ ግብግብ እያሉ ለመንተክተክ ፈቀዱ? ለምንስ የአፍሪካ ሀገራት ከዚህ ግራ-ገብ ቡድን ራሳቸውን ሊያገሉ ፈለጉ? እኮ ለምን “አንገታቸውንና ልባቸውን ለማደንደን ጨከኑ? መልሱ ቀላልም ውስብስብም ነው። አንድ ታሪካዊ ሁኔታ በብእረ መንገዴ አስታውሼ ልለፍ።
እ.ኤ.አ በ1885 በጀርመን በርሊን የተሰባሰቡት ምዕራባውያን ቅኝ ገዢዎች አፍሪካን እንዴት ሙሉ ለሙሉ እንደሚቀራመቱ ዕቅድ ነድፈው እንደነበር ይታወሳል። በወቅቱ ለቅርጫ ከቀረቡት የአፍሪካ ሀገራት መካከል የአራጆቻቸውን ጭካኔ ለመታዘብ አንድም ሀገር አልተገኘም ነበር። ዛሬም ኢትዮጵያ ላይ ተሰብስበው ካራ ለመሳል ከተጠራሩት ሀገራት መካከል አንድም አፍሪካዊ ሀገር ያለመገኘቱ በ135 ዓመታት ታሪክ ራሱን እንደገና ለመድገሙ ጥሩ ማሳያ ይሆናል።
የአውሮፓን ፖለቲካ በመዘወር የሚታወቁት እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመንና ጣሊያን ዛሬም ከ17ቱ መካከል ቀዳሚዎቹ ናቸው። በታዛቢነት ስም ከጀርባ የሚገፉት አሜሪካንን መሰል አገራትም በጊዜ ወለድ ጠላትነታቸውን ካስመሰከሩት መካከል ይጠቀሳሉ። እነዚህ ሀገራት በኢትዮጵያ ላይ ፊታቸውን ያጠቆሩበት እርግጠኛው ምክንያት ወደፊት በዝርዝር ሊገለጽ ቢችልም በግላጭ የሚስተዋለው ግን የመጋለቢያ ፈረሳችንን የሕወሓት ጀርባ ለምን ገባጣ አደረጋችሁት የሚል ቁጭት እንደሆነ ግልጽ እየሆነ ነው።
አንድ የቅርብ ወዳጄ ያስታወሰኝን ታሪካዊ ጉዳይ ጠቅሼ ርዕሴን ልደምድም። ከላይ የተጠቀስኳቸውን ሀገራት ስም እየዘረዘረ ያስፈገገኝ እንዲህ በማለት ነበር። “ቢረሱ ቢረሱ የምኒልክን ውለታ እንዴት ይዘነጉታል? በማንም ሀገር ያልተደረገላቸውን የተንጣለለ መሬት ለኤምባሲ ጽ/ቤቶቻቸው ያደሉት ያንሳችኋል እባካችሁ ሰፋ አድርጉት እያሏቸው አልነበረም። ” ወዳጄ እውነቱን ነው። የዛሬውን የእንግሊዝ ኤምባሲን ግቢ ልብ ብሎ ላስተዋል፣ በጀርመን ኤምባሲ ቅጥረ ግቢ በኩል ያለፈ፣ የኢጣሊያን ኤምባሲን የቃኘ፣ ጉብታ ላይ የተሰየመውንና የተንጣለለውን የፈረንሳይ ኤምባሲ ግቢ የመተረ፣ የአሜሪካን ኤምባሲን ሁዳድ የለካ ወዘተ. እውነትነቱን በቀላሉ መረዳት ይችላል። በማሰላሰያ ጥያቄ ልሰናበት። ለመሆኑ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደ ስሙ ለኢትዮጵያ ድጋፍ ሀገራትን አስተባበረልን ወይንስ ለጥፋት ተባበሩብን? የአውሮፓ ኅብረት መባሉስ ለመልካምነት ወይንስ ለሴራ ቅንጅት? ልብ ያለው ልብ ያድርግ !? ሰላም ይሁን!።
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ታህሳስ 9/2014