ሻምበል አበበ አለሙ ይባላሉ። የአገራቸውን ዳር ድንበር ለማስጠበቅ በ17 ዓመታቸው በ1960ዎቹ የዘመቱ ናቸው። ስለአገራቸው ሀብትና ንብረታቸው ተዘርፎ ሳያዩት የቆዩና የአገር ንብረትን በመጠበቅም የምስጋና ወረቀት የተቸሩ ሲሆኑ፤ አሁንም ቢሆን ለስልጣኑ ያልሳሳ መሪ ባለባት አገር ውስጥ የእኔ መቀመጥ ምን ይፈይዳል የሚል አቋም ይዘው ለመዝመት የቋመጡ እንደሆኑ ይናገራሉ። ከተፈቀደላቸውና ገደቡ ከተሻሻለ ዛሬ ባሉበት በ71 ዓመታቸው ጭምር ለመዝመት ቁርጠኛ መሆናቸውንም ከንግግራቸው ተረድተናል።
እንዲያውም ያሉን ‹‹መውጣት መውረድ ባልችል መደገፍና ስልት ማሳየት፤ መግደል ባልችል መሞት እፈልጋለሁ›› ነው። ስለአገራቸውና ስለኢትዮጵያ ሰራዊት ጥንካሬ ተናግረው አይበቃቸውምም። ሁሌም ምስክርነታቸውን ቢሰጡም ይደሰታሉ። ለዛሬ ‹‹የሕይወት ገጽታ›› አምዳችን እንግዳ ስናደርጋቸውም ይህና መሰል የሕይወት ጉዟቸው ብዙዎችን የሚያስተምር ሆኖ ስላገኘነው ነው። እናም ሕይወታቸውንና ልምዳቸውን ትቀስሙ ዘንድ ጋበዝናችሁ። መልካም ንባብ።
የወታደር ልጅ ወታደር
ሐምሌ 21 ቀን 1943 ዓ.ም ነው እዚሁ አዲስ አበባ በተለምዶ ሲግናል ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በወታደሮች ካምፕ ውስጥ ተወልደው ያደጉት። አብዛኛው የልጅነት ጉዟቸውም በዚሁ ቅጥር ግቢ ውስጥ ያለቀ ነው። ስለዚህም ውትድርና ልምዳቸው ብቻ ሳይሆን ኑሯቸው ሆኖ ዓመታትን አስቆጥረዋል። ሕይወታቸውም አድርገውት የመኖራቸው ምስጢር ልጅነታቸው ላይ የተቀረጸባቸውና የተሰራባቸው ነገር እንደሆነ ያስረዳሉ። ውትድርና በስነምግባርና በአቋም መጠበብም በመሆኑ እርሳቸውም በእነዚህ ነገሮች አብበው ልጅነታቸውን ኖረውታል። ስለዚህም ጨዋ ያሳደገው የጨዋ ልጅ ሆነዋልም። በእርግጥ ይህንን ሁሉ ታሪካቸውን የሰጧቸው አባታቸው ናቸው። ምክንያቱም እርሳቸው የክቡር ዘበኛ ጦር ሰራዊትና የኮርያ ዘማች ሲሆኑ፤ ዓመታትን አገራቸውን ሲያስጠሩ ቆይተዋል። በካምፕ ውስጥ የቆዩትና የውትድርናን ሕይወት እያዩ እንዲያድጉ የሆኑት በዚህ ምክንያት ነው።
ሻምበል አበበ ከእናታቸው ጋር ብቻ በመሆን ነው ያደጉት። ይሁን እንጂ በአካባቢው ያሉ አባቶች ሁሉ አባታቸው ናቸው። ስለዚህም አባት አጥተው አያውቁም። አባታቸውም ቢሆኑ ከጎናቸው ብዙም ባይቆዩም ባሉበት ጊዜ አስደስተዋቸው፣ በሌሉበት ጊዜ ደግሞ በርቀትም ሆነው ከደሞዛቸው ተቆራጭ እያደረጉላቸው ዘና ብለው እንዲኖሩ አድርገዋቸዋል። ስለዚህም የአባትም የእናትም ፍቅር አልተለያቸውም። በግቢው ውስጥ የሚሰጣቸው መመሪያም ቢሆን እናት አባት ከሚያደርገው የሚተናነስ ስላልሆነ ምንም ነገር አላሳጣቸውም።
እማዬና አባዬ የሚሉት የግቢውን ሰው በሙሉ ብቻ ሳይሆን ውጪውንም ስለነበረ ልጅነታቸው በሁሉ ነገር የተሳካም እንደነበር ያስታውሳሉ። ምክንያቱም ሁሉም የሚቆነጥጠው፣ ሁሉም የሚቆጣውና መስመሩን እንዳይስት የሚያደርገው ልጅ ስኬታማና አገር ወዳድ የማይሆንበት ምክንያት አይኖርም። እርሳቸውም ይህ ስለተሰጣቸው በአገራቸው የማይደራደሩ ሆነዋል። ዛሬ የመዝመታቸው ምስጢርም ይህ እንደነበር ይናገራሉ። በሁሉም ያደጉ በመሆናቸው ለሁሉም መኖርና መሞትን ተምረዋል። ዛሬ ላለው ትውልድ የሚሰጡት ነገር እንዲኖራቸው ያደረጋቸውም ይህ እንደሆነ ያስረዳሉ።
ልጅነት ላይ የሚሰራ ሥራ ሽምግልና ድረስ የሚደርስ እንደሆነ የሚያስረዱት ሻምበል አበበ፤ ትናንት ስለ አገር ወዳድነት የአካባቢው ሰው ባያስተምራቸው ኖሮ ዛሬ ይህ ስሜት እንደማይኖራቸውና ተለሳልሰው አገራቸውን እንደ ባንዳው ሕወሓት ይሸጡ እንደነበር ይናገራሉ። ማንም ያላቀደውንና ያልተማረውን አይተገብርምና ለእርሳቸው ዛሬ ላይ በ71 ዓመታቸው ስለአገሬ ቢፈቀድልኝ ልሙት ያስባላቸው ይኸው ጉዳይ መሆኑን ያነሳሉ።
በወታደር ቤት ማደግ ጨዋታም ሆነ የትምህርት ሁኔታ በዚያ መስመር የሚጓዝ መሆኑ ግድ ነው። እናም ለእርሳቸው ተመራጭ ጨዋታ ሙዚቃና ኳስ እንዲሁም ሩጫ ናቸው። ከሁሉም በላይ ግን ሙዚቀኛ መሆን በጣሙን ያስደስታቸው ነበር። ለዚህ ደግሞ መሰረቱ የወታደር ቤተሰብ በሳምንት አንድ ቀን ማለትም ቅዳሜ በነጻ ሙዚቃ መጋበዙ ነው። እናም እንደ እነጥላሁን አይነት ዘፋኝ መሆንን ከልጅነታቸው ጀምሮ ይመኙት ነበር። ድምጻቸው መረዋ እንደነበርም ያስታውሳሉ። በጭፈራም ሆነ በዳንስ አይታሙም። ነገር ግን ማንም እድሉን አልሰጣቸውምና አልቀጠሉበትም። ከዚያ ይልቅ አቅማቸውን የሚያሳዩበት የቦክስ ውድድር ነበርና እዚያ ላይ ብዙ ሰርተዋል። ጥንካሬያቸውም በአካባቢውም ሆነ በአለቆቻቸው ዘንድ ምስክር አሰጥቷቸዋልም።
በሲግናል ካምፕ ውስጥ ኢትዮጵያ ነበረች። ብዙ ባህል፣ ብዙ ችሎታ፣ ብዙ አመለካከት ብዙ ብዙ… ነገር ነበረ የሚሉት ሻምበል አበበ፤ ከዚህ ሁሉ እሴት እያንዳንዱ ልጅ ይቋደስ ነበር። ኢትዮጵያዊነትንም የሚያየው ከዚህ ከሁሉም ክፍልና አቅጣጫ ነው። ብሔር ከኢትዮጵያዊነት አይልቅም እያለ እንዲኖርም የሆነው በዚህ ውስጥ በማደጉ ነው። ማንም ሰው አስተዳደጉን ይመስላል። ቤተሰቡንና አካባቢውንም እንዲሁ። ስለዚህም የዛሬ ልጆችም እየሆኑት ያሉት በአስተዳደጋቸው ውስጥ ያለፈውን ማንነት እንጂ በራሳቸው የፈጠሩትን ነገር አይደለም። እናም ልንፈርድባቸው አይገባም። ከዚያ ይልቅ ያቀሸማቸውን ስርዓት ንደን አገራዊ ፍቅራቸውን ልናጎለብትላቸው ያስፈልጋል ይላሉ።
አስተዳደግ በዘመን፣ በስርዓት ይወሰናል። ምክንያቱም እነዚህ ነገሮች ትልቅነትም፣ ትንሽነትም ናቸውና። በእነርሱ ዘመን ገንዘቡ ትንሽ ቢሆንም በትንሹ የሚኖርበት በመሆኑ እንደ እርሳቸው ያሉ ሰዎችን በማርና በወተት ያሳድጋል። ስርዓቱም መልካም በመሆኑ ስነምግባሩ የተበላሸ ሰው ከብዙ በጥቂቱ ነው የታየው። ማክበር መከባበር ትልቅ ቦታ ይሰጠዋል። ግዴታን እንጂ መብትን ብቻ የሚያይም ብዙ ሰው የለም። በአገር ጉዳይም ማንም ድርድር ውስጥ አይገባም። ይህ ደግሞ ቤተሰብ ራሱ ጸንቶ ለልጆችም እንዲተርፍ ያደርጋል። አዲስ ትውልድን በአገር ወዳድነትም ይፈጥራል። ዛሬም መሆን ያለበት ይህ ነው ይላሉ።
በዘመኑና በስርዓቱ የተሰቃየውን ትውልድ ተስፋ ቆርጦ የዛሬ ልጅ ከማለት ይልቅ ተስፋ ሰጥቶ የነገዋ የአገሬ ልጅ ማለት ያስፈልጋል የሚሉት ባለታሪካችን፤ ዛሬ የኢትዮጵያ ስም ሲጠራ ነፍሱን ሳይሳሳ እየገበረ ያለው ወጣት ትናንት የተነገረው ነገር እንዳለ ማመን ተገቢ ነው። ውስጡ የተቀመጠ የአገር ስሜት አለ። ስለሆነም ተወቃሽ እንዳንሆን እኛ በወደድነው ልጅነት እኩል የዛሬን አገር ተረካቢ ዜጋ ማሳደግ እንደሚገባ ያሳስባሉ።
የመሪ እንጂ የተመሪ መጥፎ የለውም። ለዚህም ማሳያው መለስ ዜናዊ ሲሆን፤ ‹‹እስካልተያዘ ድረስ፣ መስረቅም ሥራ ነው›› የሚል መሪ ነበር። በዚህ ደግሞ ትውልዱ አገር ወዳድ ሳይሆን ሰርቆ የሚኖር ሆኗል። ምክንያቱም ልጆች ያልናቸውን፣ የነገርናቸውን ነው የሚሆኑት። እናም ለዛሬው ትውልድ ሰርቶ የሚያሳይና ንግግሩን በተግባር የሚለውጥ ሰው ወይም መሪ ያስፈልገዋል። ስለዚህም ዘመንን የሚለውጠው ሰው ነውና አሁን ያለውን ዜጋ ኢትዮጵያዊ ማድረግ ለነገ መባል የለበትም፤ ወላጆችና መሪዎች ይህንን ማድረግ የውዴታ ግዴታቸው እንደሆነ ሊያስቡ ይገባልም ብለዋል።
ትምህርት
ከትምህርት ጋር የተተዋወቁት በአገራችን እንደተለመደው በቄስ ትምህርት ነው። እስከ ዳዊት ድረስ ተምረዋል። ከዚያ ዘመንኛውን ትምህርት እንዲቀላቀሉ ሆነዋል። ይህም ኮከበ ጽባሕ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ሲሆን፤ እስከ ስምንተኛ ክፍል ተከታትለውበታል። ቀጥሎ ያለውን ክፍል የተማሩት ደግሞ በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ነው። እስከ አስረኛ ክፍል በዚያ ቆይተዋል። ከአስረኛ ክፍል በኋላ የውትድርና ትምህርትን እንጂ ሌላ አልቀጠሉም።
ሻምበል አበበ ወታደር መሆንን ገና በልጅነታቸው የሚያልሙት ጉዳይ ነው። ስለዚህም በትምህርታቸው ምንም እንኳን ጎበዝ ቢሆኑም መቀጠል አልፈለጉም። ውትድርና ውስጥም ብዙ የሚቀስሙት ልምድና ትምህርት እንዳለ ያምናሉና ከጓደኞቻቸው ጋር በመሆን ሙያውን ተቀላቀሉት። ውትድርና በራሱ ጥበብ ነው፤ ሳይንስም ነው። ከተራ እግረኝነት ጀምሮ ያለ ትምህርት የሚሆን አንዳች ነገር የለበትም የሚለውን ነገርም በአግባቡ የተረዱት ከገቡበትና ትምህርቱን እየተማሩ የሻምበልነት ማዕረግን እስከተቀዳጁ ድረስ ነው።
ሕክምና ያልተማረ ሀኪም እንደማይሆን ሁሉ ውትድርናውን ያልተማረም እንዲሁ ወታደር ሊባል አይችልም። ምክንያቱም መተኮስም ሆነ ተራራ መውጣት ይከብደዋል፤ ሳይበላ መቆየትና በጥበብ መራመድም አይሳካለትም የሚሉት እንግዳችን፤ ከፍተኛ የሕይወትም የሳይንስም ትምህርት የሚሰጥበት ቦታ እንደሆነ ገና የመጀመሪያ ስልጠና ሲወስዱ እንዲረዱት ሆነዋል። የቅየሳ ትምህርትን ተምረው ቀያሽ መሆን ችለዋልም።
በውትድርናው ዘርፍ ቀያሽነት ብዙ የሚያለፋ ነው። ካርታና መሬትን በሚገባ ማዋሃድን ይጠይቃል። ለድልና ለሽንፈትም ወሳኝ ጉዳይ እንደሆነ ይታመንበታል። ምክንያቱም ወታደር ለመተኮስ ይህ ነገር ከሌለው በፍጹም ጉዞው ሊሳካለት አይችልም። እናም እርሳቸው ይህንን ትምህርት ወስደው በሥራው ላይ መሰማራታቸው እጅጉን እንደሚያስደስታቸው ይናገራሉ።
በውትድርና ጉዞ ውስጥ ሌላው ተማርኩት የሚሉት ነገር ትችላለህ አይባልምና ሁሌ ወደፊት መጓዝን ነው። ሌሎችን በልጦ ለመገኘት መሥራትንም እንዲሁ። አልችለውም የሚል ነገርም በውስጣቸው እንዳይኖር አግዟቸዋል። በዚህም ከተራ ወታደርነት እስከ ሻምበልነት ሲሸጋገሩ ይህንና መሰል ትምህርቶችን ቀስመው ነው። በተለይ መድፈኛው ላይ ሲገቡ የሚወሰዱ ትምህርቶችን ሲያስታውሱ እጅግ ከባድ እንደነበር አይረሱትም።
የውትድርና ጉዞ
ከቤተሰብና ከአካባቢ ማህበረሰብ ቀጥሎ በስነምግባር ኮትኳቹ ወታደር መሆን ነው። ከተራ ወታደር እስከ ጀነራል ድረስ ያሉ ወታደሮች እንደየማዕረጋቸው ሁሉም በውትድርና ሕይወት ውስጥ የራሳቸውን አሻራ ያኖራሉ። ሁሉም ወታደር ለመሆን አቅም ይፈጥራሉ፤ አገራዊ ስሜትንም ይሰጣሉ። ከሁሉም በላይ ደግሞ ቤተሰባዊ ፍቅርን፤ ወንድማማችነትን ይመግባሉ። ይህ ደግሞ ዘላለም ወታደር መሆንን ያስመኛል። እኔም ረጅሙን እድሜዬን በዚያ ያሳለፍኩት ይህ ስለሆነልኝ ነው ያሉን ባለታሪካችን፤ ውትድርናውን የተቀላቀሉት የተፈሪ መኮንን ተማሪ እያሉ ነበር።
የ10ኛ ክፍል ውጤት ለመቀበል ሰኔ ላይ ተገናኝተው ሳለ ጓደኞቻቸው ውትድርና ተመዝግበው ሊሄዱ እንደሆነ ሰሙ። ትተዋቸው ይህንን በማድረጋቸውም ተናደዱባቸው። በእርግጥ እነርሱ ምክንያት ነበራቸው። አክስታቸው ጋር ተንደላቀው እየኖሩ ስለነበር ይዘምታሉ ብለው አልገመቱም። በዚህም ለመሰናበት እንጂ ፍላጎታቸውን ለመጠየቅ አልነበረም የነገሯቸው። በአገር ፍቅር ውስጣቸው የነደደው ሻምበል አበበ ግን በሁኔታው ተበሳጩ። የመመዝገቢያ ቦታው የት እንደሆነም ጠየቋቸው። ጊዜ ሳይፈጁም አብረዋቸው ሄደው ተመዘገቡ። ፈተናውንም በጥሩ ውጤት አልፈው የተለያዩ ምርመራዎችን በማድረግ በመጨረሻዋ ቀን አለፉ። የተመኙትን ሙያም ተቀላቀሉት።
ውትድርናውን ቤቴ፣ ኑሮዬ ብለው የጀመሩት እንግዳችን፤ በ17 ዓመታቸው በ1960 ዓ.ም የክቡር ዘበኛ መድፈኛ ሻለቃ አባል ሆነውም ነበር የመጀመሪያ ሥራቸውን የጀመሩት። ከዚያ ቀያሽ ሆነው ማገልገላቸውን ቀጠሉ። ሱማሌ ኢትዮጵያን ስትወር ደግሞ የክቡር ዘበኛ ወታደሮች እንዲዘምቱ በመደረጉ ከዘመቱት መካከል አንዱ ሆነው በባሌ በኩል ዘመቻውን ተቀላቀሉ።
እስከ ኤርከሬ ድረስ በመሄድም ተዋግተዋል። በተለይ ከሐረር ወደ ባሌ ያሉ መስመሮችን በትንሽ ኃይልም ቢሆን ለማሸነፍ የቻሉ እርሳቸውን ጨምሮ የዘመቱ ጓዶቻቸው ናቸው። ከሦስት ሺህ በላይ የሚሆኑ ጠላቶችን በ34 ሰው ተዋግተው ማሸነፋቸው ዛሬ ድረስ ኢትዮጵያዊያን ምን ያህል ቆራጥና ጠንካራ እንደሆኑ የሚያስታውሳቸው እንደሆነ አጫውተውናል።
በሱማሌ ጦርነት የማያውቋቸውን የጦር መሳሪያዎች ጭምር እንደማረኩ የሚገልጹት እንግዳችን፤ ጥይት ያለአግባብ መተኮስ ትልቅ ዋጋ እንደሚያስከፍል ቢረዱም አር.ፒ.ጂ በሚባለውና በማይታወቀው የጦር መሳሪያ ብዙዎችን ሊያደበያቸው እንደሆነ ሲያውቁ ሳይፈቀድላቸው መትተው እንደጣሉትና ጦሩን እንደበተኑት ያስታውሳሉ። ለዚህ ደግሞ ምስጋና እንደተቸራቸው አይረሱትም። ከዚያ ጉዟቸው በመድፍ መቀጠል ስላለበት መድፉን ለማምጣት ወደ አዲስ አበባ ተመልሰዋል። ይሁን እንጂ ዳግም ወደ ጦርነቱ የመሄዱን እድል አላገኙም። ምክንያቱም የመኮንንነት ኮርስ አልፈዋልና ትምህርት ሆነ ሥራቸው።
በ1970 ዓ.ም በምክትል መቶ አለቅነት ዲፕሎማቸውን ካገኙ በኋላ ደግሞ በቀጥታ አራተኛ መድፈኛ ብርጌድ 43ኛ መድፈኛ ሻለቃ ዘጠነኛ ባትሪ አዛዥ ሆነው በአዋሽ አርባ እንዲሠሩ ሆኑ። ይህ መደብ የአራት መድፎች አዛዥ ማለትም ነው። እናም ቦታውን ሳይለቁ ለሰባት ዓመታት በአዛዥነት ሠርተዋል። መድፈኛን ይዘው ሲዘምቱም ከእሙን ሀጀር የኤርትራ ድንበር እስከ ከረን ድረስ በሚጓዙበት ጊዜ መኪና የሚባል ነገር ስለሌለ በእግራቸው ሦስት ወር ተጉዘዋልም። ይህ ሲሆንም ከውጊያ ጋር ጭምር እንደነበር ያስታውሳሉ።
በውትድርና ሕይወት ውስጥ የሚሠራ ማንኛውም ተግባር ጠላትን አባሮ ከመያዝ ጋር የተቆራኘ ነው። ነገር ግን ደስታን ለራስ እየፈጠሩ የሚሠራ በመሆኑ ሁልጊዜ ማድረግን ያስመኛል። በተለይም ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎቹ ለእርሳቸው ልዩ ስሜት ቀስቃሽ እንደነበሩ አይዘነጉትም። ስፖርተኛ የሆነ ሰው አይደክምም የሚል ብሂል ያላቸውም ለዚህ ነው። እርሳቸው ገና ከልጅነታቸው ጀምሮ የቤት ሥራ እንደተሰጣቸው ያውቃሉ። ምክንያቱም በዚያን ጊዜ እዚያ ግቢ ውስጥ ለምን እንደተቀመጡ ሲነገራቸው ‹‹የአባቶቻችሁ ምትክ ትሆናላችሁ፤ የአገር መከታ፤ ከለላና ጠበቃ የምትሆኑት እናንተ እንጂ አባቶቻችሁ አይደሉም። እነርሱ ዛሬን ጠብቀው ለእናንተ አውርሰዋል። እናንተ ደግሞ ከዛሬ ጀምራችሁ ነገን ጠብቃችሁ ለተተኪው ታስረክባላችሁ›› ይባላሉ። ስለዚህም ያ ህልማቸውና አደራቸው ወደ ውትድርናው እንዳስገባቸውና እያንዳንዱን ተግባር ሲከውኑም ያንን እያሰቡ መሆኑን ያስረዳሉ።
ኢትዮጵያ በጠንካራ ዲሲፕሊን ነገር ግን በአነስተኛ ኃይል ማሸነፍን ለአለም ያስተማረች እንደሆነች አድዋ ምስክር ነው የሚሉት ሻምበል አበበ፤ በውጊያ መደሰት የሚችለው ጀግና ብቻ ነው። የኢትዮጵያ ሰራዊት ደግሞ ይህ ባህሪው ነው። ጀግና በጦርነት እንደማይሸነፍ በተለያዩ አውድማዎች አሳይቷል። ድልን ይለብሳል እንጂ ሽንፈትን አይከናነብም። ብዙ በደልና ስቃይ ደርሶበት ‹‹በኢትዮጵያ አምላክ›› ከተባለ ሁሉን ነገር የሚረሳም ነው። ምክንያቱም አገሩ ለእርሱ ሁሉ ነገሩ ናት። አገሩ እናቱ ናት፤ ሊደራደርባት፣ ሊቀልድባት አይችልም። ስለዚህም ሰራዊቱ “እኔ ብሞት የተረፈው ለአገር ይኖራል” የሚል ተስፋ ያለው እና ለተተኪ ትውልድ የሚያልም ዜጋ ነው። በመመታታቸው ወደ መሀል አገር እንዲቀየሩ የተደረጉት ሻምበል አበበ፤ በቦርድ ተወስኖ እንዲወጡ ታዞ እንደነበር ያስታውሳሉ። ይሁን እንጂ ጠንካራ ዶክተር ስለገጠማቸው ከሦስት ጊዜ ቀዶ ህክምና በኋላ በአመራርነት እንዲሰሩ እድል ተሰጣቸው። በዚህም አገራቸውን ወደማገልገሉ ዳግም ተመለሱ። አዲስ አበባ ላይ በተለያዩ ክፍሎች ተዘዋውረው እንዲያገለግሉም ሆኑ። መጀመሪያ ምድር ጦር ማመላለሻ ውስጥ በትራንስፖርት ስምሪት ኃላፊነት ሠሩ። ከዚያ ምዕራብ እዝን በመቀላቀል በብርጌድ ምክትል አዛዥነትና በመድፈኛ አስተባባሪነት እንዲሰሩ ሆነ። ቀጥለው ደግሞ በደቡብ እዝ በኩል ኤርከሌ የሚባል ቦታ ላይ አሁንም በብርጌድ አዛዥነት ወደማገልገሉ ገቡ።
በሥራቸው የሚያውቋቸውና ብቃታቸውን የሚረዱ የቀድሞ አዛዣቸው እንፈልግሀለን በሚል ወስደዋቸው ሻኪሶ ለገደንቢ የወርቅ ፋብሪካን የጥበቃ አስተዳደሩን በብርጌድ ደረጃ በኃላፊነት እንዲመሩ ተደርገዋልም። እስከ 1983 ዓ.ም ድረስም ቦታውን በሚገባ አስጠብቀዋል። ጦሩ በሚሸሽበት ጊዜ ሳይቀር እርሳቸው የአገሬን ሀብት አላዘርፍም በሚል ጠብቀዋል። ብዙ ችግር እየደረሰባቸውና ቤትና ሀብታቸው ሲዘረፍ እንኳን ሳያስተውሉት ቆይተዋል። በዚህም የምስጋና የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል። ያው የኢህአዴግ ነገር የውሸት ሆነ እንጂ።
ህወሓት እንደእርሳቸው አይነት የአገር ጠበቃን የማይፈልግ መሆኑን ያዩት ገና ከመግባቱ ጀምሮ ነበር። ምክንያቱም ቦታውን ለመያዝና የኢትዮጵያን ሀብት ንብረት ለመዝረፍ አዕምሮህን አሳርፍ በሚልም ማባበያ ወደ ሆለታ ልከው እንዲለቁ አድርገዋቸዋል። ከዚያም አልፈው እንዳይቃወሙዋቸው ወህኒ አውርደው ለስድስት ወር ያህል አሰቃይተዋቸዋል። ይህንንም ሲያስረዱ እንዲህ ነበር ያሉን ‹‹ኢህአዴግ በተለይም ህወሓት የአገሬን ንብረት በመጠበቄ በጣሙን ተናዶብኛል፤ በአንድ በኩል ለእርሱ እንዳስረከብኩት ሲረዳ አመስግኖኛል። ነገር ግን ምስጋናውን የመለሰው እኔን በማሰቃየት ነበር። ሁኔታውን ስለምረዳበት ሊገለኝም ይፈልጋል። በዚህም እረፍት ያስፈልግሃል በሚል ሰበብ ጦላይ ወህኒ ቤት ነበር ያወረደኝ። ተመልሰህ ትሰራለህ ብለውኝ ነበርና ጠይቄያቸዋለሁ። ማንም ግን ሊያቀርበኝም ሆነ ሊያየኝ አልወደደም።››
በሕወሓት ሴራና አድራጎት ራሳቸውን እስከማጥፋት ድረስ አስመኝቷቸው እንደነበር የሚያነሱት እንግዳችን፤ ሁልጊዜ ለአገሩ መልካምን የሚመኝ ሰው ወድቆ አይወድቅም። የኢትዮጵያ አምላክ ነገሮችን ያመቻችላቸዋል ይላሉ። ለዚህም በአብነት የሚያነሱት እርሳቸውን ከሞት ያተረፋቸውን ሰው ነው። ሰውዬው የትናንቱን አስታውሶ ነው የደገፋቸው። እርሱ በሚማርበት ጊዜ እርሳቸው ድንበር አካባቢ ይሰሩ ነበርና ትንሽ ሳንቲም ይሰጡታል። ግን አያስታውሱትም እርሱ አላቸው እንጂ። እናም ኑሮውን አሜሪካ አድርጎ ለመዝናናትና ቤተሰቡን ለማየት ሲመጣ በአጋጣሚ አገኛቸው። ከነበሩበት ስሜት እስኪወጡ ድረስም ሳይመለስ ጠበቃቸው። በዚህም ተስፋቸው ለመለመ። ዳግም መሥራትን የተመኙትም ከዚህ በኋላ ነው።
ሰውዬው ወደ አሜሪካ ከተመለሰ በኋላ በቀጥታ የጥበቃ ሠራተኞች ኃላፊ ሆነው በራሳ አምባ ሆቴል የተቀጠሩት ሻምበል አበበ፤ 20 ዓመታትን ከሥራ ሳይርቁ አሳልፈዋል። ይህ ሲሆን ቤተሰብ አጥተው አልነበረም። ባዶ እጃቸውን መጠጋት ውርደት ስለመሰላቸው እንጂ። በዚያ ላይ ወታደር ቶሎ እጅ አይሰጥም የሚል አቋም አላቸው። እናም ሽንፈታቸውን በውስጣቸው ይዘው መሥራት የሌለባቸውን ሥራ ወደማከናወኑ ገቡ። ይሁንና ቦታው ላይ ብዙም እድገት አለመኖሩና ያሰቡት ላይ አለመድረሳቸው ደስተኛ አላደረጋቸውም። በዚህም ቦታውን ለቀቁና ለተወሰኑ ወራት ሌላ ሥራ እያፈላለጉ ተቀመጡ።
‹‹ሳይደግስ አይጣላ›› እንዲሉ ሆነና ነገሩ በአንድ አጋጣሚ ነገሮች የተቀየሩላቸው ሻምበል አበበ፤ ከአራት ዓመታት ቆይታ በኋላ አንድ ስልክ ተደወለላቸው። አቶ ይላቅ ይባላሉ። ወንድማቸው አንተነህ ኃይሌ እርሳቸውን ማገዝ እንደሚፈልጉ ለመግለፅ ነበር የደወሉላቸው። አንተነህን የሚያውቁት ራስ አምባ ሆቴል ጥበቃ ሆነው በሚሰሩበት ወቅት ነው። ወታደር መሆናቸውን ሲያውቅ ያሉበት ቦታ በጣም ያናድደው ስለነበር ከዛሬ ነገ ተሳክቶልኝ አግዛቸዋለሁ ብሎ ያስባል። ነገር ግን ከአራት ዓመት በኋላ ነው ይህ እቅዱ የሞላለት። ቢሆንም እርሳቸው የነበሩበት ሁኔታ አሳሳቢ በመሆኑ የዛሬው ደራሻቸው ስለሆነላቸው እጅጉን አምላካቸውንም እርሱንም ያመሰግኑታል።
አንተነህ ‹‹እኔ ስማር እናንተ ነጻነቴ ነበራችሁ፤ አገሬን ተንከባክባችኋታል። ስለዚህም እኔም በተራዬ ለአገሬ የአገለገልኩ እንዲመስለኝ አንተን ልንከባከብህ›› በሚል ቋሚ ተቆራጭ ማድረግ እንደጀመረላቸው የነገሩን እንግዳችን፤ አሁን ኑሯቸውን እየገፉ ያሉትም በእርሱ እገዛ እንደሆነ አጫውተውናል። በሕወሓት በደል ቢደርስብኝም እንዲህ አይነት ሰዎችን አምላክ አበርክቶልን እየታገዝኩ በመሆኑ ደስተኛ ነኝ፤ ለአገሬ ያደረኩትም እየተከፈለኝ እንደሆነ ይሰማኛል ብለውናል።
ሰራዊቱ ለምን ፈረሰ
የኢትዮጵያ ሰራዊት የፈረሰበት ዋነኛ ምክንያት ዲስፕሊን ያለው፣ በጥሩ መኮንኖች የተማረና ኩሩ ኢትዮጵያዊ መሆኑ ለሕወሓት አሰራር ስለማይመቹ ነው። በተለይም በአገራቸው የማይደራደሩና የማይበገሩ መሆናቸው ስለሚታወቅ እነርሱን ዝም ማለት ሞታቸውን ማፋጠን እንደሆኑ ይገነዘባሉ። እናም ጭካኔ የተሞላ ተግባራቸውን በላያቸው ላይ በተደጋጋሚ እንዲፈጽሙባቸው ሆነዋል ብለውናል።
ሌላው ወያኔ የኢትዮጵያ ሰራዊትን ያሸነፈው በምን ሁኔታ እንደነበር ስለሚረዳ ነው። እርሱ ሰራዊቱን ያሸነፈው በሁለት ምክንያት ነበር። የመጀመሪያው ሕዝቡ ለውጥ ፈላጊ ስለሆነ የፈለገውን ስላመቻቸለት ሲሆን፤ ሁለተኛው መንግስቱን ለመገልበጥ በተለይም አለቆች ሹክቻ ውስጥ መግባታቸውና የእርስ በእርስ መጠላለፍ በመካከላቸው መፈጠሩ ነው። እናም በእርሱ ብቃትና ስሌት የሆነ ነገር ስለሌለ ይፈራቸዋል። በዚህም ሰራዊቱን ለማጥፋት ከ45 ዓመት በፊት አሲረውበታል። ለአገሩ የሚከፍለውን መስዋዕትነት ስለሚገነዘቡም እርሱን አጥፍቶ ኢትዮጵያን መዝረፍ እንዲችሉበት ሆነዋል። ሕወሓት ሰራዊቱን ቃል አክባሪ ለሙያው የሚሞተው እንደሆነ ጠንቅቆ ያውቀዋልና አፍርሶታል ይላሉ።
‹‹አገሬን ከአደጋ ስከላከል የሥርዓት እንጂ የክህደት ድርጊት ይመጣል ብዬ አልነበረም። ስርዓት በስርዓት ይለወጣል። ሁሉም ችግር ይኖርበታልና ያንንም ለማሻሻል አስፈላጊ ነው ብዬ አስብ ነበር። ሆኖም ሕወሓት ግን ይህ አልነበረም። አገር ማፍረስ የእርሱ ዘመቻ ነበር። በዚህም በተደጋጋሚ የአገሪቱን የጀርባ አጥንት የሆነውን ሰራዊት ብዙ ችግር አድርሶበታል። ዛሬም እያደረገ ያለው ይህንኑ ነው። አገር፣ ክብር፣ ባንዲራ የእርሱ አጀንዳ አይደሉም። ስልጣንና ብር ብቻ ነው ሕይወቱ። ስለሆነም ከማንም ጋር አብሮ ይህንን እስካገኘ ድረስ አድርግ የተባለውን ያደርጋል። ጭካኔዎቹም የመጡት ከዚህ መነሻነት ነው›› የሚሉት ባለታሪካችን፤ አሁን ሕዝቡ መረዳት ያለበት ሕወሓት ትናንትም ሆነ ዛሬ አንድ መሆኑን ነው። ሰራዊቱ ግን ከዚህ የተለየ ነው። ዝመት ሲባል ምንም የማያቅማማ፣ ለመሞትም ዝግጁ የሆነ ነው። ሕወሓት በእርሱ ላይ ያደረሰበትን ብቻ አይቶ ሳይሆን ለአገር አስፈላጊ እንዳልሆነ ስለሚያምን እርሱን ለመጨረስም ቁርጠኛ ነው። ስለዚህም ይህንን ተገንዝቦ እያንዳንዱ ዜጋ ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበትም ይናገራሉ።
ሕወሓት በማንኛውም ክልል ያልተገነባ ሰራዊት በክልሉ ላይ የገነባ ነው። ከተራ ወታደር እስከ ጀነራል ድረስ ማንኛውንም ኃላፊ በራሱ ቁጥጥር ሥርና የራሱን ብሔር አድርጎ ሲሠራ የቆየም ነው። በባድማ ዘመቻ ሰበብ እንዳንወረር በሚል ብዙ መሳሪያ ማከማቸቱ ከማንም የተደበቀ አይደለም። አሁን ዋጋ ለማስከፈልም የሞከረው ይህንን እቅዱን ሲከውን ማንም ስላልተረዳው ነው። ሰራዊቱንም ከማፍረስ እስከ መምታት የደረሰው ይህ ኃይል ስለነበረው ነው። ነገር ግን አሁን ነገሮች ተቀይረዋል። ሁሉም አውቋቸዋል። እየዘመተ ያለው የአገሬ ሰራዊትም ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ይህንን አስቦ ነው። ስልጣን ሳይሆን አገር፣ ብር ሳይሆን ክብር፣ የሚያሳስበው ዜጋና ሰራዊት አሁንም እንዳለ እያየንም ነው። በዚሁ ያጽናልን እንጂ ብለውናል።
መልእክት
ጀግና አይናገርም፣ አይለፈልፍም። ዶክተር ዓቢይም ያደረጉት ይህንኑ ነው። ሕወሓት ግን በወሬ ብቻ ዛሬ ድረስ እየኖረ ነው። ለዚህ ያበቃው ደግሞ ሳይማሩ ተምረሃል ብሎ ማዕረግ የሰጣቸው ጀነራልና ኮሎኔሎቹ ናቸው። አንድ ሰራዊት አንድ ማዕረግ ለማግኘት ቢያንስ ሰባት ዓመታትን ይፈጃል፤ ይማራልም። የሕወሓት ግን እቁብ እንኳን በማይደርስበት በሳምንት ውስጥ ይከናወናል። ስለዚህም አመራርም ሆነ አካሂድ እንዲሁም ስነምግባር ሊኖራቸው አይችልም። ድባቅ የመመታታቸው ምስጢርም ይኸው ይመስለኛል። አሁንም ቢሆን እነርሱ የዘረፉት ሀብት ንብረት ብቻ ሳይሆን ዶላርና ዩሮ በመሆኑ ያንን ማስረገፍና ለአገር ማድረግ ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ ሁሉም መረባረብ ይኖርበታል የሚለው የመጀመሪያው መልእክታቸው ነው።
ሌላው ያነሱት ነገር ኢትዮጵያን የሚያድናት ያልተማረ ገበሬ ጭምር እንደሆነ ነው። ምክንያቱም ዶክተርና ፕሮፌሰር ሆነው የሽግግር መንግስት እንመስርት በሚል ከጠላት ጋር የሚያብሩ መማር ብቻ ለአገር እንደማይፈይድ ያሳየናል። እናም እኛ አንጠቅምም ሳንል ማዕረጋቸውን አይተን ለእነርሱ ብቻ አሳልፈን ሳንሰጥ የድርሻችንን ማበርከት አለብን። ጁንታውና የአገር ከሀዲዎች ከጎናችን ስለሆኑም በተጠንቀቅ እያየናቸው አገራችንን አስበልጠን ይህንን ዘመቻ በድል ማጠናቀቅ ይገባናል የሚል ነው።
ኢህአዴግ ገዛ የሚለውን ሀሳብ እንደማይቀበሉት ያጫወቱን እንግዳችን፤ አገር ሲያፈርስ እንጂ አገርን ሲያሳድግ አልታየም። የራሱን ስልጣንም ሲያደላድል ነው የቆየው። በዚህም መሪ ሳይሆን አሳልፎ ሰጪ በሚለው እስማማለሁ። ከደርግ በኋላ በአገሩ የማይደራደር መሪ የመጣውና ከአፉ ላይ ጭምር የኢትዮጵያ ስም የማይጠፋው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓቢይ አህመድ ነው። ስለዚህም እንደ አጼ ሚኒልክ ምሎ አገሩን ለማዳን ተግቷል፤ ሳልሳዊ ምኒልክ ሆኖም ዳግማዊ አደዋን በቅርቡ ያሳየናልና ሁላችንም በቻልነው ልክ ልንደግፈው ይገባል ሲሉ ይመክራሉ።
ኢትዮጵያዊያን ኢትዮጵያዊ ያላደረጋቸው ሥርዓቱ እንደነበር ዛሬ ሆ ብለው በመነሳታቸው አሳይተዋል። ይህንን ልዩነት ማን እንዳደረገው ስለተረዱ ድሉን ለማግኘት እየተረባረቡ ነው። ድሉን ለማግኘት 64 ዓመት ድረስ ተብሎ ተገደበ እንጂ ዛሬ ባለው ሁኔታ እኔም ብሆን መግደል ባልችል መሞት እፈልግ ነበር። ስለሆነም እድሉ ያለው ሁሉ ኢትዮጵያዊ መሆኑን በተግባር የሚያሳይበት ጊዜ ላይ ስላለ ይጠቀምበት። በእምነትና በብሔር ከፋፍሎ መመደብ የሕወሓት ሥራ በመሆኑ ከእርሱ ወገን እንዳንሆን እንጠንቀቅ የሚለው ሌላው መልዕክታቸው ነው።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ታህሳስ 3 ቀን 2014 ዓ.ም