ኮሚካል አሊን እያስናቀ ያለው ጌታቸው ረዳ ሰሞኑን በተከታታይ እየደረሰባቸው ያለውን ሽንፈት ለማስተባበል የሚችለውን ያህል ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡ ከአፋር እና አማራ ክልል ተጠራርጎ የወጣበትን ሂደት ለመሸፈን እና የደጋፊዎቻቸውን ሞራል ሳይሰበር ለማቆየት ጥረት በማድረግ ላይ ነው፡፡ የጁንታው ሰራዊት ከሁለቱ ክልሎች በኢትዮጵያ ሃይሎች ጥምረት ተደቁሶ ቢወጣም ጌታቸው ግን በእቅዳችን መሰረት ነው የወጣነው ብሏል፡፡
ይህን ንግግሩን ስንሰማ በመጨረሻ ጌታቸው ረዳ ራሱ የተካነበት ውሸት እየጠፋበት እንደሆነ ተረድተን ከመሳቅ ውጭ ሌላ ምንም አማራጭ አላገኘንም፡፡ በእውነቱ ግን ሕወሓት በእቅዱ መሰረት እየተጓዘ ነውን? እንደዛ ለማለት እስከዛሬ እቅዳችን ነው ሲሉ የነበሩትን ማየትና በነዚያ እቅዶች ላይ ያላቸውን አፈጻጸም ገምግመን መወሰን የተሻለ ነው፡፡ እንግዲህ እነ ጌታቸው እና ደብረጽዮን ሲነግሩን እንደከረሙት አፋር እና አማራ ክልልን የወረሩት ተደረገብን የሚሉትን “ከበባ” ለመስበር ነው፡፡ በዚህም መሰረት ከበባውን ለመስበር በምእራብ በኩል የሱዳንን ኮሪደር በምስራቅ የጅቡቲን ኮሪደር ለማስከፈት ነበር እቅዳቸው፡፡ ነገር ግን በምእራቡ በኩል ለበርካታ ጊዜያት ደጋግመው ሞክረው አልተሳካላቸውም፡፡ በምስራቁ በኩልም ሚሌ ላይ ደርሰው የኢትዮጵያን የመግቢያ እና የመውጫ በር ለመያዝ ያደረጉት ሙከራ በጀግናው መከላከያ ሰራዊት እና በተአምረኛው የአፋር ሕዝብ ከባድ ቡጢ ደርሶባቸው እቅዳቸው ከሽፏል፡፡ ስለዚህም አለ የሚሉትን ከበባ የመስበር እቅዳቸው ሙሉ ለሙሉ ብላሽ ሆኗል፡፡ ሁለተኛው እቅዳቸው መንግሥትን በግድ ለድርድር እንዲቀመጥ ማድረግ ነው፡፡ ለዚህም ሲባል የአማራ እና የአፋር ክልሎችን በመቆጣጠር መንግሥትን ጫና ውስጥ ለመክተት ሞክረዋል፡፡
ነገር ግን ይሄም እቅድ አልተሳካም። በተቃራኒው መንግሥትን ወደ ድርድር ከመሳብ ይልቅ የኢትዮጵያን ሥዝብ ሆ ብሎ በራሳቸው ላይ ለዘመቻ እንዲነሳ ማድረግ ብቻ ነው የቻሉት፡፡ ስለዚህም ይህ እቅዳቸውም ከሽፏል፡፡ እርግጥ ሕወሓቶች ድርድር ይፈልጉ ነበር ወይ የሚለው አጠራጣሪ ነው፡፡ ምክንያቱም የድርድር ሃሳብን የሚያነሱት ሽንፈት የበረታባቸው ሰሞን ብቻ ነው፡፡ እነ ጻድቃን ገብረትንሳይ የሚነዱት ሽፍታ ወደ አዲስ አበባ የቀረበ የመሰላቸው ሰሞን ስለ ድርድር በጋዜጠኞች ሲጠየቁ “የምን ድርድር ነው ፤ ጦርነቱ አልቋል እኮ” ብለው ሲፎክሩ ነበር፡፡
እነ ደብረጽዮንም መንግሥት ያቀረበልንን የድርድር ጥያቄ ውድቅ አድርገናል እያሉ ሲኮፈሱ ነበር፤ ደፋሮች እኮ ናቸው፤ ደብረጽዮን እጅ ስጡ ጦርነቱ አብቅቷል ሲልም ነበር፡፡ በሌላ ጎን ደግሞ የምንዋጋው መንግሥት ሁሉንም ሰላማዊ የድርድር መንገዶች ስለደፈነብን ነው ሲሉም ተሰምተዋል፡፡ የሆነ ሆኖ በዚህ ጦርነት የሕወሓት እና የነሱ ነጂዎች (እነሱ መኪናም ይሁኑ ከብት፤ ያው የሚነዳው መኪና ወይም ከብት አይደል፤ የሚያስብ ፍጡር ይህን ሁሉ ግፍ በገዛ ወገኑ ላይ አይፈጽምም፤ እንስሳ ካልሆነ በቀር) እቅዳቸው የነበረው መንግሥት እጁን ጠምዝዞ ወደ ድርድር ጠረጴዛው ማምጣት ቢሆንም ይህም እቅድ አልተሳካም፡፡
ሌላኛው እቅዳቸው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን መንግሥት ከሥልጣን አስወግዶ ዳግም ወደ ሥልጣን መመለስ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ አዲስ አበባ መግባት አማራጭ የለውም፡፡ እሱስ እንዴት ሆነላቸው? እሱም ቢሆን አልተሳካም፡፡ ጊዜው 1983 አይደለምና አሁን ደጀን ሆኖ መንገድ እየመራ እና ስንቅ እያቀበለ ወደ አዲስ አበባ የሚመራ ሰው አልተገኘም፡፡ በየቦታው ከአማራ እና ከአፋር ሕዝብ ጠንካራ ፍልሚያ ጠበቃቸው፡፡ መከላከያው ደግሞ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ባደረገው አስደናቂ መልሶ ማጥቃት እንኳን አዲስ አበባ መግባት ወደ መቀሌ መመለስም ቀላል እንዳልሆነ አውቀዋል፡፡ በነዚህ ዘመቻዎች ስፍር ቁጥር የሌላቸው የሽፍታው ተዋጊዎችም ሟች እና ቁስለኛ ሆነዋል፡፡ አዲስ አበባ ያለው ህዝብ ጁንታውን ለመውጋት ወደ
ግንባር ሲተም ሲያዩ ደግሞ ጋላቢዎቻቸው ይሄ አዲስ አበባ የመግባት እቅድ ቢቀርብን ብለዋቸዋል፡፡ በዚህም የተነሳ አዲስ አበባ ገብቶ ሥልጣን የመቆጣጠር እቅዳቸውም ከሽፏል፡፡ ሌላኛው እቅድ ራሳቸው ተመልሰው ሥልጣን እንደማይቆጣጠሩ ሲያውቁ ቢጤዎቻቸውን ጸረ ኢትዮጵያ ሃይሎች ሰብስበው የሽግግር መንግሥት የሚል ድራማ መጀመር ነበር፡፡
የሽግግር መንግሥቱ እቅድ ገና ሳይጀመር ነበር የከሸፈው፡፡ የሽግግር መንግሥት ነን ብለው ሕወሓት የሰበሰባቸው የኡበር ሹፌሮቹ ማሕበር ማሳካት የቻለው ትልቁ ስኬት የኢትዮጵያን ሕዝብ ሆዱን ይዞ ፍርፍር ብሎ እንዲስቅ ማድረጉ ነበር፡፡ እነ ልደቱ አያሌው እና ሀብታሙ አያሌውም ቢሆኑ በውልብልብ ምላሳቸው የሽግግር መንግሥቱን አጀንዳ ወደ ኢትዮጵያውያን ሊያሰርጉ ቢሞክሩም አልተሳካላቸውም፡፡
በስውር ሲዶለት የነበረው የእነ ኤፍሬም ይስሀቅ እና እሌኒ ገብረመድህን እቅድም ሳያስቡት ሾልኮ ወጥቶ የውርደት ካባን አከናንቧቸዋል፡፡ በአጭሩ የሽግግር መንግሥቱ እቅድም ከሽፏል፡፡ ታዲያ ከሕወሓት እቅድ የተሳካው የቱ ነው፡፡ አንድ እቅድ ተሳክቶላቸዋል፡፡ እሱም የአማራ ሕዝብን የመበቀል እቅዳቸው ነው፡፡
እሱ እቅድ እድሜ ሰብዓዊነት ለተለያቸው ሽፍታዎቻቸው እና እድሜ ለውስጥ ባንዳዎች በከፊልም ቢሆን ተሳክቶላቸዋል፡፡ እሱም ቢሆን ከእቅዳቸው አንጻር ያሰቡትን ያህል አልተሳካም፡፡ ቢሆንላቸው ምኞታቸው አማራ የሚባልን ክልል መደምሰስ እና ሕዝቡን ከምደረ ገጽ ማጥፋት ነበር። በዚያ ደረጃ ላይ መድረስ አልተሳካላቸውም፡፡
ሌላኛው እቅዳቸው ኢትዮጵያን የማፍረስ ነበር፡፡ ይህ እቅድ ከዋና ጋላቢዎቻቸው ጋር ሆነው ያቀዱት ነበር፤ ግን ከታሰበው በተቃራኒው ሆኗል፡፡
ጭራሽ የኢትዮጵያን አንድነት አጠናክሯል፡፡ ከዚህ ይልቅ የሕወሓት እቅድ ለኢትዮጵያ አዳዲስ እድሎችን ፈጥሯል፡፡
ልብ አርጉ በሕወሓት እቅድ ባይሆን ኖሮ ይህን አንድነት ከየት እናመጣው ነበር? ሕወሓት በእቅዱ መሰረት አማራ እና አፋር ክልልን ባይወር ኖሮ ምን ያህል አረመኔ እንደሆኑ በምን እንገነዘብ ነበር ? ሕወሓት በእቅዱ መሰረት ወደ ሚሌ ባይገሰግስ ኖሮ የአፋርን ሕዝብ ጀግንነት እንዴት እናስተውል ነበር ? ሕወሓት ወደ አዲስ አበባ ባይቀርብ ኖሮ እንዴት ያደፈጡትን የውስጥ ባንዳዎች መለየት እንችል ነበር ? ሕወሓት ጦርነቱን ባያረዝመው ኖሮ እንዴት ይህን ሁሉ አርበኛ እናገኝ ነበር? ሕወሓት በእቅዱ መሰረት እብደቱን ባይጀምር ኖሮ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊትን ተአምራዊ ጀግንነት እንዴት እንመሰክር ነበር? የሕወሓት እቅድማ ለኛ ብዙ ነገር አሳይቶናል ! ሙአዘ ጥበባት ዳንኤል ክብረት እንዳለው፤ ሕወሓት የራሱን እቅድ ከመፈጸም ይልቅ የእኛን አቅማችንን አሳይቶናል፡፡ ዲ/ን ዳንኤል እንዲህ ይላል “ኢትዮጵያ አቅሟ ያልተነካ ብቻ ሳትሆን አቅሟ ያልታወቀ አገር ናት፡፡ በተሟላ መልኩ ምን እንዳላት የሚያውቀው ፈጣሪዋ ብቻ ይመስለኛል፡፡
ያ ሁሉ ዘማች ከየት መጣ? ያ ሁሉ ባለ ሀብት ከየት መጣ? ያ ሁሉ የኪነ ጥበብ ሰው ከየት መጣ? ሚሊዮኖች ሆነው ስንቅ የሚያዘጋጁት ከየት ተገኙ? ያ ሁሉ ምድርን ቁና የሚያደርግ ዲያስፖራ የት ነበር? እነዚያ ሁሉ በፈረንጅ አደባባይ የሚሞግቱልን የውጭ ወዳጆች ከየት ተገኙ? ያ ሁሉ በግና ፍየል፣ ያ ሁሉ በሬ፣ ያ ሁሉ እህልና ፍራፍሬ ከየት ተገኘ? ሚሊዮኖችን ከመቀነታቸው ፈትተው የሚያዋጡ የቁርጥ ቀን ልጆች ከየት ብቅ አሉ? ኢትዮጵያ ለካ ባለ ጸጋ አገር ናት፡፡” እንዲያው በአጭሩ ስንጠቀልለው የሕወሓት እብደት ለኛ ያለ እቅዳችን ብዙ ለዓመታት የተመኘናቸውን ነገሮች እንድናገኝ አድርጎናል፡፡ በተቃራኒው ሕወሃት እቅዶቹ በሙሉ አፈር ድሜ እየበሉበት ነው፡፡
በርካታ ምሳሌዎችንም ቀደም ብለን አይተናል፡፡ ለዚህም ነው ጌታቸው ረዳ በእቅዳችን መሰረት ወደኋላ እያፈገፈግን ነው ሲለን የማናምነው፡፡ እስካሁን ከእቅዳቸው ያሳኩት የለም፤ ወደፊትም አያሳኩም፡፡ አሁንም በእቅዳቸው መሰረት ሳይሆን በኢትዮጵያ ሃይሎች ሕብረት ተሸንፈው ወደ ተንቤን ዋሻ እየሸሹ ነው፡፡
አቤል ገ/ኪዳን
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 4/2014