በመዲናዋ ከአንድ ሺህ 300 በላይ አዳዲስ የኢንቨስትመንት ፈቃድ ተሰጠ

አዲስ አበባ፡- የአዲስ አበባ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን በ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት አንድ ሺህ 303 አዳዲስ የኢንቨስትመንት ፈቃድ መስጠቱን አስታወቀ።

የኮሚሽኑ የእቅድና በጀት ዝግጅት ክትትል ግምገማ ዳይሬክተር ወይዘሮ እናትነሽ ታመነ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በግማሽ ዓመቱ ለአንድ ሺህ 500 ባለሀብቶች አዲስ ኢንቨስትመንት ፈቃድ ለመስጠት ታቅዶ አንድ ሺህ 303 አዳዲስ የኢንቨስትመንት ፈቃድ ተሰጥቷል። አፈፃፀሙም የእቅዱን 86 ነጥብ 9 በመቶ ይሸፍናል ብለዋል።

በተጨማሪም ለ120 ባለሀብቶች ማስፋፊያ ኢንቨስትመንት ፈቃድ ለመስጠት ታቅዶ ለ151 ባለሀብቶች መስጠት መቻሉን የጠቆሙት ዳይሬክተሯ፤ ለ220 ባለሀብቶች ለውጥ ወይም ማሻሻያ የኢንቨስትመንት ፈቃድ ለመስጠት ታቅዶ፣ ለ191 ባለሀብቶች ፈቃዱን መስጠት መቻሉን ገልጸዋል።

ለ900 ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ዕድሳት ለመስጠት ታቅዶ፤ ለአንድ ሺህ ስምንት ባለሀብቶች እድሳት መፈጸም መቻሉን ገልጸው፤ ከኢንቨስትመንት ፈቃድና ፈቃድ ነክ አገልግሎት እና ከተለያዩ የድጋፍና ጨረታ ከ12 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን ዳይሬክተሯ ጠቅሰዋል።

በግማሽ ዓመቱ 243 ፕሮጀክቶችን ከቅድመ ትግበራ ወደ ትግበራ ለማሸጋገር ታቅዶ 248 ፕሮጀክቶችን ወደ ትግበራ ማሸጋገር መቻሉንም አመልክተው፤ 77 ፕሮጀክቶች ወደ ማምረት ወይም አገልግሎት መሸጋገራቸውን ነው የገለጹት።

በግማሽ ዓመቱ ሦስት ነጥብ 96 ቢሊዮን ብር ሥራ ላይ ለማዋል ታቅዶ አራት ነጥብ 68 ቢሊዮን ብር ሥራ ላይ ውሏል። ይህም የዕቅዱን 118 በመቶ ይሸፍናል ብለዋል፡

እንደ ዳይሬክተሯ ገለጻ፤ ለተገልጋይ ፈጣን እና ቀልጣፋ በሆነ መንገድ አገልግሎት እንዲያገኝ ከሥራ ሰዓት በተጨማሪ በምሳ ሰዓት ጭምር አገልግሎት ሳይቆራረጥ መስጠት መቻሉን ጠቁመው፤ ለተገልጋይ የሃሳብ መስጫ እና ቅሬታ ማቅረቢያ በሞባይል ቴክኖሎጂ ባር ኮድ በማዘጋጀት በአዲስ መልክ መሥራት በጥንካሬነት ተጠቅሰዋል።

የኢንቨስትመንት ማበረታቻ የወሰዱ ባለሀብቶች ለክትትል ሥራ የማይሠራ ወይም የተሳሳተ ስልክ መስጠት፣ አድራሻ ለውጥ ማድረግ እንዲሁም መረጃ ለመስጠት ፍቃደኛ አለመሆን፣ በፌዴራል ደረጃ በወጡ መመሪያ እና ደንቦች ላይ አሻሚ የሆኑ ግልፀኝነት የሌላቸው ያልተካተቱ ሥራዎች መኖራቸው የሚሉ ጉዳዮች በስድስት ወራት ያጋጠሙ ተግዳሮቶች መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ከጉምሩክ ኮሚሽን ጋር በመቀናጀት በታክስ ከፋይነት መለያ አድራሻ ለማግኘት በጋራ መሥራት፣ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመወያየት የአሠራር ማኑዋል ማሻሻያ እንዲሠራ ማድረግ በኮሚሽኑ የተወሰዱ የመፍትሔ ርምጃዎች መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ፋንታነሽ ክንዴ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ታኅሣሥ 30 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You