ጦርነት የሰው ልጆች ሁሉ የሚያጠቃ ጠላት ነው። በተለይ በሴቶች ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ስነ ልቦናዊ ጠባሳውም ከፍተኛ ነውና በቃላት ብቻ የሚገለፅ አይሆንም። በጦርነት ሴቶች ከአስገድዶ መድፈር ጀምሮ ለተለያዩ ጥቃቶች ተጋላጭ እንዲሆኑ ያደርጋል።
ሴቶች ህፃናትም ሆኑ ወንዶች በጦርነቱ ሲጎዱ በሕብረተሰቡ ዘንድ ካለባቸው ድርብ ኃላፊነት አኳያ ጥምር ተጎጂዎች ናቸው። ይሄ እንደተጠበቀ ሆኖ አሸባሪው ሕ.ወ.ሓ.ት ከውስጥና ከውጪ ኃይሎች ጋር ተባብሮ በከፈተው ጦርነት ከሠው አልፎ እንደ በሬና ላም ያሉትን እንስሳትንም በጥይት ደብድቦ ሲገድል ተስተውሏል። በመሆኑም ጦርነትና ጾታዊ ጥቃት በህፃናት እና በተለይ በሴቶች ላይ የሚያሳድረው ስነልቦናዊ ስብራት አንፃር ሲታይ ሁለቱም የአንድ ሣንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው ማለት ያስችላል።
ለዚህም ነው የአዲስ አበባ ሴቶችና ህፃናት ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ከሴቶች ማህበር፣ ከአዲስ አበባ ብልፅግና ሴቶች ሊግ ጋር በጋራ በመሆን ህፃናትና ሴቶችን የበለጠ ተጠቂ እያደረገ ካለውና አሸባሪውና ከሀዲው ሕ.ወ.ሓ.ት በሀገራችን ላይ ከከፈተው ጦርነት ጋር ተሣስሮ እንዲከበር ያደረገው።
በዓሉ ዘንድሮ ‹‹ሠላም ይስፈን በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚደርሰው ጥቃት ይቁም›› በሚል መሪ ቃል በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ30ኛ በሀገራችን ደግሞ ለ16ኛ ጊዜ ካሳለፍነው ህዳር 16 ጀምሮ እስከ ህዳር 30/2014 ዓ.ም ሲከበር ቆይቷል። ታህሳስ 1/2014 ዓ.ም በሌግዠሪ ሆቴል በተካሄደው የመዝጊያ መርሐ ግብር ላይ በአዲስ አበባ ሴቶችና ህፃናት ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ የስርዓተ ጾታ ጉዳዮች ቡድን መሪ ወይዘሪት በረከት በቀለ እንደገለፁት ላለፉት 16 ቀናት በዓሉ በተለያዩ ዝግጅቶች ሲከበር ቆይቷል።
ጾታዊ ጥቃት በተዛባ የስርዓተ ጾታ አመለካከት የሚመጣ እንደመሆኑ መጠን የተዛባውን አመለካከት ለመለወጥ እና የስርዓተ ጾታ ዕኩልነትና ፍትሃዊነት ለማረጋገጥ በሚያስችሉ መርሐ ግብሮች መከበሩን አውስተዋል። ከነዚህ ዝግጅቶች መካከል በጾታዊ ጥቃቶችና በስርዓተ ጾታ ጉዳዮች ላይ በርካታ ስልጠናዎችና ግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ሲሰራ መቆየቱ አንዱ ነው።
ግንዛቤ ማስጨበጫና ስልጠናው ለፍትህ አካላት፣ ለመምህራን፣ ርዕሳነ መምህራን፣ ለተማሪዎች፣ እንደ ዕድር፣ የሴት እና ወጣቶች ማህበራት ያሉ የሕዝብ አደረጃጀቶች፣ ለዘርፍ መሥሪያ ቤቶች፣ ለሐይማኖት አባቶች፣ ለአንድ ማዕከል የአገልግሎት ሰጪ አካላትና ለተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች መሰጠቱንም ተናግረዋል። በተለይ ስልጠናውንና ግንዛቤ ማስጨበጫውን ከወሰዱት አንድ ማዕከላት መካከል በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙት ሦስት የህክምና ተቋማት መጠቀሳቸውንም ገልፀዋል።
ማዕከላቱ ምኒልክ፣ ጋንዲና ጥሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታሎች ናቸው። ሆስፒታሎቹ ጥቃት ደርሶባቸው ለሚመጡ የሕብረተሰብ ክፍሎች አገልግሎቱን ምቹ ለማድረግ የሚያስችላቸው ድጋፍ ተደርጎላቸዋል። አገልግሎት የሚሰጡ ባለሙያዎቻቸውም በየጊዜው አቅማቸውን ለማጎልበት እንዲሁም በሥራው ሊደርስባቸው የሚችለውን ጫና ለመቅረፍ የሚያስችሉ የተለያዩ ስልጠናዎች እንዲወስዱና ድጋፎችን እንዲያገኙ ተደርጓል።
ከዚህ በተጨማሪም የሀገራዊ የህልውና ዘመቻውን እንቀላቀላለን በሚል ፅዳት ዘመቻና ጾታዊ ጥቃትን በመከላከል ረገድ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ፓናል ውይይት መርሐ ግብር ተካሂዷል። ጾታዊ ጥቃት ደርሶባቸው ለሚመጡ ሴቶችና ህፃናት እንክብካቤ የሚሰጡ ማገገሚያ ማዕከላት ጉብኝት ተከናውኗል። የቴሌቪዥን ስፖት በማዘጋጀት መልዕክት ማስተላለፍ፣ የዕለቱ የዘመቻው መዝጊያ ስነስርዓት ጨምሮ በቀጣይ አራት ተከታታይ ሣምንታት በወንዶች አጋርነት ላይ ያተኮረ ቶክ ሾው ማዘጋጀት የ16ቱ ቀን የፀረ-ጾታዊ ጥቃት ዘመቻው አካል መሆኑን ወይዘሪት በረከት አብራርተዋል።
የቴሌቪዥን ስፖት በማዘጋጀት መልዕክት ማስተላለፍ ሲሠራበት መቆየቱንና በቀጣይም በወንዶች አጋርነት ላይ ለአራት ተከታታይ ሳምንታት ቶክ ሾው እንደሚዘጋጅ ገልፀዋል። የዕለቱ የማጠቃለያ መርሐ ግብርም ከ16ቱ ቀናት የንቅናቄ ሥራዎች አንዱ ነውም ብለዋል። የማጠቃለያ ውይይት መካሔድም የዚሁ አካል መሆኑን አንስተዋል።
‹‹ጾታዊ ጥቃት ላይ የተለያዩ ተቋማት በጋራ ይሰራሉ›› ያሉት ወይዘሪት በረከት ጥቃቱ ሪፖርት የሚደረግበት ሁኔታ የተለያየ በመሆኑ በአሁኑ ወቅት የደረሰው ይሄን ያህል ነው ለማለት እንደሚቸግርና ሪፖርቱ ተጠቃሎ ሲደመር መናገር እንደሚቻል በመግለፅ ሀሳባቸውን አሳርገዋል።
‹‹ቀደም ሲል በኮሮና ከዓመት ጀምሮ ደግሞ ከሀዲዎች በሀገራችን ላይ በከፈቱት ጦርነት ሣቢያ በህፃናትና ሴቶች ላይ የሚደርሰው የወሲብና ሌሎች ጥቃቶች ጨምረዋል›› ያሉት የአዲስ አበባ ሴቶችና ህፃናት ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኃላፊና የሴቶች ዘርፍ ኃላፊ ወይዘሮ ሜሮን አራጋው በመርሐ ግብሩ መዝጊያ ስነስርዓት ላይ እንደተናገሩትም የዕለቱ የመዝግያ መርሐ ግብርም ሆነ የ16ቱ ቀን የፀረ ጾታ ጥቃት ዘመቻ የተካሄደበት ዋናው ዓላማም ይሄው መሆኑን አውስተዋል።
እንደ ኃላፊዋ በዓለም ከሦስት ሴቶች አንዷ በሕይወት ዘመኗ አካላዊ ጥቃት፤ ከአምስት ሴቶች መካከል ደግሞ አንዷ አስገድዶ የመድፈር ሙከራ ይደርስባታል። ሆኖም ከሚደርሱት ጾታዊ ትንኮሳዎች ሪፖርት የሚደረጉት 20 በመቶዎቹ ብቻ ናቸው። ኃላፊዋ በፈረንጆቹ 2016 ዓ.ም ይፋ የሆነውን የስነ ሕዝብ ጤና ዳሰሳ (DHS) መረጃ ዋቢ አድርገው በኢትዮጵያ ያለውን ተመሳሳይ የጥቃት ሁኔታ እንደገለፁት ከ15 እስከ 49 ዓመት ከሚገኙና ካገቡ ሴቶች መካከል 24 ነጥብ 9 በመቶው አካላዊ እንዲሁም 24 በመቶ ስነ ልቦናዊ ጥቃት ደርሶባቸዋል።
በዚህ ዕድሜ ከሚገኙት ሴቶች 65 ነጥብ 2 በመቶው ግርዛት ተፈፅሞባቸዋል። 11 ነጥብ 1 በመቶው ወሲባዊ፣ እንዲሁም 28 በመቶ ወሲባዊ ወይም አካላዊ ጥቃት የደረሰባቸው መሆኑ ተገልጿል። በተጨማሪም መረጃው 35 ነጥብ 2 በመቶው አካላዊ ወይም ወሲባዊ አሊያም ስነ ልቦናዊ ጥቃት በትዳር አጋሮቻቸው ወይም አብረዋቸው በሚኖሩ ወንዶች የተፈፀመባቸው መሆኑን ያሳያል።
በ16ቱ ቀናት ፀረ-ጾታዊ ጥቃት ዘመቻ በተለይ የጥቃት ግብረ ኃይል በማቋቋም በኩል እንዲህ ዓይነቶቹን ወንጀሎች አስቀድሞ የተሰራው ሥራ ጉልህ ድርሻ ነበረው። በ125ቱ ወረዳዎችና በ11ዱም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሚገኙ ክፍለ ከተሞች የጥቃት ተከላካይ ግብረ ኃይል የተቋቋመበት ሁኔታ አለ። የተቋቋመው ግብረ ኃይል ብዛቱ 132 ሲሆን በእነዚህ ግብረ ኃይሎች ሥር ደግሞ 1 ሺህ 716 አባላት አሉ። አባላቱ ጾታዊ ጥቃት እንዳይደርስ ማህበረሰቡን የማነቃቃት ሥራ ይሰራሉ። አመለካከቱም እንዲቀየር ያደርጋሉ። በአሁኑ ሰዓት ጥቃት እንዳይደርስ አስቀድሞ የመከላከል ሥራ እየሠሩ ይገኛሉ።
ምክትል ቢሮ ኃላፊዋ ወይዘሮ ሜሮን እንደተናገሩት ለእነዚህ በኮሚቴ ደረጃ ለተዋቀሩ የጾታዊ ጥቃት ተከላካይ ግብረ ኃይሎች በሕግ ጉዳዮች፣ በጾታዊ ጥቃት፣ በቅንጅታዊ አሠራር እንዲሁም በስርዓተ ጾታ ጉዳዮች ላይ በተለያዩ ጊዜያት ጥቃቱን መከላከል የሚችሉበት ስልጠና ተሰጥቷቸዋል።
‹‹በህልውና ዘመቻው ከስንቅ ዝግጅት ጀምሮ የተለያዩ ድጋፎችን እያደረጉ ከሚገኙት የህብረተሰብ ክፍሎች 55 በመቶ ያህሉ ሴቶች ናቸው›› ያሉት ወይዘሮ ሜሮን ከ16ቱ ቀናት የፀረ-ጾታዊ ጥቃት ዘመቻ ጋር ተያይዞም ለህልውና ዘመቻው የተለያየ ድጋፍ ሲደረግ መቆየቱን ነግረውናል።
እንደ ኃላፊዋ ገለፃ በተለያዩ አደረጃጀቶች ተዋቅረው ሴቶች አካባቢያቸውን ከፀረ-ሠላም ኃይሎች የሚጠብቁበትም ሂደት የዚሁ አካል ነው። በዚህም እንደ ከተማ አስተዳደሩ በሁሉም ወረዳዎች ሴቶች ለሠላም ዘብ እንዲቆም ማድረግ ተችሏል።
ከ70 ሺ በላይ ከከተማ አስተዳደሩ 11ዱም ክፍለ ከተማ የተውጣጡ ሴቶች በሠላም ዙርያ እንዲወያዩ ተደርጓል። በሴትነት ጾታቸው ካላቸው ድርብ ኃላፊነት በበለጠ አካባቢያቸውን ከማንኛውም በራሳቸውና በማህበረሰቡ ሕይወት፣ አካልና ንብረት ላይ ከሚሰነዘር ጥቃት ነቅተው እንዲጠብቁ የሚያስችል ነበር ውይይቱ። የአዲስ አበባ ሴቶች ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ በጦርነቱ ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ወገኖችና ለሠራዊቱ ከሴቶች ማህበር፣ ከአዲስ አበበ ብልፅግና ሴቶች ሊግ ጋር በጋራ በመሆን ለመከላከያ ሰራዊት ደም የመለገስ ተግባር ተከናውኗል። እንደ ምክትል ቢሮ ኃላፊዋ ወይዘሮ ሜሮን በደም ልገሣው ከ11ዱም ክፍለ ከተሞች የተውጣጡ 2008 ሴቶች ተሣታፊ ሆነውበታል።
ቢሮው በ125ቱ ወረዳ ላይ ያሉ ሴቶችን በማነቃነቅ ደም እንዲለግሱ በማድረግ፣ የሚዘምቱ ሴቶችን እንዲዘምቱ በማነሳሳት፣ እዚህ ያሉ ስንቅ እንዲያዘጋጁ በማድረግ፣ ሠራተኛው የወር ደሞዙን እንዲሰጥ በማበረታታት፣ ሴቶች በየብሎካቸው ወጥተው ሌሊትና ቀን እንዲጠብቁ በማድረግ ሲሠራ መቆየቱንና በዚሁ ዙርያ አሁን ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ እንደሚገኝ አውስተዋል።
ወይዘሮዋ እንዳከሉልን በቅርቡም ከሴት አደረጃጀቶች ጋር በመሆን በዓይነት የተሰበሰበ 12 ሚሊዮን ብር የሚገመት ገንዘብ ለመከላከያ ሠራዊት አስረክበዋል። ድጋፉ ለተፈናቀሉ ወገኖችም ጭምር የሚውል ነውም ብለውናል። ከዚህ በተጨማሪም እንደ ቢሮ በቅርቡ መንግስታዊ ተቋማትን በመቀስቀስና በማስተባበር ከስድስት ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ማድረጋቸውንም አብራርተውልናል።
ድጋፉም ሆነ አካባቢን ተደራጅቶ መጠበቁ ጦርነቱ አስኪጠናቀቅና ሠላምና ፀጥታ እስኪሰፍን ተጠናክሮ ይቀጥላል። ፀረ ጾታዊ ዘመቻውም የአንድ ወቅትና የአንድ ተቋም ሥራ ብቻ ባለመሆኑ ከዚሁ ከወቅታዊ የሀገራችን ሁኔታ ጋር ከሚሠራ ሥራ ጋር ተሰናስሎ ይከናወናል። በመሆኑም ምክትል ቢሮ ኃላፊዋ የመንግስት ሠራተኞች፣ አዛውንቶች፣ ወጣቶችና ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍሎች ከሴቶች ጋር በመቀናጀት ለሀገራቸው አንድ ሆነው እንዲቆሙና ይህችን ወቅት ኢትዮጵያን እንዲያሻግሩና የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ በማስተላለፍ የሰጡንንና በመድረኩም የተናገሩትን ሀሳብ ቋጭተዋል። በመድረኩ የተለያዩ የሥራ ኃላፊዎች የተገኙ ሲሆን ከፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮማንደር አፀደ እንደነገሩን ጥቃቱን ለመከላከል ከአዲስ አበባ ፖሊስ ጋር በመቀናጀት ነፃ የስልክ ጥሪ ቅበላ መስመር (Hoteline)(991) በይፋ ተጀምራል።
የመከላከል ሥራው በዚህና በአጭር መልዕክት ማስተላለፊያ 7200 መስመሮች እየተከናወነ እንደሚገኝም ተናግረዋል። ሆኖም ጾታዊ ጥቃትን የመከላከል ሥራው በጥቂት ተቋማት ብቻ ሳይሆን በሁሉም ተቋማትና ሕብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፎ ዓመቱን ሙሉ የሚሰራ ሥራ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል። ዓለም አቀፍ የፀረ-ጾታዊ ጥቃት ቀን (የነጭ ሪቫን) በየዓመቱ እንዲከበር የተወሰነው እ.ኤ.አ በ1981 አቦጎታ ኮሎምቢያ ውስጥ በተካሄደው በመጀመርያው የላቲን አሜሪካ ፌሚኒስቶች ጉባኤ ላይ ነበር።
እ.ኤ.አ ታህሳስ 6 ቀን 1989 ዓ.ም በካናዳ ሞንትሪያል ከተማ አንድ የ25 ዓመት ወጣት ኢኮል ፖሊ ቴክኒክ በተባለው ኮሌጅ ውስጥ ይማሩ የነበሩ 12 የኢንጂነሪንግ ሴት ተማሪዎች፣ አንድ የነርሲንግ ሴት ተማሪ እና አንድ ሴት የኮሌጁ ሴት ሰራተኛ በጠቅላላው 14 ሴቶችን በሚማሩበት ክፍል ውስጥ የግፍ ግድያ የተፈፀመበትን ዕለት ለማስታወስ በሚል በጥቂት ካናዳውያን ወንዶች እንደተጀመረም መረጃዎች ያሳያሉ።
ሠላማዊትውቤ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 5/2014