የበዓል ተረፈ ምርቶችን በአግባቡ ማስወገድ እንደሚገባ ኤጀንሲው አሳሰበ

አዲስ አበባ:- የገና በዓል ሰሞን ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በየአካባቢው የሚመረቱ ተረፈ ምርቶችን ባግባቡ በመያዝ ለሚመለከታቸው የጽዳት ባለሙያዎች ብቻ መስጠት ተገቢ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ የጽዳት አስተዳደር ኤጀንሲ ገለጸ።

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር እሸቱ ለማ (ዶ/ር) ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ በዓሉ ሲከበር ከበዓሉ ጋር ተያይዞ የሚመረቱ ተረፈ ምርቶችን ባግባቡ መያዝ እና ለሚመለከተው አካል ብቻ መስጠት ተገቢ ነው።

ከተማዋ ውብ እየሆነች፣ አረንጓዴ እየለበሰች እና ደረጃዋም ከፍ እያለ ይገኛል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ይበልጥ ጽዱ ከተማ እንድትሆን እያንዳንዱ ከተማዋን ጽዱ በማድረግ ሊተባበር ይገባል ብለዋል። ቆሻሻን የሚጥሉ ሳይሆኑ የሚሰበስበቡ እጆች ሊበራከቱ እንደሚገባ አመልክተው፤ በከተማ ጽዳት ሁሉም ሃላፊነቱን መወጣት እንዳለበትም አሳስበዋል።

በዓል ሲመጣ የተወሰኑ የህብረተሰብ ክፍሎች በአካባቢያቸው የእንስሳት እርድ የሚያከናውኑበት ሁኔታ ይስተዋላል። ይህንን ተከትሎም በርካታ የእርድ ተረፈ ምርቶች ይመረታሉ። ተረፈ ምርቶቹን በአግባቡ በመያዝ ለሚመለከታቸው የጽዳት አስተዳደር ባለሙያዎች ማስረከብ እንደሚገባም አመልክተዋል።

የእንስሳት እርድ መከናወን ያለበት በቄራዎች ድርጅት መሆኑን የገለጡት እሸቱ ለማ (ዶ/ር) ፤ ድርጅቶቹ ከእርድ በፊት የእንስሳቶች ምርመራ ያከናውናሉ፤በዚህም ለምግብ የሚቀወርበው ስጋ ጤንነቱን የጠበቀ እና ጉዳት የሌለው መሆኑን እንደሚያረጋግቱ ጠቁመዋል።

በየአካባቢው የሚከናወነው የእንስሳት እርድ የሚከናወነው ቅድመ ምርመራ ሳይደረግ በመ፣ሆን ለጤና ችግር ይዞ ሊመጣ ይችላል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ፤ ከጤና ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ የጤና ስጋቶችን ጉዳቶችን ለመከላከል የመጀመሪያው መፍትሄ የእንስሳት እርድ በቄራዎች ድርጅት እንዲከናወን ማድረግ ነው ብለዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ ቆሻሻ የሚያነሱ ስምንት ሺህ አባላት ያሏቸው 107 የሽርክና ማህበራት እንዳሉ ጠቁመው፤ በሳምንት ሁለት ቀን ቆሻሻ ይሰበስባሉ። ከዚያም ባለፈ እየተመላለሱ የሚሰበስቡበት አሰራር አላቸው ብለዋል።

ማህበራቱ እየሰሩ ባለበት ሁኔታ ግዴለሽነት ካልሆነ በስተቀር ቆሻሻን ወደ ውጭ አውጥተው የሚጥሉበት አስገዳች ሁኔታ እንደሌለ ያለመከቱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ችግሮች ካሉ በ6199 የስልክ ጥሪ ቢያሳውቁ ወዲያውኑ ምላሽ እንሰጣለን ብለዋል። የእርድ ተረፈ ምርቶች በየቦታው በሚጣሉበት ጊዜ በአካባቢ ብክለት እና በጤና ላይ የሚያስከትሉት ከፍተኛ ጉዳት በመሆኑ ባግባቡ ተይዘው ሊወገዱ እንደሚገባም አመልክተዋል።

ኮሪደር ልማቱ ለከተማው ጽዳትና ውበት ከፍተኛ ፋይዳ አበርክቷል። ጽዳትና ውበት እንዲሁም ጽዳትና አረንጓዴ ልማት የማይነጣጠሉ ናቸው። እያጸዳን አረንጓዴ እያለበስን በመቀጠል የከተማውን ውበት ከፍ ማፍረግ ከሁላችንም ይጠበቃል ብለዋል።

ህብረተሰቡ ቆሻሻን የሚያስወግድበት ስርዓት ባግባቡ ሊሆን ይገባል፤ በዚህ ዙሪያ ግንዛብ ለመፍጠር ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው ያሉት ዋና ዳሪክተሩ፤ የሚመረተውን ደረቅ ቆሻሻ ባግባቡ መያዝ እና ማስወገድ ለጤናም ሆነ ለአካባቢ ንጽህና ወሳኝ እንደሆነ አስታውቀዋል።

በ2016 ዓ.ም የህብረተሰቡ ግንዛቤ ያለበት ደረጃን በሚመለከት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ባሰራው ጥናት መሰረት 94 በመቶ የሚሆኑት የህብረተሰብ ክፍሎች በቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ሂደት ግንዛቤው ቢኖራቸውም በተግባር ወደ ስራ የመቀየር ክፍተት እንዳለባቸው ገልጸዋዋል።

ይህንን ችግር ለመቀየር ትኩረት ሰጥተን ተጨማሪ ስራዎችን እየሰራን ነው። ንጹህ አካባቢ ውስጥ መኖር አለብኝ የሚል ማህረሰብ እስኪፈጠር ድረስ ተደጋጋሚ የግንዛቤ ፈጠራ ስራዎች ይቀጥላሉ ብለዋል።

ከአራት ሺህ በላይ ወጣቶች በሃይላንድ፣ በወረቀት፣ በብረታ ብረት እና በተፈጥሮ ማዳበሪያነት ስራ ላይ ተሰማርተው በመልሶ መጠቀም ኢኮኖሚያዊ ጥቅም አግኝተው ሕይወታቸውን እየቀየሩ እንደሚገኙም ዋና ዳይሬክተሩ አመልክተዋል።

ዘላለም ግዛው

አዲስ ዘመን ሰኞ ታኅሣሥ 28 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You