. ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይና ፕሬዚዳንት ኢሳያስ በኤርትራ የልማት ሥራዎችን ጎበኙ
አዲስ አበባ ፡- የኢትዮጵያ ፣የኤርትራና የደቡብ ሱዳን መሪዎች የቀጠናውን ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ትብብር ለማጠናከር እንደሚሰሩ አስታወቁ ፡፡ የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ፣የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂና የደቡብ ሱዳኑ ፕሬዚዳንት ማያርዲት ሳልቫኬር ትናንት ደቡብ ሱዳን ጁባ ውስጥ በቀጠናዊ ጉዳዮች ከተወያዩ በኋላ በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
መሪዎቹ በመግለጫቸው ለደቡብ ሱዳን ሰላም መረጋገጥ እየሰሩ ያሉትን ሁሉን አቀፍ ተግባሮች አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አስታውቀው፣ በቀጠናዊና በዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ትብብር ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ገልፀዋል፡፡ ቀጠናዊ ትብብራቸውን ማሳደግ አስፈላጊ መሆኑንም መሪዎቹ አስታውቀው፣ የሦስቱ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችና ሌሎች የመንግሥት ኤጀንሲዎች የቀጠናውን ኢኮኖሚያዊ ትብብርና የጋራ ብልፅግና ለማሳካት የተያዘውን የጋራ ፕሮጀክት ከግብ ለማድረስም ተስማምተዋል፡፡
ከደቡብ ሱዳን ጉብኝት አንድ ቀን ቀደም ብሎ የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድና የኬንያው ፕሬዚዳንት አሁሩ ኬንያታ አስመራን መጎብኘታቸው ይታወቃል፡፡ ከኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋርም በተመሳሳይ የሁለትዮሽ ውይይት አካሂደዋል፡፡ የሦስቱ ሀገራት መሪዎች በወቅታዊ የቀጠናው ጉዳዮች ዙሪያ የሦስትዮሽ ውይይትና የተናጥል ስብሰባ እንዳካሄዱም የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስትር አቶ የማነ ገብረመስቀል ገልፀዋል፡፡
ለኬንያው ፕሬዚዳንት በአስማራ አየር ማረፊያ አሸኛኘት ካደረጉላቸው በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድና ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ከአገራቱ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት ጋር በመሆን በሀገሪቱ ደቡብ ክፍል የተለያዩ ጉብኝቶችን አድርገዋል፡፡ በዚህም የሎጎና ሚስላን ግድቦችን፣ የወተት ልማትና እንዲሁም በግንባታ ላይ የሚገኝ የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ጎብኝተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ልኡካን ቡድን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁን፣ የጦር ኃይሎች ኤታ ማዦር ሹም ሰአረ መኮንን እንዲሁም የብሄራዊ ደህንነት ኤጀንሲ ዳይሬክተር ጀነራል ጀነራል አደም ኢብራሂምን ያካተተ ነው፡፡ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ባለፈው ሰኔ የተፈረሙ የሰላም ስምምነቶች ለአፍሪካ ቀንድ አካባቢ አዎንታዊ ሚና እንዳላቸው የበርካታ ወገኖች እምነት መሆኑን ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት መረጃ አመልክቷል፡፡ በሁለቱ ሀገሮች እንዲሁም በአካባቢው አባል ሀገሮች መካከል ያለውን ግንኙነት ለማሻሻል የተከናወኑ ተግባሮች የኢኮኖሚ ትብብር ለማድረግ ለተያዘው ሥራ በር መክፈታቸውም ተገልጿል፡፡
መረጃው እንዳመለከተው፣ኤርትራና ኢትዮጵያ አጠቃላይ የትብብር ስምምነቶች ለመፈራረም የሚያስችላቸውን ሥራ እያጠናቀቁ ሲሆን፣ ይህም በሁለቱ ሀገሮች መካከል የተጀመረውን የኢኮኖሚ ግንኙነት በመደበኛ መልኩ እንዲፈጸም የሚያስችል ይሆናል፤በንግድና መሰረተ ልማት እንዲተሳሰሩ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል፡፡
ሁለቱ ሀገሮች የየሀገራቸውን የንግድ እንቅስቃሴ፣ የድንበር ንግድ ፣የወደብ አጠቃቀም፣የጉምሩክ ሥነ ሥርዓት ፣የስደተኞች ጉዳይ ፣እና የትራንስፖርት ትስስሮችን ተቋማዊ በማድረግ ላይ መወያየታቸውንም መረጃው ጠቁሟል፡፡ በቀጣይ የኢትዮጵያና የኤርትራ መሪዎች ስምም ነቶች ከተፈራረሙ በኋላ የስምምነቶቹን ትግበራ እና የሁለትዮሽ ግንኙነት የሚከታተል ኮሚሽን እንደሚያቋቁሙም ተመልክቷል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 26/2011
አስናቀ ፀጋዬ