አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያ ከሦስት ዓመት በኋላ እ.አ.አ በ2021 የተፈጥሮ ጋዝ ወደ ውጭ መላክ እንደምትጀምር በማዕድንና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር የነዳጅ ዘርፍ ሚኒስትር ደኤታ አስታወቁ።
የተፈጥሮ ጋዙ በዓመት እስከ አንድ ቢለዮን የአሜሪካ ዶላር ያስገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅም ገለጹ፡፡ ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር ኳንግ ቱትላም በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት፤ በሶማሌ ክልል የተገኘውን የተፈጥሮ ጋዝ የሚያለማው የቻይና ኩባንያ ሲሆን፣ የተፈጥሮ ጋዙ ከኢትዮጵያ ወደ ጅቡቲ የሚጓጓዘው በቱቦ ይሆናል፡፡ ቱቦ የመዘርጋቱን ሥራ ለማካሄድ ከኩባንያው ጋር ስምምነት መፈረሙንና ይህም ሥራ በሦስት ዓመት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ሚኒስትር ዴኤታው አስታውቀው፣ ጅቡቲ በሚተከል ማቀነባበሪያ ከተዘጋጀ በኋላ ወደ ውጭ እንደሚላክም ገልጸዋል፡፡
እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ፤የተፈጥሮ ጋዙ ወደ ውጭ በሚላክበት የመጀመሪያ ዓመት ለኢትዮጵያ እስከ አንድ ቢሊዮን ዶላር ያስገኛል፡፡ ወደ ውጭ መላክ ከተጀመረ ከስድስትና ሰባት ዓመት በኋላ ደግሞ ገቢው በየዓመቱ እየጨመረ ሄዶ ሰባት ቢሊዮን ዶላር ይደርሳል፡፡
ለነዳጅ ማጣሪያው በጅቡቲ የሚገነባው ማቀነባበሪያ በዓመት ሦስት ሚሊዮን ኪዩቢክ ጫማ ጋዝ እንደሚያቀነባብር ዶክተር ኳንግ ተናግረው፣ በድሬዳዋም በዓመት ግማሽ ሚሊዮን ኪዩቢክ ጫማ የሚያመርት የጋዝ ማቀነባበሪያ እንደሚገነባም ገልጸዋል፡፡ ጋዙ ኢትዮጵያና ሞሮኮ በሽርክና (Joint venture) በድሬዳዋ ለሚገነቡት የማዳበሪያ ፋብሪካ እንድ አንድ ግብአት እንደሚያገለግልም ጠቁመዋል፡፡
ለእዚህ አቅርቦትም ከኩባንያው ጋር ሰሞኑን የመግባቢያ ሰነድ መፈረሙን ጠቁመዋል ። እስከ አሁን የተፈጥሮ ጋዝ ፍለጋና ልማቱ እስከ አንድ ሺ ለሚደርሱ ኢትዮጵያውያን የሥራ ዕድል መፍጠሩንም ገልጸዋል። ልማቱ እየሰፋ ሲሄድ የሠራተኞች ቁጥር እንደሚጨምር ጠቅሰው፣አካባቢው የበለጠ እንደሚለማና በተጓዳኝ ሌሎች የሥራ ዕድሎች እንደሚፈጠሩ አስረድተዋል ። የተፈጥሮ ጋዝ ክምችቱ ከስምንት እስከ አስር ትሪሊዮን ኪዩቢክ ጫማ እንደሚደርስም ሚኒስትር ዴኤታው ጠቁመዋል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 26/2011
ኃይለማርያም ወንድሙ