ዜና ትንታኔ
በመላው ኢትዮጵያ የሚከበረውን ሃይማኖታዊ ጥምቀት በዓል ተከትሎ ብዙ ሺህ ጎብኚዎች ይገባሉ፤ በቅርቡ ደግሞ የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ይካሄዳል፡፡ በዓሉንና ጉባኤውን ተከትሎ ቱሪስቶች ቆይታቸውን እንዲያራዝሙ የሆስፒታሊቲ ዘርፉ ሚና ከፍ ያለ መሆኑ ይነገራል። የዝግጅት ክፍላችንም ጎብኚዎች ቆይታቸውን እንዲያራዝሙ የሆስፒታሊቲ ዘርፉ (ሆቴሎች) ድርሻ ምን መሆን አለበት ሲል ባለሙያዎችን አነጋግሯል።
የኢትዮጵያ ቱሪስት አስጎብኚዎች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ እንደኛነው አሰፋ፤ እንደሚለው፤ ጥምቀት በዓልና የአፍሪካ የመሪዎች ጉባኤን አስመልክቶ ሆቴሎች እንግዶችን ለመቀበል ሁለንተናዊ ዝግጅት ማድረግ ይገባቸዋል።
‹‹በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ቱሪስቶችን የሚያስተናግዱ ሆቴሎች የሚያስከፍሉት ዋጋ ‹ከፍተኛ ነው› በሚል ትችት ይቀርብበታል። እኔም በዚህ ሃሳብ እስማማለሁ›› የሚለው አቶ እንደኛነው፤ ቱሪስቱ በዓላቱን ተከትሎ የሚኖረው ቆይታ የተራዘመ እንዲሆን ዋጋቸውን ተመጣጣኝ ማድረግ ይገባቸዋል ይላል። አንዱ ቆይታቸውን እንዳያራዝሙ ምክንያት የሚሆነው የዋጋ ትመና መሆኑን ይገልፃል። የኢትዮጵያ ቱሪዝም ከተለያዩ ጫናዎች በማገገም ላይ የሚገኝ ዘርፍ እንደመሆኑ መጠን፤ ዘላቂ ጥቅም ሊያመጣ በሚችል መልኩ የዋጋ ተመን ማድረግ ተገቢ መሆኑን ያስረዳል።
ገናና ጥምቀትን በመሰሉ ቱሪስቶች በብዛት በሚገኙባቸው በዓላት ላይ ሆቴሎች ከሦስት እጥፍ በላይ ዋጋ ይጨምራሉ የሚለው የአስጎብኚ ባለሙያዎች ፕሬዚዳንቱ፤ ይህ ቆይታቸውን እንዳያራዝሙ ምክንያት እንደሚሆን ይናገራል። ለዚህ መፍትሔው ተወዳዳሪ የሆነ ዋጋ በማቅረብ ቱሪስቶች ከበዓላቱም ባሻገር በኢትዮጵያ መስህቦችን ለመጎብኘት እንዲቆዩ ምክንያት መሆን ይገባል ይላል።
‹‹ጎብኚዎች ቆይታቸውን የሚያራዝሙበት ሌላኛው ገፊ ምክንያት ተገቢውን አገልግሎትና እንክብካቤ ሲያገኙ ነው›› የሚለው የማህበሩ ፕሬዚዳንት፤ በሆስፒታሊቲ ዘርፉ ላይ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው የአገልግሎት ጉዳይ መሆኑን ያነሳል። በዓላቱን ተከትሎ እንግዶችን ለመቀበል ዝግጅት እያደረጉ የሚገኙ ሆቴሎች በእንግዶች አቀባበል፣ በአገልግሎት አሰጣጥ ጥራት እና ሌሎችም የቱሪስቶችን እርካታ የሚጨምሩ ጥቃቅን ጉዳዮች ላይ ጭምር በጥንቃቄ መሥራት እንደሚገባቸው ይናገራል።
በሆቴሎች ላይ የሚሰጠው አገልግሎት ጥሩ አለመሆኑ እንግዳው ስለ ኢትዮጵያ መልካም ስም ይዞ እንዳይመለስ ምክንያት መሆኑን የሚያነሳው ፕሬዚዳንቱ፤ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት አድርገው ዓለም አቀፍ ሆቴል የገነቡና እንግዶችን የሚቀበሉ ሆቴሎች ሙያዊ ስነምግባርን የተከተለ፣ የጎብኚውን እርካታ የሚጨምርና ቆይታውን የሚያራዝም ሁለንተናዊ ቁመና ሊገነቡ እንደሚገባ አስረድቷል።
አቶ ሳህሌ ተክሌ የቱሪዝምና ሆቴል መምህርና የጥናትና ምርምር ባለሙያ ነው። እርሱም የአቶ እንደኛነው ሃሳብን ይጋራል፤ በበዓላት ወቅት በቁጥር በርከት ያሉ ቱሪስቶች የሚገኙ በመሆኑ ይህንኑ የሚመጥን ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት ተገቢ መሆኑን ያነሳል። የቱሪስቱ ቆይታን የማራዘምና ሌሎች መስህቦችን የመጎበኘት ፍላጎት የሚጨምረው በተለይ በሚያርፍባቸው ሆቴሎች በተመጣጣኝ ዋጋ የሚያገኘው አገልግሎት መሆኑን ይገልፃል።
‹‹ቱሪስቶች እርካታ ተሰምቷቸው በከፈሉት ገንዘብ ልክ አገልግሎት ሲያገኙ ቆይታቸውን የማራዘም ፍላጎት ይኖራቸዋል›› የሚለው የቱሪዝምና የሆቴል ማኔጅመንት ባለሙያው አቶ ሳህሌ፤ ሆቴሎች አቅርቦታቸውን በዚህ ልክ ማድረግ ሲሳናቸው ቱሪስቶች ከሆቴልና ግለሰቦችን ከማማረር ባለፈ ሀገራዊ ገፅታን የሚያበላሹ መልካም ስም የሚያጎድፉ ተሞክሮዎችን ይዘው እንደሚመለሱ ይናገራሉ። በመጪዎቹ በዓላት ላይም ጉዳዩን በጥንቃቄ በመያዝ የሆስፒታሊቲ ዘርፉ አንቀሳቃሾች በቂ ዝግጅት ማድረግ እንደሚኖርባቸው ይመክራሉ።
እንደ አቶ ሳህሌ ማብራሪያ፤ ቱሪስቶች ተገቢውን አገልግሎት እንዲያገኙ ሆቴሎች የሚቀጥሯቸውን ባለሙያዎች ብቃት ማሻሻል ይኖርባቸዋል። ገናና ጥምቀትን የመሳሰሉ በርካታ ቁጥር ያላቸው የውጪ ሀገራት ቱሪስቶች በሚገኙባቸው በዓላት ወቅት ለሠራተኞቻቸው አጫጭር ስልጠናዎችን በመስጠት ብቃታቸውን እንዲያሻሽሉ መሥራት ይገባቸዋል። ይህንን ማድረግ ከቻሉ ቱሪስቱ ቆይታውን የሚያራዝምበት አጋጣሚ ይፈጠራል ብለዋል።
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ ሆቴሎች ገናና ጥምቀትን አስመልክቶ ለጉብኝት ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ቱሪስቶችን ለመቀበል ዝግጅታቸውን አጠናቅቀዋል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዓሎቹ በልዩ ድምቀት በሚከበሩባቸው እንደ ላልይበላና ጎንደር ባሉ አካባቢዎች ተጨማሪ በረራዎችን እንደሚያደርግ አስታውቋል።
የቱሪስት አስጎብኚ ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዚዳንት፤ ቱሪስቶች ቆይታቸውን እንዲያራዝሙ እንደሚሠሩ ገልጸዋል። ባለሙያዎቹ ሆቴሎቹ የቱሪስቱን ቆይታ ለማራዘም የሚሰጡት አገልግሎት ጥራት ስለሚወስን ልዩ ትኩረት እንዲሰጥ አሳስበዋል።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ታኅሣሥ 30 ቀን 2017 ዓ.ም