ያለፉት ሶስት ዓመታት ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ከበድ ያለ የፈተና ጊዜ ነበር። አሁንም ችግሮቹን አልተሻገርናቸውም። ሆኖም ግን ሊነጋ ሲል ይጨልማል እንደሚባለው ሁሉ አሁን የጨላለመ ቢመስለንም የመንጊያው ሰዓት መድረሱን የሚያበስሩ ብዙ የዶሮ ጩኸቶች እየተሰሙ ናቸው። ዛሬ መለስ ብለን የአገራችንን መከራዎች መቁጠር ያስፈለገን እንዲያው በደፈናው አይደለም። በአንድ ወገን ሳይታሰብ ድንገት ከተፍ ያለው የኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝ በርካታ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮቻችንን አመሰቃቅሎብናል። አሁንም በተመሳሳይ ከዚህ ቫይረስ ጋር ተያይዞ በርካታ ዘርፎች ማነቆ ውስጥ ይገኛሉ።
ሌላው በነዚህ ዓመታት ውስጥ የኢትዮጵያውያንን መከራ ያበዛው በንዋይ ፍላጎትና በጭካኔ ብዛት ማየትም ሆነ ማስተዋል የተሳነው የህወሓት የሽብር ቡድን ነው። ይህ ስብስብ የኮሮና ወረርሽኝ ካደረሰብን ጥፋት እና እያደረሰብን ካለው ጉዳት በብዙ እጥፍ የአገራችንን ምጥ አብዝቶታል ። ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ምስቅልቅል በማምጣት ዜጎች በሚወዷት አገራቸው ሰርተውና ለፍተው በሰላም እንዳይኖሩ የእሾህ አሜኬላ ሆኖ ለገላጋይ አስቸግሮ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የቻለውን ሁሉ እያደረገ ይገኛል።
ታዲያ እነዚህ በኢትዮጵያውያን ላይ የተጋረጡ ሁለት ሰንኮፎች በርካታ ጥፋት አድርሰዋል። በዋናነት ግን የአገራችን ኢኮኖሚ ፈተና ውስጥ እንዲገባ አድርገውታል። በተለይ ሊሰሩ በእቅድ ተይዘው የነበሩ ፕሮጀክቶች እንዲስተጓጎሉና በግዜ ተጠናቀው ጥቅም ላይ እንዳይውሉ አድርገዋል። በጀት ታጥፎ ጠላትን ለመመከትና ወረርሽኝን ለመከላከል ለሚደረግ ጥረት ውሏል። ይሄ ደግሞ የተያዘው የእድገት ግስጋሴ ላይ ያሳረፈው አሉታዊ አሻራ በአጭር ግዜ የሚፈታ እንዳይሆን አድርጎታል።
አገራችን ባጋጠማት ችግር በእጅጉ ከተጎዱ ዘርፎች መካከል የቱሪዝም ኢንደስትሪው ቀዳሚው ተጠቃሽ ነው። የኮሮና ወረርሽኝ በተከሰተ ግዜ እንቅስቃሴው ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ቆሞ ነበር። ይህ ደግሞ በዘርፉ ሙሉ አቅምና ገንዘባቸውን አውጥተው የሚሰሩ በርካታ ተቋማትን፣ ግለሰቦችንና እንጀራቸውን በቱሪዝም ዘርፍ ላይ የመሰረቱ አካላትን ጎድቷል። አገርም የምታገኘው ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እንዲስተጓጎል ሆኗል። ይህ ያልታሰበ ዱብ እዳ ቀስ በቀስ የሚወገድበት ስልት መንግስት እየነደፈና መፍትሄ እያበጀ የመጣ ቢሆንም “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንዲሉ የቱሪዝም ዘርፉን ጭርሱኑ በዳዴ የሚያስኬድና አገር የሚጎዳ ችግር ተከሰተ። እርሱም የትህነግ እብሪትና በሰሜኑ ክፍል የለኮሰው ጦርነት ነው።
ቱሪዝም ከምንም ነገር በላይ ሰላምና መረጋጋትን የሚሻ ነው። ዓለም አቀፍ ጎብኚዎችም ሆነ በአገር ውስጥ የተለያዩ መስህቦችን ለመመልከት የሚሄዱ ዜጎች ደህንነታቸው ካልተረጋገጠ አስጊ ሁኔታ ውስጥ እራሳቸውን አይከቱም። በዚህ ምክንያት እቅዳቸውን ይሰርዛሉ።
በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታም የተከሰተው ይሄው ነው። ሽብርተኛው ትህነግ የኢትዮጵያን እጅግ በርካታ የቱሪዝም ሃብቶች በያዘው የሰሜኑ ክፍል እጅግ ጭካኔ የተሞላበት ጥቃት አድርሷል። ይህ ደግሞ በፊትም በቋፍ ላይ የነበረውን የቱሪዝም ዘርፍ እንቅስቃሴ እንዲገታ አድርጎታል። መንግስትም ይህን ክህደት ለመመከትና ሽብርተኛ ቡድኑን ለመግታት በሚያደርገው ጥረት ምክንያት የተገታውን የቱሪዝም እንቅስቃሴ ማነቃቃት አልቻለም። ምክንያቱም ዘርፉ ከሰላምና ፀጥታ ጋር ቀጥተኛ ቁርኝት ስላለውና በቅድሚያ እርሱን ማስተካከል ስለሚሻ ነው።
ሽብርተኛው ትህነግ በሰሜን እዝ ላይ የጭካኔ በትሩን ከሰነዘረ በኋላ ወደ በረሃ ሲሸሽ የቱሪዝም መዳረሻ የሆነችውን የአክሱም ከተማንና የአየር ማረፊያውን እንዳልነበር አድርጎ አውድሞት ነበር። ጦርነቱን በመቀስቀሱ ብቻ ከተለያዩ የአለም ክፍላት ይመጡ የነበሩ ጎብኚዎች ሙሉ ለሙሉ እንዲገቱ አድርጓል። በዚህ ሳያበቃ መንግስት በተናጠል የወሰደውን የተኩስ አቁም አዋጅ በመጣስ ወደ አማራ ክልል ተስፋፍቶ ቆይቷል።
በነዚህ አራት ወራት ጊዜያት ታላላቅ ሃይማኖታዊ ፋይዳ ያላቸውን ቅርሶች፣ የመስህብ ስፍራዎች አውድሟል። አሸባሪው የህወሓት ቡድን በአማራና አፋር ክልሎች የዘር ማጥፋት፣የቅርስ ማውደም ወንጀል ( “ጄኖሳይድ”) መፈጸሙን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን እንዲህ ሲል ነበር የገለፀው።
ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ በሰጡት መግለጫ “አሸባሪው የህወሓት ቡድን በአፋርና አማራ ክልሎች
በጭና፣ በአጋምሳ፣ በጋሊኮማ፣ በቆቦ ፣በኮምቦልቻ እና በተለያዩ አካባቢዎች ዜጎችን በጅምላ መግደሉን በማስታወስ ትክክለኛውን ሃቅ የፈለገ በአካባቢዎቹ ተገኝቶ መመልከት ይችላል ብለዋል። የዓለም አቀፉ ማህበረሰብም ጉዳቱን በአግባቡ እንዲያውቀው ማድረግ ቀሪ የቤት ስራችን ይሆናል ብለዋል።
አሸባሪ ቡድኑ ባደረሰው ጉዳት በደቡብ ጎንደር በላስታ ላሊበላና የተለያዩ የአማራ ክልል አካባቢዎች እንዲሁም በአፋር ክልል በቱሪዝም ሃብት ላይ ጉዳት አድርሷል። ሐይማኖታዊ ቅርሶች የቱሪዝም አገልግሎት መስጫዎችና ጥብቅ ስፍራዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት አስከትሏል። ዲያስፖራውም በተቻለ መጠን ድጋፍ ሊያደርግ ይገባል።
ከላይ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን እንደገለፀው በትህነግ ቡድን በርካታ በደሎች ደርሰዋል። በተለይ የቱሪዝም ዘርፉ እንዲዳከምና እንዳያንሰራራ ጭካኔ የተሞላበት ስራን ሰርቷል። እንኳን በሰዎች ላይ ለሰራው በደል ይቅርና በቅርስ፣ በባህል፣ በታሪክና ተፈጥሯዊ ነገሮች ላይ ባደረሰው ወንጀል ትህነግ ምህረት ሳይሆን በልኩ ሂሳብ ማወራረድ እንዳለበት የሚያሳይ ነው።
የላሊበላ ከተማ በአለም ላይ በእጅጉ በዝናቸውና በተወዳጅ ስፍራነታቸው ከሚጠቀሱ ቦታዎች ቀዳሚዋ ነች። የኢትዮጵያውያን የኪነ ህንፃ መራቀቅንና እጅን በአፍ ላይ የሚያስጭን የጥበብ ባለቤት መሆንን በተምሳሌትነት ማየት ከተፈለገ ከላሊበላ በላይ ምንም አይነት አስረጂ ማግኘት አይቻልም።
የላሊበላን ከተማ በዋነኛነት ታዋቂ ያደረጓት በ13ኛው መቶ ክፍለዘመን እንደ ተሰሩ የሚነገርላቸው 11 አብያተ ክርስቲያናት ናቸው። በኢትዮጵያ ትውፊት መሰረት እነዚህ አብያተ ክርስቲያናት በንጉሥ ላሊበላ ዘመን በቅዱሳን መላዕክት ረዳትነት እንደተሰሩ የሚታመን ሲሆን ከነዚህም ውስጥ ቤተ ጊዮርጊስ (ባለ መስቀል ቅርፁ) ፣ ቤተ መድሃኔዓለም ደግሞ ከሁሉም ትልቁ ነው።
በላሊበላ (ዳግማዊ ኢየሩሳሌም) የገና በዓል ታህሳስ 29 በልዩ ሁኔታና ድምቀት ይከበራል፣ “ቤዛ ኩሉ” ተብሎ የሚጠራው ዝማሬ በዚሁ በዓል የሚታይ ልዩና ታላቅ ትዕይንት ነው። የሚደረገውም ከቅዳሴ በኋላ በቤተ ማርያም ሲሆን ከታች ባለ ነጭ ካባ ካህናት ከላይ ደግሞ ባለጥቁር ካባ ካህናት በቅዱስ ያሬድ ዜማ ቤዛ ኩሉ እያሉ ይዘም ራሉ።
ከዓለም ዙሪያ እጅግ በርካታ ጎብኚዎች እነዚህን ድንቅ የኪነ ህንፃ ውጤቶችና ሃይማኖታዊ ስነስርዓት ለመጎብኘት ይመጣሉ። ቅርሱም ከ30 ዓመታት በፊት በዓለም የቅርስ መዝገብ በዩኔስኮ ተመዝግቦ ልዩ ጥበቃ ይደረግለታል።
ታዲያ ባለፈው አንድ ዓመት ሽብርተኛው ትህነግ የከፈተውን ጦርነት ተከትሎ ቅርሱን ለመጎብኘትና ታሪክን ለማወቅ የሚመጡ የውጪና የአገር ውስጥ ዜጎች በዚህ ስፍራ እንዳይገኙ እንቅፋት ሆኗል። ከዚህም አልፎ በላስታ ላሊበላ አካባቢ (ውቅር አብያተ ክርስቲያኖቹ በሚገኙበት) ጦርነቱ እንዲስፋፋ ምክንያት በመሆኑ በአራት ወራት ውስጥ አያሌ ጉዳቶችን አድርሷል። ድንቅ የታሪክ፣ የባሕልና የሐይማኖት መዲናና የዓለም አቀፍ ቅርሶች መገኛ የሆነችው የቅዱስ ላሊበላ ከተማ ማኅበረሰብ በቁጥር ወደ 70 ሺህ የሚገመት ሲሆን ከ90 በመቶ የማያንሰው ደግሞ በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ በቱሪዝም የሚተዳደር ነው። ይሁንና ቀደም ብሎ በኮቪድ 19 ምክንያት የቱሪስት ፍሰቱ በመዳከሙ አሁን ደግሞ ከአራት ወራት በላይ በትሕነግ ወራሪዎች ተይዞ በመቆየቱ ለከፍተኛ ችግርና ረሀብ ተጋልጦ ሕልውናው አደጋ ላይ ወድቋል።
ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር ቆይታ ካደረጉት የላሊበላ ነዋሪዎች መካከል የላሊበላ ከተማን ለማፍረስ ከመጣውና በጭካኔ ተግባሩ ከሚረካው የህወሓት ወራሪ ኃይል ነፃ በመውጣታቸው መደሰታቸውን ገልፀዋል። የሽብር ቡድኑ በከተማዋ በቆየባቸው ጊዜያት መልከ ብዙ ሰቆቃ ያደረሰባቸው ከመሆኑም በላይ በላሊበላ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ዝርፊያና ውድመት ማድረሱን ተናግረዋል።
የቅዱስ ላሊበላ ደብር አስተዳዳሪ ቆሞስ አባ ጽዬስላሴ መዝገቡ በሰጡት አስተያየትም በጦርነቱ ምክንያት አገልግሎት መስጫ ተቋማት በመውደማቸው ህብረተሰቡ ለከፍተኛ ችግር መዳረጉን ተናግረዋል። ወላድ እናቶች በሕክምና እጦት ህይወታቸው እንዳያልፍ የጤና ተቋማት አገልግሎት እንዲሰጡ ቤተ ክርስቲያኗ የበኩሏን እገዛ ብታደርግም የመድሃኒት፣ የነዳጅና የኦክሲጅን እጥረት ተከስቷል። በወራሪው ቡድን ያሳለፉት የመከራ ወራት ዛሬ አልፎ በመመልከታቸው ፈጣሪን ያመሰገኑት አስተዳዳሪው፣ ከተማዋን ለቆ ያልወጣው የህብረተሰብ ክፍል በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ማለፉን ነው የተናገሩት ።
በወረራ ጊዜ ሁሉም ያለውን ምግብና ገንዘብ በማምጣት እርስ በእርስ ተዛዝኖና ተካፍሎ እየበላ ችግሩን አሳልፏል። “ያሳለፍነው አራት ወር ከአራት ዓመት ቢበልጥብንም መተዛዘንን፣ መረዳዳትና አብሮነትን አስተምሮናል” ብለዋል። መንግስት አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ሥራ እንዲጀምሩ ማድረግና ለህብረተሰቡ የእለት ደራሽ ምግብ በአስቸኳይ በማቅረብ ዜጎችን ከሞትና ከረሃብ እንዲታደግም ጠይቀዋል። ጀግናው መከላከያ ሠራዊት፣ ልዩ ኃይል፣ ሚሊሻው፣ ፋኖውና ህዝባዊ ሠራዊቱ አሸባሪውን ህወሃት አይቀጡ ቅጣት በመቅጣት የተለያዩ ከተሞችን ነጻ እያወጣና ወደ ፊት እየገሰገሰ ስለመሆኑ መንግስት መግለጹ ይታወሳል።
በጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚመራው የህልውና ጦርነት ምክንያት የትህነግ እኩይ ዓላማ እየተገታ ይገኛል። በዚህ ምክንያት በወራሪው ሃይል የተያዙ በርካታ ቦታዎች ተለቅቀዋል። ከዚህ ውስጥ በመስህብ ስፍራነታቸው ዓለም እንደ አይኑ ብሌን የሚያያቸው አካባቢዎችም ተጋርጦባቸው ከነበረው አደጋ አገግመዋል። በእርግጥ ትህነግ አያሌ ጥፋቶችን በቱሪዝም መስህብ ስፍራዎች አድርሷል። አሁንም እያደረሰ ይገኛል። በጀግናው የመከላከያ ሰራዊት ከዚህ አደጋ ነፃ ከወጡት ውስጥ የቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ይጠቀሳሉ። ተወዳጇ ከተማም አሁን የሰላም አየር መተንፈስ ጀምራለች። አሁን የቀረው በምን መንገድ ድጋሚ ሊቃጣ የሚችል የሽብርተኛውን ጥፋት በአግባቡ መመከት ይቻላል የሚለው ጥያቄና በቱሪዝም ሃብቶቹ ላይ የኢኮኖሚ ገቢውን የመሰረተው ማህበረሰብ ዳግም ተመልሶ ወደ እለት ተእለት ተግባሩ ይገባል የሚሉት ጥያቄዎችን መመለስ ነው የቀረው።
መንግስት በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ አማካኝነት የክርስትና እምነት ተከታዮች የሚያከብሩትን የክርስቶስ ልደት (ገና) አስመልክተው ወደ አገራቸው እንዲገቡ ጥሪ አድርገዋል። ይህ በዓል ደግሞ በተለይ በዓለም አቀፍ ቱሪስቱ፣ ዲያስፖራውና በአገር ውስጥ ባሉ በርካታ ዜጎች ከዚህ ቀደም በላሊበላ ከተማ የመከበር ልምድ ነበረው። ዘንድሮ ደግሞ የአሜሪካና ምእራባዊያን ጫና ለመከላከል ዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው እንዲገቡ ተጋብዘዋል።
ይህን በማስመልከት የላሊበላ መስህቦችንና የተጎዳውን ማህበረሰብ የመካስ ስልት ሊዘረጋና በጦርነቱ ምክንያት የተዳከመውን ቱሪዝም እንዲያንሰራራ እንደ መልካም አጋጣሚ መወሰድ ይኖርበታል።
የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ሚኒስቴር ዲኤታ ሰላማዊት ካሳም በአሸባሪው ቡድን ወረራ ስር በነበሩ አካባቢዎች ላይ ቡድኑ በቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች ላይ፣ በሃይማኖት ተቋማትና በአለም ቅርስነት በተመዘገቡ ቦታዎች ላይ ጭምር ጥፋቶችን ማድረሱን ተናግረዋል። እንደ እርሳቸው ገለፃ በሃገራችን የምጣኔ ሃብት እድገት ምንጭ ይሆናሉ ተብለው ተለይተው እየተሰራባቸው ከሚገኙት 5 ዋና ዋና ዘርፎች መካከል የቱሪዝም ዘርፍም አንዱ ነውና ይህንን ለማነቃቃት በጦርነቱ የወደሙትንም የቱሪስት መዳረሻዎችን መልሶ ለመገንባት ትልቅ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።
በቱሪስት ፍሰት ገቢ ያገኝ የነበረውን ዜጋ ለማገዝና በጦርነቱ ምክንያት የተመሰቃቀለው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እንዲያገግም ለማድረግም ዲያስፖራው የሚያበረክተዉ አስተዋፅኦ የጎላ ነው። ጦርነቱ በተካሄደባቸው ክልሎች ውስጥ በቱሪስት መዳረሻዎችና በሃይማኖት ተቋማት ላይ የህወሓት የሽብር ቡድን ያደረሰውን ጉዳት በተመለከተ አጣሪ ቡድን ተቋቁሞ ዝርዝር ምርመራ ማድረግ ጀምሯል። ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት የኢትዮጵያ የምጣኔ ሃብት እድገት ምንጭ እንዲሆን ታስቦ እየተሰራባቸው ከሚገኙ ዘርፎች መካከል የቱሪዝም ዘርፍ አንዱ በመሆኑ ዘርፉ እንዲያንሠራራ ለማድረግ በብዛት ወደሃገሩ የሚመጣው ዲያስፖራ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ መንግስት ጥሪውን ያቀርባልም ነው ያሉት።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 3 ቀን 2014 ዓ.ም