
አዲስ አበባ፡– የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል ከሐምሌ 28 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ከ80 ሺህ በላይ ለሚሆኑ መምህራንና የትምህርት አመራሮች ልዩ የክረምት የአቅም ግንባታ ሥልጠና እንደሚሰጥ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ አማራጭ የመምህራን ሥልጠና በ2018 ዓ.ም በስድስት ዩኒቨርሲቲዎች እንደሚጀመርም ጠቁመዋል፡፡
በትምህርት ሚኒስቴር የአጠቃላይ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ አየለች እሸቴ የ2ኛው ዙር የመምህራንና የትምህርት አመራሮች የአቅም ግንባታ ሥልጠና ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ትናንት ሲካሄድ እንደገለጹት፤ ሚኒስቴሩ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የተለያዩ ተግባራት እያከናወነ ይገኛል፡፡
የመምህራን ብቃትና ተነሳሽነት ማጎልበት ለትምህርት ጥራት ወሳኝ ሚና አለው ያሉት ወይዘሮ አየለች፤ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል በመምህራን ልማት ባለፈው ክረምት 52 ሺህ ለሚደርሱ መምህራንና የትምህርት አመራሮች የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡ በዘንድሮው ዓመትም ከ80 ሺህ በላይ ለሚሆኑ መምህራንና የትምህርት አመራሮች ልዩ የክረምት የአቅም ግንባታ ሥልጠና እንደሚሰጥ ገልጸዋል።
መምህርነት በዕውቀት፣ በክህሎትና በሥነምግባር በማነጽ ችግር ፈቺ ዜጎች ለማፍራት ትልቅ ሚና የሚጫወት ሙያ መሆኑን ጠቅሰው፤ የትምህርት ጥራትን በማስጠበቅ በኩልም የመምህራንና የትምህርት አመራሮች ያላቸው ድርሻ ከፍተኛ ነው፡፡ የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠናዎችም ተነሳሽነትን በማሳደግ ውጤታማ የመማር ማስተማር ሁኔታ ለመፍጠር እንደሚያስችሉ ገልጸዋል፡፡
ሚኒስቴሩ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በሥርዓተ ትምህርት፣ በመምህራንና አመራሮች ልማት፣ ትምህርት ቤቶችን ምቹ በማድረግና ሌሎች በርካታ ሥራዎችን በማከናወን ላይ መሆኑን አመልክተው፤ የመምህራንና የትምህርት አመራሮችን ብቃት ለማሳደግ ባለፈው ዓመት በተሰጠው ሥልጠና ከተወሰዱ ልምዶች በመነሳት የታዩ ክፍተቶችን ሊቀርፉ የሚችሉ ስልቶችን በመንደፍ ከመጪው ሐምሌ 28 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ለ2ኛ ጊዜ ከ80 ሺህ ለሚበልጡ መምህራንና የትምህርት ቤት አመራሮች ሥልጠና እንደሚሰጥ ጠቁመዋል፡፡
በአሠልጣኞች ሥልጠና የሚሳተፉ መምህራንም የተጣለባቸውን ትልቅ ሀገራዊ ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡም ሚኒስትር ዴኤታዋ አሳስበዋል፡፡
የመምህራንን እጥረት ለመቅረፍ ከ2018 ዓ.ም ጀምሮ የመምህራን አማራጭ ሥልጠና እንደሚጀመር ያመለከቱት ወይዘሮ አየለች፤ ሥልጠናው ከ2018 ጀምሮ በስድስት ዩኒቨርሲቲዎች መሰጠት ይጀምራል፡፡ ወደዚህ ሥልጠና የሚገቡትም በተለያያ ሙያ መስኮች ሠልጥነው በጥሩ ውጤት የተመረቁ፣ ለመምህርነት ሙያ ፍላጎት ያላቸውና ሌሎችም የተቀመጡ መስፈርቶችን የሚያሟሉ እንደሚሆኑ ጠቁመዋል፡፡
የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ብርሃነመስቀል ጠና(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ እንደሀገር የተከሰተውን የትምህርት ስብራት ለመጠገንና የትምህርት ጥራት ለማሻሻል መምህራን የማይተካ ሚና አላቸው። የትምህርት ሥርዓት የመፈጸም አቅምን ለማጎል በትም የመምህራንና ትምህርት አመራሮች ስልጠና የሚካሄድ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ባለፈው ክረምት 52 ሺ መምህራንና አመራሮች ሥልጠና መሰጠቱን አስታውሰው፤ በዘንድሮ ክረምትም ከ80 ሺህ በላይ መምህራንና የትምህርት አመራሮች ሥልጠና የሚሰጥ ይሆናል፡፡
ሥልጠናውም የትምህርት ዓይነት ይዘትና የማስተማር ሥነዘዴ፣ የትምህርት ቴክኖሎጂ እና የአዕምሮ ጤና ሥነ ልቦናና ማኅበራዊ ድጋፍ ላይ ያተኮረ መሆኑንም አመልክተዋል።
በትንትናው ዕለት በተጀመረው የአሠልጣኞች ሥልጠና እስከ ሐምሌ 18 ቀን 2017 ዓ.ም እንደሚቆይ የተጠቆመ ሲሆን፤ ከሐምሌ 28 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ በ20 ቀናት ያህል በ30 ዩኒቨርሲቲዎች የሚሰጠው የመምህራንና የትምህርት አመራረሮች ሥልጠና እንደሚጀመር ተመላክቷል፡፡
ፋንታነሽ ክንዴ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ሐምሌ 17 ቀን 2017 ዓ.ም