ቢሾፍቱ፡- የአካባቢ ጥበቃ ሕጎችን ለማስከበር የሚደረገው ጥረት ልማትን የሚያደናቅፍ ተግባር ተደርጎ እየተወሰደ መሆኑን የኢፌዴሪ የአካባቢ፣ የደንና አየር ንብረት ለውጥ ከሚሽን የሕግ ፖሊሲና ደረጃዎች ዳይሬክተር ጄኔራል አስታወቁ፡፡
በደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ላይ ወጥ የሆነ የግንዛቤ ሥራ መሥራት እንደሚገባ ተጠቆመ። በኮሚሽኑ የሕግ ፖሊሲና ደረጃዎች ዳይሬክ ተር ጄኔራል ዶክተር አየለ ሔገና እንዳሉት፤ በሀገሪቱ የደረቅ ቆሻሻዎች አወጋገድ ችግር እያጋጠመ ነው፡፡ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ደረጃ ተናቦ የመሥራት ልምድ አለመኖሩንና ሁሉም የራሱን ሥራ ለማስፋፋት እየጣረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በዚህ ሂደት የአካባቢ ጥበቃ ሕጎችን የማስከበሩን ሥራ ልማትን የሚያደናቅፍ አድርጎ መመልከት እንደሚስተዋል አቶ አየለ ጠቁመው፣ ‹‹በኮሚ ሽኑ ላይ ኢንቨስትመንት እንዳይስፋፋና፣ ሥራ አጥነት እንዳይጠፋ ትጥራላችሁ›› የሚል የተሳ ሳተ አመለካከት ገዝፎ እንደሚታይም ጠቅሰው፣ ከውጭ ምንዛሪ ጋር የሚያያይዙትም እንዳሉ ተናግረዋል። ችግሩ በ1970ዎቹ አካባቢ በአደጉት ሀገ ራት ተከስቶ የነበረ አይነት መሆኑን አቶ አየለ አብራርተው፣በወቅቱም ከብክለት ጋር በተያያዘ ከፍተኛ አለመግባባት ከመንግሥታት ጋር ተከስቶ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
ሕዝብም ያጉረመረመበት ወቅት እንደነበር ገልጸዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በምዕራባውያን ዘንድ በአካባቢ ጥበቃ ጉዳይ ላይ ማንም ለማንም እንደማይናገር ገልጸው፣ ችግሩን በመገንዘብ ለውጥ ማምጣታ ቸውን አስታውቀዋል። እንደ አቶ አየለ ገለጻ፤ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ኢንዱስትሪን ለማስፋፋት፣ ኢንቨስት መንት ኮሚሽንም ባለሀብት ለመሳብ የሚያደርጉት ጥረት ጥሩ ቢሆንም፣ የማንኛውም ኢንቨስትመንት ሥራ ከመጀመሩ በፊት የአካባቢ ተፅዕኖ ዳሰሳ ማካሄድ አለበት፡፡
ዘላቂ የአካባቢ ጥበቃ ከሌለ ማኅበራዊ ዕድገቱ እንደሚገታ አቶ አየለ ተናግረው፣ሥራዎች ሲሰሩ የአካባቢ ጥበቃን ከብክለት ነፃ ማድረግን ታሳቢ ባደረገና በተናበበ መልኩ መሆን እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡ የኮሚሽኑ የአካባቢ ሕግ ተከባሪ ዳይሬክተር አቶ መሐሪ ወልደሚካኤል ጥናት ጠቅሰው፤ የሕዝብ ቁጥር መጨመር፣ የከተሞች መስፋፋት፣ የምጣኔ ሀብት ዕድገት እና ልማት በደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደፈጠረ አስታውቀዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ በቀን 300 ሚሊዮን 156 ሺ ኪሎ ግራም ደረቅ ቆሻሻ እንደሚመነጭ ጠቅሰው፣ ቆሻሻ የገቢ ምንጭና ሀብት መሆኑ እየታወቀ መምጣቱንም ገልጸዋል፡፡ በቆሻሻ አወጋገድ ላይ የህዝብ ተሳትፎ ማነስ እንደሚስተዋልም ተናግረዋል፡፡ ከተሞች የዕድገትና የማኅበራዊ ለውጥ መሠረት፣ የሀገር ኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ሞተሮች ናቸው ያሉት አቶ መሐሪ ፣ የደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ችግርን በመፍታት ከተሞችን የአካባቢ ለውጥ መሣሪያዎች እንዲሆኑ ለማስቻል ጥረት መደረግ እንዳለበት ገልፀዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 26/2011
ኃይለማርያም ወንድሙ