ከትዝታ ማስታወሻ
ወርቅ ወርቅ መሆኑ የሚታወቀው በእሳት ከተፈተነ በኋላ ነው። እሳት ውስጥ ይጣላል፣ በእሳት ይጠበሳል። እውነተኛ ወዳጅም እንደዚሁ ነው፤ በሰላም ጊዜ ብቻ ሳይሆን በፈተናና በችግር ጊዜያትም በጽናት ቆይቶ፣ ከባዱን ጊዜ በአሸናፊነት አልፎ፣ ይበልጥ ፍቅሩን አጠናክሮ እውነተኛ ወዳጅ በመሆን ያረጋግጣል። ፈተናን በጽናት ተቋቁሞ፤ በደህና ጊዜ ብቻ ሳይሆን በችግር ጊዜም ወዳጅ ሆኖ ካልተገኘ ግን ትክክለኛ ወዳጅ መሆኑ ሊታወቅ አይችልም።
የወርቅ ወርቅነቱ የሚረጋገጠው በእሳት ተፈትኖ እንደሆነ ሁሉ የሰውም ወዳጅነቱ የሚለካው በችግር ቀን ይሆናል። አለበለዚያ ስላብረቀረቀና ወርቅን “ስለመሰለ” ብቻ ነሐሱም መዳቡም “ወርቅ ነኝ”፤ አስመሳዩና ሰው መሳዩ ሁላም “እውነተኛ ወዳጅ ነኝ” በሚል ሲያሳስት ይኖራል። አሁን ላይ ምዕራባውያን “ወዳጆቻችን” በእኛ ላይ እያደረጉት ያሉትም ይኸው ነው።
ምዕራባውያን በሕወሓት ጊዜ እንደልባቸው የእነርሱን ጥቅም ብቻ እያስከበሩ በነበሩበት ወቅት ከኢትዮጵያ ጋር በአንድ ገበታ ካልጠጣሁ የሚሉ “የልብ” ወዳጆቻችን ነበሩ። ለሁሉም ጊዜ አለውና አሁን ላይ የሕወሓት የግፍና የአፓርታይድ የጭቆና ጀንበር አዘቅዝቆ፣ እርሱና አዛዦቹ ምዕራባውያን ብቻ የሚጠቀሙበት ዘመንም አልቆ የእኛም ጥቅም የሚከበርበት ጊዜ ሲደርስ ግን የወዳጆቻችን እውነተኛ ማንነታቸው ተገልጦ መታየት ጀመረ።
የሰው እውነተኛ ማንነቱ በችግር ጊዜ ነውና የሚገለጠው ኢትዮጵያ በሃብቷ ለመጠቀም ወገቧን ታጥቃ መሥራት ስትጀምር እንድትኖር ሳይሆን እንድትፈርስ ሲመራት ከነበረው ከሃዲው ሕወሓት ጋር ህልውናዋን ለማስቀጠል ተገዳ በግድ የሕልውና ጦርነት ውስጥ ስትገባ የጥቅም ወዳጆቿ ምዕራባውያን ዓይንሽ ላፈር አሏት። እንዲያውም ችግር እውነተኛ ማንነታቸውን አጋልጦባቸው በይፋ ከአፍራሿ ጎን ተሰልፈው ሊወጓት ተነሱ። አረመኔው አሸባሪ የፈጸመው ተዘርዝሮ የማያልቅ ግፍና በሰው ልጆች ላይ የፈጸመው ሰብዓዊ ወንጀል አልታይ አላቸው።
እስከ ቅርብ ጊዜ በማያቸው ፊልሞች እና በውሸታም ሚድያዎቿ ነውልዬ የዲሞክራሲ እናትም አባትም ላረኳት እኔማ ይበለኝ ብያለሁ። እንደኔው በርካቶች በደንብ መደፍረስ ሲጀምር ስለ ዲሞክራሲ አታውቁም እናስተምራችሁ ብለው የሚጥሉትን ሁሉ መቀበል እንድናቆም አይን ገላጭ ሆኖልናል።
ያኔ መደፍረስ ሳይጀምር እነሱ የዲሞክራሲ ጠላት ናቸው፤ ሲሉ አብሬ ከመሰሎቼ ጋር ሳወግዛቸው የነበሩት ሀገራት እውነታም የነሱ ሚዲያዎች ሲነግሩን ከነበረው የተለየ ሊሆን እንደሚችል መለስ ብዬ እንዳስብ አድርጎኛል።
መደፍረስ ሲጀምር ማን እውነተኛ ወዳጃችን እንደሆነና ማን የራሱን ጥቅም ብቻ አስቦ ከውስጥ ባንዳዎች ጋር ሲሰራ እንደከረመ መለየት አስችሎናል። ለዚህም ማሳያ ደፍርሶ እንዲቀር የፈለጉት የሰጡንን የቀረጥ ነጻ እድል እንነጥቃችኋለን ሲሉ፤ የደፈረሰውን አብረውን ሊያጠሩ ወዳጅ ሀገራት የግብርና ምርታችሁን ከቀረጥ ነጻ የምታስገቡበት እድል እንፈጥራለን በማለት አጋርነታቸውን አሳይተውናል። ምእራባውያን ውጡ እያሉ ሲለፍፉ የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሚስተር ያንግ ሀገራችን ሰላም መሆኑን በተግባር ሊያስመሰክሩ በሰላም መጥተው ተመልሰዋል። ሩሲያ በውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ በኩል አዲስ አበባ በከበባ ውስጥ እንደሆነች በምእራባውያን ሚዲያ የሚወራው ሀሰት መሆኑን አሳውቃለች።
የደፈረሰው መጥራት ሲጀምር የሀገር ሽማግሌ የሰላም አባት ምሁር ስራ ፈጣሪ እያልን ያለምግባራቸው ስም ሰጥተን ስናንቆለጳጵሳቸው የነበሩትን ማንነት ለይተናል። በዚህም ሀገር ሰላም በናፈቃት ጊዜ ማን ለሰላሟ የሚሰራ የሀገር ልጅ እንደሆነና ማን አድብቶ ለውድቀቷ እንደሚሰራ አውቀናል።
አምባሳደር ታደለች ኃይለሚካኤል “ዳኛው ማነው?” በሚል ርዕስ ባሳተሙት መጽሐፍ ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ስልጣን ላይ እያሉ እሳቸው በአውሮፓ ትምህርት በሚከታተሉበት ጊዜ በሀገር ቤት የተከሰተውን ድርቅ በመስማት ተማሪዎች በማዘን እርዳታ ለማሰባሰብ እንቅስቃሴ መጀመራቸውን ያነሳሉ። ይሄንን የሰሙ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ሰራተኞች ይሄ የተቀደሰ ሥራ ነው በምንችለው እናግዝ በማለት ለድጋፍ እጃቸውን ቢዘረጉም የተማሪ ማህበሩ አባላት ግን ምን ሲደረግ ድርቁ እንዲከሰት ካደረገው ስርዓት አገልጋይ ጋር አንተባበርም። በማለት አሻፈረኝ ማለታቸውን ጽፈዋል። ይሄ እውነታ በንጉሳውያን ጊዜ የነበረ ብቻ ሳይሆን እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በዲያስፖራው እና በመንግስት መሀል የቀጠለ እውነታ ነበር።
አሁን ግን የደፈረሰው መጥራት ሲጀምር ይህ ተቀይሮ የዲያስፖራው ማኅበረሰብ እናት ሀገሩ በባንዳ እና በምእራባውያን ሴራ ሲጠነሰስባት እኛ እያለንልሽ አንቺ አትፈርሺም ሲሉ ጠላትን በጦር ግንባር ለመፋለም በርሃ ከመውረድ አንስቶ ከጉድለታቸው ቀንሰው ለወገን ስንቅና ትጥቁን እየላኩ ነው። አሜሪካ ልደግፋችሁ ብላ የሰጠችንን የአግዋ እድል እንደፍላጎቴና ምኞቴ አላጎበደዳችሁልኝም በማለት አነሳሁት ብትል ዲያስፖራው እንዲያውም በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ ነው በማለት አይዞን ኢትዮጵያ የሚል የዲጅታል መተግበሪያ በማቋቋም በአንድ ፈርጁ ሀገራችን የምንዛሬ እጥረት እንዳይገጥማት በሌላ በኩል በሽብር ቡድኑ ሕወሓት ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች አጋር እንሁናቸው በማለት እየተረባረቡ ነው።
ጀግናው መሪያችን የደፈረሰውን ሊያጠራ የአባቶቹን አርዓያ ተከትሎ እኔ ሞቼም ቢሆን የኢትዮጵያን ክብር አስቀጥላለሁ ብሎ ወደ ግንባር ሲወርድ፤ አብረውት የደፈረሰውን ሊያጠሩ ሞተው ኢትዮጵያን ከአፍራሾች ሊታደጉ በርካቶች ወደግምባር ዘምተዋል። የደፈረሰው መጥራት ስለጀመረ ባንዳው ከሀገር ወዳዱ ተለይቷል። ለገበሬ የሚከብደው አንዴ አረሙን ከሰብሉ መለየት እንጂ አንዴ ከተለየ አረሙን መንቀል ቀላል ነው። በተለይ በደቦ ከተሰራማ የአፍታ ስራ ነው።
በሀገር ውስጥም በውጪም ያለን ተረባርበን ስለ ሀገር ማሰብ መጀመራችን የደፈረሰው እየጠራ የጨለመው እየነጋ ለመሄዱ ማሳያ ነው። እኛ አንድ ሆነን ለሁሉም ልክ አለው በቃ (No more) ብለን መነሳታችን የስኬት ሁሉ ጥግ ነው። ስራ በደቦ ሲሰራ ጊዜም ይቆጠባል፤ ድካምም ይቀንሳል።
አሁን የነብርን ጭራ አይዙ ከያዙም አይለቁ እንዲሉ የጋላቢውንም የተጋላቢውንም ጭራ ላንለቅ ይዘናል። ለአደፍራሾች ሴራ ሳንወድቅ የውስጥ ባንዳን እየመነጠርን መጽናት ያሻል። በዚህም የደፈረሰው ይጠራል፤ ኢትዮጵያም በክብር ከፍ ትላለች !
አዲስ ዘመን ታህሳስ 8 / 2014