እዛ ሰፈር ጭር ብሏል። የሞት መላእክት እያንጃበበ ነው። ገሚሱን ወስዶ ከፊሉ ይቀረዋል። ጭው እንዳለ በረሃ ውጥረትና ነግሶ ጭንቀት አይሎ ነው የሚታየው። የአንድ ሰሞን ከበሮ ድለቃው እምጥ ይግባ ስምጥ ሳይታወቅ በድንገት በፍፁም ዝምታ ታጅቦ መቅበዝበዝ ታክሎበት እያስተዋልን ነው። አጃኢብ ነው! ያ ሁሉ ፉከራና ቀረርቶ የት ገብቶ ይሆን?
አሸባሪው ትህነግ ሰፈር የሃዘን ዳስ ተጥሏል። ዱብ እዳውን ግን አምኖ መቀበል፣ ደረት መደቃትና ፀጉር መንጨት አልተቻለም። “እንዲህ አይነት ሃዘን ለጠላትም አይስጥ” ይላሉ አባቶቻችን የነገሩን ክብደት ቅልብጭ ባለች አማርኛ ሲገልፁ። የተዳፈነ ሃዘንና ሲቃ እንደማለት። “ቀድሞ ነበር እንጂ መጥኖ መደቆስ፤ አሁን ምን ያደርጋል ድስት ጥዶ ማልቀስ” ትላለች አያታችን ደግሞ። እውነቷን ነው። የሽብር ቡድኑም ይህ አይነት ጉድ ነው የገጠመው።
እበላ ብለው በሶስት ቀን ዘመቻ የአማራና የአፋር መሬት እንደ እሳት ፈጅቷቸው፤ የመከላከያው ጥምር ጦር ክንድ እንደ ጌሾ ወቅጧቸው፤ አይናገሩት ሽንፈት አያስታምሙት ቁስል ሆኖባቸው በእውር ድንብር መውጫ ቀዳዳ እየፈለጉ ይገኛሉ።
እርግጠኛ ነን ዛሬ “ምነው ያኔ አማራ ምድር ሳልገባ የቆላ ተንቤይ መሬት ተከፍታ ብትውጠኝ” ብለው የሃዘን ማቅ ውስጥ መግባታቸው አይቀርም። የእንጉርጉሮ አታሞ የሚደልቁት እንደ ፍም ከሚፋጀው ኢትዮጵያዊ ክንድ ጋር የገጠሙት ባንዳዎች ብቻ አይደሉም። “ግፉ በርቱ” ሲሉ የከረሙት አዛዦቻቸውም ጭምር እንጂ።
ለአራት ወራት እናት “ማህፀኔን በዘጋው” ብላ ፈጣሪዋን እስክታማርር የጭካኔ ሰይፋቸውን በወረሩት አካባቢ ነዋሪዎች ላይ ፈፅመዋል። እንደማይሳካላቸው ቢያውቁትም “ባልበላውም ጫጭሬ ልድፋው” ብለው ከፊት ለፊታቸው ያገኙትን ነብስ ያለውንም ግኡዙንም አካል እንዳልነበር አውድመዋል። ይሄን ግፍ ኢትዮጵያዊ የሆነ ሁሉ ለመጪው ትውልድ ሲነግረውና ሲያስታውሰው ይኖራል። በምድራችን ላይ እነሱን የመሰለ አውሬ ዳግም እንዳይፈጠር “የሴጣናዊነት” ምሳሌ ሆነው እንደ ማስተማሪያ እንጠቀምባቸዋለን።
የመጨረሻዋን ሳቅ ልንስቅ ጥቂት ቀርቶናል። እኛ እንጂ እነርሱ የሚያወራርዱት ሂሳብ እንደሌለ እርግጥ ሆኗል። ከርቀት ሆነው የአዲስ አበባ ትኬት የቆረጡላቸው ምእራባውያንና አሜሪካኖቹ ከመንገድ ሲቀሩባቸው የሚይዙት የሚጨብጡት አጥተው እንደነጣሪ ኳስ ከአንዱ አገር ወደ አንዱ እየዘለሉ መካሪና ዘካሪ ለመሆን እየቃጣቸው ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትራችን ደግሞ ወደ ሰዎቹ መንደር ከባድ የዲፕሎማሲ ቃል በወንጭፍ ወርውረዋል “እናንት ጎሊያዳውያን ሆይ ከእንግዲህ የኛን ጉዳይ ያለኛ መወሰን አትችሉም” ብለው እንቅጩን ነግረዋቸዋል። ይህን የተናገሩት የአሸባሪው ትህነግን ሠራዊት ወደ ሞት መላእክ ሸኝተው ሲኦል እንኳን ገና ሳይደርስ ነው። ጦር ግንባር ሲደርሱ ብርክ ይዞት በየጥሻው ገደል ገብቶ ያለቀውን ጠላት ጀርባ ሰጥተው ቤተመንግሥት ደጃፍ ከመድረሳቸው ወደ ምእራባውያን ሰዎችም ከባድ ነገረ ሚሳኤል ተኩሰዋል። በእርሳቸው አንደበት የተሰደደው መልእክት የኢትዮጵያውያን ሁሉ ቃል ነው። በአጭሩ “የሚንበረከክ ጉልበት የሚርበተበት አንደበትም ሆነ ተቅለስላሽ ማንነት ከእኛ ዘንድ የለችም” ይላል።
ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት በዘመን ልኬት ሞልቶ የፈሰሰ ግፍ እያስተናገደ ነው። የፈተናዎች ሁሉ ፈተና እየተጋፈጠ ነው። “ላያስችል አይሰጥ” እንደሚባለው ግን እየደረሰበት ያለውን መከራ ሁሉ እየተሻገረው ነው። ወገኖቻችን ተፈናቅለው የሚልሱት የሚቀምሱት አጥተዋል። እንዲያም ሆኖ ግን ቀሪው ወገን ለወንድም እህቶቹ ለመድረስ የሚያደርገው ጥረት አስደናቂ ነው። ጠላት ሲገፋ ግንባር ድረስ ሄደው “ከወገኔ በፊት እኔ” ብለው ግንባራቸውን የሰጡ እልፍ ጀግኖች ስናስብ እንባችን ይታበሳል።
ከሆነብን ይልቅ ፅናትና አሸናፊነታችን ልባችንን ያደነድነዋል። ከመከዳታችን በላይ ጥቃታችንን ለመከላከል የፈጠርነው አንድነትና መተባበር ያፅናናል። ይሄ የፅናት መሠረት ደግሞ ጊዜያዊ ሳይሆን ዘላቂ ድል እንደሚያስገኝልን ለቅፅበት ተጠራጥረን አናውቅም። ምክንያቱም እኛ ኢትዮጵያውያን ነን።
ከውጪም ከውስጥም የመጡብንን ጠላቶች የምንዋጋበት ግልፅ አላማ አለን። ለዚያ ነው “ላታመልጡን አታሩጡን” የምንላቸው። እኛ አገር በማዳን እረድፍ ላይ ስንሰለፍ እነርሱ ደግሞ ከእኛ በተቃራኒው ቆመዋል። ምርጫ የለንም። የህልውና ትግል ውስጥ ነን። የምናሸንፈው ደግሞ በዚህ ግልፅ ምክንያት ነው። የምናሸንፈው ኢትዮጵያውያን ስለሆንን ከዚህ በላይም በታችም ምንም ምክንያት ስለሌለን ነው።
ለዚያ ነው ሳይውል ሳያድር እዛኛው ቤት ሃዘን ያጠላው። አገኘነው የሚሉትን ድል አጣጥመው ሳይጨርሱ በብርሃን ፍጥነት ደረታቸውን እንዲደቁ ያደረግናቸው። ጀግና ደግሞ እየፎከረ ሳይሆን ድንገት ነው ከተፍ የሚለው። እነዛ ሰዎች መንደር እንደ ጦር የሚወጋ፣ እራስን የሚደልቅ ሽንፈት ገብቷል። ከዚህ የከፋው የመጥፋታቸው ጊዜ ደግሞ ከምንም ነገር በላይ አፍንጫቸው ስር ነው።
ለትግራይ እናት ልጆቿን ከምን እንዳደረሱባት የሚነግሯት አንዳች መልስ አያገኙም። ለምን ሲሉ የልጇን ደም እንደጠጡት “ይነግሯት መርዶ ያመካኙት ሰበብ” የላቸውም። ከቆንጥሩ፣ ከገደሉ ስር ድፍት ብሎ የቀረው ልጇን ለምን አላማ ሕይወቱን እንደገበሩት ያስረዱበት አንደበት፣ ቀና ብለው በወኔ የሚያዩበት ዓይን የላቸውም።
በዚህ ምክንያት ዛሬም ይፎክራሉ። የምእራቡ ወዳጆቻቸውን ይማፀናሉ። ወጣቱን አስገድደው ወደ መግደያ ጣቢያ ጎትተው ይከታሉ። ምክንያት ሲጠየቁ መልሳቸው “እያሸነፍን ነው። ለስልት ነው ያፈገፈግነው። የኢትዮጵያ ጉዳይ አፈሩ የተማሰ ልጡ የተራሰ ነው” በማለት የሃሰት ድልና ፕሮፖጋንዳ ውስጥ ይሸሸጋሉ። የሰሞኑን መራር ሽንፈት በዚህ መንገድ ለመከላከል እየሞከሩ ነው። ነገር ግን ዝሆንን በሻሽ ለመደበቅ እንደመሞከር ነው። ቀቢፀ ተስፋ።
እኛ ደግሞ ይህን እንላለን የምናሸንፋችሁ እውነት ከእኛ ጋር ስለሆነች ነው። የምንረታችሁ ድል ልማዳችን ስለሆነ ነው። ሕዝባችን ጥቃትን ከጥንትም የመመከት፤ ግፍና መከራን በፅናት የማለፍ ልማድ ስላለው ህልማችሁን እናከሽፈዋለን። ዳግም በምድራችን ላይ የባህር ማዶዎችን ቅዠት ይዛችሁ ሉዓላዊነታችንን እንዳትዳፈሩ ሕዝባችን አንድ ሆኖ ተነስቷል። ይህን የሚያቆም ምድራዊ ኃይል የለም። እናሸንፋችኋለን ምክንያቱም እኛ ኢትዮጵያውያን ነን።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 9 ቀነ3 2014 ዓ.ም