ዜና ትንታኔ
በተለያዩ ምክንያቶች አብዛኛው የሀገር ውስጥ ሸማች ምርጫው ከሀገር ውስጥ ምርቶች ይልቅ ከውጭ በሚገቡት ላይ ነው። ይህ እውነታ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ተጨባጭ ችግር እንዳለው የዘርፉ ምሁራን ይስማሙበታል። መንግሥትም ችግሩን በመረዳት የሀገር ውስጥ ምርቶችን በጥራት እና በአይነት በስፋት ለማምረት የሚያስችል ፖሊሲና ስትራቴጂ ቀርጾ እየተንቀሳቀሰ ነው።
የሀገር ውስጥ ምርቶችን መጠቀም ለሀገራዊ እድገት የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ምንድ ነው? የሀገር ውስጥ ምርቶች በጥራትና በብዛት እንዲጨምሩስ ምን መሠራት አለበት? ለሚሉ ጥያቄዎች የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች የሚሉት አሏቸው። አበራ ባይሳሳሁ (ዶ/ር) ፣ በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በአካውንቲንግ እና ፋይናንስ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ናቸው። እሳቸው እንደሚሉት፤ የአንድ ሀገር የኢኮኖሚ እድገት ትክክለኛነት ከሚመዘንባቸው መስፈርቶች መካከል ቀዳሚው በሀገር ውስጥ ምርት የራስን ፍላጎት መሸፈን መቻል ነው።
ከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ እየወጣባቸው ወደ ሀገር ቤት የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካት መቻል ዘላቂና አስተማማኝ እድገትን ለማረጋገጥ ወሳኝ ነው። በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከሰት የውጪ ምንዛሬ ንረትን ተከትሎ የሚመጣን የዋጋ ግሽበትን ለመከላከልም ያስችላል ።
በሌላ በኩል የሀገር ውስጥ ምርት እያደገ መምጣት የውስጥ ፍላጎትን ከመሸፈን ባለፈ በሚፈጠረው ውድድር ጥራት ያለው ምርት ለማምረት በር እንደሚከፍት የሚናገሩት አበራ (ዶ/ር)፤ጥራት ያለውና በዓለም አቀፍ ገበያ ተቀባይነት የሚኖረው ምርት ማምረት መቻል የውጪ ምንዛሬ ከማስቀረት በዘለለ፤ የውጪ ምንዛሬ ገቢ ለማስገኘትም የሚጠቅም ይሆናል።
ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ እድገትን ለማረጋገጥ የሀገር ውስጥ አምራችን ማብቃት የግድ ነው የሚሉት ዶክተር አበራ፤ የሀገር ውስጥ አምራችን በማብቃት ምርትን ለማሳደግ በፋይናንስ አቅርቦት ረገድ ያለውን ክፍተት መቅረፍ ያስፈልጋል፤ ለዚህም አንዱ አማራጭ የአክሲዮን ገበያን ማስፋት እንደሆነ ይናገራሉ። አምራች ድርጅቶች በቂ ፋይናንስ ሲያገኙ የሀገር ውስጥ ምርትም በዚያው ልክ የሚያድግበት እድል የሚፈጠር ይሆናል።
ከውጪ የሚመጡ ባለሀብቶችም በሀገር ውስጥ ማምረት ሲጀምሩ ምርታቸውን ለሀገር ውስጥ ፍጆታ ያቀርባሉ፤ይህም በውጪ ምንዛሬ የሚገቡ ምርቶችን በማስቀረት የውጪ ምንዛሬን ማዳን ይቻላል። በሌላ በኩልም ደረጃውን የጠበቀ ምርት በማምረት ወደ ውጪ በመላክ የውጪ ምንዛሬ ግኝትን ማሳደግ ይቻላልም ባይ ናቸው።
የውጪ ምንዛሬ መጨመር በራሱ በሀገር ውስጥ የማይመረቱ ጥቂት ምርቶችን ብቻ ከውጪ ለማስገባትና አዳዲስ ኩባንያዎችን በመመስረት በጊዜ ሂደት አብዛኛውን የሀገር ውስጥ ፍጆታ በሀገር ውስጥ ምርት ለመሸፈን የሚያስችል እንደሚሆን ይገልጻሉ።
በአንድ ሀገር ውስጥ የሚኖር ዜጋ በአብዛኛው የሚጠቀመው ምርት የውጪ ከሆነ ምርቱ ለሚመረትባቸው ሀገራት ዜጎች የሥራ እድል ይፈጠራል ማለት ነው የሚሉት ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት ዶክተር አጥላው አለሙ ናቸው ።
እንደ እሳቸው ማብራሪያ፤ እንደ ሀገር በሚቀረጹ ፖሊሲዎች የሥራ እድል መፈጠር ዋነኛውን ስፍራ ይይዛል። እንደ ኢትዮጵያ በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠር ሥራ የሚፈልግ ወጣት ላለበት ሀገር ደግሞ የሥራ እድል ፈጠራ ወሳኝ ጉዳይ እንደሆነ ይናገራሉ።
ለዜጎች የሥራ እድል በመፍጠር ሂደት ውስጥም፤ የሀገር ውስጥ ምርትን በጥራት እና በአይነት በስፋት ማምረት የሚያስችል ሁኔታዎችን ማመቻቸት ያስፈልጋል። ከውጪ ምርትን ማስገባት የውጪ ምንዛሬ ከመፈለጉ ባለፈ በጣም በጥቂት ነጋዴዎች ብቻ የሚከናወን በመሆኑ በቂ የሥራ እድል የመፍጠር አቅም የለውም ።
በግልባጩ የሀገር ውስጥ ምርትን በስፋት ማምረትና መጠቀም ሲቻል ግን ለዜጎች የሥራ እድል ተፈጥሯል ማለት ነው። ይህ እየጨመረ ሲሄድ የሚፈጠረው የሥራ እድልም በዛው ልክ እየሰፋ ይሄዳል።
የሀገር ውስጥ ምርት መጠቀም ለሥራ እድል ፈጠራ ሁነኛ መንገድ ከመሆኑ ባለፈ የቴክኖሎጂ አቅምን ለማጎልበትም ትልቀ ፋይዳ ይኖረዋል። እንደ ጨርቃ ጨርቅ ጫማ እና በትንንሹ የሚታሸጉ የምግብ ምርቶችን ማምረት በዚህ ረገድ ያለውን የቴክኖሎጂ እውቀትም ሆነ ተጠቃሚነት የሚያሳድግ ነው። በየወቅቱ አዳዲስ የሀገር ውስጥ ምርቶችን ለመጀመርም የሚያስችል ውድድር እንዲኖር ያደርጋል።
አዳዲስ ምርቶችን ማውጣት ባይቻል እንኳን የውጪ ሀገራት ምርቶችን አመሳስሎ በማምረት አቅምን ማጎልበት ይቻላል የሚሉት በዚህ ሂደት ጥራት የሚለውም ጉዳይ በሂደት የሚመጣ ይሆናል። ይህ እውን ሊሆን የሚችለው ግን ፋብሪካዎችን ለማቋቋም የሚያስችል ምቹ ሁኔታ መኖር፣ የመሰረተ ልማት መሟላት ለምርት ግብአት የሚሆኑ ጥሬ እቃዎችን ከሀገር ውስጥም ሆነ ከውጪ በበቂ ሁኔታ ማስገባት ሲቻል ነው። ምርትን ከቦታ ወደቦታ ለማጓጓዝ ሰላም መኖር የሀገር ውስጥ ምርትን ብቻ ሳይሆን የአምራች ፋብሪካዎችም ቁጥር እንዲጨምር የሚያስችል ይሆናል።
በሌላ በኩል የሀገር ውስጥን ምርት በመጠቀም ረገድ እንደ መንግሥትም እንደ ዜጋም ሰፊ ክፍተት መኖሩ ሊታወቅ ይገባል የሚሉት ዶክተር አጥላው፤ ማህበረሰቡ ካለው የኑሮ ውድነት አኳያ የሀገር ውስጥ አልያም የውጪ ምርት ብሎ ከመለየት ይልቅ የሚያየው ርካሽ መሆኑን ብቻ ነው። ይህ ለፋብሪካ ምርት ብቻ ሳይሆን በግብርናውም ዘርፍ ለገበያ በሚቀርቡት ላይ የሚታይ ነው።
መንግሥት በዚህ ረገድ ከፖሊሲ ማውጣት ጀምሮ የሀገር ውስጥ ምርት ጥቅም ላይ እንዲውል ተጨባጭ እርምጃዎች መውሰድ ይኖርበታል። ለምሳሌ የመንግሥት ተቋማት ግዢ ጨረታ ሲወጣ ለሀገር ውስጥ ምርት ቅድሚያ መስጠት ይጠበቅበታል። የመንግሥት ከፍተኛ ኃላፊዎችም ለሥራም ሆነ ለግል አገልግሎት የሚያውሏቸውን ነገሮች ከሀገር ውስጥ ምርት በመጠቀም የተግባር አርአያ ሊሆኑ ይገባል። በዚህ ረገድ በአሁኑ ወቅት የሚታየው ነገር በሚጠበቀው ደረጃ ነው ለማለት አያስደፍርም። በመሆኑም ለውጡ ከመንግሥት ሊጀመር ይገባል ብለዋል።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ታኅሣሥ 30 ቀን 2017 ዓ.ም