አሜሪካኖች ከነግሳንግሳቸው ለምን ለአገራችን ሽብርን ይመኛሉ? ገፍቶ ከመጣም እንድትበታተን ይፈልጋሉስ? ለምንስ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ገለልተኛ አቋም መያዝና ገንቢ የሆነ አስተዋጽኦ ለማድረግ ፍላጎት አጡ? እውነት የዴሞክራሲ እጥረት፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና የሰብዓዊ እርዳታ ችግሮች አሳስቧቸው ነውን? በአሜሪካ የሚመራው የምዕራብ አገራት ትክክለኛውና እውነተኛው በኢትዮጵያ ላይ ያላቸው ፍላጎቶች ምንድን ናቸው? ፍላጎታቸውን ለማስከበር ምን እያሴሩ ነው?
አሜሪካኖች በዓለም ላይ እንዲስፋፋ እንፈልጋለን የሚሉትና በአብዛኛው የውጭ ግንኙነት ስትራቴጂያቸው ማዕከልና ለግንኙነቶቻቸው ስኬት እንደ ቁልፍ ጉዳይና ማሳያነት የሚያነሱት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መስፈን፣ ሰብዓዊ መብቶች መከበር እና የሰብዓዊ እርዳታ ወዘተ ናቸው። የሚወራውና ወረቀት ላይ ያለው ስትራቴጂያቸው በተግባር ሲታይና ሲመዘን ግን በሰው አእምሮ ውስጥ ጥያቄ የሚጭሩ ጉዳዮች አሉ። ይህንን በኋላ ላይ እናነሳለን። ዓለም ላይ በፍጥነት እየተለወጠ ከመጣው የዓለም አገራት መንግሥታዊ የአስተዳደራዊ ሥርዓት የተነሳ አገራት ሙሉ በሙሉ መንግሥታዊ የአስተዳደር ሉዓላዊነታቸውን አስከብረው መቀጠል እያዳገታቸው መምጣቱ የሚካድ ጉዳይ አይደለም። ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጎለበተ የመጣው ዓለም አቀፋዊነትና በአገራት መካከል የሚፈጠሩ ትስስሮች በዓለም አገራት መካከል ከፍተኛ የሆነ የካፒታል፣ የንግድ፣ የዕውቀት፣ የቴክኖሎጂ፣ የባህልና የሕዝብ ፍሰት እንዲጨምር ማድረጉን የዓለም ባንክ በ2016 ዓ.ም ያዳረገው ጥናት ሪፖርት ያመላክታል።
ይህ ጥናት ከ1950 እስከ 2003 በአገራት መካከል በተደረገው የንግድ ልውውጥ የተነሳ ለአገራት አጠቃላይ የምርት መጠን (GDP) ያለው አበርክቶ በእጥፍ ወይም ከ25 ወደ 60 በመቶ እንዲያድግ አስተዋጽኦ ማድረጉን፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ለአገራዊ አጠቃላይ የምርት መጠን (GDP) በተመለከተ በ1970 ከ10 በመቶ በታች የነበረው በ2011 ከ40 በመቶ በላይ እንዲያድግ ለማድረግ መቻሉን ያመላክታል። ይህ በእንዲህ እንዳለ የዓለም አቀፍ የውጭ እዳ በአገራት አጠቃላይ ምርት መጠን ውስጥ የነበረውን ድርሻ ከ11 በመቶ ወደ 90 በመቶ እንዲያሻቅብ ማድረጉን ያመላክታል።
ከዚህ መረዳት የሚቻለው በአገራት መካከል የሚፈጠረው ዓለም አቀፋዊ ትስስር በጎና ጎጂ ጎኖች እንዳለው ነው። ስለሆነም ነጻ፣ ገለልተኛና ዴሞክራሲያዊ ዓለም አቀፍ የአስተዳደር ሥርዓት ተፈጥረው እነዚህንና ሌሎች ዓለም አቀፍ ጉዳዮች እንዲመክሩበት ማድረግ የውዴታ ሳይሆን የግዴታ እየሆነ የመጣበት እውነታ ተፈጥሯል። እስከ አሁን ባለው ሁኔታ ይህ የዓለም አቀፍ አስተዳደር ሥርዓት በዋናነት አሜሪካ በምትመራው የምዕራብ ዓለም አገራት ስብስብ የበላይነት ነው በመመራት ላይ የሚገኘው።
ሥርዓቱም ኢ-ዴሞክራሲያዊ፣ ወገንተኛና የምዕራቡን ዓለም አገራት ፍላጎትና ተልኮ አስፈጻሚ እንደሆነና መታደስ እንዳለበት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በቻይና፣ ራሺያ፣ አፍሪካ፣ ኤዥያና የላቲን አሜሪካ አገራት ከፍተኛ ጫና እየተደረገ ይገኛል። ነገር ግን አሜሪካና የአውሮፓ አገራት ፍቃደኛ አልሆኑም። ይህ ባለመሳካቱ በራሺያና ቻይና አስተባባሪነት ሌላ አማራጭ የዓለም አቀፍ አስተዳደር ሥርዓት እንዲፈጠር ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ።
ቻይናና ራሺያ ለመፍጠር ጥረት በማድረግ ላይ የሚገኙት አዲስና አማራጭ ሥርዓትን በማስመልከት ባለፈው ወር በአሜሪካ የቻይና አምባሳደር የተናገረውና በዚያው ሰሞን በጽሑፍ መልክ በበይነ መረብ ላይ የታተመውም ቁርጠኝነታቸውን በግልጽ የሚያሳይ ስለሆነ እንዳለ አስቀምጬው ልለፍ።: China, Russia ambassadors urge to stop using “value-based diplomacy” to provoke division, confrontation. “This trend contradicts the development of the modern world. It is impossible to prevent the shaping of a global polycentric architecture but could strain the objective process,” Chinese Ambassador to the United States Qin Gang and Russian Ambassador to the United States Anatoly Antonov say, adding “China and Russia firmly reject this move.” http://www.news.cn/english/2021-11/28/c_1310338755.htm
ይህ የእነቻይናና ራሺያ አዲስና አማራጭ የዓለም አቀፍ የአስተዳደር ሥርዓት የመፍጠር እንቅስቃሴ አዲስ ተፎካካሪ ኃይል እየተፈጠረባቸውና የበላይነታቸውን ይዘው እንዳይቀጥሉ እንደሚያደርጋቸው ዘግይቶም ቢሆን በቅርብ የተረዱት በጆ ባይደን በምትመራው አሜሪካ አስተባባሪነት የምዕራቡ አገራት ስብስብ የእነ ቻይናና ራሺያ የጀመሩት የአማራጭ ሥርዓት ግንባታን በእቅጩ ለመቅጨት የሞት የሽረት ትግል ወደ ማድረግ ገብተዋል። የቀድሞ የትራምፕ መንግሥት የዓለም አቀፍ አስተዳደርን አስመልክተው አሜሪካ ሊኖራት የሚገባ አስተዋጽኦ አናሳ እንዲሆን ማድረጉ ቻይናና ራሺያ በዚህ ደረጃ ጉዳዩን እንዲገፉበት እንዳደረገ በቁጭት ያነሳሉ።
ይሄንን ለመቀልበስ ነው ጥድፊያ ውስጥ ገብተው የሚታዩት። የምዕራብ አገራት ከሰሞኑ የሚያደርጉት ያልተገቡ እንቅስቃሴዎችም አገራችንን ሁለት ጎራ ለይተው በሚደረገው ትግል አካል ልትሆን ሊያደርጋት እንደሚችል ይገመታል። ቀድሞው በተለይ ከሁለተኛ ዓለም ጦርነት ማግስት በአሜሪካኖች እና በምዕራብ አገራት ትብብር ተዘርግተው እስከ አሁን ምንም ሪፎርም ሳይደረግበት እየተሰራበት ያለውና አሁንም ያለምንም ተፎካካሪና አማራጭ ሥርዓት እንደነበረ እንድቀጥል የሞት የሽረት ትግል እያደረጉ የሚገኙበት የአስተዳደር ሥርዓት እንዴት ኢትዮጵያ አገራችንን ጨምሮ ሌሎች የዓለም አገራትን ሲበዘበዙበት እንደነበረ እንደሚከተለው ለማቅረብ ተሞክሯል።
የምዕራቡ ዓለም አገራት አሜሪካን ከፊት በማስቀደም የዓለም አገራትን በአንድ እዝ ሥር በማስገባት ተዘርግተው በሚገኘው ወጥ የሆነ የዓለም አቀፉ አስተዳደር ሥርዓት በበላይነት ይዘው መቀጠል ይፈልጋሉ። ግባቸው ደግሞ አሁን ላይ በሰሜንና ደቡብ እንዲሁም በምዕራብና በምስራቅ መካከል የሚታየውን መሃል ዳር (core-periphery) ወይም ሀብታም-ደሃ፣ የበለጸጉና የሰለጠኑ-ያላደጉና ኋላቀር ተብለው የዓለም አገራትን ለያይቶ የተመደቡበትን ነባራዊ ሁኔታ (status quo) ትርጉም ባለው መልኩ ሳይቀየር ማስቀጠል ነው።
ለዚህ ግብ ስኬት ከሚገለገሉባቸው መሳሪያዎች አንዱና ዋናው ያልተፃፈ ሕጋቸው ነው፤ በሕጉ መሠረትም ከምዕራብ አገራት በስተቀር ሉዓላዊ አገርና መንግሥት እንዲፈጠር አይፈቀደም። በተጨማሪ ሉዓላዊነት “globalization”ን የግባቸው ማስፈጸሚያ ፍልስፍናና ስልት አድርገው ይጠቀማሉ። በእነርሱ ዕይታ ግሎባላይዜሽን አገራትን በማስተሳሰር የእውቀት፣ የቴክኖሎጂ፣ የሰለጠነ የሰው ሃይልና ካፒታል ከሰሜንና ከምዕራብ የዓለም አገራት ወደ ደቡብና ምሥራቅ የዓለም አገራት እንዲፈስ ያደርጋል።
ፍሰቱ የተጠናከረና ያለገደብ እንዲሆን መቻል የደቡብና ምሥራቅ የዓለም አገራት ዕድገትና ልማት እንደሚያፈጥን አጥብቀው ለማሳመን ይሞክራሉ። በተለይ የትምህርት ተቋማቶቻቸውንና ሚዲያዎቻቸውን በመጠቀም ይህን እይታ ለማስረጽ ተጽዕኖ (ጫና) ይፈጥራሉ።
ምንጊዜም ቢሆን እነሱ ፍላጎታቸውንና ግባቸውን ለማሳካት ለደቂቃም እንደማያርፉና ውጤት ያመጣልናል የሚሉትን ማንኛውንም ሴራ ከመዘየድና ከመተግበር ወደኋላ እንደማይሉ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለሰከንዶች እንኳ መዘንጋት ፈፅሞ የለብንም። አሁን ላይ ከአሸባሪው ሕወሓት ጎን ቆመው እየደገፉ ያሉት ምዕራባውያን ከእነማን ጋር ሆነው፣ ለምን ምክንያት፣ ምን ዓላማዎችና ግቦችን ለማሳካት ኢትዮጵያን ተቀናጅተው እየወጉ እንዳሉ በሰሞኑ ሙከራዎቻቸውና ተግባራት ለጥርጣሬ እንኳ ዕድል በማይሰጥ አግባብ ግልጽ አድርገው አሳይተዋል። በነዚህ ኩነቶች አማካኝነትም ዋነኛውን በሽታና የበሽታውን መንስኤ ምንነት በደንብ ተለይተው ታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ደግሞ የአገሩን ህልውናና ሉዓላዊነት እንዲሁም ነጸነቱን አሳልፎ ለማንም የማይሰጥ ስለመሆኑ ታሪካችን ህያው ምስክር ነው። ዛሬም ቢሆን ሕዝባችን አገሩን ለባዕድ አሳልፎ በመስጠት ባህሪውና ተላላኪነቱ የሚታወቀውን እንደ ሕወሓት ያለ ባንዳ ቡድን ተመልሶ ማንሰራራትና ችግር ሊሆን በማይችልበት አግባብ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንደሚያክመው ቅንጣት ታክል ጥርጥር የለም።
ሕዝቡ እንዲህ ባለ ድፍረት የተሞላ ወረራ በተፈጸምበት የታሪክ አጋጣሚ አንድነቱን ከአለት በላይ በማጠናከርና አስፈላጊውን ሁሉ መስዕዋትነት ሁሉ በመክፈል ከአያቶቹና ቅድመ አያቶቹ የወረሰውን ባንዳና ባዕድ ወራሪዎችን የማሳፈር አልሸነፍ ባይነቱን፣ አይበገሬነቱን እና የነጻ ሕዝብ ምልክትነቱን ያስከብራል። ብሄራዊ ኩራቱንም አስጠብቆ እንደልማዱ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ተመሳሳይ ጫና ስር ለሚገኙ ለሌሎች የአፍሪካ አገራትም ዳግም ቀንዲል ሆኖ ያበራል!
ዶ/ር ሃሰን ዩሱፍ የወለጋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት
አዲስ ዘመን ታህሳስ 8 / 2014