
የዓለም ባንክ ሥራ በቀላሉ የሚጀመርባቸውን ሀገሮች ዝርዝር በየዓመቱ ይፋ ያደርጋል፡፡ በዚህም መሰረት በተያዘው የፈረንጆቹ ዓመት 2019 ኢትዮጵያ ከ190 ሀገሮች 159ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡ ይህም ሀገሪቱ ንግድና ኢንቨስትመንት በቀላሉ ከማይጀመርባቸው ሀገሮች መካከል መቀመጧን ይጠቁማል፡፡
ድርጅቱ ይህን ደረጃ የሚያወጣው ጊዜን ፣ አዲስ ንግድና ኢንቨስትመንት ለመጀመር የሚያስፈልጉ ወጪዎችን፣ የንብረት ምዝገባን፣ የፋይናንስ አቅርቦትንና የመሳሰሉትን በመለኪያነት በመጠቀም ነው፡፡ ሀገሪቱ ከእነዚህ መመዘኛዎች አንጻር ሲታይ ብዙ የሚቀራት እንዳለ ካለው የንግድና ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴም መረዳት ይቻላል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድም በሀገሪቱ ያለው የኢንቨስትመንት ሁኔታ ለውጭም ሆነ ለሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ፈታኝ መሆኑን በመግለጽ ሀገሪቱ የንግድና ኢንቨስትመንት ሥራ ቶሎ ለመጀመር ፈተና የበዛባት አገር ስለመሆኗ አረጋግጠዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ባለስልጣን መረጃም ችግሩ ግዙፍ እንደሆነ ያመለ ክታል፡፡ መረጃው እንደሚያመለክተው፤ንግድ ቶሎ እንዳይጀመር ደንቃራ ከሆኑት መካከል አዲስ ንግድ ለመጀመር 32 ቀናት እንዲሁም የኤሌክትሪክ ኃይል ለማስገባት 93 ቀናት መውሰዱ ፣ከታክስ ህግጋት ጋር ያለውን ሂደት ለማለፍ 300 ሰዓቶች መጠየቁ የሚሉት ለአብነት ተቀምጠዋል ፡፡ በእርግጥ ሀገሪቱ የቢሮክራሲ መንዛዛት የሚበዛባት፣ የፋይናንስ እጥረት እና የመሰረተ ልማት ችግሮች የሚስተዋሉበት ሆና መቆየቷ ይታወቃል፡፡ይሁንና እነዚህንና ሌሎች መሰል ችግሮችን በመለየት ለመፍታት ባለፉት ዓመታት የተለያዩ እርምጃዎች ወስዳለች፡፡
በዚህም የመሰረተ ልማት ችግርን በኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ ማቃለል ተችሏል፤ በተለይ በኢንዱስትሪ ፓርኮችና በአንዳንድ ተቋማት የአንድ መስኮት አገልግሎት እንዲኖር በማድረግ የባለሀብቶችን እንግልት በመቀነስ ጊዜያቸውን የማምረቻ መሳሪያዎቻቸውን በመግጠም በቀጥታ ልማቱ ላይ እንዲያተኩሩ ለማድረግም ተሰርቷል፡፡ ሌሎች የቢሮክራሲ ውጣ ውረዶችን ለመቀነስም ጥረት ተደርጓል፡፡ ይሁን እንጂ ከችግሩ ግዙፍነት እና ከሀገሪቱ የመልማት ፍላጎት አኳያ ሲታይ እነዚህ ጥረቶች በቂ አይደሉም፡፡ በቂ ላለመሆናቸውም ሀገሪቱ ንግድና ኢንቨስትመንት ቶሎ ከማይጀመርባቸው ሀገሮች ተርታ መሰለፏ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡
መንግሥት እነዚህንና ሌሎች ማነቆዎች በፍጥነት ለመፍታት የሚመለከታቸውን ባለድርሻ አካላት ያካተተ ብሄራዊ ስትሪንግ ኮሚቴ አዋቅሮ እየሰራ ነው፡፡ በዚህ መሰረት የአጭር የመካከለኛ እና የረጅም ጊዜ መፍትሄዎችን ለማስቀመጥ እየተሰራ ነው፡፡ 80 የሚሆኑ አሰራሮችን በመለየት መፍትሄ የማስቀመጥ ሥራም ጀምሯል፡፡ እንደሚታወቀው ሀገሪቱ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መዳረሻ እየሆነች ትገኛለች። ስለሆነም ሀገሪቱ ንግድና ኢንቨስትመንት ቶሎ የሚጀመርባት እንድትሆን በመንግስት የተጀመረው ሥራ ወቅታዊም እና ተገቢም ነው፡፡ ሀገሪቱ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በስፋት እያለማች ትገኛለች፡፡
ከኢንዱስትሪ ፓርክ ውጪ ሌሎች የውጭ ባለሀብቶች እንዲመጡ ይፈለጋል፡፡ ለእዚህ ደግሞ ባለሀብቱን አላላውስ ያሉትን አሰራሮች በማስወገድ እና በአዲስ በመተካት ወይም በማሳጠር የውጭ ባለሀብቶችን የበለጠ መሳብ ያስፈልጋል፡፡ የውጭ ባለሀብቶችን መሳብ ብቻ ኢኮኖሚውን የሚፈለገው ደረጃ ላይ አያደርሰውም፡፡ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን ወደ ኢንዱስትሪው ዘርፍ ማምጣት፣ ሥራ ፈጠራን ማበረታታት ያስፈልጋል፡፡
ይህም እውን ሊሆን የሚችለው የኢንቨስትመንት ከባቢው ምቹ ሲሆንና ሥራን በፍጥነት መጀመር ሲቻል ብቻ ነው፡፡ አሁን ባለው የተንዛዛ አሰራር የሚጠበቀውን ያህል የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን በኢንዱስትሪው መስክ ማሰማራት አይቻልም፤አዲስ ንግድና ኢንቨስትመንት ቶሎ ወደ ሥራ ማስገባትም አይቻልምና መንግሥት የንግድና ኢንቨስትመንት ደንቃራዎችን ለመጥረግ የያዘው ጥረት ሊበረታታና ሊደገፍ ይገባዋል፡፡ የወጪ ንግዱ በቤተሰብ የተያዘ ነው ይባላል፡፡
ይህ ማለት የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ወይም ኢኮኖሚ ቤተሰብ መዳፍ ውስጥ ነው እንደማለት ነው፡፡ ክፉኛ የተዳከመውን የሀገሪቱ የወጪ ንግድ ለማነቃቃትም አዳዲስ መንገዶችን የሚያስቡ ባለሀብቶችንና ሥራ ፈጣሪዎችን ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ማምጣት ያስፈልጋል፡፡ በመሆኑም የንግድና ኢንቨስትመንት ደንቃራዎችን በማስወገድ ሌሎች ዘርፉን እንዲቀላቀሉ ማድረግ ይገባል፡፡ በመሆኑም አዲስ የንግድና ኢንቨስትመንት ሥራን ማቀላጠፍ ወቅቱ የሚጠይቀው አብይ ተግባር ነውና ለስኬታማነቱ መረባረብ ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 26/2011