አዲስ አበባ፦ ሴቶች በሀገር የሰላም ግንባታ ድርድር እና ስምምነቶች ላይ ያላቸውን ተሳትፎ ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑን ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቿ እና በኢትዮጵያ የሴቶች የሰላም ቡድን አባል ገለጹ።
ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቿ እና በኢትዮጵያ የሴቶች የሰላም ቡድን አባሏ ዝምድና አበበ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ ሴቶች የተሳተፉባቸው የሰላም ድርድር እና ስምምነቶች ዘላቂ እና ስኬታማ ሰላም የሚያስገኙ መሆናቸውን ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ ሆኖም በመስኩ በቂ ብቃት እና የካበተ ልምድ የላቸውም በሚል አግላይ አስተሳሰብ ምክንያት በተገቢው ሁኔታ ተካተው የድርሻቸውን አስተዋፅዖ እንዲያበረክቱ እየተደረጉ አይደለም፡፡ በመሆኑም እንደ ሀገር ሴቶች በድርድርና ስምምነቶች ያላቸው ተሳትፎ እጅግ ዝቅተኛ ሆኗል ብለዋል።
ሰላም በተለምዶ የጦርነት አለመኖር ብቻ ተደርጎ በብዙዎች ዘንድ መታየቱን የጠቆሙት የሰብዓዊ መብት ተሟጋቿ፤ ጥልቅ ድህነት፤ በሽታ፤ የምግብ እጥረት፤ ብዝበዛ፤ ጭቆና እና ከጦርነት በተጨማሪ ሌሎች የሰው ልጅን ሕይወት ሊያጎሳቁሉ እና ሕይወቱን ሊነጥቁም የሚችሉ ተግባራትን ስለማካተቱም ገልጸዋል፡፡
የሰላም ግንባታ ከሚይዛቸው ሥራዎች መካከል የሰብዓዊ ርዳታ ማድረስ፤ የሰው ልጆችን መብት መጠበቅ፤ ደኅንነትን ማረጋገጥ፤ እርቅ እንዲፈፀም ማድረግ፤ የተጎዱ የማኅበረሰብ ክፍሎች ሥነ-ልቦናዊ ሕክምና እንዲያገኙ ማድረግ እንደሆኑም ጭምር ጠቁመው፤ ሴቶች ይሄን ኃላፊነት የመወጣት ብቃት ይኖራቸዋል ተብሎ ባለመታሰቡ ተሳትፏቸው ዝቅተኛ ሊሆን እንደቻለ አብራርተዋል፡፡
“ሴቶች በሰላም ጉዳይ እንዳይሳተፉ ማግለል የሥርዓተ ፆታ እኩልነት እንዳይኖር ያደርጋል፤ ዘላቂ ሰላም የማስፈን ዕድልንም ያቀጭጫል” ያሉት የሰብዓዊ መብት ተሟጋቿ፤ ሴቶች በፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት አለመካተታቸውን እንደ አንድ ማሳያ ጠቁመዋል፡፡
ከኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች እሳቸውን ጨምሮ ሀገር እና ዓለም አቀፍ ተሰሚነት ያላቸው 15 ሴቶች ተሰባስበው ሴቶች በሰላም ድርድርና ስምምነቶች እንዲሳተፉና በሰላም ግንባታ የድርሻቸውን እንዲወጡ ውትወታ ማድረግ መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡ “ሴቶችን ያካተተ የሰላም ሂደት በተለያዩ ወገኖች ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረው እና የተሻለ ቅቡልነት እንዲኖር ያስችላል” ያሉት የሰብዓዊ መብት ተሟጋቿ፤ ከሰሜኑ የሀገራችን ጦርነት በኋላ እሳቸውን ጨምሮ ከሀገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች የተውጣጡት 15 ሴቶችን ያቀፈው የሰላም ቡድን በአፍሪካ ኅብረት ተመርቶ በነበረ ሽምግልና ላይ ለሰላም ያላቸውን አቋም ስለማንፀባረቃቸውም አስረድተዋል፡፡
በወቅቱ ማዳም ፑምዝሌ የተሰኙት ፓን አፍሪካኒዝም አቀንቃኝ ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች ግጭቱ እንዲቆም በማድረጉ ረገድ ቡድኑን በመደገፍ ድምፅ ለመሆን መቻላቸውንም አመልክተዋል፡፡
በፕሪቶርያው ስምምነት ሴቶች አለመካተታቸውን ምክንያት በማድረግ ከአፍሪካ ኅብረቱ መድረክ በተጨማሪ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ አኮርድ በሚባል ድርጅት እንዲሁም ኬንያ ውስጥ የሰላም ስምምነት ንግግር ላይ በመሳተፍ ለሴት የሰላም ድርድርና ስምምነት ተሳታፊዎች ድምፅ ለመሆን መቻላቸውንም ተናግረዋል፡፡
ቡድኑ ሴቶች የመደራደር አቅማቸው እንዲጨምር ትምህርቶች፤ ሥልጠናዎች፤ የግንዛቤ ማስጨበጫዎችና የተለያዩ የአቅም ግንባታ ሥራዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ሲሠራ መቆየቱን እና አሁንም ሴቶች በሰላም ድርድርና ስምምነት ያላቸውን ተሳትፎ ለማሳደግ እየሠራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
የሴቶች የሰላም ቡድን ተሳትፎ በውሳኔ ሂደት ውስጥ አካታች እና ወካይ ውሳኔ እንዲወሰን ዕድል ይፈጥራል፤ በተለያዩ ወገኖች ዘንድ የሰላም ስምምነቱ ተቀባይነት እንዲኖረው እና በሰፊው ማኅበረሰብ ዘንድ የተሻለ ቅቡልነት እንዲፈጠር ያደርጋል፡፡
የሴቶች የሰላም ቡድኑ የቀድሞ አምባሳደሮችን፤ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችን፤ ነጋዴዎችን፤ ኤክስፐርቶችን፤ በግጭት የጥቃት ሰለባ የሆኑና የተለያዩ ሴቶችን ያቀፈ እንደሆነ ታውቋል፡፡
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ሐምሌ 17 ቀን 2017 ዓ.ም