አዲስ አበባ፡- ህብረተሰቡ መጪዎቹን የልደትና የጥምቀት በዓላት ሲያከብር ለእሳትና ለድንገተኛ አደጋ ለሚያጋልጡ ነገሮች ከፍተኛ ትኩረትና ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እሳትና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አሳሰበ።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እሳትና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን መኮንን ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ በዓመት በዓል ሰሞን ከጥንቃቄ ጉድለት የሚመጡ አደጋዎችን ለማስቀረት ህብረተሰቡ አስፈላጊውን ቅድመ አደጋ ጥንቃቄ ማድረግ አለበት።
አብዛኛዎቹ ዓመት በዓሎች ከምግብ ዝግጅት፣ ከሻማ ማብራት እና ከዴኮሬሽን ጋር የተያያዙ ናቸው ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ህብረተሰቡ በእሳትና በኤሌክትሪክ አጠቃቀም እንዲሁም በሌሎች ጉዳዮች ላይ ጥንቃቄ በማድረግ የአደጋ ተጋላጭነቱን እንዲቀንስ አሳስበዋል።
በምግብ ማብሰያ ቤት ያለ የኤሌክትሪክ ሲልንደርን ፣ እንደ ጧፍ ፣ ሻማና ከሰል የመሳሰሉትን በጥንቃቄ መጠቀም ያስፈልጋል ያሉት ዳይሬክተሩ፤ በአንድ የኤሌክትሪክ ሶኬት ላይ ደራርቦ ያለመጠቀም፤ የተቀጠሉና ኮንታክት ሊፈጥሩ ይችላሉ በተባሉት ሽቦዎች ላይ ክትትል እያደረጉ ስራን ማከናወን እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
የልብስ መተኮሻ ካውያ፣ ለበዓል ድምቀት ተብለው የሚለኮሱ ዲኮሬሽኖች አደጋ እንዳያስነሱ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፤ ‹‹ካምፕ ፋየር›› የማድረግ ልምድ ያላቸው ሰዎችም ዝግጅታቸውን ከጨረሱ በኋላ የእሳቱን መጥፋት ሳያረጋግጡ ከቦታው እንዳይሄዱ አሳስበዋል። አሽከርካሪዎች ጠጥቶ ከማሽከርከር እንዲቆጠብ፤ ማህበረሰቡ ደስታውና መዝናናቱ ለአደጋ እንዳያጋልጡት ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የአዲስ አበባ እሳትና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አደጋ ከመከሰቱ በፊት ቅድመ መከላከል ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሠራ ጠቅሰው፤ ይህ መልዕክትም ቅድመ አደጋን የመከላከል አንዱ አካል ነው ብለዋል።
ጥንቃቄዎችን አልፎ የሚከሰቱ አደጋዎችን በፍጥነት ለመቆጣጠር ተቋሙ 24 ሰዓት ዝግጁ እንደሆነም አመልክተዋል። በእለቱ ፈቃድ ላይ የነበሩ ሰራተኞችም ፈቃዳቸውን ትተው በቅርንጫፍ መስሪያ ቤቶች ጭምር በተጠንቀቅ እንደሚቆሙ፤ በጎ ፈቃደኞችም ድጋፍ ለመስጠት እንደተዘጋጁ ገልጸዋል።
አደጋ በሚከሰት ጊዜ ህብረተሰቡ በ939 ነጻ የስልክ ጥሪ በመደወል ትክክለኛ መረጃ በፍጥነት በማድረስ እንዲተባበርና የእሳት አደጋ ተሽከርካሪዎች አደጋ ወደ ተከሰተበት ቦታ ሲንቀሳቀሱ ጎዳናዎችን ለተሸከርካሪዎች ክፍት በማድረግ እንዲተባበር ጥሪ አቅርበዋል።
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን ሰኞ ታኅሣሥ 28 ቀን 2017 ዓ.ም