ምንም እንኳ ሀገር ሲወረር ፤ ሉዓላዊነት ሲደፈር ልዩነታችንን ትተን ቀፎው እንደተነካ ንብ በአንድነት መትመማችን የሚገባ ቢሆንም ፤ ወረራንና ጥቃትን እየጠበቅን አንድ የምንሆነው የታሪክ ልምምድ ምቾት አይሰጠኝም። አንድ ለመሆን መወረርና መደፈር አለብን ወይ የሚል ጥያቄ ያጭርብኛል ። በሰላሙ ጊዜ ለምን ለልማት ለለውጥ በአንድነት አንነሳም !? ከሀዲው ትህነግ የሰሜን እዝን ከጀርባው መውጋቱና መጠቃቱ፤ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦልም ቢሆን እወርዳለሁ ማለቱ ፤ የተናጠል የተኩስ አቁሙን እረግጦና እንደ መልካም አጋጣሚ ተጠቅሞ የታሪካዊ ጠላቶቻችንና የምዕራባውያንን ተልዕኮ በመቀበል በዴሞክራሲያዊ ምርጫ የተመረጠን መንግስት ለመለወጥ ወረራ በመፈጸሙ ፤ በሀገራችን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ከአማራ ጋር የማወራርደው ሒሳብ አለኝ በማለቱ በአንድነት እንድንቆም አድርጎናል። ሆኖም ሰላም ሲሆን“ የቱ ጋ ነበር ያቆምነው ? “ ብለን በይደር ወዳቆየነው የልዩነትና የጥላቻ አዙሪት የምንመለስ ከሆነ ለዚህ ሲባል ወረራንና ጦርነትን የሚሰራ ተቋም ወይም እንደ አፄ ልብነድንግል መሬትን 40 እየገረፈ ጦርነት አውርድ የሚል ንጉሱ ያስፈልገናል ማለት ነው።
ኢትዮጵያውያን ከሰላም ጊዜ ይልቅ በጦርነት ጊዜ አንድነታቸው ይበልጥ እንደሚጠነክር በሰሞኑ የሕግ የበላይነትና የህልውና ዘመቻ፤ በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት፤ በሶማሊያ የሲያድባሬ ወረራ፤ በጣሊያን ሁለተኛ ወረራ፤ በአድዋ ጦርነት፤ ወዘተረፈ ተመልክተናል። የታሪክ ዳናዎቻችን ሺህ አመታት ወደኋላ ተመልሰን ብንከተል ሀቁ ከዚህ የተለየ አይሆንም። በአብዛኛው በችግር በተለይ በጦርነት ጊዜ የማንኛውም ሀገር ዜጋ ልዩነቱን ወደጎን ብሎ በአንድነት ከባንዲራው ከመሪው ጀርባ ይሰለፋል። ይሁንና ሰላም ሲሆን ወደጎን ወዳቆየው ልዩነት ይመለሳል ማለት አይደለም።
ሆኖም በመንግስት እንዝህላልነት፣ ከፋፍሎ ለመግዛትና ስልጣን ላይ ለመቆየት ካለው ፍላጎት እና የሕዝቡን አንድነት የሚያዘልቁና የሚያጸኑ ስትራቴጂካዊ ተግባራትን ባለማከናወኑ ፤ በልሒቃን በተለይ በፓለቲካ ልሒቃን ስውር ፍላጎት የተነሳ ፤ በመደበኛና በማህበራዊ ሚዲያ በሚከሰቱ መጓተቶችና ጽንፍ ረገጥ ሚዲያዎች ሳቢያ ፤ ወዘተረፈ የሀገርና የሕዝብ አንድነት ወደ ኋላ ሊንሸራተት ይችላል። በአንጻሩ እነዚህ አካላት ወይም ተቋማት በቅንጅት ለአንድነት ከተነሱ ሀገራዊ አንድነቱን እንደ ብረት እንደሚያጠነክሩት የታሪክ ድርሳናት ያትታሉ ።
የንጉስ ምኒልክ ወደዙፋኑ መቃረብ ያስደሰተው የጣሊያን ወኪል ፔትሮ ኢንቶኔል ግንኙነቱን በፊርማ ለማረጋገጥ ሚያዚያ መገባደጃ ላይ በ1881 ዓ.ም ውጫሌ ላይ የሁለትዮሽ ስምምነት ለመፈራረም በቃ ። ዳሩ ግን ውሎ ሳያድር የስምምነቱ አንቀፅ 17 ውዝግብ አስነሳ ። በዚህ አንቀፅ የጣሊያንኛ ቅጅ መሰረት ኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነቷን የምታደርገው በጣሊያን በኩል እንደሆነ የሚያስገድድ መሆኑ በተዘዋዋሪ ሀገሪቱን በጣሊያን ሞግዚትነት የምትተዳደር ያደርጋታል ። የአማርኛው ቅጅ ግን የውጭ ግንኙነት ማድረግ ትችላለች ይላል። በስምምነቱ አንቀፅ 19 ላይ የአማርኛና የጣሊያንኛ ቅጅዎች እኩል ተቀባይነት እንዳላቸው መደንገጉ አለመግባባቱን አካረረው።
በ1887 ዓ.ም በወርሀ መስከረም በገበያ ቀን ቅዳሜ አፄ ምኒልክ ታሪካዊውን የ “ ወረኢሉን “ ክተት አዋጅ አስነገሩ። “ …ሀገርንና ሀይማኖት የሚያጠፋ ጠላት ባሕር ተሻግሮ መጥቷል ። እኔም የአገሬ ሰው መድከሙን አይቼ ብታገሰውም ፤ እያለፈ እንደ ፍልፈል መሬት ይቆፍር ጀመር ፤ አሁን ግን በእግዚአብሔር እርዳታ አገሬን አሳልፌ አልሰጠውም።
ያገሬ ሰው ጉልበት ያለህ ተከተለኝ ፤ ጉልበት የሌለህ በጸሎትህ እርዳኝ ፤ …” አዋጁን ተከትሎ በአፄ ምኒልክ አዝማችነት ፣ ከመላው ሀገሪቱ በከተቱት መኳንንትና መሳፍንት ባለሟልነት ከ100ሺህ በላይ ወዶ ገብ የገበሬ ጦር እና 29ሺ ፈረሰኞች በኢትዮጵያዊ አንድነት ፣ ጀግንነት ፣ ቆራጥነት ፣ አልበገር ባይነት፤ ዳርድንበሩን ፣ ሉዓላዊነቱን ሊያስከብር ቀፎው እንደተነካ ንብ ወደ ሰሜን ተመመ ። በዚህም ታላቁ ፣ አኩሪውና አንጸባራቂው የሰው ልጆች በተለይ የጥቁር ሕዝቦች ሁሉ ድል የሆነው አድዋ እውን ሊሆን ችሏል። ድህረ አድዋ በኢትዮጵያውያን ዘንድ አንድነትን ከመፍጠሩ ባሻገር ሀገሪቱን በወቅቱ ከነበረው ቴክኖሎጂ ጋር እንድትተዋወቅ በር ከፍቶላታል። ድሉ ያስገኘው እውቅና እና ክብር ከውጭ ሀገራት ጋር ሰፊ ግንኙነት እንዲመሰረት ረድቷል። ይህን ተከትሎ ለዘመናዊ አሰራርና አስተዳደር እርሾ የሆኑ ተግባራት እንዲከናወኑም አስችሏል።
ከዚህ ባሻገር በጭቆና ቀንበር ይማቅቁ የነበሩ የሰው ልጆችን በተለይ ጥቁሮችን ለጸረ ጭቆና ትግል ከማነሳሳቱ ባሻገር ። ለፓን አፍሪካኒዝም ፣ ለብላክ ኮንሽየስ፣ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት/ ለአፍሪካ ሕብረትና ሌሎች ንቅናቄዎች መሰረት በመሆን አገልግሏል። ካርል ማርክስ ታሪክ እራሱን ይደግማል እንዳለው ፤ የአሜሪካንንና የምዕራባውያንን አይን ያወጣ አዲስ የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ በመቃወም “#በቃ !#No more !” የሚል አለማቀፍ ንቅናቄ ተፈጥሯል። በሀገር ውስጥ ግን የቅድመም ሆነ ድህረ አድዋን አንድነት ማዝለቅ ፣ ማጥለቅና ማስፋት ላይ ውስንነት መኖሩን ከንጉሱ ሞትና ከልጅ እያሱ መምጣት በኋላ የተፈጠሩ ልዩነቶችን በአብነት ማንሳት ይቻላል። አሁንም ይሄን ታሪካዊ ስህተት በመድገም ታሪክም ትውልድም እንዳይወቅሰን መጠንቀቅ አለብን ። ከዚህ በላይ ለመሔድ ግን ዘመነ ጓዴነት / ኮንቴምፓራሪነስ/ ይገድበኛል።
በሁለተኛው የጣሊያን ወረራ ኢትዮጵያውያን ምንም እንኳ እንደ አድዋው ባይሆንም ወረራውን ለመቀልበስ ዳር እስከ ዳር በአንድነት ተነቃንቋል። ሆኖም በተፈጠሩ ወታደራዊ ስህተቶች እና ጣሊያን ዘመናዊና የኬሚካል ጦር መሳሪያ እስከ አፍንጫው ታጥቆ ስለነበር ጦሩ ሊፈታና ጃንሆይም መንግስታቸውን ይዘው ወደ እንግሊዝ ሊሰደዱ መንስኤ ሆኗል።
ያፈገፈገው ጦርና አርበኛ እንደገና ተደራጅቶ፤ ጣሊያን የቆየባቸውን አምስት አመታት ሲዖል አድርጎበታል ። በመጨረሻም በእንግሊዝ ድጋፍና በጀግኖች ተጋድሎ ፋሽስት ጣሊያን ተጠራርጎ ሊወጣ ችሏል። ከስደት የተመለሰው የግርማዊነታቸው መንግስት አጋጣሚውን በመጠቀም የተፈጠረውን አንድነት ከማጠናከር ከማዝለቅ ይልቅ ፤ በዱር ገደሉ ከወራሪው ጋር እየተዋደቀ ሀገር ያቆየውን አርበኛ ከመሾም ከመሸለም ይልቅ በአምስት አመቱ የጣሊያን ቆይታ ለጣሊያን አድረው ሀገር የከዱ ባንዳዎችን በመሾማቸው እና በመንግስታቸውም ለውጥና ማሻሻያ ያደርጋሉ ተብሎ ሲጠበቅ በዛው በመቀጠላቸው መጨረሻቸው እንዳያምር ከማድረጉ ባሻገር ሀገሪቷንና ሕዝቡን ለወታደራዊ አስተዳደር ደርግ እና ዛሬ ለምንገኝበት ምስቅልቅል ዳርጓታል።
ደርግ ወደ ስልጣን እንደመጣ መሬት ላራሹን በማወጅ እና ጊዜያዊ ማሻሻያ በማድረግ ያገኘውን ተቀባይነት ማጣት በጀመረበት ሰዓት ፤ በእብሪተኛው የወቅቱ የሶማሊያ ገዢ ዚያድባሬ ታላቋን ሶማሊያ እመሰርታለሁ በሚል የቀን ቅዠት ፤ የኢትዮጵያ አንድነት በውስጥ ተቃውሞና በሻዓብያ የትጥቅ ትግል ተዳክሟል በሚል የተሳሳተ ግምገማ በተወሰደ ውሳኔ የሀገራችንን ድንበር ጥሶ እስከ መሀል ሀገር 700 ኪሎ ሜትር ዘልቆ በወረረን ጊዜ መላው ኢትዮጵያዊ ከየማዕዘናቱ የሀገሩን ዳር ድንበርና ሉዓላዊነቱን ለማስከበር ተመመ። በጥቂት ወራት ወታደራዊ ስልጠና የእብሪተኛውን የዚያድባሬ ጦር አይቀጡ ቅጣት በመቅጣት የግዛት አንድነቷን አስከብሯል።
ይሁንና ደርግ ይህን ሀገራዊ መነሳሳትና አንድነት ለብሔራዊ መግባባትና እርቅ ከመጠቀም ይልቅ ጠመንጃ ወደ ማምለክና ልዩነቱን ሁሉ በኃይል ጸጥ ለማድረግ በመንቀሳቀሱ መጨረሻው ምን እንደነበርና እርሱም ሀገሪቱን ለጠባቡና ቂመኛው ትህነግ አሳልፎ በመስጠት ለውርደት ዳርጓታል ። የሚያሳዝነው በእግሩ የተተካው ከሀዲውና እፉኝቱ ትህነግ ከደርግ ውድቀትም ሆነ ከራሱ ስህተት ለመማር ዝግጁ አለመሆኑ መጨረሻው የሽንፈት ከሉን መከናነብ ሆኗል።
ከሀዲው ትህነግ ከሻዓብያ ጋር በድንበር የተነሳ ወደ ጦርነት ሲገባ ፤ የሀገር ሉዓላዊነት ለአደጋ ሲጋለጥ፤ ሀገር ሲወረር ፤ ኢትዮጵያውያን ዳር እስከዳር በትህነግ ከፋፍሎ የመግዛት መርህ ፤ አድሎአዊና ኢፍትሐዊ በሆነ አገዛዙ ፤ በአፈናውና በጭቆናው ፤ በኤርትራ መገንጠል በነበረው ወራዳ ሚና ፤ አይን ባወጣው ዘረፋው ፤ ወዘተረፈ የተከፉና ያዘኑ ቢሆንም ከትህነግ ጋር የነበራቸውን የማይታረቅ ልዩነት አቆይተው ከጎኑ ተሰልፈዋል ። በነቂስ ተመዋል ። በከፍተኛ መስዋዕትነት የሀገር ዳርድንበርና ሉዓላዊነት ወደነበረበት ተመልሷል።
ሆኖም ትህነግ ይህን ሀገራዊ አንድነት ለጊዜያዊ ጥቅም እንጂ ለዘላቂ ሀገራዊ መግባባት ፣ መቀባበልና መቀራረብ ስለማይፈልገው ልጆቻቸውን ያጡ ወላጆች እንባ ሳይደርቅ ወደለመደው ከፋፍለህ ግዛው ፣ አፈናውና አድልዎ ተመለስ ። ከሀዲው ትህነግ ይህን መልካም አጋጣሚ ለሀገራዊ አንድነት ፣ ለብሔራዊ እርቅ ፣ ለለውጥና ለሪፎርም ቢጠቀምበት ኑሮ እንዲህ መውጫው ባልጠፋው ፤ ማጣፊያው አጥሮት አጥፍቶ ጠፊ ባልሆነ።
እንደ መውጫ
እፉኝቱና ከሀዲው ትህነግ በጾም ፣ በጸሎት፣ በልመና እና በምህላ በለኮሰው እሳት ተለብልቦ የውርደት ከሉን ተከናንቧል ።
በሰሜን ዕዝ የፈጸመው ክህደትና ግፍ በምንም ነገር የማይተመን ቢሆንም ሕግ የማስከበርና የህልውና ዘመቻው ሀገሪቱን እንደ መዥገር ተጣብቆ ደሟን ሲመጥ የኖረውን የትህነግን ስብስብ ግብዓተ መሬት በ51 ቀናት ለመፈጸም ምክንያት ከመሆኑ ባሻገር ተዳፍኖ የነበረውን ሀገራዊ አንድነት በመላው ሀገሪቱ አቀጣጥሏል። ይህ የግጭት፣ የልዩነትና የደባ ቀፍቃፊ እስከወዲያኛው መሸኘቱ ለሀገሪቱና ለሕዝቧ እፎይታ ከመሆኑ ባሻገር መጻኢ እድሏ ላይ አዎንታዊ ተፅዕኖ ይኖረዋል። የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትርንና የመንግስታቸውን የአመራር ጥበብና ብቃት እንዲሁም ተቋማት በእርግጥ እየተገነቡ መሆኑን በመከላከያ ሰራዊት ግዳጅን የመፈጸም ብቃትና ጀግንነት አረጋግጠናል ። ይህን ተከትሎ በሀገሪቱ የተፈጠረውን መነቃቃትና አንድነት መንግስት ፣ ልሒቃን ፣ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ መገናኛ ብዙኃን ፣ አክቲቪስቶች ግለቱን ጠብቆ በማስቀጠል ለዘላቂ አንድነትና ብሔራዊ መግባባት መሰረት መጣልና ተቋማዊ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።
ዲያቆን ዳንኤል ክብረት እንዳለው ድሉ ካጎናጸፈን ልዕልና እንዳንወርድ ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች ወደ መንደርና ጠባብ አስተሳሰብ ዝቅ እንዳይሉ እንዳሳሰበው፤ በዚህ አንጸባራቂ ድል ማግስት” ፖለቲካችን የቱ ጋ ነበር የቆመው !? “ ብለን ወደ ቀደመው የሴራ ፖለቲካ፣ አቅላይነት ፣ ጥላቻ ፣ ልዩነት፣ ጎጠኝነት፣ ምቀኝነት፣ መጠራጠር ፣ ዘረፋ ፣ ወዘተረፈ የምንመለስ ከሆነ ከታሪካችን አልተማርንም። ታጥቦ ጭቃ ፣ አድሮ ቃሪያ ነን ማለት ነውና ወደ ኋላ መመለስና መንሸራተት የለብንም ። የብልጽግና ስራ አስፈጻሚ አካታች ሀገራዊ ምክክር እንዲካሄድ በወሰነ ማግስት የሚንስትሮች ምክር ቤት የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የማቋቋሚያ አዋጅን ማጽደቁ መንግስት በገባው ቃል መሠረት አዲስ ምዕራፍ እያስጀመረ መሆኑን ተገንዝቦ በዚህ ልክ መገኘት ይጠበቅብናል።
ሀገራችን ኢትዮጵያ በሀቀኛ ጀግኖች ልጆቿ ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር !!!
አሜን።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ታህሳስ 3 ቀን 2014 ዓ.ም