አዲስ አበባ፡- በፀሐይ ኃይል በመታገዝ ለሁለት ሺህ 500 አርሶ አደሮች ከፍሎራይድ የፀዳ ንጹህ የመጠጥ ወሃ አጣርቶ ማቅረብ የሚችል ማሽን ተተክሎ ለአገልግሎት መብቃቱ ተገለፀ፡፡
በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል በስልጤ ዞን ላንፋሮ ወረዳ ሰሞኑን ተመርቆ ለአገልግሎት የበቃው ይህ ማሽን በሪቨርስ አሞሲስ ሥርዓት ፍሎራይድን የሚያስወግድ ነው፡፡ በምረቃው ሥነሥርዓት ወቅት የተገኙት የውሃ መስኖና ኢነርጂ ምክትል ኮሚሽነር ወይዘሮ ሸዋነሽ ደመቀ እንደተናገሩት፣ መሳሪያው በቀን 30 ሺህ ሊትር ውሃ በማጣራት ለሁለት ሺህ 500 የአካባቢው ህብረተሰብ ለእያንዳንዱ ነዋሪ በየቀኑ ከ10 ሊትር በላይ ውሃ የሚያቀርብ ነው፡፡
እንደ ምክትል ኮሚሽነሯ ገለፃ የንጹህ ውሃ አቅርቦቱን ችግር ለመቅረፍና የአገልግሎት አሰጣጥ ደረጃን ለማሻሻል ከፍተኛ ጥረት የሚጠይቅ ሲሆን በተለይ በስምጥ ሸለቆ ውስጥ የሚገኘው የከርሰ ምድር ውሃ ሀብት ከፍተኛ የፍሎራይድ መጠን ያለበት ስለሆነ በህብረተሰቡ ጤና ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳረፈ ይገኛል፡፡ በዚህም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ህዝቦች በፍሎራይድ ምክንያት በችግር ላይ እንደሚገኙ በተለያዩ ወቅቶች በስምጥ ሸለቆ አካባቢ የተደረጉ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡
ይህን ችግር ለመቅረፍም መንግሥት የብሄራዊ ፍሎሮሲስ መከላከል ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት በማቋቋም ሁለት የመፍትሄ አማራጮችን ተግባ ራዊ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ የላንፍሮ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ አባስ ሀሰን በበኩላቸው ከዚህ ቀደም በቀበሌው ይቀርብ የነበረው ውሃ በአንድ ሊትር ውስጥ 13 ነጥብ10 በመቶ ሚሊ ግራም እንደነበር አስታውሰው፣በኮሪያው ቲ ኤንድ ሲ ኩባንያ በተከተለው መሳሪያ አማካኝነት በአንድ ሊትር ውሃ ውስጥ ያለው የፍሎራይድ መጠን ወደ 1ነጥብ5 ሚሊ ሊትር እንዲቀንስ ስላደረገው ህብረተሰቡ ጤናው እንዲጠበቅ ማድረጉን አመልክተዋል፡፡
ባለፈው ዓመት ውሃው በጄነሬተር ሲወጣ በነበረበት ወቅት በቀን 5 ሺህ ሊትር ውሃ ብቻ ለህብረተሰቡ ይቀርብ እንደነበር ጠቅሰው፣ አሁን ይህ ቀርቶ ህብረተሰቡ በቀን 30 ሺህ ሊትር ውሃ ማግኘት በመቻሉ ከፍተኛ እርካታ አግኝተናል ብለዋል፡፡ እንደ እርሳቸው ገለጻ በአሁኑ ወቅት ውሃው ለሦስት ጉዳዮች ጥቅም ላይ ይውላል፡፡
ለመጠጥ፤ ለቤት፣ለገላና ለአካባቢ ጽዳት እንዲሁም ለአንድ ሄክታር መስኖ እርሻ የሚሆን ውሀ የሚመረት ሲሆን የፍሎራይድ ይዘታቸውም የተለያየ ነው፡፡ እጅግ የፍሎራይድ መጠኑ አነስተኛ የሆነው ውሀ ለመጠጥ ፍጆታ ይቀርባል፡፡ 400 ሺህ ዶላር የሚያወጣ ይኸው ማሽን የፀሐይ ኃይልን የሚጠቀም ሲሆን፣ ከውሃ ማጣራት ሥራው በተጨማሪ ዳቦና እንጀራ መጋገሪያ እንዲሁም የልብስ ስፌት ማሽን አብሮ የተገጠመለት በመሆኑ ለሴቶችና ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር የሚያስችል መሆኑም ተጠቅሷል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 26/2011
አበበ ወልደጊዮርጊስ