አዲስ አበባ፡- በአማራ ክልል የተካሄደው አንደኛው ዙር የማህፀን በር ካንሰር ክትባት ከሦስት ወረዳዎች በስተቀር በስኬት መጠናቀቁን የክልሉ ጤና ጥበቃ ቢሮ አስታወቀ፡፡
የቢሮው የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ወይዘሮ ፀጋነሽ ገድሉ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት፤ ካለው ወቅታዊ የፀጥታ ችግርና በማህበራዊ ድረገፅ ሲራገቡ ከነበሩ አንዳንድ የተዛቡ መረጃዎች ጋር በተያያዘ በክልሉ የሚሰጠው የማህፀን በር ካንሰር ክትባት ከፍተኛ ስጋት ተድቅኖበት ነበር፡፡ክትባቱ ከመጀመሩ በፊት በርካታ የዝግጅት ሥራዎች በመሰራታቸው ስጋቱ ተወግዶ ክትባቱን በተሳካ መልኩ በመስጠት ማጠናቀቅ ተችሏል፡፡
እንደ ዳይሬክተሯ ገለፃ ፤ለሁሉም የጤናው ዘርፍና ለክልሉ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች፣ የዘርፍ መስሪያ ቤት የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሮች ስልጠናና እውቅና መሰጠቱ፤ በዋናነትም የክልሉ ተወላጅ አክቲቪስቶችን በማሳተፍ ውይይት ተደርጎ ለዚሁ አላማ እንዲቆሙ ማድረግ መቻሉ ለክትባቱ ስኬት ጉልህ ሚና ተጫውተዋል፡፡ ከሃይማኖት ተቋማት ተወካዮችና በክልሉ ከሚገኙ በርካታ የባህል ህክምና አዋቂዎች ጋር በክትባቱ አስፈላጊነት ዙሪያ ጤና ቢሮው ያደረገው ውይይት የጋራ መግባባት በመፍጠር ለክትባቱ ውጤታማነት የራሱን አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡
በክልሉ የመገናኛ ብዙሃን አማካኝነት ለአንድ ወር በተከታታይ በክትባቱ ዙሪያ ለህብረተሰቡ መረጃ እንዲደርስ መደረጉን የገለፁት ዳይሬክተሯ፤ በዚህም መሰረት የመጀመሪያው ክትባት በህዳር ወር በፍኖተ ሰላም ከተማ በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በይፋ ተጀምሮ በቀጣይም በሁሉም የክልል ወረዳዎች ላይ ምንም አይነት ችግር ሳያጋጥም መስጠት ተችሏል» ብለዋል። ይሁንና በማዕከላዊ ጎንደር በሚገኙ ሶስት ወረዳዎች ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት ክትባቱን መስጠት አለመቻሉን ዳይሬክተሯ አስረድተዋል።
በክትባት መርሐ ግብሩ በክልሉ የሚገኙ ዕድሜያቸው 14 ዓመት ለሞላቸው 276 ሺ 402 ልጃገረዶች ክትባቱን ተደራሽ ማድረግ መቻሉን ጠቁመው፤ በዚህም የእቅዱን 64 ነጥብ 4 በመቶ መፈፀሙን እንደሚያሳይ አብራርተዋል። እንደ ወይዘሮ ፀጋነሽ ገለጻ፤ ክልሉ 428 ሺ 921 ልጅ አገረዶችን ለመከተብ እቅድ ተይዞ የነበረ ቢሆንም፣ከፌዴራል መንግሥት ለክልሉ የደረሰው የክትባት መጠን ግን 286 ሺ 641 ብቻ ነው፡፡
ይህም ክልሉ ከደረሰው የክትባት መጠን አኳያ ሲታይ 96 ነጥብ 4 በመቶ የሚሆነውን ማሳካት እንደተቻለ ይጠቁማል፡፡ በቀጣዩ ሰኔ ወር በሚሰጠው ሁለተኛው ዙር ክትባት 428 ሺ 921 ልጅአገረዶች ተደራሽ ከማድረግ በተጓዳኝ፣ በመጀመሪያው ዙር ክትባቱን ያላገኙን ለመድረስ እንደሚሰራም ዳይሬክተሯ አስገንዘበዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 26/2011
አስናቀ ፀጋዬ