አዲስ አበባ፡- የኢፌዴሪ እንባ ጠባቂ ተቋም በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተፈጠረውን የፀጥታ ችግር ተከትሎ የተፈናቀሉ ዜጎችን በዘላቂነት መልሶ ለማቋቋም እየተሰራ ያለው ሥራ በቂ አለመሆኑን አስታወቀ፡፡
የጎዳና ተዳዳሪዎችን ለመታደግ የሚደረገውም ኢኮኖሚያዊና ሥነ ልቦናዊ ድጋፍ ቅንጅት እንደሚጎድለው ገለጸ፡፡ ተቋሙ በተፈናቃዮችና በጎዳና ተዳዳሪዎች ላይ ባካሄደው የቁጥጥር ጥናት ግኝት ላይ ትናንት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት ባደረገበት ወቅት በተቋሙ የቁጥጥርና ጥናት ዳይሬክተር አቶ አዳነ በላይ እንዳሉት ፤ ከፀጥታ ጋር በተያያዘ የተፈናቀሉ ዜጎች በተለይም ልዩ ድጋፍ የሚሹትን በዘላቂነት ለማቋቋም ተገቢው ድጋፍ እየተደረገላቸው አይደለም፡፡
በጊዜያዊነት የሚደረግላቸው ድጋፍም ከአቅርቦትና ስርጭት ጋር በተያያዘ ክፍተት አለበት፡፡ እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፤በአሁኑ ወቅት የሱማሌ፤ ሀረርና ጋምቤላን ክልሎችን ሳያካትት በኢትዮጵያ 1 ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ተፈናቃዮች በሀገሪቱ ይገኛሉ፡፡ ከነዚህ ውስጥ በመጠለያ ካምፕ ሆነው ወደ ትውልድ ቀያቸው በመሄድ የሚረዱትን ጨምሮ አንድ ሚሊዮን ሃያ ሺ የሚደርሱት ወደቀ ዬቸው ተመልሰዋል፡፡ ለተመለሱትም ሆነ በመጠለያ ላሉት እየተደረገ ያለው የዘላቂ ማቋቋሚያ ድጋፍ ግን በቂ አይደለም፡፡
ዳይሬክተሩ በመፍትሄነት በመንግሥት በኩል የተቀናጀ ክትትልና ድጋፍ ማድረግ፡፡ ዩኒቨርሲቲዎች፤ የሃይማኖት አባቶችና የስነ ልቦና ባለሙያዎችም ድጋፍና ክትትል ማድረግ እንደሚጠበቅባቸውም ተናግረዋል፡፡ በተቋሙ የሕጻናት የሴቶችና አካል ጉዳተኞች ጉዳይ ስልጠና ባለሙያ አቶ አበራ ሕርቀታ ‹‹የጎዳና ተዳዳሪዎችን ለማቋቋም የሚሰራው ሥራ የተቀናጅ አለመሆኑን ጠቅሰው፣ እስካሁን ከሰባት ጊዜ በላይ ተነስተው የተመለሱ እንዳሉም አስታውቀዋል፡፡
በእቅዱ መሰረት ከ14 ዓመት በታች ያሉ ተደጋፊዎች ወደ ቤተሰብ ቀሪዎቹን ወደሥራ ለማሰማራት ይሰራል ያሉት አቶ አበራ ‹‹ይሄ በተለያዩ አካላት የሚከወን በመሆኑና ቅንጅት ባለመኖሩ ድጋፍ ከተደረገላቸው አብዛኛዎቹ ተመልሰው ለጎዳና ሕይወት ይዳረጋሉ፡፡›› ብለዋል፡፡ ክፍተቱ በመረጃ አያያዝም ይታያል ያሉት ባለሙያው ፣መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት አጠቃላይ በሀገሪቱ ያለውን የጎዳና ተዳዳሪ ቁጥር 600 ሺ እንደሚያደርሱት፣ ሴቶች፣ ወጣቶችና ህፃናት ሚኒስቴር በአዲስ አበባ ሕፃናት ብቻ 100 ሺ መሆናቸውን እንደሚገልጹ አስታውቀዋል፡ ፡
ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ በበኩሉ ይሄንን ቁጥር 150 ሺ እንደሚያደርሰው ተናግረዋል፡፡ የተቋሙ ዋና እንባ ጠባቂ ዶክተር እንዳለ ሀይሌ እንዳሉት ፤የዜጎች በነጻነት በሀገሪቱ በየትኛውም ቦታ ተዘዋውሮ የመስራት፣ ሀብት የማፍራትና በወደዱት ቦታ የመኖር መብት ያላቸው ቢሆንም፣ይህን መብት በመንግሥት አስፈጻሚ አካላት በአግባቡ መጠበቅና ማስጠበቅ ባለመቻሉና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ጫፍ በመድረሳቸው፡፡
በሚሊኖች የሚቆጠሩ ዜጎች በማንነታቸው ምክንያት ከቀያቸው ተፈናቅለዋል፡ በርካታ የሚሆኑት ለእንግልትና ለጉዳት ተዳርገዋል፡፡ ዶክተር እንዳለ መንግሥት ለዜጎች የመኖሪያ ቤት የመስሪያ ቦታ ወይንም ቤት የማቅረብ ኃላፊነት እንዳለበት ጠቅሰው፣በአቅም ውስንነት መንግሥት ቦታና ቤት ባላቀረበበት ሁኔታ ዜጎች ባገኙት አጋጣሚ መኖሪያ ቤት ለመስራት ሲገደዱ ካለምንም ቅድመ ሁኔታ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የተሰሩ ቤቶችን የማፍረስ እርምጃ በመወሰዱ ለዜጎች ሞትና መፈናቃል ምክንያት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
እንደ ዋና እምባ ጠባቂው ማብራሪያ፤ እነኚህ ችግሮች እንዲፈቱ ለማድረግ ተቋሙ በርካታ ሥራዎችን ቢያከናውንም፣ነፃና ገለልተኛ ሆኖ የህዝብ ድምጽ በመሆን ዜጎች በመንግሥት የሥራ አስፈጻሚ አካላት የሚደርስባቸውን በደል በመፍታትና መልካም አስተዳደርን በማረጋገጥ በኩል በአዋጅ ከተሰጠው ነፃነትና ከህብረተሰቡ ፍላጎት አንጻር ውጤታማ አልነበረም፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 26/2011
ራስወርቅ ሙሉጌታ