ኢትዮጵያውያን ትሕነግና ተባባሪዎቹ የውጭ ኃይሎች የአገራቸውን ሉዓላዊነት በመዳፈር እየፈጸሙ ያሉትን የተቀናጀ ጥቃት በመመከት የአያት ቅድመ አያቶቻቸውን ታሪክ ለመድገም ከዳር እስከ ዳር ተነቃንቀው እየተዋደቁ ይገኛሉ::
መንግሥት ምዕራባውያኑ በኢትዮጵያ ተላላኪ ደካማ መንግሥት ለመመስረት በከሀዲው ትሕነግ ተላላኪነት እያከናወኑ ካሉት የጥፋት ተግባር አገሩን እንዲከላከል ጥሪ ማቅረቡን ተከትሎ ኢትዮጵያውያን በአገራቸው ጉዳይ ዘብ አንደሚቆሙ በማረጋገጥ በተፈለጉበት መስክ ሁሉ አገራቸውን ለማገልገል ወስነው ርብርባቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል::
የሕይወት መስዋዕትነትን ለመክፈል መከላከያን፣ ልዩ ኃይሎችንና ሌሎች የጸጥታ ኃይሎችን ከመቀላቀል አንስቶ በገንዘብ፣ በሞራል፣ በዲፕሎማሲና በፕሮፖጋንዳ ድጋፍ ማድረጋቸውን ተያይዘውታል :: ወጣቶች ውለው ሳያድሩ ነበር ወደ ወታደራዊ ማሰልጠኛዎች የገቡት:: እናቶች አባቶች ለእዚህ ታላቅ አገራዊ ጥሪ ልጆቻቸውን አልሰሰቱም፤ መርቀው ስመው በድል ተመለሱ ብለው ሸኝተዋል::
የጠቅላይ ሚኒስትሩን በግንባር ሆኖ ጦሩን መምራት እና ሕዝቡ እንዲከተላቸው ያቀረቡትን ጥሪ ተከትሎ ታዋቂ ሰዎች ጭምር ወደ ግንባር ዘምተዋል:: ሕዝቡ ደጀንነቱን ለማረጋገጥ በገባው ቃል መሠረት ድጋፉን እያረጋገጠ ነው::
ይህ ተግባር የተጀመረው ከወራት በፊት ቢሆንም አሁንም ከእነግልቱ ቀጥሏል:: በገንዘብ፣ በዓይነት /ሰንጋ፣ በግና ፍየሎች/ ለመከላከያ ድጋፍ እየተደረገ ነው፤ እናቶች በሶ ፣ ድርቆሽ፣ ዳቦ ቆሎና የመሳሰሉትን እያዘጋጁ እየላኩ ናቸው:: በጦር ግንባር አካባቢ ያለው ማኅበረሰብ ትኩስ ምግቦችን እያዘጋጀ ሠራዊቱን እያጎረሰ ይገኛል:: ጦርነቱ ብዙ መልክ ያለው እንደመሆኑም በፕሮፖጋንዳው በኩልም ተመሳሳይ ተግባር እየተከናወነ ነው:: ሕዝቡ ሕወሓትና ተባባሪዎቹ በሚነዙት ሐሰተኛ መረጃ እንዳይፈታ እየተሠራ ነው:: ፊት ላይ ትሕነግና ተባባሪዎቹ በሐሰተኛ መረጃቸው ዓለምን ጠልፈውት የነበረ ቢሆንም፣ እውነትና ንጋት እያደር ይጠራል እንዲሉ ኢትዮጵያውያን በፕሮፖጋንዳውና በዲፕሎማሲው መስክ አሁን መሪነቱን መጨበጥ ችለዋል:: ጠላቶቻቸው የሚሉት አጥተው እየቀባጠሩ ናቸው::
የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ማኅበረሰብ በመላ ዓለም የተለያዩ ከተሞች ምዕራባውያኑ በኢትዮጵያ ላይ እያሳደሩ ያሉትን ጫናና ለትሕነግ እየሰጡ ያሉትን ድጋፍ የሚቃወሙ ሰላማዊ ሰልፎች ተጠናክረው ቀጥለዋል:: በቅርቡ በአንድ ቀን ብቻ በ27 የዓለማችን ታላላቅ ከተሞች ሰላማዊ ሰልፎችን መካሄዳቸው ኢትዮጵያውያኑ ምን ያህል በዲፕሎማሲው መስክ እየሠሩ ስለመሆናቸው አንድ ማሳያ ነው::
በተለይ የበቃ! ‹‹ኖ ሞር›› ንቃናቄ መላ ዲያስፖራ ኢትዮጵያውያንን በእጅጉ አስተሳስሯቸዋል:: ንቅናቄው ጠላትንም ወዳጅንም እያስገረመ ነው:: ይህ በትዊተርና በሰላማዊ ሰልፍ እየተካሄደ የሚገኝ ንቅናቄ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ድምጻቸው ይበልጥ እንዲሰማ አርጓል:: ንቅናቄው ከኢትዮጵያውያም አልፎ የአፍሪካውያን፣ የእስያውያንም ድምጽ የሰማበት እስከ መሆን ደርሷል::
ትውልደ-ሴኔጋላዊ አሜሪካዊው ታዋቂ ዘፋኝና ዜማ ደራሲ አኮንም በቅርቡ መድረኩን ተቀላቅሎታል:: 80 ሚሊየን የማኅበራዊ ሚዲያ ደጋፊ ያለው አኮን በኢንስታግራም ገፁ ላይ ‹‹አፍሪካን ተከላከሉ፤ ይበቃል›› “DEFEND AFRICA nomore የሚል ቲ-ሸርት በመልበስ ነው ዘመቻውን በይፋ የተቀላቀለው። ቤተሰቦቹ ከቤኒን ዘር የሚመዘዙትና ፈረንሳይ ውስጥ የተወለደው የፓን አፍሪካኒዝም አቀንቃኝ እና አንቂ ከሚ ሰባም ይህን ንቅናቄ ተቀላቅሎታል:: በፈረንሳይኛ ተናጋሪዎች ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ ታዋቂ እና ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆነው ይህ አንቂ ፣ ኢትዮጵያን በምንችለው ሁሉ መርዳት አለብን፤ ኢትዮጵያ ከተሸነፈች አፍሪካም ትሸነፋለች ሲልም መልዕክቱን አስተላልፏል።
ከምሥራቅ አፍሪካ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ፤ ከምዕራባዊው ክፍል ደግሞ ማሊ፣ ቡርኪና ፋሶ እና ኒጀር ለምዕራባውያን የእጅ አዙር ቅኝ ግዛት “በቃ !አሻፈረኝ” በማለት ድምጻቸውን አሰምተዋል። የቀድሞ ቅኝ ገዢያቸው ፈረንሳይ በውስጥ ጉዳያቸው የምታደርገውን የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝና ኢኮኖሚያዊ ብዝበዛ በመቃወም እስካሁን ሦስት የምዕራብ አፍሪካ አገራት ዜጎች ለተቃውሞ ወደጎዳናዎች ወጥተዋል።
በእንግሊዝ የሚኖሩ የአፍሪካና የካሪቢያን ዲያስፖራ ምሑራንም ምዕራባውያን በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ የሚያደርጉትን ጣልቃ ገብነት እንዲያቆሙ ጠይቀዋል:: ምሑራኑ ምዕራባውያን የጥቁር ሕዝቦች የነጻነት አርማ በሆነችው ኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ የሚያደርጉትን ጣልቃ ገብነት እንዲያቆሙ ነው ያሳሰቡት:: ማቱዋጆበብ ሪቻርድ የተባለ ኡጋንዳዊ የፓን አፍሪካኒዝም አቀንቃኝ ኢትዮጵያን ከጥቃት መከላል ማለት ጥገኛ ያልሆነና የነፃ አፍሪካዊነቴን ሕልውና መከላከል ማለት ነው ሲል ተናግሯል:: ጥቁር አሜሪካውያንና ጀማይካውያን ይህን ንቅናቄ እየተቀላቀሉት ነው::
የ”በቃ! አሻፈረኝ” nomore ንቅናቄ ከማኅበራዊ ዘመቻነት ወደ ዓለም አቀፍ ሕዝባዊ ንቅናቄነት እየተሸጋገረ ይገኛል። የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሁለት ከፍተኛ ኃላፊዎች “በቃ” የሚለውን መፈክር በማኅበራዊ ገፃቸው በማጋራት በዴሞክራሲ ስም የሚፈፀሙ ወንጀሎች መቆም እንዳለባቸው አሳስበዋል። የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በቅርቡ ኢትዮጵያን የጎበኙትም ምዕራባውያኑ በተለይም አሜሪካ አዲስ አበባ ተከባለች ፤ አዲስ አበባን ልቀቁ እያሉ ዜጎቻቸውንና ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ሲያስፈራሩ በነበረበት ወቅት ነው:: ይህ በክፉ ቀን የተደረገ ትልቅ አጋርነት ነው:: የኖ ሞር ንቅናቄው የምዕራባውያኑንም ቀልብ እየሳበ ነው::
አሜሪካዊው የአፍሪካ የፖለቲካና ኢኮኖሚክ ጉዳዮች ተንታኝ ሎውረንስ ፍሪማን አሜሪካ ዜጎቿን ከኢትዮጵያ ውጡ እያለች በምትወተውትበት ወቅት ወደ ኢትዮጵያ መጥተዋል :: ፍሪማን ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ አሜሪካና ምዕራባውያን የመገናኛ ብዙኃን ኢትዮጵያ ላይ በውሸት ላይ የተመሰረተ የስነልቦና ጦርነት ከፍተዋል፤ ይህንን የሚያደርጉት መረጃ ተሳስተው ሳይሆን ሆን ብለው፣ አቅደው መረጃ እንዲዛባ ፈልገው ነው ይላሉ።
ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ እንጂ ከምዕራቡ ዓለም እየተሰፈረ የሚሰጥ መፍትሔ አፍሪካን ለድህነት እንጂ ለብልጽግና አላበቃም:: ችግራችንን የምንፈታው በምዕራባውያን ቸርነት አይደለም:: እናቅላችኋለን ፤ መሪ እንመርጥላችኋዋለን ማለታቸውንም አንቀበልም:: በአገራችን በተካሄደው ምርጫ ድምፅ የሰጠነው ያሻንን ለመምረጥ ነው እንጂ ምዕራባውያኑ እንዲመርጡልን አይደለም:: ሚስማር በመዶሻ ሲመታ እየጠበቀ ይሄዳል፤ ኢትዮጵያንም በጫና ለመበታተን የሚደረግ ሩጫ ዜጎቿን ይበልጥ እንዲተሳሰቡ ለአገራቸውም እንዲሞቱ የአገር ፍቅራቸው እንዲጨምር ያደርገዋል፤አድርጎታልም::
እናም መላ ኢትዮጵያውያን ሆይ ! አውሮፓውያንና የሚዘውሯቸው ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ተብዬዎች ከትሕነግ ጋር ሆነው ተቀናጅተው ለከፈቱብን ጦርነት ማርከሻውን አግኝተናል:: ኢትዮጵያውያን በ‹‹ኖ ሞር›› በቃ ዘመቻችን ከዳር እስከ ዳር ይህን ያህል መነቃነቃችን አልፎም ተርፎም አፍሪካዊ አጋሮች ማግኘታችን ለምዕራባውያኑ ሐሰተኛ የፕሮፖጋንዳና የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ዘመቻ የአጸፋ ምላሽ ትርጉሙ ከፍተኛ ነው:: ለውጥም እያመጣ ነው:: ትህነግና ተባባሪዎቹ በጦር ሜዳ ቅሌት እየደረሰባቸው ነው፤ በፕሮፖጋንዳውም ቀንዳቸው እየተመታ ይገኛል፤ የኢትዮጵያውያን ድምጽ ከፍ ብሎ እየተሰማ ነውና::
ትህነግ አሁን እንዳበደ ውሻ ጭራውን ሸጉጦ እየተክለፈለፈ ይገኛል:: ዘመቻው አሁንም ተጠናክሮ መቀጠል አለበት:: ማፈርን ቢያውቁ አሜሪካና ተባባሪዎቿ አንዳንድ የአውሮፓ መንግሥታት፣ እነሱ የሚዘውሯቸው ዓለም አቀፍ ተቋማትና መገናኛ ብዙኃን ውርደት ምን እንደሆነ ቢያውቁት ኖሮ ይህ ዘመን ክፉኛ የተዋረዱበት ዘመን ነው:: በሐሰተኛ መረጃቸው ከፉኛ ተዋርደዋል:: ሴራቸው እየከሸፈ ነው::
እነዚህ ምዕራባውያን ጠላቶቻችን ንቅናቄው ከዳር እስከ ዳር የፈጠረው አንድነትና አሻፈረኝ ባይነት አሳስቧቸዋል:: ዘመቻው መፍትሔ እያመጣ ነው:: ለእዚህም ነው እጀ ረጅምነታቸውን ተጠቅመው የበቃ ዘመቻውን ለማኮላሸት ትዊተርን ማገድ ውስጥ የገቡት:: ብረትን እንደ ጋለ ነው እንዲሉ አሁንም ዘመቻውን አጠናክሮ መቀጠል ያስፈልጋል::
እንደጠቀስኩት ዘመቻው በጦር ሜዳ ድልም እየታጀበ ነው:: በፕሮፖጋንዳውም በጦር ሜዳውም ድሎች እየተዘመገቡ ናቸው:: የሕወሓት ግብዓተ መሬት እስከ ሚፈጸም ድረስ ብቻ ሳይሆን ምዕራባውያን እጃቸውን ከእኛ ላይ እስከሚያነሱ የበቃ ዘመቻው መቀጣጠል ይኖርበታል::
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 2/2014