አዲስ አበባ፡– ከወደብ ጭነው ያመጡትን ነዳጅ በማደያዎች ከማራገፍ ይልቅ የዋጋ ክለሳ ይደረጋል በሚል አልያም በጥቁር ገበያ ለመሸጥ በማሰብ በየጥሻውና በየከተማው ነዳጅ እንደጫኑ ተደብቀው የሚገኙና እጅ ከፍንጅ የሚያዙ ቦቴዎች ለሦስት ወራት ከሥራ እንደሚታገዱ የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን አስታውቋል።
በነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን የኮሙዩኒኬሽን እና ሕዝብ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ወይዘሮ በቀለች ኩማ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ መንግሥት ለሕዝብ ጥቅም ሲል በድጎማ የሚያስገባውን ነዳጅ ከወደብ ጭነው ከመጡ በኋላ ፤ ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት ሲሉ በየጥሻውና በየከተማው ተደብቀው የሚገኙና እጅ ከፍንጅ የተያዙ የነዳጅ ቦቴዎች ለሶስት ወራት ከሥራ ይታገዳሉ።
ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ የነዳጅ አቅርቦትና ስርጭትን በተመለከተ ዘወትር ከመነሻ እስከ መዳረሻ ድረስ በጂፒኤስ እና በሌሎች ቴክኖሎጂዎች ቁጥጥር እንደሚያደርግ ተናግረው፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ነዳጅ ወደ ሀገር ውስጥ እየገባ በሰው ሰራሽ ችግር ምክንያት እጥረት እንዲፈጠር እየተደረገ ነው ብለዋል።
በማደያዎች አካባቢ የነዳጅ እጥረት የሚፈጠረው፤ በሁለት ዋና ዋና ምክንያቶች መሆኑን ገልጸው፤ የመጀመሪያው ምክንያት በወሩ መጨረሻ የዋጋ ክለሳ (የታሪፍ ጭማሪ) ሲደረግ ጨምረን በመሸጥ የበለጠ ትርፋማ እንሆናለን በሚል የነዳጅ ቦቴዎች የጫኑትን ነዳጅ እንደያዙ በየጥሻው፣ በየመንገዱ እና በየከተማው ተደብቀው የሚቆሙበት ሁኔታ እንዳለ አመልክተዋል።
ከሰሞኑ ከጂቡቲ ነዳጅ ጭነው የመጡ በርካታ ቦቴዎች በአፋር ክልል የተለያዩ ወረዳዎች በየጥሻውና ጉራንጉሩ ተደብቀው መገኘታቸውን አውስተው፤ አንድ ነዳጅ የጫነ ቦቴ ከጂቡቲ ተነስቶ አዲስ አበባ ለመድረስ በአማካይ አራት ቀናት ብቻ እንደሚፈጅበት የተቀመጠ አለ።በአፋር አካባቢ ተደብቀው የተገኙት ተሽከርካሪዎች ግን ከጂቡቲ ጭነው ከተነሱ አስር ቀናትና ከዚያ በላይ ያሳለፉ ናቸው ብለዋል።
እነዚህን በአፋር ክልል ጢሻ ውስጥ ተከማችተው የተገኙ ቦቴዎች በጂፒኤስ ክትትል የተደረሰባቸው ስለመሆኑም ጠቁመው፤ ቦቴዎቹ በብልሽት ምክንያት ስለመቆማቸው ሪፖርት ያላቀረቡ መሆኑንና በአንድ ጊዜ በአንድ አካባቢ በርካታ ነዳጅ የጫኑ ተሽከርካሪዎች በብልሽት ቆሙ ቢባል እንኳ አሳማኝ አለመሆኑን ተናግረዋል።
ከአፋር ክልል መንግሥት ጋር በመተባበር ቦቴዎቹ ከተደበቁበት እንዲወጡና እጀባ ተደርጎላቸው ወደ መዳረሻቸው እንዲሄዱ ተደርጓልም ያሉት ወይዘሮ በቀለች፤ በሁለት ቀናት ውስጥ የጫኑትን ነዳጅ ገብተው እንዲያራግፉ ለኩባንያዎቻቸው ደብዳቤ ስለመጻፉ ገልጸዋል።
ነዳጅ ለኅብረተሰቡ ተጠቃሚነት ሲባል በመንግሥት ድጎማ እየተደረገለት የሚገባ መሠረታዊ ፍጆታ ነው ያሉት ወይዘሮ በቀለች፤ የነዳጅ ቦቴዎች ሕግና ሥርዓትን ተከትለው የማይሠሩ ከሆነ ግን ነዳጅ አቅራቢ ድርጅቶች መንግሥት በሚያደርገው ድጎማ ላይ የሚደርሰውን ኪሳራ እንዲሸፍኑ አቅጣጫ ተቀምጧል ብለዋል።
ነዳጅ በማደያዎች ከተራገፈ በኋላ ሌሊት ደብቆ በመቅዳት ለጥቁር ገበያ የማዋሉ ነገር ሌላው ሰው ሰራሽ ችግር እንደሆነም ጠቅሰዋል። ማደያዎች ነዳጅ ካስሞሉ በኋላ አልሸጡም እንዳይባሉ በአንድ ማሽን ብቻ እየቀዱ ሌላውን ቆጥበው በማስቀረት ለተለያየ ጥቅም እንደሚያውሉት ተደርሶበታል ነው ያሉት። እንዲህ አይነት አሻጥር የሚሰሩ ማደያዎችም በተመሳሳይ ለሦስት ወራት ከስራ ውጪ እንዲሆኑ ይደረጋል ብለዋል።
ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ በቀጣይም ማን ምን እንደጫነ፤ ከመነሻው እስከ መድረሻው የሚያደርገው ጉዞ ምን እንደሚመስል፤ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ቁጥጥሩን አጠናክሮ በመቀጠል ሕገ-ወጥ ሥራ በሚሠሩ ቦቴዎች እና ማደያዎች ላይ ርምጃ የሚያስወስድ መሆኑን ተናግረዋል። ኅብረተሰቡም በያለበት ቦታ ሁሉ ከነዳጅ ጋር ተያይዞ የሚፈጸሙ ሕገ-ወጥ ግብይቶችን በመጠቆም የቁጥጥሩ አካል እንዲሆን ወይዘሮ በቀለች ጥሪ አቅርበዋል።
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ታኅሣሥ 30 ቀን 2017 ዓ.ም