አገር የእናት ተምሳሌት ናት። አገር ያለመስፈርት በሙሉ ልብ የምትወደድ የእናት አምሳያ ጌጥ ናት። የእናትና አገር ፍቅር አይለካም።ጥልቀትና ርቀቱም አይታወቅም።ማንም ጤነኛ አእምሮ ያለው እናቱ ምንም ትሁን ምን አክብሮ ያተልቃታል እንጂ ንቆ አያሳንሳትም። ለእናቱ ጀርባ አይሰጥም። በእናትህ ጉዳይ አይታክትም።
ለኢትዮጵያውያን ኢትዮጵያ እናት እና የህልውናቸው መሰረት ናት።እሷ ወድቃ እነርሱ አይቆሙም። እሷ እያዘነች እነሱ አይደሰቱምም።እሷን ረስተው እነርሱ አይታወሱም።እሷ ከሌለች የእነርሱ በሕይወት መቆየት ትርጉም አልባ ነው።
ለኢትዮጵያውያን አገራቸው የነፃነታቸው ምንጭ ናት። የሚኖሩት በእሷ ተከብሮ መቆየት ውስጥ ነው። እርሷ ሰላሟን አጥታ ሕሊናቸው አትረጋጋም። ኢትዮጵያ ጎድሎባት እነርሱ አይሞላላቸውም። እርሷ ዝቅ ብላ እነርሱ አይገዝፉም። የሚኖራቸው አገራቸው ሲኖራት ነው። ያለ ኢትዮጵያ የሚበሉት አይጣፍጣቸውም። የሚጠጡት አያረካቸውም።
አገር ውስጥ እንዳለው ሁሉ በውጭ የሚኖረው ኢትዮጵያዊም ከምንም በላይ የአገሩን ፍቅር በልቡ ይዞ የሚኳትንና በአካል ርቆ ቢገኝም በመንፈስ ሁሌም ኢትዮጵያ የሚገኝ ነው። አብዛኛው አገሩን የሚወድ፣አገሩ ተሻሽላና አድጋ ማየት የሚፈልግ፣አንድ ጠንካራ ኢትዮጵያ እንድትኖር ከልብ የሚመኝና ለዚያም የሚታገል ነው።ይህ ማለት ግን በዘርና በጎሳ ልክፍት የተለከፉት ከአሸባሪው ሕወሓት ዓላማ ጋር የሚመሳሰል ጸረ ኢትዮጵያና ጸረ ኢትዮጵያዊነት አቋም ያላቸው የሉም ማለት አይደለም፤እንዳሉ አይካድም።
ይሁንና ኢትዮጵያዊውን በአካል ከኢትዮጵያ ታወጣው እንደሆነ እንጂ ኢትዮጵያን ከኢትዮጵያዊው ውስጥ ማውጣት አይቻልም ፣ እውነተኛ ኢትዮጵያውያንም መቼም ቢሆን ለአገራቸው ያላቸው ፍቅርና አክብሮት የሚለወጥ አይደለም። ልባቸውን እንጂ ጀርባቸው ለኢትዮጵያ የሚሰጡም አይደሉም። እድገቷን እንጂ ዝቅታዋን፣ደስታዋን እንጂ ኃዘኗን፣ክብራን እንጂ ውርደቷን ፈፅሞ አይመኙም።
ይህ ስሜታቸውም በተለይ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ በግልፅ አደባባይ የታየ ነው። በዶክተር ዐቢይ አመራር በተመዘገቡ ለውጦች ምክንያት በኢትዮጵያና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን መካከል የነበረውን ርቀት በአስደናቂ ፍጥነት ጠቧል። በሁሉ ረገድ የሚያስተሳስር ድልድይ ተገንብቷል። በፖለቲካ ቅራኔ እና በተለያዩ ምክንያቶች ከአገሩ ጋር ተኳርፎ የነበረው የአገር ልጅ ኩርፊያው ሽሯል። ዳግም ከእናት አገሩ ጋር ያለው ትስስር ታድሷል።
በአሁን ወቅትም በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አገራቸውን በመደገፍ በጎ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ናቸው።
ከቀን ማኪያቶው ላይ እየቀነሱ ለአገራቸው ልማት በተለይም የሕዳሴው ግድብ ግንባታ ቀጥታ ድጋፍ እየሰጡ ናቸው።
አሸባሪው የሕውሓት ቡድንና ከውጭ አይዞህ የሚሉት አጫፋሪዎቹ ኢትዮጵያ ላይ የደቀኑትን አደጋ ለመቀልበስ በሚደረገው ትንቅንቅም በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሁለንተናዊ አበርክቶ እጅጉን የሚደንቅ ነው።
ለዚህ ሕዝባዊ ተነሳሽነት ሰሞኑን በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚደረጉ “no more” ወይንም ‹‹በቃን” በተሰኘው ከተማ አንቀጥቅጥ ሰላማዊ ሰልፎች በቂ ምስክሮች ናቸው። በእነዚህ ሰልፎች ላይ የኢትዮጵያውያን የአገር ፍቅር ሁሌ እንደጋለ ሳይቀዘቅዝ የሚኖር ፍም እሳት እንደሆነ፣ ኢትዮጵያውያንም አገራቸውን የነኩባቸው ዕለት ትንታግና አይነኬ አራስ ነብር እንደሚመስሉ፣በአገራቸው ለመጣ ሞትን እንደ ሰርግ እንደሚቆጥሩት አስመስክረዋል።
ኢትዮጵያ ላይ የተከፈተውን የሚዲያ ጦርነት ለመመከት የተለያዩ ቋንቋዎችን ተጠቅመው የአገራቸውን እውነታ በማስረዳት ኃላፊነታቸውን መወጣት ረገድ አስደናቂ ተጋድሎ እያስመለከቱ መሆናቸውም ፈፅሞ የሚዘነጋ አይደለም።
ይሁንና በተለይ በአሁን ወቅት ኢትዮጵያ ካለችበት ውስብስብ ችግር እንድትወጣ ሁለንተናዊ አስተዋፆአቸው ይበልጥ መጨመር ይኖርበታል። ድጋፎችም ከሰላማዊ ሰልፍ ባለፈ በኢኮኖሚ በተለይም ወደ ገንዘብ ድጋፍ ሊሸጋገሩም ይገባል።
እንደሚታወቀው፣የሰሜኑ ጦርነት ካደረሰው ሰብዓዊ ኪሳራ በተጨማሪ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በእጅጉ ፈትኖታል። እብሪተኛው ቡድንም በርካታ መሠረተ ልማቶችን አውድማል። ከዚህማ በላይ ግን ኢትዮጵያን ለመበተን የሚፈልጉ የውጭ ረጃጅም እጆች ኢኮኖሚውን ለማናጋት በየአቅጣጫው ተዘርግተዋል።
ይህ ሴራ ለመሻገር ታዲያ የሕልውና ተጋድሎውን በኢኮኖሚው ግንባርም መደገም የግድ ይላል። ወቅቱም የኢትዮጵያን ችግሮች የመሸሽ ሳይሆን የማሸሽ ተጋድሎን ይጠይቃል። በዚህ ረገድም በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሚና እጅጉን ወሳኝ መሆኑ አያከራክርም።
በርካታ አገራት በተለይ በቀውስ ወቅቶች የወጭ የሚገኙ ዜጎቻቸውን አቅምና ዕውቀት በመጠቀም ፈተናዎችን በቀላሉ መመለስ ችለዋል። ኢትዮጵያ ነገ ማሳመር የሚችሉት ደግሞ ኢትዮጵያውያን ብቻ ናቸው።
እድገቷም ውድቀቷም በልጆቿ እጅ ላይ ያረፈ ነው። በተለይ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን አገራቸው ከኢኮኖሚ ጥቃት ለመታደግ ከቀን ማኪያቶው መቀነስ ጀምሮ እንደ አቅማችሁ በመሳተፍ የአገሩ መከታ መሆናቸው ማስመስከር ይጠበቅባቸዋል።
አሁን ላይ እናት አገር ኢትዮጵያ እየተጣራች ነው። ልጆቿ አቤት በሏት። ለኢትዮጵያ ያላችኋት እናንተ ናችሁ። ለእናንተም ያለችው እርሷ ናት። ስንትኖሩላት ታኖራችኋለች። ስትዋደቁላት ታቆማችኋለች። ስትበረቱ ትበረታለች። ስትደክም ትጠነክራለች።
አሁን ላይ እናት አገር ኢትዮጵያ እየተጣራች ነው። ልጆቿ አቤት በሏት። ምሬቷን በሐሴት ቀይሩላት። መከፋቷን በደስታ ለውጡላት፡ ዝቅታዋን ለሚመኙ ከፍታዋን አሳዩላት። ወዟን ከሚነጥቁ ውበቷንም ከሚሰርቁ ታደጓት።
በኢትዮጵያ ለመጣ ምንም ነገር ወደ ኋላ አትበሉ። በክብሯ ሲመጡ በሰብዕናችሁ እንደመጡ አስቡ ። እርሷን የነካ አይናችሁን የነካ እንደሆነም እወቁ። አይናችሁን አታስደፍሩ።በአይን አይቀለድም። ለኢትዮጵያ አስተማማኝ ምርኩዝ ሁኗት። ኢትዮጵያ ካለ እኔና እናንተ አትበረታም። በነጻነት መቆም ከፈለግን በያለንበት አገራችንን አንጣላት።
የአውሮፓውያኑን አዲስ ዓመት በኢትዮጵያ ለማክበር ይፋ የሆነውን አንድ ሚሊዮን ዲያስፖራ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ወደ አገር ቤት እንዲገቡ የማድረግ ጥሪን ተቀብላችሁ ወደ አገራችን ለመግባት ሻንጣችሁን ከወዲሁ አዘጋጁ።
በተለያዩ አጋጣሚዎች ወደ አገር ቤት በመምጣት ከእናታችሁ ጎን ለመቆም ያልቻላችሁና በተለይ ለአገራችንም ሆነ ፣ለወዳጅ ዘመዱ ገንዘብ መላክ የፈለጋችሁም ገንዘብ በምትልኩ ጊዜ ሕጋዊ የገንዘብ ማስተላለፊያ አገልግሎቶችን ብቻ መጠቀም አትዘንጉ። ይህን አለማድረግ የጁንታውን ቡድን ማጠናከርና በአረመኔ ተግባርና ጥፋቶቹ እንዲገፋበት ምቹ ሁኔታን መፍጠር መሆኑን ተረዱ።
አገር ለመገንባትና ለማሻሻል ገንዘብ ብቻም በቂ አይደለም። ዕውቀት፣ቀና አስተሳሰብ፣አገር ወዳድነትን፣ጠባብነትን መቃወምና ማስወገድም ያጠቃልላል። እነዚህ ከገንዘብና ከነጻነት መቆም ጋር ሲደመሩ አገር ያድጋል፡ ይለማል፤የሕዝብ ኑሮ ይሻሻል።
እናት ኢትዮጵያ እየተጣራች ነውና በውጭ አገራት የምትኖሩ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች በተለይ በኢንቨስትመንት ዘርፍ በመሰማራት፣ የውጭ ኢንቨስትመንትን በመሳብ፣ የአገራቸውን የቱሪዝም መስህቦችና ምርቶች ለዓለም በማስተዋወቅና በሌሎችም መስኮች በመሳተፍ ለምትወዳት አገራችሁ ታሪካዊ አሻራቸውን የማሳረፍ ጊዜው አሁን ነው። ኤምባሲዎችና ቆንሲላ ጽሕፈት ቤቶች ይህንን ኃይል ከአገሩ ጋር ለማቆራኘት ለሚጠብቃቸው ሰፊ ሥራዎች ራሳቸውን ማደራጀትና ይህንን ማስተናገድና መሸከም የሚችል አቅም መገንባት ይጠበቅባቸዋል።
እናት ኢትዮጵያ እየተጣራች ነው። በውጭ አገራት የምትኖሩ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች አቤት በሏት። ቀና ብላችሁ ለመኖር ከሚያስጎነብሷት ሁሉ ጠብቋት።ይህን ስታደርጉ ኢትዮጵያን የተበተቡ ሰንሰለቶች ይበጣጠሳሉ። የተቆለለባት የሴራ ተራራ ይናዳል። የጨለማውን ዘመን አልፋ ብርሃን በእናት አገራቸው ጸዳል ላይ ያበራል።
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 3 ቀን 2014 ዓ.ም