ለኢትዮጵያውያን ሀገራቸው የነፃነታቸው ምንጭ ናት። የሚኖሩት በእርሷ ተከብሮ መቆየት ውስጥ ነው። እርሷ ሰላሟን አጥታ ሕሊናቸው አይረጋጋም። ኢትዮጵያ ጎድሎባት እነርሱ አይሞላላቸውም። እርሷ ዝቅ ብላ እነርሱ አይገዝፉም። የሚኖራቸው ሀገራቸው ሲኖራት ነው። ያለ ኢትዮጵያ የሚበሉት አይጣፍጣቸውም።
የሚጠጡት አያረካቸውም። ኢትዮጵያዊያን መቼም ቢሆን ለሀገራቸው ያላቸው ፍቅርና አክብሮት የሚለወጥ አይደለም። ልባቸውን እንጂ ጀርባቸው ለኢትዮጵያ የሚሰጡም አይደሉም። እድገቷን እንጂ ዝቅታዋን፣ ደስታዋን እንጂ ሃዘኗን፣ ክብሯን እንጂ ውርደቷን ፈፅሞ አይመኙም።
ሀገር ውስጥ እንዳሉት ሁሉ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንም የእዚህ እሳቤ አንጸባራቂዎች ናቸው። ከምንም በላይ የሀገራቸውን ፍቅር በልባቸው ይዘው የሚኳትኑና በአካል ቢርቁም በመንፈስ ሁሌም ከኢትዮጵያ ጎን የሚገኙ ናቸው። አብዛኞቹ አገራቸውን የሚወዱ፣ አገራቸው ተሻሽላና አድጋ ማየት የሚፈልጉ እና አንድ ጠንካራ ኢትዮጵያ እንድትኖር ከልብ የሚመኙና ለእዚያም የሚታገሉ ናቸው።
ይህ ስሜታቸው በተለይ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ በግልፅ በአደባባይ የታየ ነው። በአሁን ወቅት በመላ ዓለም የሚገኙ ዲያስፖራዎች ‹‹ለእናት ሀገራችን ለኢትዮጵያ አናንስም፣ ባለን ሁሉ እንቆምላታለን›› ብለው ተነስተዋል። በኢትዮጵያ እየተካሄደ ባለው የህልውና ዘመቻም በተለያየ መልኩ እየተሳተፉ ይገኛሉ። በተለይ ኢትዮጵያ ላይ የተከፈቱ ወቅታዊ ሴራዎችን ለመቀልበስ ዓለም እውነቱን እንዲረዳ ድምጻቸውን በማሰማት ታላቅ ገድልን እየፈጸሙ ናቸው። ለእዚህ ህዝባዊ ተነሳሽነት ሰሞኑን በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚደረጉ ‹‹no more›› ወይም ‹‹በቃን›› በተሰኘው ከተማ አንቀጥቅጥ ሰላማዊ ሰልፎች በቂ ምስክሮች ናቸው። ከሰሞኑ ደግሞ ‹‹the great Ethiopian home coming›› በሚል ለመጪው በዓል ወደ አገር ቤት የመግባት ግዙፍ ንቅናቄን ተቀላቅለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድም በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ወደ ሀገር ቤት በመግባት በዓላቶችን እንዲያከብሩ ጥሪ አቅርበዋል። ጥሪውን ተከትሎ አንድ ሚሊየን ዲያስፖራዎች ወደ አገር ቤት ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል። የኢፌድሪ ቱሪዝም ሚኒስቴርም የቀረበውን ሀገራዊ ጥሪ ተቀብለው ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ አንድ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን እንግዶችን ለመቀበል ዝግጅት እያደረገ ይገኛል።
የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ ከቀናት በፊት በሰጡት መግለጫም ይህንኑ አረጋግጠዋል። እንግዶችን ለመቀበል በሚደረገው ዝግጅት ከቱሪዝም ዘርፍ ተዋናዮች ጋር ውይይት መደረጉን የተለያዩ ማበረታቻዎች መዘጋጀታቸወም ታውቋል።
የቱሪዝም ሚኒስቴር የመዳረሻ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ስለሺ ግርማም፣ የአየር ትኬት፣ የሆቴል መኝታ አገልግሎት፣ የመኪና ኪራይ፣ የቱር ኦፕሬተሮች ጥቅል ሽያጭ ዋጋና የቱሪስት ጋይድ ክፍያዎች በሙሉ 30 በመቶ ቅናሽ እንደተደረገባቸው ይፋ አድርገዋል። የኢትዮጵያ ዲያስፖራ የተግባር ምክር ቤትም የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ‹‹ወደ ሀገር ቤት እንግባ›› የጥሪ ግብዣ በመደገፍ ለተግባራዊነቱ አጋር ሆኖ ለመስራትና ማስተባበር ዝግጁ ስለመሆኑ ‹‹እወቁልኝ›› ብሏል።
አዲስ ዘመን ጋዜጣ የዲያስፖራው አገር ቤት መግባት ለአገሪቱ ወቅታዊ ፈተና ምን ምላሽ ይኖረዋል? ኢኮኖሚው ላይ የሚኖረው ትርጉምስ? የዲያስፖራውን አቅም ለመጠቀም ቀጣይ ተግባራትስ ምንድን ናቸው? የሚሉ ጥያቄዎችን በማንሳት የተለያዩ ምሁራንና አመራሮችን አነጋግረናል።
በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን ከሰጡን የምጣኔ ሃብት ምሁራን መካከል በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር ዶክተር ሞላ አለማየሁ አንዱ ናቸው። ዶክተር ሞላ፣ የዲያስፖራው ማህበረሰብ ለሀገሩ ማበርከት የሚችለው የገንዘብም ሆነ የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር እጅጉን ከፍተኛ ስለመሆኑ ያስረዳሉ። አንዳንድ ሀገራትም ከወጭ ንግድ ከሚያገኙት ገቢ ባልተናነሰ መልኩ ከዲያስፖራው እንደሚያገኙም ያነሳሉ። ለአብነት ቻይና በትንሹ እስከ 20 ቢሊየን ዶላር ከዲያስፖራው ማኅበረሰብ እንደምታገኝ ይጠቅሳሉ። ‹‹ኢትዮጵያ በአንጻሩ ባላት ልክ የዲያስፖራዎችን አቅም ተጠቅማበታለች ማለት እጅግ አስቸጋሪ ነው›› የሚሉት ዶክተር ሞላ፤ ችግሩ ዲያስፖራውን በአንድነት አስተባብሮ በሀገሩ ጉዳይ እንዲተባበር በማድረግ ረገድ በቂ የሆነ ሥራ መስራት ያለመቻል ስለመሆኑ ያስገነዝባሉ።
በአሁን ወቅት የዲያስፖራው ወደ ሀገር ቤት መግባት ፋይዳው ዘርፈ ብዙ ስለመሆኑ የሚያስረዱት ዶክተሩ፣ በተለይም ምዕራባውያኑ ከተለያየ አቅጣጫ በተቀነባበረ መልኩ የሃሰት ዘገባን በማራገብ ዓለም ኢትዮጵያን በተሳሳተ መንገድ እንዲገነዘብ የማስጨነቅ፣ የመክሰስ፣ የመወንጀል ዘመቻን በተያያዙበት በዚህ ወቅት መሆኑ ትርጉምን የላቀ እንደሚያደርገው ያሰምሩበታል።
‹‹ከሁሉ በላይ በገፅታ ግንባታ ኢትዮጵያ እንደሚባለው እንዳልሆነች ግልጽ መልእክት ያስተላልፋልም›› ይላሉ። ይህን እሳቤ የሚያጠናክሩት የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊም፣ የጸጥታ ችግር በሌለባት አዲስ አበባ ተቀምጠው ዜጎቻቸው እንዲወጡ የሚወተውቱ ሀገራትና ተቋማት እንዲሁም ውሸትን የሚያናፍሱ መገናኛ ብዙኃን ግልጽ አላማቸውን ዓለም እንዲረዳ ለማድረግ እጅግ ወሳኝ ስለመሆኑ ይገልፃሉ።
ከዚህም ባለፈ ዲያስፖራው የአገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታ ተገንዝቦ በሚሄድበት አገር ሁሉ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆኖ የቱሪስት መስህቦችንና መዳረሻ ቦታዎችን ለማስተዋወቅ እንደሚያግዝ ያክላሉ። የምጣኔ ሃብት ምሁራኑ እንደሚያስረዱት ከሆነም፣ ዲያስፖራው ወደ አገር ውስጥ መግባት የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በተለይ የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን ለማሳደግና ለማዘመን የራሱን ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል። በተለይም በጦርነቱ የወደሙትን የቱሪስት መዳረሻዎችን መልሶ ለመገንባት በቱሪስት ፍሰት ገቢ ያገኝ የነበረውን ዜጋ ለማገዝና በጦርነቱ ምክንያት የተመሰቃቀለው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እንዲያገግም ለማድረግ አስተዋፅኦ የጎላ ነው።
‹‹የዲያስፖራው መግባት በኢኮኖሚ ረገድም በተለይ ለአገልግሎት ዘርፉና ለተዋናዮቹ ከፍተኛ እድል ይፈጠራል›› የሚሉት ዶክተር ሞላ አለማየሁም፤ የእንግዶቹ ቆይታ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ሰላማዊ ሁኔታ ለቱሪዝም እንቅስቃሴ ያለውን ምቹነት ለማሳየት እንደሚያስችል ያሰምሩበታል።
በጉዳዩ ላይ አስተያየት ካጋሩን ምሁራን መካከል ሌላኛው በዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር ረዳት ፕሮፌሰር ደምመላሽ ሃብቴ፤ በአሁን ወቅት ኢትዮጵያን ከወቅታዊ ችግሮቿ ለማላቀቅ ከሀገር ውስጥ ባሻገር በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም የኢትዮጵያ ወዳጆች እጅግ አስደናቂ ድጋፍና ደጀንነታቸውን እያሳዩ እንደሚገኙ ይመሰክራሉ።
የእነዚህ የአገር ልጆች ወደ ሀገር ቤት መግባትም ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አለው፤ በተለይ ለቱሪዝም ዘርፉ ትንሳኤ ፋይዳው የጎላ ነው ይላሉ። የአገልግሎት ዘርፉን ከገባበት ድብርት በማነቃቃት በአንድ ደረጃ ከፍ እንደሚያደርገውና ሀገሪቱ በአሁን ወቅት ያለባትን የውጭ ምንዛሬ እጥረት በማቃለል ረገድ አስተዋጾው ቀላል የሚባል እንዳልሆነም አፅእኖት ይሰጡታል።
‹‹በተለይም ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም የኢትዮጵያ ወዳጆች ወደ ሀገር ቤት ይዘውት የሚመጡትን ገንዘብ በሕጋዊ መንገድ የሚለውጡት ከሆነ የሀገሪቱን ትልቅ የውጭ ምንዛሬ ሸክም ለጊዜውም ቢሆን ሊያቃልል ይችላል››ይላሉ። ወደ ሀገር ቤት ከሚገባው ዲያስፖራው ተጠቃሚ ለመሆን እነሱን ማስተናገድ የሚያስችል አቅም መገንባት እንደሚያስፈልግም ይታመናል።
አንድ ሚሊየን የሚሆን ዲያስፖራ ወደ ሀገር ከመጠራት ባሻገር እነርሱን ማስተናገድ የሚያስችል አቅም ስለመኖሩም ታሳቢ ማድረግ የግድ እንደሚል አፅእኖት የሚሰጡት ዶክተር ሞላም፣ ከትራንስፖርት እስከ ሆቴል እንዲሁም ሌሎችም አገልግሎቶች እንግዶችን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ማደራጀት የግድ እንደሚል ሳያስገነዝቡ አላለፉም። ፍላጎትና አቅርቦት በማመጣጠን ረገድ ዘርፈ ብዙ ተግባራት ማከናወንና ሌላውን ህዝብ በማያውክ መልኩ ልዩ የሆነ መስተንግዶ ማቅረብ የሚቻልባቸውም አማራጮችን ታሳቢ ማድረግ እንደሚያስፈልግም ነው ያመላከቱት።
ዲያስፖራዎቹ በኢትዮጵያ የሚኖራቸውን ቆይታ ያማረ እንዲሆን አገልግሎት ሰጪና አቅራቢዎች ሚና ከፍተኛ ስለመሆኑ የሚያመለክቱት ዶክተር ሞላ አለማየሁ በበኩላቸው፤ ምክንያታዊ ባልሆነ መልኩ ያልተገባ ጥቅም ፍለጋ እና ደረጃውን ያልጠበቀ አገልግሎት የእንግዶችን ቆይታ ከማሳጠር ባለፈ በቀጣይም ወደ ሀገራቸው እንዳይመጡ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ታሳቢ ማድረግ እንደሚያስፈልግም ሳያስገነዝቡ አላለፉም። አንዳንዶችም አስፈላጊ ጥንቃቄ ማድረግ ካልተቻለ የዲያስፖራዎቹ መምጣት በተለይ ወቅታዊውን የዋጋ ግሽበት ከፍ ሊያደርገው ይችላል የሚል ስጋቶችን ያስቀምጣሉ። በዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር ረዳት ፕሮፌሰር ደምመላሽ ሃብቴ፣ በአንፃሩ ይህን ስጋት አይቀበሉትም።
ተጽእኖ አይኖረውም ለማለት ባይደፍሩም ወደ ሀገራቸው መምጣታቸው ከሚያስከትለው ጉዳት ይልቅ ጥቅሙ የገዘፈ ስለመሆኑም አፅእኖት ይሰጡታል። በዚህ አይነት ተሳትፎ ውጤት የሚጠበቀውም ሆነ የሚለካው በአጭር ጊዜ ድምር አለመሆኑን የሚያስገነዝቡት ረዳት ፕሮፌሰሩ፤ ‹‹የአሁኑ ጅማሮ ለቀጣዩ ትልም ትልቅ መሰረት የሚጥል ነው፤ ይሁንና የአንድ ጀንበር ስራ መሆን የለበትም››ይላሉ።
ከዲያስፖራው ጋር የሚኖር ጤናማ ግንኙነት ማስቀጠል ከተቻለ ዘርፈ ብዙ ትሩፋቶችን መቋደስ እንደሚቻልና በተለይም የቱሪዝም ዘርፉ ለማጎልበት ከፍተኛ አቅም እንደሚፈጥር የሚያስገነዝቡት ረዳት ፕሮፌሰር ደምመላሽ፤ በእውቀትና ሃብት ድጋፍና ኢንቨስትመንት ተሳትፎም በተለይ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት የሆነው የግብርና ዘርፍ ከዘመናዊ ቴክኖሎጂ ጋር በማዛመድ ረገድ ዲያስፖራው ትልቅ አቅም ሊሆን እንደሚችልም ነው ያመላከቱት። ዶክተር ሞላ መንግሥት ከአንድ ሰሞን ባለፈ በውጭ ሀገራት ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም የኢትዮጵያ ወዳጆች ጋር ወዳጅነቱን አጠናክሮ መቀጠልና አቅምና አቅማቸውን አስተባባሮ ወደ ፊት መራመድ የሚችል ከሆነም የሀገሪቱ ችግር በጥቂት ጊዜያት ውስጥ የማይቃለልበት ምንም አይነት ችግር እንደሌለም ሳያስገነዝቡ አላለፉም።
በተለይ በጉብኝት ብቻ ሳይሆን ለተለያዩ ኢንቨስትመንት ዘርፎች ለመሰማራት ወደ ሀገራቸው እንዲመጡ ማድረግ ላይ ተግቶ መስራትና ለዚህም ምቹ ከባቢን መፍጠር ከተቻለ ውጤቱ አመርቂ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም ብለዋል። የረዳት ፕሮፌሰሩን እሳቤ ዶክተር ሞላም ይጋሩታል። ከዚህ ቀደም ዲያስፖራውን በሀገሩ ለማሳተፍ የፖለቲካ ተቃዋሚና ደጋፊ የሚል ልየታ እንደነበር የሚያስታውሱት ዶክተር ሞላ፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርም ሆነ ኤምባሲዎች ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሀገሩን ለመጥቀም እስከፈለገ በእኩል ዓይን ተመልክተው አቅሙን መጠቀም እንዳለባቸውም ነው አፅእኖት የሰጡት። ዶክተር ሞላ እንደሚገልፁት፤ መንግሥት የዲያስፖራውን አቅም ለመጠቀም ራሱን የቻለ ልዩ አሠራር መዘርጋት እንዲሁም ማሻሻያ ማድረግ አለበት።
ሀገራቸውን በማልማት ረገድ ተሳታፏቸውን ለማጎልበት የተለያዩ ማበረታቻዎችን ተግባራዊ ማድረግ ይኖርበታል። አገልግሎቶችን ጥራታቸውን የጠበቁና ቀልጣፋ ማድረግም መዘንጋት የለበትም። በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በኩል የተደራጀውን የዲያስፖራ ዳይሬክቶሬት ይበልጥ ማጠናከር ያስፈልጋል። ከሁሉም በላይ ዲያስፖራው ምን ይፈልጋል? አቅሙ ምን ያህል ነው? አገሪቱስ ለዲያስፖራዎች ምን አዘግጅታለች? የሚለውን አስቀድሞ ማጥናትና አደራጅቶ ማቅረብ ይጠይቃል።
ኤምባሲዎችም ከቀድሞው በተለይ ዲያስፖራው ቀርበው መስራት የግድ ይላቸዋል። መንግሥት በተለይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና በሥራ የሚገኙ ኤምባሲዎችም የዲያስፖራውን ማኅበረሰብ በማሳተፍ ሂደት ቁጭ ብለው በራሳቸው እስኪመጣ ከመጠበቅ አባዜ መላቀቅ እንዳለባቸው የሚያስገነዝቡት ዶክተር ሞላ አለማየሁ፤ ከዚህ ይልቅ ከቀድሞው በተለይ ዲያስፖራው ጋር ይበልጥ ቀርበው መስራት የግድ እንደሚላቸውም ነው ያሰመሩበት።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲም፣ መንግሥት የተለያየ አመለካከት ያላቸው የዲያስፖራው ማኅበረሰብ አባላት በአገራቸው ጉዳይ ላይ ተገቢውን ተሳትፎ እንዲያደርጉ በቅርበት ለመሥራት ማቀዱን እወቁት ብለዋል።
ሀገሪቱ የገጠማትን ፈታኝ ሁኔታ በማስገንዘብ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ያለምንም የፖለቲካ አመለካከት ልዩነት እልህ አስጨራሽ ተጋድሎ እያደረጉ ስለመሆኑ ያመላከቱት አምባሳደሩ፤ የውጭ ጣልቃ ገብነትን ከመመከትና በሌሎች ዘርፎች የዘንድሮው የኢትዮጵያ ዳያስፖራ እንቅስቃሴም የሚደነቅ ነው ሲሉ ገልጸውታል። በቀጣይም ዲያስፖራው ማኅበረሰብ በሀገሩ ጉዳይ ላይ ሁሉም እኩል ተሳትፎ እንዲያደርግ በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውን ነው ያስረዱት።
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 5/2014