‹‹ግጭት ወዳዶችን በቃችሁ በማለት ሀገርን ከችግር ማውጣት ያስፈልጋል›› – አምባሳደር ዲና ሙፍቲ

አዲስ አበባ፡እንደ ሀገር ሕዝብ ከሕዝብ ጋር የሚጋጭበት ነገር ባይኖርም ሕዝብ ከሕዝብ ጋር ጠብ እንደገጠመ የሚያስመስሉ ግጭት ወዳዶችን በቃችሁ ማለት የሀገርን ዘላቂ ሰላም ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ተናገሩ።

አምባሳደር ዲና ሙፍቲ እንደተናገሩት፤ በየትኛውም ዘመንና ዓመት ውስጥ እንደ ሀገር ሕዝብ ከሕዝብ ጋር ተጋጭቶ አያውቅም። ግጭቶች የሚከሰቱት ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ በሚያራግቡ ሰዎች ነው። በዚህም ሀገር ዋጋ እየከፈለች መሆኑን አስገንዝበዋል።

ግጭት ወዳዶች ሕዝብ ከሕዝብ ጋር እንደተጋጨ በማስመሰል ግጭት እንዲባባስ ዘመቻ በሚመስል መልኩ እንደሚያከናውኑ ጠቁመው፤ በዚህ ምክንያት ረጅም ዓመታትን ሀገር ዋጋ ከፍላለች ነው ያሉት።

አሁንም ኢትዮጵያ በተለያየ መልኩ ችግርን እያስተናገደች እንደምትገኝ አመልክተው፤ ዜጎች ይህንን ጉዳይ በሚገባ ልብ ሊሉ ይገባል። ሰላምን የሚያደፈርሱ ኃይሎች እምቢ ማለት መጀመር አለብን። ሕዝቡ የግጭት ዘመቻ መቼም ቢሆን እንደማይጠቅም ተረድቶ ለሰላም ዘብ መቆም ይጠበቅበታል ብለዋል።

የሕዝብ ጥያቄ ጤና፣ መንገድ፣ ትምህርት፣ ማዳበሪያ፣ ውሃና አጠቃላይ ልማትን ነው ያሉት አምባሳደሩ፤ የሕዝቡ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ፣ ማኅበራዊ ትስስሩ እንዲጠናከርና በሰላም ወጥቶ እንዲገባ ሰላምን ማረጋገጥ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ሕዝቡ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈንም በየአካባቢው በሕዝብ ስም የሚነግዱ ግጭትና ዘመቻ ወዳድ አካላትን ሊቃወማቸው እንደሚገባ አስገዝበው፤ ሰላሙ በራሱ እጅ ላይ እንደሆነ በማመንም ለሰላሙ ዘብ የመቆሚያ ጊዜው አሁን መሆኑን አስረድተዋል።

አሁን ሕዝቡ ያለው አንድ መርከብ ውስጥ እንደሆነ ማመን አለበት ያሉት አምባሳደር ዲና፤ መርከቡም ሰላሙ ነው ብለዋል። ሰላሙን በአግባቡ መጠበቅ ካልቻለ አብሮ እንደሚሰጥም መረዳት ይገባዋል ሲሉ ተናግረዋል።

አሁን ብዙ ሀገራት ሰላምን ከማጣታቸው ምክንያት የሚኖሩበትን ሀገር ጥለው ተሰደዋል። እኛ ከራሳችን ሳይሆን ከሌሎች መማር ይጠበቅብናል ነው ያሉት። በሀገራችን ሰላምን የማረጋገጥ ጉዳይ የማንም ሳይሆን የራሳችን ጉዳይ መሆኑን መረዳት አለብን ሲሉ አሳስበዋል።

የግሎባል ፒስ ባንክ መሥራችና ሥራ አስኪያጅ አቶ አረጋው አየለ በበኩላቸው፤ ይቅር ባይ ያልሆነ ሰው ግጭትን ያባብሳል እንጂ በምንም መልኩ ሰላምን ሊያሰፍን አይችልም። የሰላም ሃሳቦችን ለመሸመትም ይቸገራል፤ በዚህም ዓለም የግጭት ስጋት ገጥሟታል፤ ሕጻናትና እናቶች በፍራቻ ውስጥ ወድቀዋል፤ በእኛ ሀገርም ያለው ይኸው ጉዳይ ነው ብለዋል።

በተወሰኑ ሰላም ጠል ሰዎች ሀገር ዋጋ እየከፈለች እንደምትገኝ አንስተው፤ አሁን ችግሩን በቃ ማለት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያውያን አማኝና ማኅበራዊ ግንኙነታቸውን በባህላቸው የገነቡ መሆናቸው ይታወቃል ያሉት አቶ አረጋው፤ ጎረቤቶቻቸውንም አጥብቀው የሚወዱ ናቸው፤ ሆኖም ይህንን መረጋጋትና ሰላምን የማይፈልጉ አካላት ፀብ አጫሪነትን እያስፋፉት እንደሚገኙ ገልጸዋል።

በእነዚህ ሰላም ጠል ቡድኖች ሥራም በሰላማቸው የማይደራደሩት ኢትዮጵያውያን በሰላም እጦት እየተፈተኑ መሆናቸውን ገልጸው፤ ትናንት በባህላችን የፈታናቸው ችግሮች ዛሬም እንከን ሊሆኑብን አይገባምና በሽምግልና ባህላችን ተቀራርቦ በመነጋገር ለችግራችን እልባት ልንሰጠው ይገባል ብለዋል።

በባህላዊ ግጭት መፍቻ ዘዴዎቻችን ተጠቅመን ነገሩን ከምንጩ በማድረቅ ላይ መረባረብ ያስፈልጋልም ሲሉ አሳስበዋል።

ራሳችንን ስንወድ ሰላማችንን መጠበቅ ምርጫ ሳይሆን ግዴታችን እንደሆነ እንረዳለን ያሉት አቶ አረጋው፤ ጎረቤታችን ከተረበሸ እንኳን ተረጋግተን ምግብ መመገብ አንችልም ብለዋል።

ሰላማችንን መጠበቅ ልዩ ጥቅምና ውለታ ፈልገን ሳይሆን ራሳችንን ለማረጋጋትና ነጋችንን ለመሥራት ብለን የምንከውነው መሆኑን መገንዘብ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

እንደ አቶ አረጋው ገለጻ፤ ሰላም መረጋጋትንና እረፍትን ያበዛል፤ ልማትን ያፋጥናል፤ ይቅር ባይነትን ያጎናጽፋል አዲስ ማንነቶችን ይሰጣል፤ መለወጣችንን ያበዛል፤ የቆየውን ቁርሾና ቅያሜ ትናንት ላይ ትተነው በአዲስ ማንነት የምንሻገርበትን ዕድል የሚያጎናጽፈን ነው፤ ለአዲስ ሥራና ለአዲስ ለውጥ በሰላም እንሻገር ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ጽጌረዳ ጫንያለው

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሐምሌ 17 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You